የቅ/ጊዮርጊሱ ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/ ተሞሸረ
“የጫጉላ ሽርሽር ላይ ስለነበርኩ ለዛሬው ጨዋታ ባልደርስም ለቡድኔ መልካም ውጤትን እመኛለው”
“ፈጣሪም መልካም ባለቤትን ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ”
የቅ/ጊዮርጊሱ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/ ባለፈው እሁድ ከባለቤቱ አዜብ ተፈራ ጋር ተወልዶ ባደገበት የጋሞ ዞን ጨንቻ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ቃለ-ህይወት ቤተክርስቲያን ውስጥ የጋብቻ ስነ-ስርዓቱን በድምቀት ፈፅሟል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ እግር ኳስን ተወልዶ ላደገበት ለአርባምንጭ ከተማ እና ለሲዳማ ቡና ቡድኖች ተጫውቶ ያሳለፈው እና በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ለቅ/ጊዮርጊስ ቡድን በመጫወት ላይ የሚገኘው ስኬታማው የመሀል ሜዳ ተጨዋች እሁድ ዕለት የጋብቻ ስነ-ስርዓቱን ሲፈፅም በርካታ ጓደኞቹና ወዳጆቹ የተገኙ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጨዋቾች እና የስታፉ አባላቶች በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ውድድር ላይ ስላሉ በፕሮግራሙ ላይ ባይገኙም ለተጨዋቹ መልካም ምኞትን እንደገለፁለት እና በእዚህ እሱም ምስጋናውን እንደገለፀላቸው ታውቋል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የብሔራዊ ቡድናችን ተጨዋች የነበረውን ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮን/ እሁድ ዕለት ስለፈፀመው የጋብቻው ስነ-ስርዓትና ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ዙሪያ የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጠር ባለ መልኩ አናግሮት ምላሽን ሰጥቶታል፤ ተከታተሉት፡፡
እሁድ ስለ ፈፀመው የጋብቻ ስነ-ስርዓት
“ከባለቤቴ አዜብ ተፈራ ጋር የፈፀምኩት የጋብቻ ስነ-ስርዓት የአማረ እና የደመቀ ነበር፤ ሰርጋችንም በፈጣሪ መልካም ፈቃድ በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል”፡፡
ስለ ባለቤቱ እና ስለ ፍቅር ጊዜ ቆይታቸው
“ከእሷ ጋር አብሮ አደግ ጓደኛ ነን፤ አብረንም ነው የተማርነው፤ ላለፉት ሁለት ዓመታትም በምርጥ የፍቅር ጊዜም ነው በጋራ ልናሳልፍ የቻልነው፤ ስለ እሷ ማለት የምፈልገው በጣም ጥሩ እና መልካም የሆነች ሴት ነች፤ ፈጣሪ የግራ ጎኔ እንዳደርጋት እሷን ስለሰጠኝም በጣም አድርጌ አመሰግነዋለው”፡፡
ስለ ሚዜዎቹ
“በጨንቻ ከተማ በሚገኘው ቃለ-ህይወት ቤተክርስቲያን በፈፀምኩት ምርጡ የጋብቻ ፕሮግራሜ የእኔ ሚዜዎች የነበሩት አብሮ አደግ ጓደኞቼ ናቸው፤ እነሱ ሰርጌን ሊያደምቁልኝም ችለዋል”፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋቾች እና የስታፉ አባላት ጋብቻውን አስመልክቶ ስለላኩለት የመልካም ምኞት መግለጫ
“እነዚህ ተጨዋቾች፣ የስታፉ አባላቶች፣ አመራሮቻችን እና እንደዚሁም ደግሞ ሌሎችም የስፖርት ቤተሰቦች ጋብቻዬን አስመልክታችሁ በስልክም ሆነ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ ለላካችሁልኝ የመልካም ምኞት መግለጫ በፈጣሪ ስም ከልብ ላመሰግናችሁ እፈልጋለው፤ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋቾች በተለይ የእኔ ሰርግ ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፤ ሰርጉን በክረምት ላይ እንዳደርገውም ይፈልጉ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ሰርጉ በእዚህ ወቅት ሆነና እነሱ ደግሞ ጅማ ከተማ ላይ በውድድር ላይ ስለሆኑ ላይገኙ ቢችሉም ቡድኑን አሁን ስቀላቀል ለእኔ የተለየ ፕሮግራም እንደሚያዘጋጁልኝ ነግረውኛልና ፈጣሪ ይባርካችሁ ነው የምለው፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ የቀድሞ ቡድንህን ስለሚፋለምበት የዛሬው ጨዋታ
“የጫጉላ ሽርሽር ላይ ስለነበርኩ ለእዚህ ጨዋታ ደርሼ ባልሰለፍም ቡድኔ ቅ/ጊዮርጊስ የዛሬውን ጨዋታ እንዲያሸንፍ መልካም ምኞቴን እገልፃለው”፡፡
በመጨረሻ…
“ቅ/ጊዮርጊስ ባለፈው ጨዋታ ነጥብን ቢጥልም ወደ አሸናፊነት መንፈሱ እንደሚመለስ አውቃላው፤ ቀሪ ጨዋታም ስላለው ከመሪው ቡድን ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበቡም የማይቀር ነው፤ ስኳዳችን ሰፊ ስለሆነም በዘንድሮው በርካታ ጨዋታዎች በሚቀረው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይም ሻምፒዮና መሆኑ የማይቀር ነው፤ ከዛ ውጪ ልል የምፈልገው ለጋብቻዬ መልካሙን ሁሉ የተመኛችሁልኝና ሰርጌም የሰመረ እንዲሆን ያደረጋችሁልኝን እንደዚሁም ደግሞ በፀሎት ጭምር እኛን በማሰብ ያገዛችሁንን የቃለ-ህይወት ቸርች አባላቶችን ሁሉ አመሰግናችኋለው፡፡