Google search engine

“የአሰልጣኙን ታክቲክ አለመተግበራችንና ከእሱ ጋርም ስምምነት ሊኖረን አለመቻሉ ቡድናችንን ውጤት አሳጥቶታል””እግር ኳስን በጣም ከምትወድና ከምታፈቅር ልጅ ጋር  ትዳርን መመስረቴ በጣም አስደስቶኛል”ሄኖክ አዱኛ /ቅ/ጊዮርጊስ/

 

የአሰልጣኙን ታክቲክ አለመተግበራችንና ከእሱ ጋርም ስምምነት ሊኖረን አለመቻሉ ቡድናችንን ውጤት አሳጥቶታል”

“እግር ኳስን በጣም ከምትወድና ከምታፈቅር ልጅ ጋር  ትዳርን መመስረቴ በጣም አስደስቶኛል”

ሄኖክ አዱኛ /ቅ/ጊዮርጊስ/

የቅ/ጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛ ሰሞኑን ከባለቤቱ ፂዮን ቴዎድሮስ ጋር ተሞሽሯል። በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በኮሪደር ስፍራው ላይ ሲጫወት የምናውቀው ይኸው ተጨዋችን በጋብቻው ዙሪያና ስለ ዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአቸው እንዲሁም ስለ ራሱ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አንስቶለት ምላሽን ሰጥቶታል፤ ተከታተሉት።

ሊግ፦  ከባለቤትህ ጋር  በቅርቡ ተሞሽረካል፤ እንኳን ደስ አለህ? ጋብቻችሁም የአብርሃምና የሳራም ይሁን?

ሄኖክ፦ በጣም አመሰግናለው። እንኳንም አብሮ ደስ አለን።

ሊግ፦ የእርስ በርስ ግንኙነታችሁ እና ትውውቃችሁ ምን ያህል ዓመት ነው? የትስ ነው የተገናኛችሁት? ቀድሞ ጠባሹስ ማን ነው?

ሄኖክ፦ የእኔና የባለቤቴ ፂዮን ትውውቅ የሚጀምረው የዛሬ አምስት ዓመት ነው።  ቀድሞ ጠባሹም እኔ ነበርኩ። ያኔ እኔ ለድሬዳዋ ከተማ በምጫወትበት ጊዜም ነው ከእሷ ጋር ልንተዋወቅም የቻልነው። በወቅቱ ታዲያ ይህቺ ወጣት አልፎ አልፎ ኳስ የምታይና የቡድኑም ደጋፊ ስለነበረች ሳያት ወደድኳት። የእዛው ሀገር ልጅም ስለነበረች በደንብ ትውውቅም አደረግን። በኋላም እየተግባባን መጣንና ሰኔ 6 ቀን ለተከናወነው የጋብቻ ስነ-ስርዓት ልንበቃ ቻልን።

ሊግ፦ ባለቤትህ አሁንም የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊ ነች ወይንስ ክለብ ቀየረች?

ሄኖክ፦ አሁንማ የሳንጃው ናት። ምክንያቱም እኔ የቡድኑ ተጨዋች ነኝና”።

ሊግ፦ እግር ኳስን በደንብ ትወዳለች ማለት ነው?

ሄኖክ፦ አዎን። የውጪ ሀገር ኳስን ጨምሮ በደንብ ትከታተላለች። የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊና የክርስቲያኖ ሮናልዶም አድናቂ ነች”።

ሊግ፦ የእግር ኳስን የምትወድ ሚስት ማግባት የተለየ ስሜትን ይሰጣል?

ሄኖክ፦ አዎን፤ በጣም። እግር ኳስን በጣም ከምትወድና ከምታፈቅር  ልጅም  ጋር  ትዳርን መመስረቴም በጣም አስደስቶኛል። ምክንያቱም እሷ ኳስን በማወቋ እኔን በደንብ አድርጋ ተረድታኛለች። ጥሩ ስሆንም ሆነ ሳልሆን ሁሌም ከጎኔ ሆና የምትሰጠኝ ምክርም አለና የእሷ እገዛ በጣም ጠቅሞኛል። ውዷ ባለቤቴን በዚሁ አጋጣሚ  ለምታደርግልኝ ነገር ሁሉ አመሰግናታለው።

ሊግ፦ ትዳር  ለስፖርተኛ ምን ይመስላል?

ሄኖክ፦ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። ከብዙ ነገሮች ተቆጥበህ እንድትቀመጥም ያደርግሃል። ከዛ ውጪም ስለ ወደፊት ግብህም አርቀህ እንድትመለከትም ያደርግሃልና ስለ ጥሩነቱዐገብታችሁ ሞክሩትም ነው የምላችሁ።

ሊግ፦ በእግር ኳስ ውስጥ ለየት ለየት ክለቦች ተጫውተህ አሳለፍክ?

ሄኖክ፦ በወሊሶ ከተማ ቡድን ውስጥ ነው መጫወት የጀመርኩት። ከዛም ለሀላባ ከተማ፣ ለድሬዳዋ ከተማና ለጅማ አባጅፋር ቡድን ከተጫወትኩ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመቀላቀል እስከ መጪው ዓመት ድረስ የቡድኑ ተጨዋች ነኝ።

ሊግ፦ በእግር ኳስ ባሳለፍከው ህይወት ደስተኛ ነህ?

