በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው ለክለቡ ሲዳማ ቡና በመጫወት ስኬታማ አቋሙን በማሳየት ላይ ይገኛል፤ ወጣት ነው፤ 69 ኪሎ ግራም ሲመዝን፣ 1.82 ሜትር ይረዝማል፡፡ ይገዙ ቦጋለ ይባላል፡፡ ተጨዋቹ ሲዳማ ቡናን ከወጣት ቡድኑ አንስቶ እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን የዋና ቡድኑን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶም ገና በወጣትነት እድሜው ተደጋጋሚ ጎሎችን ለማስቆጠር መቻሉ ወደፊት በኳስ ችሎታው የተሻለ ደረጃ ላይ ሊያደርሰው እንደሚችል ምልከታን እየሰጠን ይገኛል፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የሶስት ሳምንት ጨዋታዎቹን አከናውኖ ውድድሩ በተቋረጠበት በአሁኑ ወቅት ለሲዳማ ቡና ክለብ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ከፋሲል ከነማው ፍቃዱ አለሙ እና ከባህርዳር ከተማው ኦሊ ማውሊ ጋር የኮከብ ግብ አግቢነቱን በመምራት ላይ የሚገኘውን ይገዙ ቦጋለ የሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ በእግር ኳስ ህይወቱ ዙሪያ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርቦለት ምላሾቹን ሰጥቷል፤ ይገዙ ቦጋለ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር በምን በምን ጉዳዮች ላይ አውርቶ ይሆን? ተከታተሉት፤ ቃለ-ምልልሱ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ሊግ፡- ጥያቄያችንን ከውልደትህና ከእድገትህ አካባቢ ብንጀምር?
ይገዙ፡- ይቻላል፡፡
ሊግ፡- የት ተወለድክ? የትስ አደግክ?
ይገዙ፡- ተወልጄ ያደግኩት በሲዳማ ክልል ውስጥ በምትገኘውና ከሐዋሳም ከተማ 48 ኪ.ሜ በምትርቀው ሀለታ ጩኮ በምትባለው ወረዳ ውስጥ ነው፡፡
ሊግ፡- እግር ኳስ ተጨዋች እሆናለው ብለህ አስበህ ነበር?
ይገዙ፡- በፍፁም፤ ልጅ እያለሁ ኳስን ስሜቴን ለማርካት እና ለመደሰት ብቻ ነበር ስጫወት የነበርኩት፤ ትንሽ ካደግኩኝ በኋላ ግን ጥሩ ችሎታ አለህ የሚሉ ነገሮች ሲነገሩኝና እንድጫወትም ስፈለግ ኳስ ተጨዋች ሆንኩኝ፡፡
ሊግ፡- እንደ ዛሬው ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር?
ይገዙ፡- ያለምንም ጥርጥር የመንግስት ሰራተኛ ነበር የምሆነው፤ ምክንያቱም ያኔ በትምህርቴ ጎበዝ ተማሪም ስለነበርኩ ያን እልሜን እንደማሳካ እርግጠኛ ነበርኩኝ፡፡
ሊግ፡- ቤተሰቦችህ በምን ሙያ ላይ የተሰማሩ ናቸው? ስንት ወንድምና እህትስ አለህ?
ይገዙ፡- ወላጅ አባቴ ነጋዴ ሲሆን እናቴ ደግሞ የቤት እመቤት ናት፤ ሁለት ወንድምና ሁለት እህቶችም ናቸው ያሉኝ፡፡
ሊግ፡- ከቤተሰቦችህ ስፖርተኛው አንተ ብቻ ነህ? ለቤቱስ ስንተኛ ልጅ ነህ?
ይገዙ፡- የመጀመሪያው ልጅ ነኝ፤ ስፖርተኛውና እግር ኳስ ተጨዋቹም እኔ ብቻ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በልጅነት ዕድሜህ የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር የቤተሰብ ተፅህኖ እንደነበረብህ አደመጥን?
ይገዙ፡- አዎን፤ ልክ ነው፤ ኳስን እንዳልጫወት በወላጅ አባቴ በኩል ከፍተኛ ተፅህኖ ይደረግብኝ ነበር፤ ይህን አጋጣሚ በደንብ አድርጌ ባወራሁም በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- እሺ ቀጥል?
