Google search engine

የሸገር ደርቢ ታላቅና ተጠባቂ ጨዋታ | አቤል ያለው /ቅ/ጊዮርጊስ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

ቅ/ጊዮርጊስ vs ኢትዮጵያ ቡና
ነገ በ10፡00 ሰዓት

የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች፣ እንደዚሁም ደግሞ የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾችና የስፖርቱ ተመልካቾች በጉጉት የሚጠብቁት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ነገ እሁድ ከ10 ሰአት ጀምሮ በርካታ የእግር ኳሱ አፍቃሪዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሚያከናውኑት የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታም ከሌላው ጊዜ በበለጠ በርካታ የእግር ኳሱ አፍቃሪዎች ግጥሚያውን ይከታተሉታል ተብሎ በመጠበቅ ላይ ሲሆን የጨዋታው ባለሜዳም ቅ/ጊዮርጊስ መሆኑም ታውቋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ታሪክ ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ በደርቢው ፍልሚያ የሁለት ዙር ጨዋታዎችን በማከናወን ሲገናኙ በእስከዛሬው የእርስ በርስ ግንኙነታቸው አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች በማሸነፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነቱን የወሰደ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ስንመለከት የአቻ ውጤት የተመዘገበበት ውጤት ቁጥሩ ከሌላው ጊዜ ግንኙነታቸው አኳያ ከፍ ያለ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች ከእዚህ ቀደም የፊንፊኔ ደርቢ የሚል ስያሜን በኋላ ላይ ደግሞ የሸገር ደርቢ የሚል መጠሪያ የያዘውን ጨዋታዎቻቸውን ከማከናወናቸው በፊት በሁለቱም ቡድን ደጋፊዎችም ሆነ ተጨዋቾች በኩል ለግጥሚያው የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር አንዳቸው አንዳቸውን አሸንፈው ለመውጣት እና ከጨዋታው በኋላም ቀኑን በፌሽታ እና በደስታ አጣጥመው ለመዋል ከፍተኛ ዝግጅትን የሚያደርጉበት ሁኔታን የተመለከትን ሲሆን የደርቢው ጨዋታ ከቅርብ ዓመታቶች ወዲህ በሜዳ ላይ ሲደረግ ግን የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች በደጋፊዎቻቸው እንደሚሰጣቸው የአማረ እና ድንቅ ድጋፍ የተመልካቹን የኳስ ስሜት የሚያረካ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ባለመሆኑ ደርቢው በሜዳ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ አንፃር አጓጊነቱ ያን ያህል የሚያስነግርለት አይደለምና በዚህ በኩል መሻሻል እንዳለበትም በሁሉም ዘንድ እየተነገረም ይገኛል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይስ በግጥሚያው ምን ያሳዩን ይሆናል? በደርቢው ጨዋታ ዙሪያና ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን ከሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች መካከል ከቅ/ጊዮርጊስ ተከላካዩን አስቻለው ታመነን እና አጥቂውን አቤል ያለውን ከኢትዮጵያ ቡና ወገን ደግሞ አማካዮቹን አማኑኤል ዩሃንስንና ሳምሶን ጥላሁንን አናግረናቸው ምላሻቸውን ሰጥተውናል፤ እንደሚከተለውም ይቀርባል፡፡
“በሸገር ደርቢው ቡናን አሸንፈን መሪዎቹን እንቃረባለን”
አቤል ያለው /ቅ/ጊዮርጊስ/
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን በሸገር ደርቢው ከመፋለሙ በፊት ጅማ አባጅፋርን ማሸነፍ ችሏል፤ አንተም የድል ግብ አስቆጥረሃል፤ ለአንዱ ጎልም ምክንያት ሆነሃል፤ ጨዋታውን እና የተገኘውን ድል እንዴት ትገልፀዋለህ?
አቤል፡- ቅ/ጊዮርጊስ የጅማ አባ ጅፋር ክለብን በተፋለመበት ጨዋታው ባለፉት ተከታታይ ግጥሚያዎቹ ነጥብ ከጣለበት ስሜት በመላቀቅ ወደ አሸናፊነት ስሜት የመጣበት ግጥሚያ ስለነበር በተገኘው ውጤት በጣም ነው የተደሰትኩት፤ በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ያንን ያህል ጥሩ አልነበርንም፤ ይህ ሊሆን የቻለውም ቀደም ባሉት ጨዋታዎች ነጥቦችን ጥለን ስለነበር ይህን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ አለብን በሚል ስሜት ወደ ጨዋታው ሪትም እስክንገባ ድረስ ጉጉት ስለነበረብን ነው፤ የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን በአቋማችን ላይ በሚገባ ለመነጋገር ስለቻልን ጨዋታውን ልናሸንፍ ችለናል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ ጅማ አባ ጅፋርን ባሸነፈበት ጨዋታም እኔ ጥሩ ከመንቀሳቀስ ባሻገር ለቡድኔም ጎል ያስቆጠርኩበት መንገድ የእኔ ጥረት ብቻ ሳይሆን የቡድኔ ጓደኞች እና የፈጣሪም እገዛ ታክሎበት ነውና በዚህም ጎል ማስቆጠሬ ልዩ የደስታ ስሜትም ሊሰማኝ ችሏል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን ለሚፋለምበት የሸገር ደርቢው የነገ ጨዋታ በምን መልኩ ተዘጋጅቷል? ከግጥሚያውስ ምን ውጤት ትጠብቃላችሁ?