ሄኖክ፦ እስካሁን ድረስ አዎን። ምክንያቱም የሊጉን ዋንጫ በጥሩ ብቃት ላይ ሆኜ በመጫወት አንድ ተጨዋች የሚመኘውን የሊጉን ዋንጫ  ከጅማ አባጅፋር  ጋር ላነሳ ችያለውና ይበልጥ ደግሞ ደስተኛ የምሆነው ከቅዱስ ጊዮርጊስም ጋር ሻምፒዮና ስሆን ነውና  ያኔ  ደስታዮም ሙሉ ነው የሚሆነው።

ሊግ፦ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታህ የሊግ ዋንጫን ለማንሳት አልቻልክም፤ ስሜቱን እንዴት አገኘኸው?

ሄኖክ፦ ከባድ ነው፤  ከባድነቱ ደግሞ ድልን ከለመደ ቡድን ጋር በተከታታይ ዓመት ላይ ለማንሳት አለመቻሌ ነው። በጅማ ቆይታዬ ዋንጫን ሳነሳ ይሄ ለእኔ ትልቅ ታሪክና ወደፊት ደግሞ ለማገኘው ልጅ የምነግረው ታሪክ ስለሚኖረኝ የተደሰትኩትን ያህል በቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን ድል ልጎናፀፍ አለመቻሌ በጣሙን እያስቆጨኝ ነው የሚገኘውና ያሳለፍናቸው ዓመታቶች ያናደዱኝም ጭምር ናቸው።

ሊግ፦ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ውስጥ ውጤት ሲጠፋ ስሜቱን እንዴት አገኘኸው?

ሄኖክ፦ ማንም ምንም ነገርን አይቀበልህም። ቤቱ እንደ ሌሎች  ቡድኖች አይደለም። ወደዚህ ቡድን ስትመጣ ሁሌም አሸናፊ ነው መሆን ያለብህ። የሽንፈትና የአቻ ውጤት እዚህ እኛ ጋር አይሰራም። ስለዚህም ቡድኑ ጋር ጫና ስላለም ሁሌም ራስህን ለስራ ነው ማዘጋጀት ያለብህ።

ሊግ፦ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ግልጋሎትን ሰጥተህ አልፈሃል?

ሄኖክ፦ በምሰለፍባቸው ጨዋታዎች የቻልኩትን ያህል ጥቅም ለመስጠት ሙከራን አድርጌያለው። ይሄ የሚታይልህ ግን ቡድኑም ለውጤት ሲበቃም ነውና የመጪው ዓመት ላይ ደግሞ አገራችንን ሰላም ያድርግልን እንጂ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ከአሁን በተሻለ ብቃት ላይ ለመገኘትና ቡድኔንም  በደንብ ለመጥቀም እጥራለው።

ሊግ፦ ቅዱስ ጊዮርጊስን ዘንድሮ ምን ውጤት አሳጣው?

ሄኖክ፦ የመጀመሪያውና ዋንኛው የአሰልጣኙን ታክቲክ አለመተግበራችን ነው ከዛም ሲቀጥል ከእሱ ጋር ስምምነት ሊኖረን አለመቻሉ ቡድናችንን ውጤት አሳጥቶታል።

ሊግ፦ ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ አንስቶታል። በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?

ሄኖክ፦ ለፍተዋልና ውጤቱ ይገባቸዋል ነው የምለው።

ሊግ፦ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም ውጤት አጥቷል። ይሄ ችግሩ ይቀረፋል?

ሄኖክ፦ በአንዴ መቶ ፐርሰንት ባልልህም ከፍተኛ ቁጭት አሉብን። ያሉብንን ችግሮችም ተጋፍጠን ማለፍም ይኖርብናል። ለዚህ ታላቅ ክለብ ከወዲሁ ብዙ ነገሮችን እያሰብንለት ከሄድን ውጤታማነቱን የማንመልስበት ምክንያት የለም።

ሊግ፦ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተሸለመ ምን አልክ?

ሄኖክ፦ እሱ ጥሩ የውድድር ሲዝንን አሳልፏል። የሚገባውን ሽልማትም ነው ያገኘውና ለእሱም ሆነ ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮኖቹ ፋሲል ከነማዎች እንኳን ደስ አላችሁ ልል እወዳለው።

ሊግ፦ ቤትኪንግ እንደተጠናቀቀ ወደየት ሄድክ?

ሄኖክ፦ ዘንድሮ ሳላርፍ ነበር የተጫወትኩትና መጀመሪያ በጣም ወደናፈቁኝ ወደ ቤተሰቦቼ ጋር ነበር ለእረፍት የሄድኩት ከዛም ካለፈው ሁለት ዓመት ጀምሮ አብራኝ ከምትኖረው ባለቤቴ ጋር ወደ ትውልድ ሀገሬ ነቀምት በመሄድ ትዳርን መሰረትኩኝ። አሁን ላይ ደግሞ የጂም ልምምዴን በማድረግ ላይ ነው ያለሁት።

ሊግ፦ በመጨረሻ?

ሄኖክ፦ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ብዙ ቻሌንጆችን አሳልፌያለው። እነዛን ተቋቁሜም ለዚህ እንድበቃ ያደረጉኝን ፈጣሪዬን፣ አሰልጣኝ ገብረመድን ሀይሌን፣ ሚሊዮን አካሉን፣ መሰረት ማኔን፥ ዘሪሁን ሸንገታንና ሌሎቹን ስማቸውን ያልጠቀስኳቸውን አሰልጣኞች ለማመስገን እፈልጋለው። ይህን ካልኩ በኋላ ደግሞ የእኔ የኳስ እልምና ግብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊግ ዋንጫን በማንሳት በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ቡድኑ እንዲነግስና በፕሮፌሽናል ተጨዋችነች ደረጃም ወጥቶ መጫወትም ነው።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P