በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የፋሲል ከነማው የአማካይ ስፍራው ተጨዋች ሱራፌል ዳኛቸው በቅርቡ ስለፈፀመው ጋብቻ፤ በፋሲል ከነማ ስላሳለፈው የጨዋታ ጊዜ፣ ስለብሄራዊ ቡድናችንና ስለራሱ ወቅታዊ የእግር ኳስ ብቃት ይናገራል፤ ምላሹም በእዚህ መልኩ ይቀርባል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የፋሲል ከነማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሰሞኑን ተሞሽሯል፤ በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ? እስኪ ስለጋብቻህ ስነ-ስርአት እና ስለተሰማህ ስሜት ጥቂት በለን…..?
ሱራፌል፡- አመሰግናለሁ፤ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም የሶስት አመት የፍቅር ጓደኛዬ ከነበረችው ወ/ሪ ሜሮን ሰለሞን ጋር አዳማ ከተማ በሚገኘው የጄኔራል ሆስፒታል ትልቅ አዳራሽ ውስጥ የፈፀምኩት የጋብቻ ስነ-ስርአት ፕሮግራሜ በጣም የሚገርም የነበረ ቢሆንም መጀመሪያ ላይ እንዲህ ያለ ሴሪሞኒንም ሆነ የሰርግ ጥሪን ከዚህ ቀደም አልወድምና በጣም ጨንቆኝ ነበር በኋላ ላይ ግን ሁሉንም ነገር ስመለከት አስደሳች ነገሮች ስለነበሩበት ሰርጉን ድገም ድገም ነው ያለኝ፤ ቪዲዮውን እናንተም ብትመለከቱት በጣም ነው የምትወዱት፤ ባለቤቴም ብዙ ጊዜ ከቤት የማትወጣ ስለነበረች ያን ዕለት ከእኔ የባሳም ፈርታ ነበርና በኋላ ላይ ሰርጉን በቪዲዮ ስትመለከት በጣም ነው የወደደችውና ፍርዓቱ ስለለቀቃት ሰርጉ ይደገም እያልኳት ነው፡፡
ሊግ፡- ከባለቤትህ ጋር የተገናኛችሁበት አጋጣሚ ምን ይመስላል? በሰርጉ ቀን ማዜዎችህስ እነማን ነበሩ?
ሱራፌል፡- የባለቤቴና የእኔ የመጀመሪያ ትውውቅ የተጀመረው በቀድሞው የአዳማ ከተማ ተጨዋች በነበረው በእነ ታከለ አለማየሁ ቤት ውስጥ ነው፤ ያን ዕለት የታከለ እህት ሞታ ነበርና ለቅሶ በደረስኩበት የእራት ሰዓት ላይ ሜሮን ለታከለ የአክስቱ ልጅ ነበረችና እጅ ታስታጥብ ነበርና አየዋት፤ እሷም አየችኝ፤ ቀጥሎም በፌስ ቡክ ሪኩዌስት ተላላክንና መፃፃፍ ጀመርን፤ እንዲህ እያልን ነው ትውውቃችንን በማሳደግ ለፍቅር እና በኋላም ላይ ለጋብቻ ልንበቃ የቻልነው፤ የሰርጌ ቀን ላይ የእኔ ሚዜዎች የነበሩት የቡድናችን ተጨዋች የሆነው በዛብህ መላዬ እንደዚሁም ደግሞ አብሮ አደጌ ገዛኸኝ ቦዶሮ እና ያሬድ ገ/መድህን /ቃዋ/ ናቸው፡፡
ሊግ፡- ባለቤትህን በጥቂት ቃላት ግልፃት?
ሱራፌል፡- የ21 ዓመት ዕድሜ ያላትን ባለቤቴን ስገልፃት በጣም ጥሩ፣ በሳል አዕምሮ ያላትና ለትዳር ህይወት የምትመች አይነት ልጅ እንደሆነች ነው፤ እሷ ለእኔ ሁሉም ነገሬ ናት፤ ለዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሴ ከእድሜዋ በላይ ጥሩ ጥሩ ሃሳቦችን በማፍለቅ እና ህይወትንም በጋራ እንዴት መምራት እንዳለብንም በማሰብ በብዙ ነገር አግዛኛለች፤ ከዛ ውጪም ለእድገቴም ወደ አልባሌ ነገሮች እንዳላመራ በማድረግ መሰረት የሆነችኝ ምርጧ ልጅ ናትና በእዚህ አጋጣሚ በጣሙን ላመሰግናት እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ያሳለፍከው የዘንድሮው ቆይታ በምን መልኩ ይገለፃል? በአዲሱ አመትስ እንዴት እንጠብቅህ?
ሱራፌል፡- የፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ያሳለፍኩት የአምናው ቆይታዬ እንደ ግልም እንደ ቡድንም መልካምና ውጤታማ የሚባል ነበር፤ ጥሩ ኳስን የተጫወትንበት እንደዚሁም ደግሞ ስኬታማ የሆንበት ዘመን ነበርና በዛ ደረጃ መገኘታችን እኔን አስደስቶኛል፤ በእዚህ ዓመት ደግሞ ከአምናው በተሻለ ጥሩ ችሎታዬን እንደዚሁም ደግሞ ስኬታማ ግልጋሎቴን በእጥፍ መልኩ ለማሳየት ተዘጋጅቻለውና ይሄን ነው ማለት የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሌሴቶ ጋር ሲጫወት አልነበርክም፤ አሁን ላይ ግን ቡድኑን ደግመህ ተቀላቅለሃል፤ ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል? ከሩዋንዳ ጋር በሚኖራችሁ የእሁዱ ጨዋታ ምን ውጤትስ ለማምጣት ተዘጋጅታችኋል?
ሱራፌል፡- ከሌሴቶ ብሄራዊ ቡድን ጋር ስንጫወት ያልነበርኩት በሰርጌ ምክንያት ነው ያንንም ለአሰልጣኛችን አብርሃም በማስፈቀድ ነግሬዎለሁ፤ እሱም በደስታ ነው መልካም ነገርን በመመኘት ሊፈቅድልኝ የቻለው፤ አሁን ላይ የዋልያዎቹን ስብስብ ከተቀላቀልኩ በኋላ እየሰራነው ያለው ዝግጅት ጥሩና ጠንካራ ነው፤ ሁሉም ተጨዋቾች በጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ ሆነውም እየተለማመዱ ይገኛል፤ በተለይ ለእሁዱ የሩዋንዳ ጨዋታ ቡድናችን የእነሱን በረጅም ኳስ ላይ ያተኮረን አጨዋወት በማጥናት ውጤቱን እዚህ ጨርሰን ለመሄድና ለድል ለመብቃት ተዘጋጅተናልና የግጥሚያውን ቀን እየተጠባበቅን ይገኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ተጨዋችነትን ሽልማት ከሚያገኙት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ትሆናለህ እየተባልክ ነው፤ትጠብቃለህ?
ሱራፌል፡- ለምን አልጠበቅም፤ ባለፈው ዓመት በነበረኝ የፋሲል ከነማ ቆይታዬ ጥሩ የውድድር አመትን ያሳለፍኩበት ነው፡፡ ጥሩ ከመጫወቴ ባሻገርም ክለቤንም ለስኬት አብቅቼዋለሁ፡፡ ከእኔ ውጪ በውድድር አመቱ ሌሎችም ጥሩ ብቃት የነበራቸው ተጨዋቾች ነበሩና የእኔ ለኮከብ ተጨዋችነት መገመት ምንም የሚያስገርም አይደለም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ሱራፌል፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባሳለፍነው አመት ስላማዊ ባልሆነ እና ብዙዎችንም ባሳዘነ መልኩ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ያ ሊደገም ስለማይገባ የ2012 የውድድር አመት ኳሳችን በስፖርታዊ ጨዋነት ታጅቦና በተሻለ መልኩም እግር ኳስን እና እግር ኳስን ብቻ መሰረት በማድረግ የምናሳልፈው የውድድር አመት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