Google search engine

“የእውነትም ተረስቻለሁ፤ ያለእድሜዬ ያገኘሁትን የቀድሞ ብቃቴንና እውቅናዬን በአጭር ጊዜ ውስጥ እመልሳለሁ”ኤፍሬም ቀሬ /ኢትዮጵያ መድን/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ቆይታው ላይ ለአገራችን እግር ኳስ በርካታ ተጨዋቾችን ላፈራው የሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ክለብ ለአምስት ዓመታት ያህል በፊት አጥቂነት ሊጫወት ችሏል፤ ከዛ ውጪም ለአዳማ ከተማ ለሶስት ወራት እንደዚሁም ደግሞ የታችኛው ሊግ ላይ ለሚጫወቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ክለብ ለአክሱም ከተማ እና በሃገር ደረጃ ደግሞ ለኢትዮጵያ የታዳጊና ወጣት ቡድን ውጪ በአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶና ዩሃንስ ሳህሌ የአሰልጣኝነት ዘመን ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ውስጥም በመጫወት እውቅናን አትርፏል፡፡
ይሄ ተጨዋች ኤፍሬም ቀሬ ሲሆን ብዙዎቹ አድናቂዎቹ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ አለመጫወቱን አስመልክተው የት ጠፋህ የሚል ጥያቄ ቢያነሱም ከሁለት ወራት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር አድጓል የሚል ውሳኔ ለክለቦች በማስተላለፉ ኤፍሬምም ወደ መድን አምርቶ ለመጫወት ዝግጁ ቢሆንም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑም መልሶ ውሳኔውን ቢሽርም ኤፍሬም ዘንድሮ በከፍተኛው ሊግ ለሚጫወተው የመድን ቡድን ለመጫወት ተገድዷል፡፡
የኢትዮጵያ መድን አዲሱ ፈራሚ እና የአጥቂው ስፍራ ተጨዋች ኤፍሬም ቀሬ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ /ድሬ/ በሚመራው ክለብ ተፈልጎ መድንን ሲቀላቀል በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ ክለቡ ይጫወታል ተብሎ ስለተነገረው ቢሆንም የተጨዋቹ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የመጫወት ፍላጎትና ጉጉቱ ባለመሳካቱ አሁን ላይ ይሄን ክለብ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ከታችኛው ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመጪው አመት ለማሳለፍ ዝግጁ እንደሆነ እየተናገረ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት የተቀላቀለው ኤፍሬም ቀሬን ከኳስ ተጨዋችነቱ ጋር በተያያዘ አናግረነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ቆይታህ ለሙገር በጥሩ መልኩ በመጫወት እስከ ታዳጊና የዋናው ብሄራዊ ቡድን ተመርጠህ ተጫውተሃል፤ ከፍተኛ እውቅናንም አግኝተሃል፤ አሁን አሁን ላይ ግን በጣም ተረስተሃል፤ የእውነት አይደል?
ኤፍሬም፡- አዎን፤ በሚገባ ተረስቻለሁ፤ ብዙዎች እኔን በደንብ የሚያውቁኝ ለሙገር በምጫወትበት ሰአት ነው፤ ያኔ ድንቅ ብቃቴንም ከማሳየት ባሻገር ለሙገር ከዛ ውጪ ደግሞ ለብሄራዊ የታዳጊና የዋናው ብሄራዊ ቡድን ውስጥም ከመመረጥ ባሻገር የተጫወትኩበትም ሁኔታ ነበርና የዛ ጊዜ የኳሱ ህይወቴ በጣም አስደሳች ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ቡድኔ ከሊጉ ወርዶና ሲፈርስ እንደዚሁም ደግሞ እኔም ወደተለያዩ ክለቦች ለመጫወት ስገባ አሰልጣኞች እንደ በፊቱ እኔ በምጫወትበት የ9 ቁጥር የፊት አጥቂነት ስፍራ ላይ ከማጫወት ይልቅ የመሃል ተጨዋች እና ወደ መስመርም ወጥቼ እንድጫወት ስለፈለጉ እነዚህና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው በምፈልገው መልኩ የእግር ኳስን እንዳልጫወት እና በሰዎችም ዘንድ እንድረሳ ያደረጉኝ፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ የተጨዋችነት ቆይታህ ላይ በምትፈልገው መልኩ ኳስን እንዳትጫወት ያደረጉህ ሌሎቹ ምክንያቶችህስ የትኞቹ ናቸው?
