Google search engine

የቅ/ጊዮርጊሱ መሐሪ መና ለህክምና ወደ ህንድ ይጓዛል “በጉዳት ከኳስ መለየት ከባድ ነው፤ ያማልም፤ በፍጥነት ድኜ ወደ ጨዋታው ዓለም እመለሳለው” መሐሪ መና /ቅ/ጊዮርጊስ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የቅ/ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች መሐሪ መና ክለባቸው ከመከላከያ ጋር አድርጎት በነበረው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ ከተመስገን ገብረ ኪዳን ጋር በመጋጨቱ በእግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበት የነበረ ሲሆን ተጨዋቹ በሀገር ውስጥ ህክምና እስከአሁን ከህመሙ ድኖ በፍጥነት ወደ ሜዳ ሊመለስ ስላልቻለ ክለቡ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ህንድ ሊልከው ተዘጋጅቷል፤ የቅ/ጊዮርጊሱ መሐሪ መና ጉዳቱ ከደረሰበት በኋላ ላለፉት አምስት ወራቶች ወደ ሜዳ ለመመለስ በሀገር ውስጥ ህክምና የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም ባደረገው ምርመራ የግድ ወደ ውጪ ሄዶ መታከም እንዳለበት ለክለቡ በማሳወቁ ይሄ ተፈቅዶለት በሳምንቱ መጀመሪያ ቀናቶች ወደ ህንድ ሀገር በመሄድ ይታከማል፡፡
የቅ/ጊዮርጊሱን የግራ መስመር ተከላካይ ስለ ጉዳቱ፣ ላለፉት አምስት ወራት በጉዳት ከሜዳ ስለመራቁ፣ በሀገር ውስጥ ህክምና ስላደረገው ክትትል እና ወደ ህንድ ሄዶ ሊታከም ስለመዘጋጀቱና በክለባቸው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎ ዙሪያ ጠይቀነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ መለያ ከታየህ አምስት ወራቶችን አስቆጠርክ፤ በጤናህ ላይ መሻሻል የለም ማለት ነው?

መሐሪ፡- አዎን፤ ለእዛም ነው በጣም የምወደው ክለቤ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ህንድ ሀገር ሊልከኝ የተዘጋጀው፡፡
በህንድም በማደርገው ህክምና በፍጥነት ድኜ ወደ ጨዋታው ዓለም እንደምመለስ እና ክለቤንም በጥሩ ሁኔታ እንደማገለግለው አምናለው፡፡
ሊግ፡- ከመከላከያ ጋር ስትጫወቱ ነበር ጉዳቱ የደረሰበህ፤ ጥቂት ወደ ኋላ ተመለስ እና በአንተ ላይ ስለደረሰው ጉዳት እና ስላደረግከው የሀክምና ክትትል የተወሰነ ነገር ብትለን?

መሐሪ፡- መከላከያን በተፋለምንበት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከተመስገን ጋር በመጋጨቴ በእኔ ላይ ጉዳቱ የደረሰብኝ በቀኝ እግሬ ላይ ነው፤ ያኔም የህመሙ ስሜት ሲሰማኝ የኤም አር አይ ምርመራን አደረግኩ፤ በምርመራ ጊዜውም ስሮቼ መበጣጠሳቸው ስለተነገረኝ ለአንድ ወራት ያህል እረፍት አድርግ ተባልኩ፤ ያኔም እረፍት እያደርግኩና ጂምም እየሰራው እያለ በራሴ ላይ ለውጥን ስመለከት የሁለተኛው ወር ላይ የኳስ ልምምድን ከክለቤ ጋር ማድረግ ጀመርኩ ያኔ ነው እንግዲህ ማይነር ጌም እየተጫወትን በነበረ ሰዓት ህመሙ ድጋሚ ሊነሳብኝ በመቻሉ እና እዚሀም ባደረግኩት ህክምናም ልድን ስላልቻልኩ ወደ ህንድ ሀገር ሄጄ ልታከም የተዘጋጀሁት፤ ስለዚህም ይህን ህክምና እንዳደርግ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ሊያደርግልኝ ለተዘጋጀው ክለቤ ቅ/ጊዮርጊስ ታላቅ ምስጋናን ማቅረብ እፈልጋለው፤ ቤተሰቦቼም ከእኔ ጎን ናቸውና ለእነሱም ምስጋና ይደረሳቸው እላለው፡፡
ሊግ፡- ከእግር ኳሱ ሜዳ ከራቅክ አሁን አምስት ወራቶችን አስቆጠርክ፤ ምንድን ነው የተሰማህ?

መሐሪ፡- በጉዳት ከኳስ መራቅ ከባድ ነው፤ በጣምም ያማል፤ የምትወደውን ነገር ያጣህ ያህልም ይሰማካልና ለእኔም ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሆነውብኝ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ህክምናዬን ወደ ውጪ ሀገር በመጓዝ ልታከም ስለተዘጋጀው ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ይመለሳል፤ ፈጣሪዬም ያድነኛል ብዬ ነው በማሰብ ላይ የምገኘው፡፡
ሊግ፡- በመከላከያው ጨዋታ የደረሰብህ ጉዳት ይሄን ያህል ከሜዳ ያርቀኛል ብለህ ጠብቀህ ነበር
መሐሪ፡- በፍፁም፤ ከእዚህ በፊት እንዲህ ያለ ምንም አይነትጉዳት አጋጥሞኝ የማያውቅ በመሆኑ ለእዚህን ያህል ጊዜ ከሜዳ ርቃለው ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፤ አንድአንዴ በህይወትህ ያልጠበቅከው ነገር ያጋጥመሃል፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በሊጉ የመጀመሪያው ዙር ተሳትፎው እንዴት አገኘከው?

መሐሪ፡- የዘንድሮው የውድድር ዘመን ላይ ክለባችን በአዲስ መልክ እና አቀራረብ ከመምጣቱ አኳያ አሁን ላይ ያለንን ተሳትፎ እኔ የምገልፀው በጥሩ መልኩ ነው፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ በጣም ተሻሽለን እንደምንመጣ ስለማውቅ አጠቃላይ ጥንካሬያችንን ያኔ እንመለከተዋለን፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ምን ውጤት ያመጣል?

መሐሪ፡- የሁለተኛው ዙር ሲጀመር ክለባችን የሚሻሻለው በሁሉም መልኩ ነው፤ ስለዚህም ዋንጫውን እናነሳለን፤ በዚህ በኩል የምንሰጋውም ነገር ምንም የለም፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P