Google search engine

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋረጠ በእዚህ ዙሪያ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ምን አሉ?


በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሊጠናቀቅ የሶስት ሳምንታት የቀረውን የፕሪምየር ሊግ ውድድር ረቡዕ እለት ዋናው እና
ምክትሉ ፕሬዝዳንት በሌሉበት ሌሎች የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቶችና የሁሉም ክለቦች ተወካዮች በተገኙበት
የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባው ሊጉን ላልተወሰነ ጊዜ ሊያቋርጡት ችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሪምየር ሊግ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ከጫፍ በደረሰበት እና ሊጉንም ፋሲል ከነማ እየመራ
ባለበት የአሁን ሰአት ላይ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ላልተወሰነ ጊዜ ለማቋረጥ ምክንያት የሆነው ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ
ቡና እና በመቐለ 70 እንደርታ መካከል በአዲስ አበባ ስቴድየም ላይም ማከናወን የነበረበትን ጨዋታ በፀጥታ ስጋት
ምክንያት ሊያካሂድ ባለመቻሉና ከእዚህ ቀን ያልተካሄደው ጨዋታ በኋላም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሁለቱን
ቡድኖች ጨዋታ በአዳማው የአበበ ቢቂላ ስቴድየም በዝግ ይካሄድ የሚል ውሳኔም በመሰጠቱ ነገሮችን በቡናዎች ወገን
ምን ስላጠፋን ነው እንዲህ አይነት ውሳኔ የተወሰነብን በሚል ነገሮችን ይበልጥ እንዲከር ስላደረገው እና በጋዜጣዊ
መግለጫቸው ላይም ቁጣን እንዲያነሱም ስላደረጋቸው መቐለዎችም ይሄ ጨዋታን ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ መጥተን
በኋላም ላይ ግጥሚያው አዳማ ከተማ ላይ ይደረጋል ተብለን ይሄን ጨዋታ ግጥሚያው በድጋሚ ይደረጋል ተብሎ
እስከተወሰነበት ሐሙስ ዕለት መጠበቅ ብንችልም ጨዋታው አለመደረጉ ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገን ነው በሚልም
ቁጣቸውን እየገለፁ በመሆኑ ይሄን ጨዋታ ጨምሮ የፕሪምየር ሊጉ አጠቃላይ ቀሪ ጨዋታዎች ላልተወሰነ ጊዜ
እንደማይካሄዱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከውሳኔ ላይ ሊደርስ ስለቻለ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ክለብ ተጨዋቾችን
አናግረናቸው ምላሻቸውን እንደሚከተለው ሰጥተውናል፡፡

“የፕሪምየር ሊጉ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡ እውነትና ትክክል ነው”
ዳንኤል ደምሴ /ኢትዮጵያ ቡና/