ኤፍሬም፡- አንደኛው ልክ የሙገር የተጨዋችነት ቆይታዬ እንደተጠናቀቀ በሲዳማ ቡና በጥብቅ ተፈልጌ ወደ አዳማ ከተማ ያደረግኩት የተጨዋችነት ዝውውር ነው፤ አዳማዎች ያኔ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አማካኝነት የፈለጉኝ ጊዜ ነበርና ወደዛ ባመራም በምፈልገው የአጥቂ ስፍራ ላይ ልጫወት ስላልቻልኩ ቡድኑ ውስጥ ለሶስት ወራት ቆይቼ በስምምነት ክለቡን ልለቅ ችያለው፡፡ የአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ አሰልጣኝ አሸናፊ እኔን ወደ ቡድኑ ያስመጣኝ በችሎታዬ ላይ እምነትን ጥሎ ነው፤ ያኔ የሙገር ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓትም በተደጋጋሚ እሱ የሚያሰለጥነው የአዳማ ከተማ ክለብ ላይ ጎልም አስቆጥሬበት ስለነበር በእኔ ችሎታ አምኖም ነው የጠራኝ፤ ወደ ክለቡ ከመጣው በኋላም ከአጥቂ ውጪ ያጫወተኝ ስፍራም ነበርና በኋላ ላይ ለአሸናፊ እኔ መጫወት የምፈልገው በፊት አጥቂነት ነው በሚል ከክለቡ ጋር ተለያየው፤ ስለዚህም የእግር ኳሱ ላይ ለእኔ መረሳት በየጊዜው የክለብ ምርጫዎቼ ላይ ስህተትን የምፈፅም ስለሆንኩና በአንድ ወቅት ደግሞ 2008 ላይ የደረሰብኝ ጠንከር ያለ ጉዳት ሊያስረሳኝ ችሏል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ቆይታህ ላይ ታዋቂ ተጨዋች ሆነህና ተሞግሰህ አሁን ላይ መረሳትህ ያስቆጭሃል..?
ኤፍሬም፡- አዎን፤ በጣም እንጂ ያም ሆኖ ግን የቀድሞ ስምና ዝናዬን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምመልሰው ፈፅሞ አልጠራጠርም፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ መድንን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ተቀላቅለሃል፤ የተሳካ ጊዜያትን ታሳልፋለህ?
ኤፍሬም፡- በሚገባ ነዋ! ለእዚህም እርግጠኛ የሆንኩት ወደ ቡድኑ ያመጣኝ አሰልጣኝ ያሬድ ቶሎራ /ድሬ/ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አሰልጥኖኝ ስለነበርና የእኔንም ችሎታ በሚገባ ያውቅ ስለነበር በእሱ ስራ ጥሩ የምጫወትበት ሁኔታ ስለሚፈጠርልኝ ነው፤ ያም አሰልጣኙ ያሬድ እኔን ቀድሞ በምታወቅበት የ9 ቁጥር የአጥቂ ስፍራ ላይ ሊያጫውተኝ በመዘጋጀቱ በመድን ጥሩ ጊዜን እንደማሳለፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ መድን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያልፏል?
ኤፍሬም፡- አዎን፤ ኢትዮጵያ መድን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ያሰባሰባቸው ተጨዋቾች ይሄንን ገድል ሊፈፅሙ የሚችሉትንና ጥሩም ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን በመሆኑም ቡድናችንን ጥሩ ከሚባለው አሰልጣኛችን ጋር በጋራ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንደምናሳልፈውና የእዚህን ታላቅ ክለብ ስምና ዝናንም እንደምናስመልሰው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ኤፍሬም፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋችነት ቆይታዬ ላይ ያለ እድሜዬ ከፍተኛ ስምና ዝና አግኝቼ የነበረው ገና ታዳጊ እያለው ነው፤ እነዛን እውቅናና ዝናም ያገኘሁት በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ስጫወት ነውና አሁን ላይ ዳግም በእዛ ደረጃ ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ፍላጎትን እያሳደርኩ ነው፤ ስለዚህም የ2013 ዓ/ም ላይ አሁን የምጫወትበትን የመድን ክለብ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግና ወጣት ተጨዋች ከመሆኔ አኳያም ያለእድሜዬ ያገኘሁትን የቀድሞ ብቃቴንና እውቅናዬን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ በጣሙን እየተዘጋጀው ነው የምገኘው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P