Google search engine

“የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ድላችንን እንደፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮናነት ነው የምንቆጥረው”በዛብህ መላዮ /ፋሲል ከነማ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

በኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ጨዋታ ፋሲል ከነማ መቀለ 70 እንደርታን በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ 1ለ0 አሸንፎ የውድድሩ ሻምፒዮና ሆኗል፡፡ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የእዚህ የዋንጫ ባለቤት በመሆኑም በቡድኑ አባላትና ደጋፊዎቹ ውስጥ ትልቅ የደስታ ስሜትን ሊፈጥርም ችሏል፡፡
ፋሲል ከነማ ይህን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ካነሳ በኋላም ስለቡድኑ ድል እንደዚሁም ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ዘንድሮ በምን መልኩ ለመቅረብ እንደተዘጋጁና ከራሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለቡድኑ ጥሩ ከሚንቀሳቀሱት ተጨዋቾች መካከል የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹን በዛብህ መላዮን አነጋግረነው ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ጨዋታ መቀለ 70 እንደርታን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምራችኋል፤ ባገኛችሁት ውጤት እናንተ ጋር ያለው የድል ስሜት ምን ይመስላል?
በዛብህ፡- የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ጨዋታ ላይ መቀለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ድል ያደረግንበት የማክሰኞ ዕለቱ ግጥሚያ ለእኛ በውስጣችን የፈጠረልን የደስታ ስሜት ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ የሆነና በጣምም ያስደሰተን ነው፤ ይሄ ድል ለቡድናችን ከጨዋታው በፊት ጀምሮ ትልቅም ትርጉም ነበረውና ግጥሚያውን በድል አድራጊነት በማጠናቀቃችን የተለየ የደስታ ስሜትም ነው ሊፈጠርብን የቻለው፡፡
ሊግ፡- በአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫው ጨዋታ መቀለ 70 እንደርታን በማሸነፋችሁ ለግጥሚያው የተለየ ትርጉም እንድትሰጡት ያደረጋችሁ ነገር ምንድን ነው?
በዛብህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ ባለፈው ዓመት ላይ ያጣንበትን ምክንያት እኛ ብቻ ሳንሆን ማንም ያውቀዋል፤ ኳሳዊ ባልሆነ ሁኔታም ነው ሻምፒዮና እንዳንሆን የተደረገውና በእዚህ የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ጨዋታ ላይ በውስጣችን ከነበረው ከፍተኛ የቁጭት ስሜት በመነሳት ነው ይህን ግጥሚያ የግድ ማሸነፍ አለብን በሚል ከፍተኛ የአሸናፊትና የጉጉት ስሜት ወደሜዳ በመግባት ጥሩ ተጫውተን የዋንጫው ባለቤት ልንሆን የቻልነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ልታነሱ ችላችኋል፤ የደስታው መጠን ግን የአሁኑ ይበልጣል፤ የተለየ ምክንያት አለው?
በዛብህ፡- አዎን፤ ቡድናችን የሁለቱም ዋንጫዎች ባለቤት ቢሆንም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ሲያነሳ የነበረው የደስታ መጠን በጣም ከፍ ያለ ነበር፤ ያንንም ያለ ምክንያት አላደረግነውም፤ ክለባችን ዓምና የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያጣበትን ሁኔታ ሁላችንም ስለምናውቀው ነው ይህን የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ እኛ አንሳን ማለት ድሉን እንደ ፕሪምየር ሊጉ ድል ስለምንቆጥረው ጨዋታውን ካሸነፍን በኋላ በጣም የተደሰትነው፡፡ ስለዚህም አሁንም ደግሜ እናገረዋለው መቀለ 70 እንደርታን ያሸነፍንበት የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ድል እንደፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮናነት ነው የምንቆጥረው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ መቀለ 70 እንደርታን ባሸነፈበት ጨዋታ በሁለቱ 45 ደቂቃዎች የነበረው አቋም ምን ይመስላል?
በዛብህ፡- ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር በነበረን የማክሰኞ እለቱ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ግጥሚያውን በድል አድራጊነት ለማጠናቀቀ ከነበረን ከፍተኛ ፍላጎት አንፃር በጉጉት እየተጫወትን ስለነበር ብዙም ጥሩ አልነበረንም፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን በጨዋታው ላይ በጣም ተሻሽለን ስለቀረብንና ከእነሱም በተሻለ መልኩ ልንጫወት ስለቻልን የጨዋታው አሸናፊ ልንሆን ችለናል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከተማ እና የመቀለ 70 እንደርታ ቡድኖች ማክሰኞ ዕለት ባደረጉት ጨዋታ ሁለታችሁም ጋር የነበረው ተመሳሳይ ነገር ምን ነበር?
