በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብን ከመቀላቀሉ በፊት ለደደቢትና ለወልዋሎ አዲግራት ቡድኖች በጥሩ ብቃቱ ተጫውቷል፤ አሁን ላይ ደግሞ በቡና ቆይታው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን እያሳየ ይገኛል፤ ይሄ ተጨዋች አለምአንተ ካሳ /ማሪዮ/ ሲባል ተጨዋቹን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግረነው የሚከተለውን ምላሽ ለዝግጅት ክፍላችን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና በኮቪድ 19 ተቋርጦ ውድድሩ እስከ መሠረዝ ደርሷል፤ አሁን ላይ ጊዜውን በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው?
አለምአንተ፡- የእግር ኳስ ውድድራችን በኮቪድ 19 ከተቋረጠ በኋላ ጊዜዬን እያሳለፍኩ ያለሁት ጠዋት እና ከሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ከመስራት ባሻገር አልፎ አልፎም የኳስ ማንቀርቀብ ልምምዶችን በመስራት ነው፤ ከዛ ውጪም የእዚህ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎም በየአካባቢው እንደሚደረገው ሁሉ እኔም በምኖርበት ሰፈሬ ኳስ ሜዳ አካባቢ ይህን ከባድና አስከፊ ቫይረስ በምን መልኩ ነው እኛና ህብረተሰቡ መከላከል የሚኖርብን በሚለው ጉዳይ ላይ ተሳታፊ በመሆንና የእዚህም ወረርሽኝ በሽታን መምጣትን ተከትሎም በአቅም ውስንነት ብዙ የሚጎዱ አካላቶች አሉና ከእነሱ ጎን በመሆን ነው የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በግሌም ሆነ ከሰፈሬ ጓደኞችና ልጆች ጋር በመሆን በምንችለው አቅም የተለያዩ እርዳታዎችን እያደረግን የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ህዝባችን እየተጠነቀቀ ነው ማለት ይቻላል?
አለምአንተ፡- በፍፁም፤ በታክሲ አካባቢ ካለው ግፊያና በአንድ አንድ የገበያ ቦታዎችም ላይ ከምመለከተው ነገር በመነሳት ህዝቡ እየተጠነቀቀ ነው ብዬ አላስብም፤ ስለዚህም በእዚህ ላይ የሚመለከተው አካልም ሆነ ህብረተሰቡ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል፡፡
ሊግ፡- አንተስ እየተጠነቀቅክ ነው ማለት ይቻላል?
አለምአንተ፡- በጣም እንጂ፤ ብዙ ጊዜም ከቤቴ አልወጣም፤ ከምወዳት ባላቤቴ ጋርም ነው እቤት ውስጥ በመዋል ደስተኛ የሆንበትን ምርጡንና ጣፋጩን የፍቅር ጊዜያታችንን እያሳለፍን የምንገኘው፤ አልፎ አልፎ ከቤቴ በምወጣበት ሰዓትም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከመንግስት የሚወጡ መመሪያዎችንም በማክበር ራሴን ብሎም ደግሞ ቤተሰቦቼንና ማህበረሰቡንም እጠብቃለው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ውድድሩ አሁን ላይ በመሠረዙ በዋናነት የናፈቀህ ነገር ምንድነው?
አለምአንተ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊና እግር ኳሱ፤ በተለይም ደግሞ የአዲስ አበባ ስቴድየም ላይ ሆነህ በእነሱ ፊት መጫወት ደስ ይላልና ያ በጣም ናፍቆኛል፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 እስካሁን ምን ያህል ሳኒታይዘር ጨረስክ?
አለምአንተ፡- እንደመሳቅ ብሎ እስካሁን አልቆጠርኳቸውም፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ተጫውተህ ባሳለፍክባቸው ጊዜያቶች ምርጡ ጨዋታዬ የምትለው?
አለምአንተ፡- የእግር ኳስ ዘመኔ ላይ ለእኔ ምርጡ ጨዋታዬ በመቐለ ኢንተርናሽናል ስቴድየም ለወልዋሎ አዲግራት ክለብ ስጫወት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያደረግነውን ነው፡፡ ይህ ጨዋታ የመጀመሪያ ምርጫዬ ሊሆን የቻለውም በጣም ጥሩ የተንቀሳቀስኩበት ከመሆኑ ባሻገር መቐለዎች እኛን ይመሩን ስለነበርና ሰአትም ይገድሉ ስለነበር በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የአቻነቱን ጎል ያስቆጠርኩበት ስለሆነ ነው፤ ከእዚህ ጨዋታ በመቀጠል ደግሞ ሌላው ምርጥና ጥሩ ጨዋታዬ የምለው ለኢትዮጵያ ቡና በሲቲ ካፑ ከሰበታ ከተማ ጋር ስንጫወት ያደረግነውን እና የጨዋታውም ኮከብ ተጨዋች የተባልኩበትን ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ተጫውተህ ባሳለፍክባቸው ጊዜያቶች በየስፍራው የአንተ ምርጥ ተጨዋቾች እነማን ናቸው?