አቤል፡- የኢትዮጵያ ቡናን ለምንገጥምበት የሸገር ደርቢው ጨዋታ ያደረግነው ዝግጅት ከሌላው ጊዜ አንፃር የተለየ የሚባል አይደለም፤ ለቡና ብለን ብቻ ልዩ ዝግጅትን አላደረግንም፤ ለሁሉም ክለቦች እንደምናዘጋጀውም ነው ግጥሚያውን እየጠበቅን የምንገኘው፤ በጨዋታው ላይ ስለሚመዘገበው ውጤት ማለት የምፈልገው የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ መቻል የግድ ወደመሪዎቹ በነጥብ የሚያቃርበንን እድል ስለሚፈጥርልን ግጥሚያውን አሸንፈን ከሜዳ ለመውጣት በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለአንተ በታሪክ የመጀመሪያ ይሆንልሃል፤ በጨዋታው ላይ መሳተፍ መቻል በውስጥህ ምን አይነት ስሜትን ይፈጥርብሃል?
አቤል፡- የቅ/ጊዮርጊስን መለያ በማጥለቅ የኢትዮጵያ ቡና ጋር የማደርገው የነገው ተጠባቂና ወሳኙ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለእኔ የመጀመሪያዬ ስለሚሆን ግጥሚያው የሚፈጥርብኝ የደስታ ስሜት በጣም ከፍ ያለ ነው፤ በእዚህ ብዙ ህዝብ በሚገኝበትና በምርጥ ድባብ ውስጥ ሆኖም መጫወት መቻል እድለኝነትን ይጠይቃልና በዚህ በኩል በጣም ታድያለው፤ እንዲህ ባሉ ታላላቅ የደርቢ ጨዋታዎች ላይ የእግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ አጋጣሚውን ላታገኝ ስለምትችልም የቅዱስ ጊዮርጊስን መለያ ለብሼ የማደርገው ይኸው የእሁዱ የደርቢ ጨዋታ ከወዲሁ ከፍተኛ የኩራት ስሜት እንዲሰማኝ እያደረገኝ ነው የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን ወቅታዊ አቋም ተንተርሰህ የነገው የሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ እነሱ ሊያስቸግሩን ይችላሉ ብለህ የምትሰጋው ነገር አለ?
አቤል፡- በፍፁም፤ የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ከቡና ስንጫወትም ሆነ በቀጣይ በሚኖሩን ሌሎች ግጥሚያዎች ላይ ለእኛ ቡድን ስጋት የሚሆንብን ቡድን ማንም የለም፤ ማንንም ቡድንም አንፈራም፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም ፈርቶም አያውቅምና የሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ከቡና ጋር ስንጫወት በጥሩ ብቃት ላይ ሆነን በመገኘትና በጨዋታም በልጠን እነሱን እናሸንፋቸዋለን፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተደጋጋሚ ጎሎችን እያስቆጠርክ ከመሆኑ አንፃር የነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
አቤል፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ ጅማሬ ጨዋታዎች ላይ ገና ቡድኑን ከመቀላቀሌ ተደጋጋሚ ጎሎችን ላስቆጥር ብችልም አሁን ላይ እኔ በዋናነት ቅድሚያን ሰጥቼ እያሰብኩ ያለሁት ቡድኔ ውጤታማ የሚሆንበትን ነገር መፍጠር መቻል ነው፤ በየጨዋታው ከጓደኞቼ ጋር እንደ ቡድን ሆኜ በመጫወት ለክለቤ ጥሩና ውጤታማ የሆነ ግልጋሎትን ለመስጠት ተዘጋጅቻለው፡፡ የሸገር ደርቢው የነገ ጨዋታ ላይም እኔ ወደሜዳ የምገባው ክለባችን እንደ ቡድን ተንቀሳቅሶ በመጫወት ቡናን እንዲያሸንፍ እንጂ እኔ ብቻ ጎል እንዳስቆጥርና ወደ ኮከብ ግብ አግቢነቱ እንዳመራ አይደለምና የነገውን ጨዋታ ጨምሮ በእያንዳንዱ ግጥሚያዎች ላይ ክለቤ ውጤታማ ለሚሆንበት ነገር ነው ቅድሚያን መስጠት የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ወሳኙ የደርቢ ጨዋታ ነገ ይካሄዳልና ከስፖርታዊ ጨዋነት አንፃር ምን ይጠበቅ?
አቤል፡- የሸገር ደርቢውን ጨዋታ ሁለታችንም ቡድኖች ነገ ስናከናውን በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ተጨዋቾች በዋናነት አተኩረን ልንሰራ የሚገባን ደጋፊን የሚያነሳሳ ነገሮችን ከማድረግ ልንቆጠብ ይገባናል፤ ቀጥሎ ደግሞ የየክለባችን ደጋፊዎች በሜዳ ላይ ጥሩ ኳስን አይተው ከሜዳ የሚወጡበትን ነገር ልናስመለክታቸው ይገባል፤ ደጋፊዎች ቢሆኑም በጨዋታው ላይ ማንም አሸነፈ፣ ተሸነፈም እንደዚሁም ደግሞ አቻ ወጣም የመጣውን ውጤት በፀጋ በመቀበል ጨዋታው ፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ግጥሚያው እንዲጠናቀቅ ሁላችንም በጋራ ልንሰራበት ይገባል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻስ አቤል ምን መልዕክቱን ያስተላልፋል?
አቤል፡- የኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚኖረንን የነገው የደርቢ ጨዋታ በአሸናፊነት እንደምንወጣና ደጋፊዎቻችችንም እንደምናስደስት ባለሙሉ እምነት ነው ያለኝ፤ ከእዚህ ውጪም ለቡድናችን ደጋፊዎች የማስተላልፍላቸው ተጨማሪ መልዕክት ቢኖር ክለባችን የአሁን ሰአት ላይ ወደ ቀድሞና አስፈሪ አቋሙ ሊመለስ ከጫፍ እየደረሰ ነውና ይሄንን በአጭር ጊዜ ውስጥ የምትመለከቱት ይሆናል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P