በዛብህ፡- በአሸናፊዎች አሸናፊው ጨዋታ በመቀለ 70 እንደርታም ሆነ በእኛ በኩል የነበረው ተመሳሳይ ነገር ቢኖር ይህን ግጥሚያ አሸንፎ በመውጣት የዋንጫው ባለቤት ለመሆን የነበረው የአሸናፊነት ፍላጎት በጣም ከፍ ያለ መሆኑ ነበር፤ ሁለታችን በምንገናኝበት እያንዳንዱ ጨዋታ ሁሌም ቢሆን እነሱ በእኛ እኛም በእነሱ መሸነፍን ፈፅሞ የማንፈልግ መሆናችንም ጭምር ያመሳስለን ነበርና ግጥሚያው በጣም ውጥረት ነበረበት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ ያጣንበትን ምክንያት እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙዎቹ የሚያውቁት ነው ብለሃል፤ ዋንጫውን በምን ነበር ያጣችሁት?
በዛብህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ላይ እኛ ያጣነው ተበልጠን ወይንም ደግሞ ፌር በሆነ መንገድ አይደለም፡፡ ውጤት ያጣነው በዳኛ ማሳበቤ ሳይሆን ዳኛው የተሳሳተ ውሳኔዎችን በማሳለፉ ነው፤ ይኸውም በጊዜው በሃገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ ካለው የፖለቲካው ችግር አኳያ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በዳኞች የማትፈርደው ነገር ስላለና ተመስገንም ብለህ የምትወጣበት እና እንኳንም በዚሁ አለፈም የምትልበት ነገር ስላለ ዋንጫውን ያጣንበትን ሁኔታ አሳማኝ አይደለም በሚል ብቻ ልናልፈው ችለናል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማጣቱ ከሽሬ እንደስላሴ ጋር ያደረገው ጨዋታ ነው በተደጋጋሚ እየተገለፀ የሚገኘው፤ ያንን እስኪ ከአንተ አንደበት እንስመው?
በዛብህ፡- አዎን፤ የሽረው ጨዋታ ዋንጫውን እንዳናነሳ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነገር ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን የአሸናፊዎች አሸናፊውን ዋንጫ አሁን ላይ ስላገኘነውና ይሄን ዋንጫም እንደ ደጋፊዎቻችን ሁሉም እኛም ድሉን እንደፕሪምየር ሊጉ ድልም ስለቆጠርነውም ያለፈውን በግፍ ያጣነውን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ድል አሁን ላይ ረስተነዋል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የሽረው ጨዋታ ላይ ተፈፅሞብኛል የሚለው በደል ምን ነበር?
በዛብህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው ላይ በሃገሪቱ ውስጥ ካለው የፖለቲካ ሽኩቻ አንፃር ወደትግራይ ክልል አካባቢ ሄዶ ውጤት ማምጣት በጣም ከባድ ስለነበር ለእኛም ፋሲል ከነማዎች የገጠመን ሁኔታ ይሄ ነበር፡፡ ወደእዛ ሄደን ስንጫወት መጀመሪያ ላይ የተፈጠረው ነገር ይፈጠር ብለን ነበር የተጓዝነው፤ ከሞትንም እንሙትም እስከማለት ደርሰንም ነበር ተጉዘን የተጫወትነው፤ በጨዋታው እኛ ሽረዎችን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል በሜዳችን እስከምንጫወት እስኪመስለን ድረስ በልጠናቸው ነበር የተጫወትነውና በኋላ ላይ ግን በእኛ ላይ የተሰጠብን ፔናሊቲ ዳኛው በጣም ዘግይቶና ከ30 ሰከንድ በኋላም ቫር አይቶ በሚመስል መልኩ ነው እኛ በካውንተር አታክ ሄደን ጎል ልናገባ ስንቃረብ የሰጠብን ነበርና ቫር በሚመስል ውሳኔ ነው የእኛ ተጨዋች ያሬድ ላይ ጥፋት ተሰርቶና ለእነሱ ተጨዋችም ቢጫ ካርድ ይሰጠዋል ብለን ስንጠብቅ በበደል እኛ ዋንጫውን እንድናጣ የተደረግነው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለማንሳት መቻሉ ድሉን እንደፕሪምየር ሊግ ነው የምንቆጥረው ብለሃል፤ ከዚህ በመነሳት ቡድናችሁ ዘንድሮ አስፈሪ ይሆናል?