ይገዙ፡- ያኔ ሰፈር ውስጥ ኳስን ስጫወት አባቴ ደግሞ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ አስገብቶኝ እንድማር ያደርግ ነበር፤ በትምህርቴም በጣም ጎበዝ ነበርኩ፤ ይሄን ጊዜ ታዲያ አንዱ ጓደኛዬ አባዮ ይባላል በሰፈር ውስጥ ኳስን እየተጫወትኩ በነበርኩበት ሰዓት ወደ እኔ ይመጣና ይገዙ የወረዳ ምልመላ አለ እዛ ሄደ ተወዳደር ሲለኝ እሺ አልኩት፤ በወቅቱ የ10ኛ ክፍል የማትሪክ ተፈታኝ ነበርኩ፤ ወደ ምልመላው ስፍራ ሄድኩና ለወረዳችን ከተመረጡት 25 ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ ሆንኩ፤ በእዚህን ጊዜም ወረዳችን ለሚያደርገው አንድ የ15 ቀናት የውድድር ቶርናመንት በሳምንት ሶስት ቀናት ልምምድን እየሰራን በምንጓዝበት ሰዓት ወላጅ አባቴ የ10ኛ ክፍል ማትሪክ ተፈታኝ ከመሆኔ በተጨማሪ በትምህርቴ ብቻ እንድጋዝ ይፈልግና የእኔን ኳስ መጫወትን ፈፅሞ ይቃወምና በመጫወቴም ደስተኛ ስላልነበር መጫወቴን ባየህ እና ባወቀ ሰዓት ወደ ስራው ሊሄድ ሲል ከእዚህ በኋላ ኳስ ብትጫወት ከእኔ ጋር ትጣላለህ ብሎ በመቆጣት አስጠነቀቀኝ፤ ወዲያው ወደስራውም ሄደ፤ ያን ዕለት ደግሞ እ በ10 ሰዓት ላይ ልምምድ ነበረንና ልሰራ ወጣው፤ ሰርቼ ስመለስም እሱ ከስራ ወጥቶ እቤታችን እየጠበቀኝም ነበር፤ ከኳስ ፍቅር የተነሳ ትዕዛዙን ጥሼም ስለነበር ምን ብዬ ነበር የሄድኩትም አለኝ? የምትባለውን አትሰማም እንዴ በሚል የቁጣ ስሜትም ሊመታኝ ሁሉ ተዘጋጅቶም ነበርና ከእዚህ በኋላ ከአቅሜ በላይ ነህ፤ የምትማር ከሆነ ተማር፤ የማትማር ከሆነም አትማር፤ እኔ ለራስህ ብዬ ነው፤ ከትምህርት ይልቅ በኳስ ራሴን እችላለሁ ብለሃል አይደል! ከዚህ በኋላ በአንተ ህይወት ውስጥ እኔ አይመለከተኝም ብሎ ቆጣ ብሎ ሲናገረኝ ወላጅ እናቴ በመሃል ገባችና ለአባቴ እባክህ ቀስ ብለህ በስርሃት ንገረው ብላው ሀሳቧን ከገለፀች በኋላ እኔ ሻወር ለመውሰድ ማሊያዬንና ጫማዬን አውልቄ ወደ መታጠቢያ ቤት ገብቼ ከታጠብኩኝ በኋላ ትጥቄን በሳፋ ውስጥ ለማጠብ ዝፍዝፌው ስለነበር ለማጠብ ስዘጋጅ ትጥቁ የለም፤ ጫማዬም የለም፤ ለእናቴ ትጥቁን ማን ወሰደው ስላት አባትህ ደበቀው አለችኝ፤ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፤ በሁለተኛው ቀን ጫማዬን ተቀዶና ተጥሎ አገኘሁት፤ ማሊያዬንና ቁምጣዬን ደግሞ አባቴ የት እንደደበቀው ስላላወቅኩኝ ላገኘው አልቻልኩም፤ ይሄን ጊዜም ነው ታዲያ ሌላ የምጫወትበት ምንም አይነት ትጥቅ ስላልነበረኝ ልምምዴን ለአንድ ሳምንት ያህል ሳልሰራ ወደ ትምህርት ቤት ብቻ በመመላለስ ስማር የነበርኩት፡፡
ሊግ፡- በኋላ ላይ ወደ ኳሱ የተመለስክበት ሁኔታስ ምን መልክ ያለው ነው?