አለምአንተ፡- የእግር ኳስን ተጫውቼ ባሳለፍኩባቸው ጊዜያቶች ለእኔ በየቦታቸው የሚመቹኝ እና ምርጥም የምላቸው ተጨዋቾች ከግብ ጠባቂዎች ታሪክ ጌትነትን ነው፤ ጥሩም ችሎታ አለው፤ ከተከላካዮች ደግሞ የመጀመሪያ ምርጫዬ አክሊሉ አየነው ነው፤ የእሱ አየር ላይ ሆኖ የሚመልሳቸው ኳሶችና፤ በራሱም የመከላከል ክፍል ላይ የሚያገኛቸውን ኳሶች በመቁረጥ እንደ መሀል ሜዳ ተጨዋቾች ኳሷን ወደፊት ይዞ የሚወጣበትና የሚሄድበት መንገድ ደስ ይለኛል፡፡ ሲጫወትም እንቅስቃሴው ይስበኛል፤ የመሃል ሜዳ ተጨዋች ሆኖ ደግሞ ለእኔ ሲጫወት በጣም ደስ የሚለኝና ቀዳሚው ምርጫዬ ሳምሶን ጥላሁን ነው፤ ሳምሶን በጣም ታጋይና ሰራተኛም ነው፤ ሜዳም ላይ በታታሪ ተጨዋችነቱ በጣምም ይለፋልና እሱ ደስ ይላል፤ ከአጥቂዎች ደግሞ የመጫወት እድሉን ከሁለቱ ጋር በአንድ ላይ ባላገኝም ጌታነህ ከበደና ሳላህዲን ሰይድ ምርጫዎቼ ናቸው፤ ሌላው ምርጫዬ አሁን አብሬው እየተጫወትኩ ያለሁት አቡበከር ናስር ነው፤ እሱም ምርጥ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ነው፤ እነዚህ አጥቂዎች እኔ ለምፈልጋቸው እንቅስቃሴዎች በጣሙን የሚመቹኝም ናቸው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ውድድራችን መቋረጡን ስትሰማ ምን አልክ?
አለምአንተ፡- እንደ አንድ የእግር ኳስ ተጨዋች የሚሰማህና ብዙም የምታስበው ነገር አለና ኳሱ መቋረጡ በጣም ያስቆጫል፤ በተለይ ደግሞ ከቡና ጋር ውጤታማና ሻምፒዮና የመሆን እልምና ሀሳብም አለና ያም ነው ትዝ ያለኝ፤ ሆኖም ግን መንግስት ይህን ኳስ ያቋረጠውና የዘጋው ለህዝቡ ጤናና ህይወት ሲልም ነውና መቋረጡ ቢያሳዝነኝም ስቴድየም ህዝብና ሰው የሚበዛበትም ቦታ ሆኖ በመገኘቱ እንደዚሁም ደግሞ ንክኪና ትንፋሽም የሚኖርበት ስፍራ በመሆኑና ለቫይረሱም የሚያጋልጥ ቦታ በመሆኑና ለሁሉም ነገርም ጤና የሚበልጥ በመሆኑ የኳሱ መዘጋት ተገቢና ልክ ነው”፡፡
ሊግ፡- አሁን በቤት ውስጥ ስትውል ፊልሞችን ታያለህ?
አለምአንተ፡- አዎን፤ በተለይ ደግሞ የእግር ኳስ የበፊት ኳሶችን አያለሁ፤ ወደ 20 የሚደርስ ሲዲም አለኝ፤ በተለይ ደግሞ በባርሴሎና በሰፊ ግብ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የባርሳና የማድሪድ ጨዋታ አይረሳኝም፤ ጨዋታው ልዩ ነበር፡፡ ዣቪና ኢኒዬስታም ያሳዩት ብቃትና የፒኬም ጎል በጣም ምርጥ ነበር፡፡
ሊግ፡- ስለ ባለቤቱና የትዳር ህይወቱ?
አለምአንተ፡- ባለቤቴ ሜሮን ብርሃኔ ትባላለች፤ ጥሩ የሆነ የትዳር ህይወትንም እጠመራን ነው የምንገኘው፤ በጣምም ነው የምወዳት፤ ለእኔ እሷ ማለት ከማወራህ በላይም ነው በልዩ ቃላቶች የምገልፃት፤ እሷ እግር ኳሱን በጥሩ ሁኔታ እንዳስኬደውና በቂ እረፍትም እንዳደርግ የሚቻላትን ሁሉ እያደረገች ነች፤ አሁን ላይ ለደረስኩበት ደረጃም የእሷ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነውና ከምስጋና በተጨማሪ በጣም ነው የምወድሽ በጣምም ነው የማከብርሽ ልላት እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንደዚሁም ደግሞ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ተጫውቶ ያሳለፈው የቀድሞ ተጨዋች ተስፋዬ ኦርጌቾ ማረፉን ስትሰማ እንደ አንድ ተጨዋች ምን አልክ?
አለምአንተ፡- የተስፋዬ ኦርጌቾ መሞትን በድረ ገፅ ላይ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት፤ እኔ እሱ ሲጫወት ባልደርስበትም ባላየውም አይደለም ኳስ ተጨዋች ማንም ሰው ሲሞት ራሱ ያሳዝናልና እኔም ከፍተኛ ሀዘን ነው የተሰማኝ፤ በተለይ ደግሞ በእነሱ ዘመንና አሁን ያለው ጊዜም የሚለያይ እና እነሱም በገንዘብ ደረጃ ያልተጠቀሙበት ዘመንም ነበርና እንደ ስፖርተኛነቴ አዝኛለው፤ ፈጣሪም ነፍሱን ይማረውለ ለቤተሰቦቹም መፅናናትን ይስጥም እላለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ?
አለምአንተ፡- ፈጣሪዬ የድንግል ማሪያም ልጅ እየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይሁን፤ ከዛ በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን፣ የኳስ ሜዳ ልጆችን በጠቅላላ ለእኔ ጥሩ ስሜትናጥሩ ቦታ ሰጥተው እዚህ ደረጃም እንድደርስ ስላደረጉ አመሰግናቸዋለው፤ በተረፈ ከኮቪድ 19 በሽታ ራሳችንን እንጠብቅ ከፈጣሪ እርዳታም ጋር ወደምንወደው ኳስ እንመለሳለን ብዬ አስባለው”፡፡ አክነላመሰከበሽታው ራሳችንን እንጠብቅ፡፡