Google search engine

“የኮከብነቱ ሽልማት የሚያስኮፍሰኝ ሳይሆን ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳኝ ነው” ፈቱዲን ጀማል /ኢትዮጵያ ቡና/

በመሸሻ ወልዴ


የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ፈቱዲን ጀማል የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ውድድር ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተሸልሟል፤ ፈቱዲን ይህን ሽልማት ያገኘው ማክሰኞ ዕለት
በነበረው የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴሉ ፕሮግራም ላይ ሲሆን ተጨዋቹ ይህን ክብር ካገኘ በኋላም “ኮከብነቱ እኔን የሚያስኮፍሰኝ ሳይሆን ለሌላ ስራ ከፍተኛ ተነሳሽነትን
የሚፈጥርልኝም ነው” ሲል አስተያየቱን ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ መሸሻ ወልዴ ጋር በነበረው ቆይታ ሊገልፅ ችሏል፡፡
የሲቲ ካፑ ኮከብ ተጨዋች ከተባለው ፈቱዲን ጀማል ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ የነበረን አጠቃላይ ቆይታም ይሄንን ይመስላልና ተከታተሉት፡፡


ሊግ፡- የአዲስ አበባ ከተማ /ሲቲ ካፕ ዋንጫ/ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ተሸልመሃል፤ ይህ ክብር ለአንተ ይገባሃል? ሽልማቱንስ አገኛለው ብለህ ጠብቀህ ነበር?
ፈቱዲን፡- አዎን፤ ምክንያቱም በእዚህ ውድድር ላይ ለቡድናችን ስጫወት ጥሩ ለመንቀሳቀስ ችዬ ነበርና ከዛም ባሻገር ቡድናችን ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ
ግጥሚያዎቻችንም ላይ የየጨዋታው የኮከብ ተጨዋችነትን /ማን ኦፍ ዘ ማች/ ሽልማትንም ያገኘሁበት እና በአጠቃላይም በውድድሩ ላይ ጎልቼ የወጣሁበት ሁኔታም ስለነበር
ይህን ክብርና ሽልማትን ማግኘቴ በጣም ይገባኛል፡፡
ሊግ፡- አንዳንዶች ኢትዮጵያ ቡና የሲቲ ካፑ ባለድል ሳይሆን ፈቱዲን እንዴት? የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ይሸለማል ይላሉ፤ ለእዚህ ያለህ ምላሽ ምንድነው?
ፈቱዲን፡- እንደ ራሴ የእግር ኳስ ተጨዋችነት አመለካከት አሁን ላይ ኮከብ ተጨዋች ተብዬ ስለተሸለምኩ ሳይሆን ማንም ቢሸለም የአንድ ውድድር ኮከብ ተጨዋች ተብሎ
መሸለምንና መመረጥን ሁሌም ቢሆን ከዋንጫ መሸለም ጋር የማያይዝ አይነት ተጨዋች አይደለውም፤ ምክንያቱም ለእኔ አንድ ተጨዋች ኮከብ ተብሎ መሸለም ያለበት በሜዳ
ላይ በሚያሳያቸው ተከታታይ እና ወጥ የሆነ ብቃቱ ነው፤ በእርግጥ ከቡድንህ ጋር ሻምፒዮና ሆነህ ብትሸለም ለአንተ የበለጠ ጥሩ እና የተሻለ ነገር ነው የሚሆንልህ፤ በሲቲ ካፑ
ተሳትፎአችን ሽልማቱ አይገባህም ያሉኝ ሰዎች ካሉ ክለባችን ዋንጫ ስላላነሳ ብቻ ይሄን ኮከብነት ሊያሳጣኝ አይገባም በሚል ነው ምላሼን የምሰጣቸው እና የአዲስ አበባ እግር
ኳስ ፌዴሬሽን ከእዚህ በመነሳት ነው በሜዳ ላይ ባሳየሁት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴና ጥሩ ብቃቴ ይህንን ክብርና ሽልማትን ሊሰጡኝ የቻሉት፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ ሳያነሳ ለአንተ ይህን ሽልማትን የሰጠበትን መንገድ እና አካሄድን እንዴት ትመለከተዋለህ?