ይገዙ፡- በእዛው በእኛ ክልል ውስጥ ለ15 ቀን የሚካሄድ አንድ የወረዳዎች ውድድር ተዘጋጅቶ ነበር፤ በዛ ጨዋታ ላይ እኔ እንድጫወት ይፈለጋል፤ ያም ሆኖ ግን በወቅቱ ይህ ውድድር ከመድረሱ በፊት እኔ በተወሰኑ ልምምዶች ከቡድኑ ጋር አልነበርኩኝምና ዋናውና ምክትሉ የወረዳ አሰልጣኞቻችን ናቸው የእኔን ልምምድ መቅረት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ እቤታችንን አፈላልገው በመምጣት ጥያቄያቸውን የጠየቁኝ፤ ለምን ቀረህም ሲሉኝ? አባቴ ኳስን እንድጫወት አይፈልግም በሚል ከእነ ምክንያቱ የጠፋሁበትን ሁኔታ ነገርኳቸው፤ እነሱም የእኔን ሀሳብ ካደመጡም በኋላ ወደሚሰራበት ንግድ ቦታ በመሄድ ስለ እኔ ሁኔታ ነገሩት፤ ለወረዳችን ኳሱን የሚጫወተው ርቆ አይደለም፤ እዚሁ በቅርብም ነው፤ ለእኛ ግድ የለም እንዲጫወት ሀላፊነቱን ስጡን፤ ፈጣሪ ብሎ በኳስ ተጨዋችነቱ ይሄ እንጀራው ሆኖ ሊያልፍለት ይችላል፤ እባኮት ይፍቀዱለት በሚል ሲለምኑት ጊዜ እሱም እሺ አለና ፈቀደልኝ፤ ወደልምምዴም ጫማና ማሊያ የለኝም ነበርና እነሱ አምጥተው ሲሰጡኝም ተመለስኩ፤ በጨዋታው ላይም ተሳተፍኩና ወረዳችን ዋንጫ እንዲያነሳም የበኩሌን አስተዋፅኦንም አበረከትኩኝ፡፡
ሊግ፡- ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ክለብህ ይመስለኛል?
ይገዙ፡- አዎን፤ አልተሳሳትክም፤ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ነበር የወረዳ ጨዋታ ላይ ከተመለከተኝና ችሎታዬንም በደምብ ካየ በኋላ አናግሮኝ ወደ ክለቡ ወጣት ቡድን ውስጥ የሙከራ እድል እንዳገኝ አድርጎኝ ለክለቡ ልመረጥ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በሲዳማ ቡና ክለብ ውስጥ ያለህ የተጨዋችነት ቆይታህ ምን ይመስላል?
ይገዙ፡- ክለቡን የተቀላቀልኩት በወጣት ቡድን ደረጃ 2008 ላይ ነበር፤ በዓመቱም ወደ ዋናው ቡድን አድግኩና በጉዳት ምክንያት ተቀነስኩ፤ በዓመቱም 2010 ላይ ወደ ዋናው ቡድን በድጋሚ ተጠርቼ መጫወት ቻልኩ፤ ከእዚያን ጊዜ አንስቶም አሁን ድረስ ለእዚህ በጣም ለምወደው ቡድኔ በጣም ደስተኛ በሆንኩበት ሁኔታ ክለቡን እያገለገልኩ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- በልጅነት ዕድሜህ እግር ኳስን ስትጫወት የትኛውን ተጨዋች ተምሳሌት አደረግክ?
ይገዙ፡- ኢትዮጵያ ሀገራችን ለአፍሪካ ዋንጫው ባለፈችበት ዘመን አዳነ ግርማን በአካል ሲጫወት ባልመለከተውም ስለ እሱ የምሰማቸው ነገሮች ጥሩ ስሜት ይሰጠኝ ነበር፤ እንደ እሱ ለመሆን በሚልም ኳስን እጫወት ነበርና አዳነን ነው ተምሳሌቴ ያደረግኩት፡፡
ሊግ፡- ለሲዳማ ቡና ያደረግከውን የመጀመሪያ ጨዋታ ታስታውሳለህ? ምን ትዝታውስ አለ?