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ ይቁም መባሉንና መቋረጡን ስትሰማ
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር አሁን ላይ በሀገራችን ከሚታየው የፖለቲካና የብሄርተኝነት ሁኔታዎች
በመነሳት ጨዋታዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጣቸው እውነት እና ትክክል ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ ያለበለዚያ ኳሱና
ፖለቲካው ባልተለየበት ሁኔታ ግጥሚያዎችን ማድረግ መቻሉ የሚያስከትለውን ነገር መገመት ከባድ አይደለምና የእግር
ኳስ ፌዴሬሽኑ በዚህ ላይ ብዙ ጥናትን ሊያደርግ ይገባል፤ የሊግ ውድድሩ ላይ ፌዴሬሽኑ በእኛና በመቐለ 70 እንደርታ
መካከል የተፈጠሩትን ነገሮች ያውቃል፤ ለዛ ውሳኔዎችን አልሰጠም፤ በሌሎች ክለቦችም የእርስ በርስ ጨዋታዎች ላይ
የሆኑትን ነገሮች በሚገባ ያውቃል፤ አሁንም ከመቐለ ጋር ልንጫወት ስንል ግጥሚያው ከፀጥታ ችግር ጋር በሚል
ሊቋረጥ ቢችልም በዝግ ስታድየም ተጫወቱ መባሉ ደግሞ ከክለቡ ጥቅም አንፃር ውሳኔው ተገቢ ስላልሆነ ይሄ
በሚገባ ሳይፈተሸ ቀርቷል፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከዚህ በኋላስ እኛ የሚቀጥለው ዓመት ላይ ጨዋታችንን ወደ
መቐለ ተጉዘን እንዴት ነው ግጥሚያችን የምናደርገውና በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት ያስፈልጋል”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች እንዳይቋረጡ ምን መደረግ አለበት
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አሁን ላይ እየተከሰቱ ካሉ የፖለቲካ እና ሌሎች አጀንዳዎች በመነሳት የምንወደው ኳስ
እንዳይቋረጥ ከፈለግን ውድድሮቻችንን በዞን በዞን አድርገን ጨዋታውን ማድረግ መቻል ነው፤ በታሪክ እንደሰማነውም
የበፊቱ የውድድር ፎርማት ግጥሚያዎች በትክክል እና በተገቢው መልኩ እንዲከናወኑ የሚያድርግም ነውና ወደዛ
አማራጭ ብንሄድ መልካም ነው”፡፡
‘‘የፕሪምየር ሊግ ውድድሩ መቋረጡ ያሳዝናል፤ የእግር ኳሱን ለማስቀጠል ጥልቅ እና ሰፋ ያለ ውይይት ያስፈልጋል”
አብዱልከሪም መሐመድ /ቅ/ጊዮርጊስ/
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ ይቁም መባሉንና መቋረጡን ስትሰማ
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ባወጣው የውድድር መርሃ ግብር መሰረት
ያጠናቅቃል ብለን ብንጠብቅም ከትናንት በስቲያ ያ ሳይሆን ቀርቶ ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቋረጥ መቻሉ እኔ ብቻ
ሳልሆን አብዛኛው የእግር ኳስ ተጨዋች የማይፈልገው ስለሆነ የዚህን የሊግ አጠቃላይ ውድድር የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ
ለማቋረጥ የቻለበት ዋናው ምክንያት በትክክል ሳይታወቅ ውድድሩ መቆሙ በጣም የሚያስገርምና የሚያሳዝን ሆኖ
ነው ያገኘሁት፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች እንዳይቋረጡ ምን መደረግ አለበት
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላልተወሰነ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉን ውድድር ከማቋረጥ ይልቅ ግጥሚያዎቹን በምንና
በጥሩ መልኩ መምራት እንዳለበት ከሁሉም የባለድርሻ አካላት ጋር ማለትም ከቡድኖች ከአመራሮች ብሎም ደግሞ

ከደጋፊዎች የተውጣጡ አንድ ወርክሾፕ በማዘጋጀት እና በጋራም እርስ በርስ በመወያየት ከእያንዳንዶቹ ጨዋታዎች
በፊት ለጨዋታው ምን አይነት ነገር መደረግ ይኖርበታል፣ የእግር ኳሱን ከዘር፣ ከፖለቲካ እና ከሃይማኖት በመነጠል
እንዴትስ ነው የምናከናውነው የሚለውም ጉዳይ ታስቦበት ውይይት ቢደረግበት ጥሩ ነው፤ ያለበለዚያ ግን ኳሱ የሌሎች
ነገሮች መጠቀሚያ በመሆኑ ስፖርቱን እየጎዳው ነውና በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ስራ ሊሰራ ይገባል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑም
በዛ ላይ ከተጓዘ በኋላም ያለምንም ማመንታት በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ከዚህ ቀደም ብር ብቻ ይቀጣ የነበረውን
ቅጣት በማሳደግ ህገ ደንብ ስላለው በዛ ከበድ ያለውን ውሳኔውን ሊያስተላልፍ ይገባል፤ ለዛ ውሳኔ ባንዘገይም ጥሩ
ነው፡፡

“የፕሪምየር ሊጉ መቋረጥ የፌዴሬሽኑን ድክመት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው”
አክሊሉ ዋለልኝ /ጅማ አባጅፋር/


ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላልተሰወነ ጊዜ ይቁም የሚለውን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ ስትሰማ ምን አልክ?
አክሊሉ፡- የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን የምንወደውን ኳሳችንን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም በማለት ከውሳኔ ላይ
የደረሰበትን ጉዳይ ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት፤ ይሄ መሆን መቻሉም የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችንን አመራሮች ድክመት
ቁልጭ አድርጎም ያሳየ ሆኗል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳሳችንን በሰላማዊ እና በሰከነ መንገድ ሳይቋረጥ ለማድረግ ታድያ ምን ቢደረግ ይሻላል?
አክሊሉ፡- የእግር ኳሳችንን ለማሳደግ እና ብሎም ደግሞ ውድድሮችን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ አካሂደን በስፖርቱ የተሻለ
ቦታ ለመድረስ ከፈለግን ሁላችንም ለስፖርቱ ቅርብ የሆንን ሰዎች በመጀመሪያ ራሳችንን ከፖለቲካው ማራቅ አለብን፡፡
ስፖርት እና ፖለቲካ መለያየት አለባቸው፡፡ ያኔ ጥሩ ውድድሮችን ማድረግ እንችላለን፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ……?
አክሊሉ፡- የእግር ኳሱን አስመልክተን ለቀጣዩ ትውልድ መልካም ነገሮችን ልናወርሰው ይገባል፡፡

“የፕሪምየር ሊጉን መቋረጥ ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት፤ እግር ኳሱንና ፖለቲካውን ልንለይ ይገባል”
በረከት ሳሙኤል /ድሬዳዋ ከተማ/


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ ይቁም ስለመባሉና ስለመቋረጡ
“በቅድሚያ የኢትዮጵያ እግር ኳስን ከፖለቲካው ጋር በማገናኘት ኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እና አሁን ላይ ደግሞ
ጭራሽ ጨዋታዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ በሚል እንዲቋረጥ የተደረገበት ሁኔታ በጣም ያሳዝናል፤ ፖለቲካን ከኳስ ጋር
ማገናኘትም ተገቢ እና ትክክልም አይደለምና እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነቴ እኔም የውድድሩን መቋረጥ ስሰማ በጣም
ነው ያዘንኩት፤ በውሳኔውም ተገርሜያለውኝ፤ የኳሱ መቋረጥም ለፉትቦላችን በጣምም ነው ውድቀት የሚሆነው”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እንዳይቋረጡ እና እንዳይቆሙ ምን መደረግ እንዳለበት
“ለእንዲሀ አይነት ነገሮች ምላሽ ሊሆኑ የሚችሉት በመጀመሪያ ፖለቲከኛ የሆኑ ሰዎች ከምንወደው ኳሳችን ላይ
ሊወጡልን ቢችሉ ነው፤ ያኔ ጥሩ ጥሩ የሆኑ ነገሮችን መስራት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ኳስና ፖለቲካውን
መለየት አልተቻለም፤ ስለዚህም እነዚህ ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለይቶ በማወቅ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፍትሃዊ እና
ትክክለኛ የሆኑ ውሳኔዎችን በመወሰን ኳሱን ሊያስቀጥለው ይገባል፤ ያለዚያ ማንም ተነስቶ የእግር ኳሱን ማቆም
አይችልም”፡፡
በመጨረሻ….
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የተፈጠሩት ችግሮችን እና አሳሳቢ ነገሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አሁን ላይ
ለኳሳችን መፍትኤ ሊሆን የሚችለው ከ28ኛው ሳምንት አንስቶ ያሉትን ጨዋታዎች ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ በዝግ
ስቴድየም ማድረግ መቻል ነው ምክንያቱም ከሁሉም በፊት የሰው ልጆች ሰላም መሆን ከሁሉ በፊት ይቅድማልና ሊጉ
ላይ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ ለውጦች ካሉ ደጋፊዎች እና የስፖርቱ አፍቃሪዎች ባሉበት ጨዋታን ማድረግ
ይቻላል ለውጥ ከሌለ ደግሞ ለውጡ እስኪመጣ ድረስ ውድድሮቹን ከማቋረጥ ያለ ተመልካች ጨዋታዎችን ማድረግ
የግድ ይላል”፡፡

“የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎቹ እንዳይቋረጡ ኳሱንና ፖለቲካውን በመለየት አስተሳሰባችን ላይ ልንሰራ ይገባል”
ከነሃን ማርክነህ /አዳማ ከተማ/


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ ይቁም ስለመባሉና ስለመቋረጡ
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ በጣም ጥቂት ጨዋታዎች በቀሩበት የአሁን እና የእዚህ ሰዓት ላይ ሊጉ
እንዲቋረጥ ተደርጎ ጨዋታዎቹ ይቁም መባሉ ደስ አይልም፤ ይህን ስሰማ ለምን እንዲህ ሆነ በማለትም ነው
የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት ከራሴ ጋር ሙግት ውስጥ ለመግባት የቻልኩትና በውሳኔው ብዙ
የተስማማው አይነት ተጨዋች አይደለውኝም”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እንዳይቋረጡ እና እንዳይቆሙ ምን መደረግ እንዳለበት

“የኢትዮጵያ እግር ኳስ በጥሩ መልኩ ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ መጀመሪያ መስተካከል ያለበት ነገር ቢኖር
ኳሱንና ፖለቲካውን ለይተን በማወቅ አስተሳሰባችን የሚቀየርበት ነገር ላይ መስራትን ስንችል ነው፤ በተለይ በዚህ
ዙሪያ የክልል ክለቦች አሁን ይዘውት የመጡት ሀሳብ ወደ ፖለቲካ ውስጥ ዘልቀው እየገቡበት ስለሆነ ይሄ መፈጠር
መቻሉ ልክ አይደለምና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በዚህ ላይ ጥሩ የውይይት መድረክን አዘጋጅቶና በሚሰጣቸው ውሳኔዎችም
ኮስትራ ሆኖ በመምጣት የእግር ኳሱን ወደተስተካካለ ጎዳና ሊያመጣው ይገባል”፡፡

“የፕሪምየር ሊጉ መቆሙ ትክክል ነው፤ ኳስና ፖለቲካው በፍፁም አልተለየም”
ባዬ ገዛኸኝ /ወላይታ ድቻ/


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ ይቁም ስለመባሉና ስለመቋረጡ
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የሀገሪቷ የተለያዩ ሜዳዎች ላይ አሁን ከሚታየው ዘረኝነት እና የፖለቲካ
አጀንዳዎች እና ዓላማዎች በመነሳት ስንመለከተው ግጥሚያዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ መደረጋቸው ትክክል
ነው፤ ኳስና ፖለቲካው በፍፁም አልተለየም፤ ሁሉም ነገር በጣምም ነው የሚያስጠላው”፡፡
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እንዳይቋረጡ እና እንዳይቆሙ ምን መደረግ እንዳለበት
“ለእዚህ መፍትሄ የሚሆነው እግር ኳሳችን ከፖለቲካ እና ከብሔርተኝነት ሲወጣ ነው፤ ያኔም የማይቋረጡ ውድድሮች
ይኖሩናል፤ ይሄን ለማምጣት ደግሞ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች የሰዎች አህምሮ የሚቀየርበት ነገር ላይ
በመስራት ቁርጠኛ እና ፍትሃዊ ውሳኔዎችን በመወሰን ያልተለሳለሰ አቋም ሊኖራቸው ይገባል”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P