ፈቱዲን፡- ይሄ ለሌሎችም ፌዴሬሽኖች ትምህርት ሊሆን ነው የሚገባው፤ በእርግጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዘንድሮ ባካሄደው የኮከብ ተጨዋቾች ምርጫ ኮከብነቱን የሰጠው
ሊጉን በሶስተኛነት ደረጃ ካጠናቀቀው የፋሲል ከነማ ተጨዋቾች ውስጥ ለሱራፌል ዳኛቸው ነበር፤ ከዚህ በፊት ግን በአብዛኛው ጊዜያቶቹ ምርጫ ዋንጫ ካነሳ ቡድን ብቻ ነበር
የሚሸልመው፤ ስለዚህ አሁንም ደግሜ መናገር የምፈልገው ኮከብ ተጨዋች ዋንጫ ካነሳ ቡድን ብቻ ሊሆን አይገባውም፤ ኮከብነት መሸለም ያለበት በውድድሩ ላይ ነጥሮ ለወጣ እና
የተሻለም ለተንቀሳቀሰ ተጨዋች ነውና ሽልማቱ ፍትሃዊ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ሊግ፡- በሲቲ ካፑ የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ስትሸለም የተፈጠረብ የደስታ መጠን የቱን ያህል ነው?
ፈቱዲን፡- እንደ እውነቱ ለመናገር በአንድ ውድድር ላይ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ስትሸለም በውስጥ የሚፈጥርብህ ደስታ በጣም ከፍ ያለ ነው፤ ለእኔ ደግሞ ይሄንን የኮከብ
ተጨዋችነት ክብርን ያገኘሁት ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፍኩበት እና ከሁሉም ክልልም በጣም ደማቅ በነበረው የአዲስ አበባ የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ ስለሆነ ያ ደስታዬን እጥፍ
ድርብም ሊያደርግልኝ ችሏል፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ተሸልመሃል፤ ሽልማቱ ለአንተ ምን ማለት ነው?

ፈቱዲን፡- የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ የኮከብ ተጨዋችነቱን ሽልማት ለማግኘት መቻሌ በጣም ነው ያስደሰተኝ፤ ይሄ ኮከብነትም ለእኔ
የሚያስኮፍሰኝ ሳይሆን ለበለጠ ስራም የሚያነሳሳኝ ነውና ኮከብነቱ ለእኔ ትልቅ ትርጉም ነው ያለው፤ በተለይ ደግሞ ለፕሪምየር ሊጉ ዋንኛው ውድድራችን ለክለባችን ውጤታማነት
ጥሩ ነገሮችን እንድሰራም ከወዲሁ የጥርጊያውን በር የከፈተልኝም ነውና ከወዲሁ ለእያንዳንዳቸው ጨዋታዎች ራሴን በብቃትም ሆነ በአዕምሮ ደረጃ በሚገባ አዘጋጀዋለሁ፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ባትሸለም ኖሮ ስሜትህ ይጎዳ ነበር?
ፈቱዲን፡- በፍፁም፤ ምክንያቱም በእግር ኳስ ህይወቴ ወደፊት ለክለቤም ሆነ ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን የማበረክታቸው በርካታ ውጤታማ ግልጋሎቶች ስላሉና ብዙም
የሚጠበቁብኝ ነገሮች ስላሉ እንደዚሁም ደግሞ በቀጣዮቹ ጊዜያት ሌሎች ሽልማቶችንም የማገኝበት ሁኔታዎች ስላሉ በምንም አይነት መልኩ የምክፋበት ነገር አይኖርም፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀውን አጠቃላይ የሲቲ ካፑን ውድድር በምን መልኩ ተመለከትከው?
ፈቱዲን፡- ከመጀመሪያ ሃሳቤ ስነሳ ውድድሩ በጣም ደስ የሚልና በጣምም ያሸበረቀ ነበር፤ በተለይ ደግሞ ይሄ ወድድር ከኳሱ በተጨማሪ በሀገራችን ውስጥም የሰላሙ ጉዳይ
በጣም አሳሳቢ ደረጃ የደረሰበትን ሁኔታም በኳስ ወደ አንድ የመለሰበትም ሁኔታ ተፈጥሮ ነበርና በስፖርታዊ ጨዋነቱ ላይ ብዙ ነገሮች አስቀድመው እንደተሰሩም ልንመለከት
ችለናል፤ ከዚህ ቀደም በሜዳ ላይ በሚያደርጉት ጨዋታ ልዩነት የነበራቸው እና አይስማሙም የሚባሉት የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም በአንድ አይነት አቋም ላይ
ሆነው እየተሞጋገሱ እና እየጨፈሩም ክለቦቻቸውን ሲደግፉም ያየንበት ሁኔታዎችም ነበሩና ይሄም በጣም ያስደስተን ሆኖም ተገኝቷል፡፡ ከውድድሩ ባሻገር ሌላ ልጠቅሰው
የምፈልገው ነገር ቢኖር በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በነበረው የመዝጊያ ቀን ፕሮግራም ላይ በርካታ ታዋቂ እና ስመ-ጥር ሰዎች በተገኙበት ሁኔታ በክብር ተጠርተህ የኮከብ
ተጨዋችነቱን ሽልማት መቀበል መቻል ያለው የደስታ ስሜት በጣም ደስ ይላል፤ ከዛ ባሻገር ለስፖርቱ የለፉና የደከሙ አካላቶችም እውቅና ያገኙበትንም ጥሩ ጥሩ ነገሮችን
ልንመለከትም ችለናልና ይሄ ሊበረታታም ቀጣይነትም ሊኖረው ይገባል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሲቲ ካፑ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን አልቻለም፤ ምክንያቱ ምን ነበር?