ይገዙ፡- የመጀመሪያ የክለብ ግጥሚያዬን ያደረግኩት ጅማ አባጅፋር የፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና በሆነበት የ2010 ዓ/ም ላይ ከራሳቸው ጋር በይርጋለም ስታዲየም የተጫወትነው ነው፤ በዛ ጨዋታ ላይ 3-1 ብንሸነፍም ተቀይሬ በመግባት አንዷን ግብ ለክለቤ አስቆጥሬያለው፤ ግቧን በማግባቴ በጣም መደሰቴንና ከዛ በኋላም ለክለቡ በቋሚነት ተሰልፌ መጫወት እንደምችልም ራሴን ያሳመንኩበትም አጋጣሚ ነበርና ያ ጨዋታ ፈፅሞ የማይረሳኝ ነው፡፡
ሊግ፡- ለሲዳማ ቡና እስካሁን ምን ያህል ጎሎችን አስቆጠርክለት?
ይገዙ፡- በቁጥር ደረጃ እስካሁን 20 ይደርሳሉ፤ የመጀመሪያው ግቤ ብዙም የመሰለፍ እድሉን ባለገኘሁበትና ክለቡም ላለመውረድ በተጫወተበት ዓመት ላይ ያስቆጠርኩት አንድ ግብ ሲሆን ከዛም 2011 ላይ እነ መሐመድ ናስርና ተመስገንን የመሳሳሉ ልምዱ ያላቸው ተጨዋቾች በነበሩበት ዘመን ላይ ተቀይሬ በመግባት እየተጫወትኩ 4 ግቦችን ላስቆጥር ችያለሁ፤ የኮቪድ ወረርሽኝ በገባበት ዓመት ላይ ደግሞ ውድድሩ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ 7 ግቦች ነበረኝ፤ ዓምና ደግሞ የሁለተኛው ሳምንት ላይ በጉዳት ከሜዳ ለረጅም ጊዜ ብርቅም ከጉዳት ስመለስ ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አካባቢ የመጫወት እድሉን በማግኘት 5 ግቦችንና ዘንድሮ ደግሞ ከጅማሪዬ 3 ግቦችን ለማስቆጠር በቅቻለው፡፡
ሊግ፡- አሁን ላይ ያለህ ወቅታዊ ብቃት ከፍተኛ ደረጃው ላይ አድርሶኛል ትላለህ?
ይገዙ፡- በፍፁም፤ ገና ብዙ የሚቀረኝ ተጨዋች ነኝ፤ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስም ጠንክሮ መስራትም ይጠበቅብኛል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነትህን የት ድረስ ልታስጉዘው ተዘጋጅተሃል?
ይገዙ፡- እንደ ፈጣሪ ፈቃድ የእኔ እልምና እቅድ ኳስ ተጨዋችነቴን ለፕሮፌሽናል ተጨዋችነት በማብቃት ወደ ውጪ ሀገር ሄጄ መጫወትን እፈልጋለው፤ ለዛም ደግሞ አሁን ላይ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጋችን በዲ. ኤስ.ቲ.ቪ እየተላለፈ የሚገኝበት ጊዜ ላይ ስለደረስንም ይሄ እልሜ ይሳካል ብዬም ነው ተስፋ የማደርገው፤ ሌላው ደግሞ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬም በመጫወት ውዲቷን ሀገሬን የማገልገልና ባንዲራዋም ከፍ ብሎ እንዲውልበለብ ከፍተኛ ፍላጎቴም ነውና ይሄን ለማሳካት በግልም በቡድን ደረጃም በርትቼ እሰራለው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ አጋጣሚን አግኝተህ እድሉን ሳትጠቀምበት የነበርክበት ጊዜ ነበር፤ እስኪ ስለዛ ሁኔታ አንድ ነገር በለን?