በዛብህ፡- አዎን፤ ምክንያቱም ይሄንን ዋንጫ ማንሳታችን የሚያኮራን ሳይሆን እንደመነሳሻ ድልም ነው የምንቆጥረው፤ ከዛ ባሻገር ውጤቱም የ2011 ዓ/ም እና ያለፈ ውድድርም አድርገን ስለምንመለከተው አሁን ላይ ለ2012 ዓ.ም ውድድራችን ነው በልዩ መልክ እየተዘጋጀን የምንገኘውና ፋሲል ከነማ አስፈሪ ቡድንን ይዞ እንደሚመጣ ምንም አይነት ጥርጣሬው የለኝም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እና የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከፋሲል ከነማ ጋር ለማንሳት ችለሃል፤ እነዚህ ስኬቶች ለአንተ ትልቁ ድሎችህ ናቸው?
በዛብህ፡- የፋሰል ከነማ የተጨዋችነህ ዘመን ቆይታዬ ላይ በአሁኑ ሰአት እያሳካዋቸው ያሉት ድሎች አዎን ለእኔ ትልቅ የሚባሉ ድሎች ናቸው፤ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ከዚህ ቀደም ከወላይታ ዲቻ ጋር ለማግኘት እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታም ላይ ለመጫወት ችያለሁ፡፡ የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ትልቁ ታሪክ ዋንጫን ለማግኘት መቻል ነውና ይሄንን ድል በማሳካቴ ተደስቻለሁ፡፡ ግን አንድ የሚቀረኝ ዋንጫ አለ፡፡ ይሄም የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ዛሬ በይፋ ይጀመራል፤ ፋሲል ከነማ ለእዚህ ውድድር በምን መልኩ ተዘጋጅቷል? ምን ውጤትስ በእዚህ ዓመት ያመጣል?
በዛብህ፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ዛሬ ለሚጀመረው የዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ውድድር እያደረገ ያለው ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፤ ከመጀመሪያው ጨዋታ አንስቶም ነው ለሚያደርጋቸው እያንዳንዱ ግጥሚያዎች በምን መልኩ ትኩረት ሰጥቶ መግባት እንዳለበት በማወቅ እና እንዴትም የጨዋታዎቹ አሸናፊ መሆን እንደሚኖርበትም በመረዳት ልምምዱን ሲሰራ የነበረው፤ የቡድናችን የመጀመሪያው ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር ከሜዳችን ውጪ የምናደርገው ነው፤ ቡድኑንም ሜዳውንም በደንብ አድርገን ስለምናውቀው የጨዋታው አሸናፊ እንሆናለን፤ በእዚህ ዓመት የምናመጣውን ውጤት በተመለከተ ፋሲል ከነማ የሊጉ አሸናፊ ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- የአዳማ ከነማ ላይ ስታደርጉት የነበረው የሲቲ ካፑ ተሳትፎ ለፕሪምየር ሊጉ ውድድር የቱን ያህል ይጠቅማችኋል?
በዛብህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ከመጀመሩ በፊት በአዳማ ከተማ ላይ ስናደርገው የነበረው የአቋም መለኪያ የሲቲ ካፕ ጨዋታችንን ምንም እንኳን በሀድያ ሆሳዕና በፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈና ለዋንጫ ለማለፍ ባንችልበትም ጥሩ መዘጋጃ ሆኖልናል፡፡ በሃድያ የተሸነፈው ጥሩ ሳንሆን ቀርተን ሳይሆን በኳስ በሚያጋጥም አይነት ሽንፈት ነው፡፡ ውድድሩ ክፍተቶቻችንን የምናይበትም ስለሆነ ዘንድሮ ጥሩ ቡድን ይዘን እንቀርባለን፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ቆይታህ በክረምቱ ወራት ያልጠበቅከው ህመምን አስተናግደህ ነበር፤ በፍጥነት አገገምክ ልበል?
በዛብህ፡- አዎን፤ ለእዛም ፈጣሪ ይመስገን፡፡ በወቅቱ ያጋጠመኝ ህመምን መጀመሪያ ላይ ቀለል አድርጌ ነበር የተመለከትኩት፤ በኋላ ላይም የጤንነት ምርመራዬን ሳደርግ ህመሜ የዲስክ መንሸራተት ሆኖ ተገኘና በጣም ነበር የተደናገጥኩት፡፡ ህመሜ ወዲያው ሲነገረኝም ለ3 ጊዜያት ያህል ኤም አር አይም ተነስቼም ነበርና ሀኪሞች ለህመሙ በቂ እረፍት ያስፈልግሃል ሲሉኝና ትርኢትም ሲያደርጉኝ የእነሱን ትህዛዝ በመፈፀምና በቂ ምርመራንም ስላደረግኩ አሁን ላይ ጤነኛ ሆንኩኝ፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማን በእዚህ ዓመት በምን መልኩ ልትጠቅመው ተዘጋጅተሃል?