ፈቱዲን፡- ኢትዮጵያ ቡናን እንደ ቡድን ስታየው ገና በመገንባት ላይ ያለና በጥሩ መልኩም ተቀናጅቶ በመምጣት ለወደፊቱ አስተማማኝና ጥሩ ቡድንን ለመስራት እየተዘጋጀ
የሚገኝ ቡድን ነው፤ ከዛ አንፃር የቡድኑ አዲስ መሆንና ራሱንም በእንቅስቃሴ ደረጃ እየተመለከተ ያለበት ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ በእዚህ ጭምርም ነው የሲቲ ካፑን ዋንጫ
ለማግኘት ያልቻልነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች መገኘት ካለበት 12 ነጥብ አምስት ነጥብን ብቻ ይዞ የውድድር ጅማሬውን አድርጓል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን
የምትለው ነገር አለ?
ፈቱዲን፡- ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ እየተሳተፈ ያለው አዲስ የተጨዋቾች ስብስብን ይዞና አዲስ የጨዋታ ፍልስፍናንም በመከተል ላይ ባለበት ሁኔታ ቢሆንም ከጅማሬው ያስመዘገብነው
ውጤት ለእኛ በቂ የሚባል አይደለም፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ላይ ክለባችን ከግጥሚያ ወደ ግጥሚያ ሲጓዝ በእንቅስቃሴ ደረጃ እየተሻሻለ እና ወደአሸናፊነትም ሊመጣ መቻሉ
እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎቻችንም ጋር ያለው ትዕግስት ጥሩ በመሆኑ ከዓላህ እርዳታ ጋር በቀጣይነት በምናደርጋቸውም ጨዋታዎች ወደ ውጤታማነት የምናመራ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአሁን ሰዓት ከያዘው ነጥብና እየተከተለ ባለው አጨዋወቱ የሚያሰጋው ነገር ይኖራል?
ፈቱዲን፡- በፍፁም፤ እኛ ክለባችንን በሚገባ እናውቀዋለን፤ የያዝነውንም አጨዋወት እየተረዳነው ነው፤ ከዚ በመነሳት ዘንድሮ የሚያሰጋን ነገር ፈፅሞ የለም፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና የሚከተለው አጨዋወት ለእናንተ ምርጥ እና የተመቻችሁስ ነው? ወይንስ በተቃራኒው?
ፈቱዲን፡- የኢትዮጵያ ቡናን የሜዳ ላይ አጨዋወትንም ሆነ እንቅስቃሴውን የአሁን ሰአት ላይ ስንመለከተው ልክ በአውሮፓውያን ደረጃ አሰልጣኞቹም ሆኑ ተጨዋቾቹ እየተከተሉት
ያለውንና በእግር ኳስም መሆን ያለበትንም እንቅስቃሴን ለመከተል ጅማሬን ያደረግንበት ወቅት በመሆኑ በእዚህ በያዝነው ነገር በጣም ደስተኛ ነን፤ ይህ እንቅስቃሴያችን ከኳስ ጋር
የተያያዘና ተስፋ ሰጪም ስለሆነ በቀጣዮቹ ዓመታት ቡና በሁሉም ነገር ወደፊትም ይጓዛል፤ ከዛም ባሻገር አጨዋወታችንም አይደለም ለክለባችን ለሀገርም ጭምር ይጠቅማልና
አሁን ላይ እግር ኳሱን ተመችቶንም ነው እየተጫወትን የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናውን አሰልጣኝ እንደ ስራው ጅማሬ በምን አይነት ሁኔታ ነው የምትመለከተው? ወደ ሜዳ ይዞት የመጣውን የጨዋታ ፍልስፍናስ ከሌሎቹ ጋር ስታነፃፅረው?
ፈቱዲን፡- የኢትዮጵያ አሰልጣኞችን በሜዳ ላይ ይዘው በሚገቡት የአጨዋወት ታክቲክ አንዱን ከአንዱ ጋር ስታነፃፅር ወይንም ደግሞ ስታመዛዝን የየራሳቸው ነገር ቢኖራቸውም
የእኛው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ግን በተለያዩ ነገሮች ከእነሱ በጣም ለየት ይላል፤ ለምሳሌ የጨዋታው ታክቲክ ኳስን ከግብ ጠባቂ ጀምረህ በመጫወት እስከ አጥቂ ድረስ ኳሶች
ሳይቋረጡ እና ኳሶች ሳይባክኑ ኮንፊደንስ ኖሮ እንድትጫወት ይፈልጋል፤ ጫናን ፈፅሞ አይፈጥርብህም፤ ሀላፊነትንም ሁሌም ይወስድልሃልና ይሄ እሱን ለየት ያስብለዋል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ መጨረሻ ሐዋሳ ከተማን በሰፊ ግብ ረታ፤ የቡድናችሁ አጥቂ እንዳለ ደባልቄ ሶሰት የድል ግቦችን በማስቆጠር ሃትሪክ ሰራም፤ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች
በምን መልኩ ትገልፃቸዋለህ?
ፈቱዲን፡- ኢትዮጵያ ቡና ሐዋሳ ከተማን 4ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ያሸነፈው በጨዋታው ከተጋጣሚው የተሻለ ስለነበርና ጥሩ የጨዋታ አቅምም ስለነበረው ነው፡፡ ከዛ ባሻገርም
አሸናፊነቱን በጥብቅ ፈልገነው ስለነበርም በከፍተኛ ፍላጎት መጫወታችን ለድል አብቅቶናል፡፡ የክለባችን አጥቂ እንዳለ ደባልቄን በሚመለከት ተጨዋቹ ጥሩ ችሎታና እምቅ
አቅምም ያለው ተጨዋች ነው፤ አሁን ላይ ለክለባችን ሀትሪክ እስከመስራት ደረጃም በመድረስ ግብ ማስቆጠር ጀምሯል፤ ወደፊት ደግሞ በእዚሁ ቀጥሎ ሌሎች በርካታ ግቦችን
እንደሚያስቆጥርልን አምናለውና በእዚሁ ቀጥል በርታም ነው ልለው የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ከሌሎች ክለቦች ምን ይለየዋል?
ፈቱዲን፡- ኢትዮጵያ ቡናን ከሌሎቹ ቡድኖች የሚለየው አንድ ነገር ቢኖር የራሱ የሆነ የጨዋታ ፍልስፍና ያለው ቡድን መሆኑ ነው፤ አንዳንድ ክለቦች በእርግጥ የራሳቸው የሆነ
መገለጫ ሊኖራቸው ይችላል፤ ያም ሆኖ ግን በዘላቂነት ሲያስኬዱት አይታይምና ለእዛ ነው ቡናን ከሌሎቹ ይለየዋል ያልኩት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ለአንድ ግጥሚያ ወደ ሜዳ ስትመጡ ከጨዋታው በፊት እና ከጨዋታው በኋላ ምን ምን ነገሮችን ይነግራችኋል?
ፈቱዲን፡- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በእዚህ በኩል የሚገርም አይነት ባለሙያ ነው፤ እሱ ከጨዋታ በፊትም ሆነ በኋላ ለእኛ ልክ እንደ ወንድም እንደ አባት እና እንደ አሰልጣኝ ጭምር
በመሆንም ነው ለቡድናችን ጥሩ ውጤት እንድናመጣና ብሎም ደግሞ ችሎታችንንም እንድናሻሽለው ጠቃሚ ጠቃሚ የሆኑ ምክሮችን የሚለግሰንና በእዚሁ አጋጣሚ ላመሰግነው
እፈልጋለውኝ፡፡
ሊግ፡- ወልዋሎ አዲግራት ፕሪምየር ሊጉን እየመራ ነው፤ ይሄን ጠብቃችሁ ነበር? የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፍፃሜውን ሲያደርግ እናንተንስ የት ደረጃ ላይ እንጠብቃችሁ?
ፈቱዲን፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በሶስት እና በአራት ጨዋታዎች ከወዲሁ እንትና መርቷል ብለህ የምትጠብቀው ወይንም ደግሞ የምትወስነው ነገር አይደለም፤ ሊጉ ጠንካራ
ውድድር ነው ገና በርካታ ጨዋታዎች ከፊቱ አሉት፤ ገና ሁለተኛው ዙርም አለና የሊጉ ውድድር ሲጠናቀቅ እኛን የምታገኙን ከአንደኛው እስከ አራተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ነው፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት መቻል የተለየ ስሜትን ይሰጣል፤ ስለክለቡስ ምን ምን ነገሮችን ሠምተህ ነው ያደግከው?
ፈቱዲን፡- ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወቴ ትልቅ የሆነ የደስታ ስሜት ነው የሚሰማኝ፤ ለቡድኑ መጫወትንም እፈልግ ነበርና ያን ምኞቴንም ነው ያሳካሁት፤ ስለቡና ሰምቼ ያደግኩት
ነገር ክለቡ የብዙ እና የምርጥ ደጋፊዎች ባለቤት ቡድን ስለመሆኑና የሃገሪቷ ምርጥ ምርጥ ተጨዋቾችም ተጫውተው ያለፉበት ክለብ ስለመሆኑም ጭምር ነውና ይሄ ነው እኔን
በጣም የሚያስደስተኝ፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ለመመረጥህ አገዘውኛል ወይንም ደግሞ ረድተውኛል ብለህ የምታመሰግናቸው አካላቶች አሉ?
ፈቱዲን፡- አዎን፤ ከሁሉም በላይ መጀመሪያ የክለባችንን አጠቃላይ ደጋፊዎች በየጨዋታዎቹ ከጎኔ ሆነውና ያበረታቱኝ ስለነበር እነሱን አመሰግናለው፤ በመቀጠል ደግሞ ለእዚህ
የበቃሁት ክለባችን በሚከተለው የአጨዋወት ፍልስፍና ነበርና አጠገቤ ያሉትን ተጨዋቾች ጨምሮ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን እንደዚሁም ደግሞ ኮቺንግ ስታፉን ላመሰግን እፈልጋለው፤
ሌላው የማመሰግነው ቤተሰቦቼን ነው፤ በአጠቃላይ ለሁሉም ልዩ ክብርም ነው ያለኝና ይሄ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- የኮከብ ተጨዋች ተብለህ በተሸለምክበት የኢንተርኮንቲኔንታል መድረክ ከአጠገብህ የኮከብ ግብ አግቢው እና የምርጥ ግብ ተሸላሚው ሳላህዲን ሰይድ ነበር ሁለታችሁ
በሽልማቱ ዙሪያ የተነጋገራችሁት ነገር ነበር?
ፈቱዲን፡- ከሳላህዲን ጋር ምንም አይነት የተነጋገርነው ነገር የለም፤ ያም ቢሆን ግን በእዚሁ አጋጣሚ እሱ ለእኔ የሃገሪቱ ትልቅ፣ የምወደው እና የማደንቀው አይነት የአጥቂ ስፍራ
ተጨዋች በመሆኑ ከእሱ ጎን ለመቆም በመቻሌ እና ልሸለምም በመቻሌ ትልቅ የሆነ የደስታ ስሜት ነው ሊሰማኝ የቻለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚጫወቱ ብዙሃኑ ተጨዋቾች ወደትዳር ዓለም እየገቡ ነው ለአንተስ? አለ ገና! አለ ገና ተብሎልሃል… ወይንስ?
ፈቱዲን፡- የአሁን ሰዓት ላይ እኔም ባለትዳር ነኝ፤ በአሜሪካን ሃገር ከምትኖረው ባለቤቴ ጋርም ቀለበት አስረን ጨርሰናል፤ ይሄ ደግሞ በቤተሰቦቻችንም ዘንድ በደንብ የሚታወቅ
ነው፡፡
ሊግ፡- ባለቤትህን ግለፃት?
ፈቱዲን፡- ባለቤቴ ፈትያ ሱናሞ ትባላለች፤ የሐዋሳ ከተማ ልጅ ነች፤ ለእኔ ሁሉም ነገሬ ናት፤ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃም የእሷ ከጎኔ መሆን በብዙ ነገር አግዞኛል ከቤተሰቦቼ
ቀጥላ ብዙ ነገር ያደረገችልኝ ስለሆነ ከልቤ ላመሰግናት እፈልጋለውኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ፈቱዲን፡- የአዲስ አበባ ከተማ ኮከብ ተጨዋች በመባሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ለእዚህ ላበቃኝ ፈጣሪዬ ዓላም ሆነ ለቤተሰቦቼ ከፍተኛ ምስጋናን አቀርባለው፤ ከዛ ውጪ በሲቲ ካፑ
ላይ ሰላማዊ ውድድርን ልንመለከት መቻላችንም ያስደሰተኝ ስለነበር በእዚሁ አጋጣሚ ለመላው የስፖርት አፍቃሪ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡናና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በሜዳ
ላይ ላሳዩት ስነ-ስርዓት ምስጋናን ማቅረብም እፈልጋለው፤ ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን ሁሌም ሠላም እንድትሆንም በፀሎት እንድናስባት መልህክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P