ኢትዮጵያ ቡና በመጪው ዓመት ላለበት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናና የእዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ለሚጠብቀው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የውድድር ተሳትፎው በቅርቡ የፕሪ-ሲዝን ልምምዱን የሚጀምር ሲሆን ከትናንት በስቲያ ተጨዋቾቹ የሜዲካል ምርመራን ማድረግ መጀመራቸው ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው ፋሲል ከነማን በመከተል ሁለተኛ ሆኖ ባጠናቀቀበት የዘንድሮ የውድድር ዘመን ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ወደ ኢንተርናሽናል ተሳትፎ የተመለሰ ሲሆን ክለቡ ስላሳለፈው የሊግ ጉዞው፣ እንደዚሁም ደግሞ በመጪው የውድድር ዘመን በምን መልኩ መቅረብ እንዳለበትና ከራሱ ብቃትም ጋር አያይዘን ጥያቄዎችን በጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አማካኝነት ያቀረብንለት የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል መስመር ተከላካይ አበበ ጥላሁን ምላሽን ሰጥቶበታል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ወጥታችሁ ውድድሩን አጠናቅቃችኋል፤ ዓመቱ እንዴት አለፈ?
አበበ፡- የእዚህ ዓመት ዋንኛ እቅዳችን የነበረው የውድድሩ ሻምፒዮና መሆን ነበር፤ ያን ግን ልናሳካው አልቻልንም፤ ቢሆንም ግን በየጨዋታው ከምንከተለው አጨዋወት አኳያ ጥሩ እና ተስፋ ሰጪ የሆነ እንቅስቃሴን ለስፖርት አፍቃሪው እናስመለክት ስለነበርን ጊዜያቶቹን በጥሩ ሁኔታ አሳልፈንበታል፤ የተገኘው ውጤትም ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ያሳለፈን ስለሆነም እኛም ሆንን ደጋፊዎቻችን በጣሙን ልንደሰትበትም ችለናል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና የሚያስፈልገው ሻምፒዮናነት እንጂ ሁለተኝነት አይደለም፤ ይሄን በደንብ ነው የምታውቀው?
አበበ፡- አዎን፤ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሚመጣ ማንኛውም ተጨዋች ይሄን አውቆም ነው ወደ ክለቡ የሚያመራው፤ ቡና ትልቅ ቡድን ነው፤ በበርካታ የሀገሪቱ የስፖርት አፍቃሪዎችና የስፖርት ቤተሰቡ ዘንድም የሚደገፍ ነው፤ ዘንድሮ ሁለተኛ መውጣት የእኛ ዋንኛ እቅዳችን ባይሆንም ይሄ ውጤት ግን ሌላኛውን አማራጫችንን ማለትም ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ተሳትፎ ከ9 ዓመት በኋላ ዳግም እንድንመለስ ያደረገን ስለሆነ በመጣው ውጤት ከላይም ገልጬዋለው ልንደሰትበት ችለናል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ የተመለሰው ከ9 ዓመት በኋላ ነው፤ የሊጉን ዋንጫ ካነሳ ደግሞ 10ኛ ዓመቱ ነው፤ ያለ ውጤት ይሄን ያህል በመቆየቱ ዙሪያ ምን አልክ?
አበበ፡- ኢትዮጵያ ቡና ትልቅና በአጨዋወቱም በጣም የሚወደድ ቡድን በመሆኑ በምንም መልኩ ይሄን ያህል ዓመታቶችን ያለ ውጤት መጠበቅ የለበትም፤ ቡና በየዓመቱ ትላልቅ ውጤቶችን ማምጣት ያለበት ቡድን ነው፤ ያ ባይሳካ እንኳን አንድአንዴ ቢያንስ በአንድ የኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎ ላይ መጫወትም ይኖርበታል፤ ይሄን ላለፉት ዓመታቶች ለማሳካት ባይችልም አሁን ግን በእኛ ጊዜ ወደዚህ የውድድር መድረክ ለመመለስ በመቻሉ እኛን ብቻ ጭምር ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ደጋፊዎቻችንንም ጭምር ሊያስደስታቸው ነው የቻለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ዘንድሮ ላለማንሳቱ በምክንያትነት የምትጠቅሰው ነገር አለ?
አበበ፡- አዎን፤ ጠንካራና ጥሩ ኳስ የሚጫወት ቡድን ቢኖረንም በአንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ የምንሰራቸው ጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሉን በመምጣታቸው ነው ከስኬቱ ልንርቅ የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ሲሰራቸው የነበሩት ስህተቶች የሚታረሙ ናቸው?
አበበ፡- በጣም እንጂ፤ ምክንያቱም የያዝነው የአጨዋወት መንገድ አዲስና ስህተቱን ለማረምም ደግሞ ቀላል ስለሆኑ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፤ ቡና በያዘው የጨዋታ ፍልስፍና ዋንኛው ነገር ስህተቶቹን መቀነስ መቻል ነው፤ ቡድኑ ከዓምናው ዘንድሮ ያሻሻለው ነገር አለ፤ በመጪው ዓመት ደግሞ ይበልጥ ተሻሽሎና ተጠናክሮም ይቀርባል፤ ያኔም የእርሱ ዋንኛ እልሙና እቅዱ የሆነውን ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከፍ አድርጎ ያነሳል፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስታመራ የአንተ እልምስ ምን ነበር?
አበበ፡- ከቡድኑ ጋር ዋንጫ ማንሳት ነዋ! ዘንድሮ ይህ እልሜ ባይሳካም፤ በመጪው ዓመት ይህ የሚሳካ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ ምርጥ ነው ማለት ይቻላል?
አበበ፡- እንደ ራሴ ምልከታ አዎን ነው የምልህ፤ ምክንያቱም ይሄን ቡድን የተቀላቀልኩት ገና ዘንድሮ ነው፤ ቡድኑ እኔ ከማውቀው አይነት እንቅስቃሴ አኳያም አዲስ አጨዋወትንም ነው የሚከተለውና በፍጥነት ቶሎ ያለመላመዱ ነገር ቢኖርም ጥሩ ነገርን በራሴ ላይ ተመልክቻለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና እየተከተለ ያለው አጨዋወት ተመችቶሃል?
አበበ፡- አዎን፤ የያዝነው የጨዋታ እንቅስቃሴ ኳስን በቀላሉ ተቆጣጥሮ በመጫወት ወደተጋጣሚ ቡድን የሜዳ ክልል ተጋግዞ በመግባት መጫወትና ግብን ማስቆጠር ነው፤ ይህን ከጅማሬው ስናየው ጥሩ ነገሮችን ተመልክተንበታል፤ ከእዚህ አንፃር የምንከተለው አጨዋወት እንደግልም እንደቡድንም ተመኝቶኝ አልፏል፤ አጨዋወታችን ለሀገራችንም ጭምር ይጠቅማል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎአችሁ አስቆጪ የምትለው ግጥሚያ ከማን ጋር ያደረጋችሁት ነው?
አበበ፡- በቀዳሚነት የምጠቅሰው ከውድድሩ ሻምፒዮና ፋሲል ከነማ ጋር ያደረግነውን ነው፤ ያ ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ ነበር፤ ብናሸንፍ በሁለት ነጥብ እንርቃቸው ነበር፤ ሌላው ከባህርዳር ጋር የነበረንን ጨዋታ አቻ መለያየታችንም ያስቆጨን ግጥሚያ ነው፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት በመጠናቀቁ ምን አልክ?
አበበ፡- እግር ኳስ ጨዋታ ፊት ለፊት የሚታይና ድብብቆሽም የሌለበት ነው፤ በተለይ ደግሞ የእዚህን ዘመን ውድድር ሁሉም ሰው የቀጥታ ስርጭት ስለነበረው በዲ.ኤስ.ቲቪም ተከታትሎታልና ለፋሲሎች ይሄ ድል ለእያንዳንዱ ግጥሚያ ከፍተኛ ትኩረትን ከመስጠታቸው አኳያና ብዙውን ግጥሚያ ደግሞ በድል አድራጊነት ከማጠናቀቃቸው አንፃር ሻምፒዮናነቱ የሚገባቸው ነው፡፡
ሊግ፡- የእናንተው አቡበከር ናስርም እኮ ይህን ዓመት በተለያዩ የኮከብነት ሽልማቶች ተንበሽብሾ ሊያሳልፍ ችሏል፤ ስለ እሱስ የምትለው ይኖርሃል?
አበበ፡- አዎን፤በአቡበከር ዙሪያ ብዙ ተብሏል፤ በቅድሚያ ከዚህ ክስተትና ታምርን ካሳየ ተጨዋች ጋር በአንድ ቡድን ውስጥ ሆኜ በመጫወቴ ራሴን ደስተኛ እና እድለኛ አድርጎኛል፤ የእሱን ችሎታና ብቃት ሳይም ካሳለፈው ምርጥ የውድድር ዘመን አኳያም ምናለ ሌላ ተመሳሳይ ተጨዋች በቡድናችን ውስጥ ቢኖርስ እንድልም አስችሎኛልና አቡበከር አሁንም ቡና በያዘው የራሱ አጨዋወት ውስጥ አሁን ከያዘው ብቃቱ የበለጠም ጥሩ ተጨዋች መሆን ይችላልና በዚህ አጋጣሚ ለእሱ አድናቆቴን ልገልፅለት እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንጉ ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን ዋንጫ አጥብቆ ይፈልጋል፤ ይሄ ድል እንዴትና በምን መልኩ የሚሳካ ይመስልሃል?
አበበ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ አሸናፊ መሆን የሚቻለው በቅድሚያ እግር ኳስን እንደ ቡድን መጫወት ስትችልና ጠንክረህም መስራት ስትችል ነው፤ በተለይ ደግሞ ከምትከተለው አጨዋወት አኳያ ስህተትህን ከቀነስክ ውጤታማ መሆን የማትችልበት ምንም ምክንያት የለምና የእኛም ስህተት ከሌሎች ቡድኖች ስህተት አኳያ ያነሰ በመሆኑ ይህን የሊግ ዋንጫ የምናነሳበት እድላችን በጣም ሰፊ ይሆናል፤ የመጪው ዓመት ላይም ይሄ እልማችን የሚሳካም ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- እናጠቃል…?
አበበ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ የእረፍት ጊዜያችንን በምን መልኩ ማሳለፍ እንዳለብን በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አማካኝነት የተሰጡ ትምህርቶች ስለነበሩ እነዛን በመጠቀም ጊዜያችንን ስናሳልፍ ነበር፤ አሁን ደግሞ ወደ መደበኛ ልምምድ ለመቅረብ እየተዘጋጀን ስለሆንን የሜዲካል ምርመራን እያደረግንም ነውና ቡድናችን ቡና በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይና በመጪው ዓመት ለሚጠብቀው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ከወዲሁ በጥሩ መልኩ ተዘጋጅቶ ደጋፊውን የሚያስደስት ውጤት ለማምጣት ሊዘጋጅ ይገባል፡፡