ይገዙ፡- ይሄ ሁኔታ የተፈጠረው ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ነው፤ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እኔን መጀመሪያ ላይ በ2013 በተካሄደው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተቀይሬ በመግባት ለሲዳማ ቡና ግቦችን ሳስቆጥር ሐዋሳ ከተማ መጥቶ ይመለከተኝ ነበርና እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው ብሔራዊ ቡድን መርጦኝ ነበር፤ እዛም በእሱ ስልጠናና ከጨዋታ በፊትና በኋላ በሚሰጣቸው ምክሮቹም በብዙ ነገሮች ተቀይሬው ጥሩ ጊዜን አሳልፌም ነበር፤ ያኔ ያገኘሁት ልምድም ነበር አሁን ላይ ጥሩ አጀማመር እንዲኖረኝ እያደረገኝም ያለው፤ ያም ሆኖ ግን በእዛን ወቅት እሱ በቀጣይነት ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መርጦ ከጠራኝ በኋላ በህክምና ባለሙያዎች የብሔራዊ ቡድናችን ተጨዋቾች ክትባት አድርጉ ሲባል እኔ ቤትና በውጪ ሀገርም ዘመዶች ስላሉኝ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጪያለው ተከተብ ተባልኩ ስላቸው እንዳትከተብ፤ ከተከተብክ በጤና ላይ ችግር /ሳይድ ኢፌክት/ ያመጣብሃል ሲሉኝ የእነሱን ምክር ሰማውና አልከተብም አልኩ፤ ይሄን ጊዜ ታዲያ አሰልጣኝ ውበቱ ካልተከተብክ ከቡድኑ ውጪ ትሆናለህ ብሎኝ በእዚሁ ምክንያት ነው ልቀነስ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- የዋልያዎቹ ጥሪ ከእዚህ በኋላ ቢደርስህስ አሁንስ አትከተብም?
ይገዙ፡- አሁን ላይ በእዚህ ዙሪያ ከብዙ ሰዎች ጋር ላወራበት ችያለሁ፤ መከተቡም ጥሩ እንደሆነና ብዙ ተጨዋቾችም ተከትበው ምንም እንዳልሆኑም ግንዛቤውን በደንብ አግኝቼያለው፤ ያኔ ካደመጥኩትና ከመፍራት ስሜት ነበር አልከተብም ያልኩት፤ አሁን ግን የብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ከደረሰኝ መከተቤ የግድ ነው የሚለው፡፡
ሊግ፡- ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ ዓመት የጅማሬ ጨዋታዎቻችሁ እናምራ፤ የእስካሁን ጉዞአችሁ ምን ይመስላል?
ይገዙ፡- በውድድሩ ላይ ክለባችንን ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎቹ እንደተመለከትኩት ከጅማሬያአችን ጥሩ ነገር ነው ያለን፤ በእርግጥ ባሳብነው መልኩ ሶስቱን ጨዋታዎች አሸንፈን ሙሉ ነጥብን ለማግኘት ባንችልም ቡድኑ ጋር ግን እያደገና እየተሻሻለ ሊሄድ የሚችል ነገርን ልናይበት ችለናል፤ ሊጉ ደግሞ ገና 27 ጨዋታዎች ከፊቱ ያሉት ነው፤ ከእዚህ በመነሳትም ቡድናችን በውድድር ዓመቱ ጥሩ ጊዜን እንደሚያሳልፍ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በጣም ያስቆጫችሁ ጨዋታስ የቱ ነው?
ይገዙ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረግነው ነዋ! በዛ ጨዋታ ግጥሚያውን ማሸነፍ ነበረብን፤ በተለይም ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ነበር ሁሉንም ነገር መጨረስ የነበረብን፤ ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን በራሳችን ስህተት ነጥብ ተጋርተን ልንወጣ ችለናል፡፡
ሊግ፡- በሐዋሳ ከተማ የደረሰባችሁን ጨዋታ ሽንፈት አምናችሁ ተቀብላችኋል?
ይገዙ፡- በሚገባ፤ እነሱ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ፤ በተለይም ደግሞ ጨዋታውን በአሸናፊነት ለመወጣት ተነሳስቶ በመጫወት በኩል በልጠውናል፤ ሽንፈቱ በራሳችን ጥፋት የተገኘም ስለሆነ ያንን አሜን ብለን በመቀበል ያ ጨዋታ ራሳችንን በሚገባ እንድናዘጋጅበት ትምህርትን ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ጉዞአችሁ የዘንድሮ እቅዳችሁ ምን ውጤትን ማምጣት መቻል ነው?
ይገዙ፡- የእኛ እልምና እቅድ ሲዳማ ቡና በኢንተርናሽናል ጨዋታ ሀገሩን ወክሎ እንዲጫወት ማስቻል ነውና በዚህ ዓመት ጉዞአችን ወይ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አለያም ደግሞ ውድድሩን በሁለተኝነት ለማጠናቀቅ ነው የምንጫወተው፡፡
ሊግ፡- በሲዳማ ቡና የተጨዋችነት ቆይታህ በአቋም ደረጃ ማስተካከል ይኖርብኛል የምትለው ነገር ምንድን ነው?
ይገዙ፡- እንደ አጥቂ ስፍራ ተጨዋችነቴ ብዙ ጎሎችን ማስቆጠር ይኖርብኛል፤ ያን ለማሳካት ደግሞ አጨራረስ ላይ ያለብኝ ክፍተት አለና እዛ ላይ ሰርቼ በመምጣት ሙሉ ተጨዋች መሆን ፍላጎቴ ነው፡፡
ሊግ፡- ሲዳማ ቡና በአንተ አንደበት እንዴት ይገለፃል?
ይገዙ፡- ሲዳማ ቡና ለእኔ ማንነቴ መገለጫዬና ልክ ደግሞ በጣሙን እንደምወዳት ውዲቷ ሀገሬ የምመለከተው አሳዳጊ ቡድኔ ነው፤ ይሄ ክለብ ለእኔ የዛሬው በኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ብዙ ነገሮችን አድርጎልኛል፤ እኔም ለእዚሁ ቡድን ብድሬን መክፈል ስለሚጠበቅብኝ ክለቡን በሚገባ ልጠቅመው ዝግጁ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከመጣ ጀምሮ ለአንተ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ነው ብለህ የምትጠቅሰው ተጨዋች ማንን ነው?
ይገዙ፡- ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ሊያሳልፍ ችሏል፤ የእሱ በወጣትነት እድሜው እነዛን ያህል ግቦችን በማስቆጠር ሪከርድ መሰባበሩም ለብዙ ወጣት ተጨዋቾች አርአያ ከመሆኑ ባሻገር ወደፊት ለሚመጡ ተጨዋቾችም መንገዱን ሊከፍት የቻለ ስለሆነ ለእሱ የተለየ አድናቆት ነው የነበረኝ፤ የዘንድሮ የውድድር ጅማሬ ላይ ደግሞ የፋሲል ከነማው ሀብታሙ ተከስተ አሁንም እንደ ዓምናው ጥሩ ብቃቱን እያሳየ ያለ ተጨዋች ነው፡፡
ሊግ፡- ከእግር ኳስ ውጪ ያለህን የእረፍት ወቅት የት ታሳልፋለህ?
ይገዙ፡- ብዙሁን ጊዜ በመኖሪያ ቤቴ ነው የማሳልፈው፤ በተለይም ደግሞ እናቴ ጋር ሄጄም ነው ቆይታ የማደርገው፡፡
ሊግ፡- በምን አይነት ባህሪህ ነው የምትታወቀው?
ይገዙ፡- ብዙም አላወራም፤ ዝምተኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ግን እኮ ከእኔ ጋር ብዙ አወራህ?
ይገዙ፡- ያው የግድ መግለጪያ መስጠት ስላለብኝ እንጂ ከሰዎች ጋር ከአንተ ጋር እንደነበረኝ ቆይታ ብዙም አላወራም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ይገዙ፡- ቤተሰቦቼ ከፈጣሪ ቀጥሎ ከምንም ነገር በላይ ለእኔ ልዩ ናቸው፤ በኳስ ህይወቴ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሴ ላደረጉልኝ አስተዋፅኦም ስለ እነሱ ለመናገር ቃላቶችም ነው የሚያንሰኝና ዋንኛው ተመስጋኞቹ እነሱ ናቸው፤ እንደ ፈጣሪዬ ሁሉ ልዩ ቦታም የምሰጣቸው ናቸው፤ ከእነሱ ባሻገር ደግሞ የአሁኑ አሰልጣኜ ገብረ መድህን ሀይሌ በሚሰጠው ስልጠናና በቲዎሪ ደረጃም ከሚነግረኝ ነገር ተነስቼ ብዙ ለውጦችን በራሴ ላይ እየተመለከትኩም ያለሁበት ሁኔታ ስላለ ለእሱም አድናቆቴን በመግለፅ ላመሰግነው እፈልጋለው፤ ሌላው የቀድሞ አሰልጣኜ ዘርዓይ ሙሉም እኔን ከወረዳ ጨዋታ ላይ በመምረጥ ወደ ኳሱ ዓለም ዘልቄ እንድገባ ያደረገና ያሰለጠነኝ ስለሆነም እሱም ተጠቃሹ ተመስጋኝ ነው፤ በፕሮጀክት ደረጃም ያሰለጠናችሁኝ አላችሁና እናንተም ተመስገኑልኝ፡፡