በዛብህ፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ የሚቀርበው የአምናውን ነገር በማስቀጠል እና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ደግሞ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ላይ በመጀመሪያ ዙር የነበረበትን ክፍተት ደፍኖ ለመምጣት ነውና ይሄ ቡድን አመቱን ሙሉ ወጥ የሆነ አቋምን እንዲያሳይ እና የፕሪምየር ሊጉንም ዋንጫ እንዲያነሳ የሚቻለኝን ነገር ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቻለው፤ እንደፋሲል ከነማ ተጨዋችነቴ ከዛ ውጪም ቡድኔን በጣም ከመጥቀም ባሻገር አምና ለብሄራዊ ቡድን ከተመረጥኩ በኋላ በጉዳት ከቡድኑ ውጪ የሆንኩበት ሁኔታ ስላለ ይሄን በድጋሚ ለብሔራዊ ቡድን የመመረጥ እድሉን ጠንክሬ ሰርቼ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁ ላይ አምና እንደቡድን የነበረባችሁ ክፍተት ወይንም ደግሞ ድክመት ምን ነበር?
በዛብህ፡- የፋሲል ከነማ ክለብ በአምናው የውድድር ተሳትፎው ላይ ክፍተት የነበረበት የተጨዋቾች ስብስቡ እንደ አዲስ ከመዋቀሩ አኳያ የመጀመሪያው ዙር ላይ ነጥቦችን ሊሰበስብ አለመቻሉ ነው፤ የሁለተኛው ዙር ላይ ግን ወደ ጥሩ አቋምና የጨዋታ ሪትም ውስጥ በመግባታችን በርካታ ነጥቦችን አግኝተን እስከዋንጫው ፍፃሜ ድረስ ልንፎካከር ችለናል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማው በዛብህ መላዮ የክለቡ አጋሩ ሱራፌል ዳኛቸው ሚዜ ነበር፤ እሱስ መች ነው ሙሽራ የሚሆነው?
በዛብህ፡- /እንደመሳቅ ብሎ/ ዘንድሮ ነዋ! ከወራቶች ቆይታ በኋላ ሙሽራ ልሆን እየተዘጋጀሁ ይገኛል፡፡
ሊግ፡- የአንተን ጥምረት ብታስተዋውቀን? እሷ ለአንተ ምን ማለት ነች?
በዛብህ፡- የእዚህ አመት ላይ እኔ የማገባት ባለቤቴ ቅድስት አመነ ትባላለች፤ የአንድ አመት ከአምስት ወራት የፍቅር ጓደኛዬም ነች፤ ከእሷ ጋር የተዋወቅንበት መንገድ ለጨዋታ ወደ መቀሌ በተጓዝንበት ጊዜ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስለነበረች በጓደኛዬ አማካይነት ነው ልተዋወቃት የቻልኩት፤ በመቀጠልም በደንብ ተግባባንና ከዛም ጥሩ የፍቅር ጓደኛሞች ሆንን፤ እሷን ስገልፃት በጣም ጥሩ ልጅ ናት፤ ሙያዬን እና ስራዬን ታከብርልኛለች፡ እንደ እናትም ሆና ነው በመልካም ሁኔታ የምትንከባከበኝ፤ ስለዚህም ለእሷ ትልቅ ፍቅርም አለኝና ላመሰግናት እወዳለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ ስለቤተሰብህ እና ስለፋሲል ከነማ ደጋፊዎች አንድ ነገር በለንና እናጠቃል?
በዛብህ፡- ቤተሰቦቼ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ናቸው፤ ዛሬ ላይ በኳስ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ብዙ ነገሮችን አድርገውልኛል፡፡ 6 ልጆች አለን፤ ከእዛ ውስጥ ሁለታችን እኔና አሁን ላይ ኳስን ያቆመው እንዳለ መላዮ ከቤቱ ኳስ ተጨዋቾች ነበርን፡፡ እኔ በኳሱ በመቀጠል እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ለፍቻለሀ፡፡ ለእዚህ ደግሞ ወንድሜ እንዳለ ያደረገልኝ አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነውና ለእሱና ሁሌም ለእኔ ለሚጨነቁትና ለሚፀልዩልኝ ቤተሰቦቼ ከፍተኛ ምስጋና አለኝ፡፡ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችን በሚመለከት እነሱ ለቡድናቸው ልዩ ፍቅር ነው ያላቸው፤ ስለ እነሱ ምን ብዬ እንደምገልፅልህ አላውቅም፤ ቡድኑን እንደ ቤተሰባቸው እና እንደማንነታቸውም ነው የሚቆጥሩትና ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: