በመሸሻ ወልዴ
የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ታደለ መንገሻ ቡድናቸው በዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው ዋንጫ ለማንሳት ባይታደልም አጠቃላይ የሊጉን ውድድር በተመለከተ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ለቀረበለት ጥያቄ የእዚህ ዓመቱን ውድድር “ፕሪምየር ሊግ ነው ብሎ መጥራት እንደማይቻልና ውድድሩም የተንዛዛ እና አስቀያሚ እንደዚሁም ደግሞ ከዚህ ቀደምም ታይቶ የማይታወቅም ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በመሀል ሜዳ ለማገልገል የዛሬ ሁለት ዓመት ፊርማውን አኑሮ የነበረውን እና አሁን ላይ የውል ዘመኑን ያጠናቀቀውን ታደለ መንገሻን የሊግ ስፖርት ጋዜጣ ስለ ዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ውድድር በሊጉ ስላሳለፉት ተሳትፎአቸውና ሌሎችን ተያያዥ የሆነ ጥያቄዎችን አቅርበንለት ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ዘንድሮም፤ ዓምናም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሊያጣ ችሏል፤ በተከታታይ ዓመታትም ይሄ ውጤት በቡድኑ ውስጥ ሲከሰት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ በዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለህ?
ታደለ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ቅ/ጊዮርጊስ ካለው የፋይናንስ አቅም እና በአመራር ደረጃም ከያዛቸው እውቀት ያላቸው ሰዎች አንፃር እንደዚሁም በተደጋጋሚ ሁሌም ጠንካራ እና ውጤታማን ቡድን ከመፍጠሩ አኳያ ትልቅ ቡድን እንደሆነ ብናውቅም የዘንድሮው የውድድር ዘመን ላይ ቡድናችን ያስመዘገበው ውጤት ክለቡን የሚመጥነው አይደለም፤ እንዲህ ያሉ ውጤቶችም ለእኛ ፈፅሞ አይገባንም፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት ተከታታይ የሊጉ የውድድር ዓመታቶች ዋንጫ ማጣቱም በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያ ሆኖ የተመዘገበ ቢሆንም ያለፈው ዓመትን ዋንጫ ያጣንበት ሁኔታ ግን ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ስለሆነ እሱን በጊዜው በከፍተኛ የሀዘንና የቁጭት ስሜት ላይ ሆነን ነው ማሳለፍ የቻልነው፤ የዓምናው የውጤት ማጣት በእኛ ላይ በደል ደርሶብን ከፍተኛ ብስጭትን በራሳችን ላይ ከመፍጠሩ ውጪ ሌላ ብዙ የምለው ነገር አይኖረኝም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ዘንድሮስ ስለማጣታችሁ የምትለው ነገር ይኖርሃል?
ታደለ፡- አዎን፤ ቅ/ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በእዚህ ዓመት እንዳያነሳ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ በአንኳርነት የምጠቅሰውና በተደጋጋሚም ጊዜ ልናገር የምፈልገው የውድድር ዓመቱን የቅድመ ጊዜ ዝግጅት በበፊቱ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ ከሰራንና በእሱ የታክቲክ ስታይልም ከተቀረፅን በኋላ የሊጉ ውድድር ሊጀመር የአንድ ሳምንት ጊዜ ሲቀረው አሰልጣኙ ተባሮ እንግሊዛዊው አሰልጣኝ በመምጣቱና አሰልጣኙም የራሱን የጨዋታ ታክቲክ እንድንጠቀም ሲፈልግ ቡድናችን በአጨዋወት ስታይሉ ሁለት ቦታ ላይ የመከፈል ሁኔታን ሊያሳይ ስለቻለ ይሄ በክለባችን ላይ ውጤትን እንዳናመጣ ከፍተኛ ተፅዕኖን ፈጥሮብናል፤ ከዛ ውጪም ሌሎች ውጤት ያጣንባቸው ነገሮች ደግሞ በተጨዋቾች ላይ የአቋም /የፐርፎርማንስ/ መውረድ እና መውጣትም በተለያዩ ጊዜያት ላይ የሚያጋጥሙበት ሁኔታና ቡድኑ በእዚህ ዓመት ላይ ከተለያዩ ክለቦች ያስመጣቸው አዳዲስ ተጨዋቾች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ ደጋፊ ያለውና ሁሌም ደግሞ ማሸነፍን የለመደ ቡድን በመሆኑ በአንዳንድ ግጥሚያዎች ላይ ውጤት በሚጠፋበት ሰአት የደጋፊውን ጫና የመቋቋምም ችግር ስላለ ይሄም ማለት ወደ ቡድናችን የሚመጡት ብዙዎች ተጨዋቾች በነበሩበት ክለብ ውስጥ በእዚህ መልኩ ተጫውተው ስለማያልፉ የእነዚህ ድምር ውጤቶች ናቸው እኛን ሊጎዱን የቻሉት፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንደከዚህ ቀደሙ በተደጋጋሚ ለማንሳት ወደ በርካታ የክልል ሜዳዎች ላይ ሄዶ የሚያስመዘግባቸው ውጤቶች በዋናነት ሲጠቅመው ቆይቷል፤ አሁን ላይ ግን ብዙ ጨዋታን ወደ ክልል ሄዶ ስለማያሸንፍ ዋንጫውን ለማጣቱ እንደ አንድ ችግር በምክንያትነት ደረጃ የሚጠቅሱ አሉ፤ ይሄን ሀሳብ ትጋራዋለህ? ወይንስ ሌላ ምልክታ አለህ?
ታደለ፡- እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋችነቴ ቡድናችን አሁን አሁን ላይ እያስመዘገባቸው ያሉት ውጤቶች ለቡድኑ አይገባውምና ከላይ የተነሳውን ሀሳብ እጋራዋለሁ፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ በፊት ልክ ነው ከሜዳው ውጪ የሚያስመዘግባቸው የድል ውጤቶች የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከማናቸውም ክለቦች በተሻለ መልኩ ይረዱት ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን እነዚያን የድል ውጤቶች ከሜዳ ውጪ በምታደርጋቸው የክልል ሜዳ ጨዋታዎች ላይ ይዘህ ለመውጣት ብዙ ቻሌንጆች ስላሉ፤ ኳሱ ፖለቲካው ውስጥ ዘልቆ ስለገባ፣ የአዲስ አበባ ክለብ የነበረው ደደቢትን የመሰለም ጠንካራ ክለብ ወደ መቀለ በማምራቱና ሌሎቹም የአዲስ አበባ ክልል በርካታ ቡድኖች ሊጉ ላይ ስለሌሉና የአዲስ አበባ ክለቦች ቁጥር በመቀነሱ ይህ ማለት ደግሞ አብዛኛውን ግጥሚያም የምታደርገው ወደ ክልል በመውጣትና 3 ነጥብን ይዞ ለመውጣት ደግሞ ሁሉም ነገር በጣም አዳጋች ስለሚሆንብህ የእውነት ነው እነዚህም ችግሮች ናቸው ውጤት ማምጣቱ ላይ ሲያስቸግሩን የሚታዩት፡፡
ሊግ፡- በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ ዓመት የውድድር ጉዞን በምን መልኩ ነው የምትገልፀው?
ታደለ፡- የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ሲካሂድ የቆየው ዓመታዊው ውድድር “ፕሪምየር ሊግ” አይመስልም፤ አስቀያሚ ነገሮችንና ብዙ የወረዱ ነገሮችንም የተመለከትኩበት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ውድድርን ተመልክቼም አላውቅም፤ ክለባችን ከእግር ኳስ ፌዴሬሸኑ ጋር በውሳኔ አሰጣጥ ዙሪያ መብቱን በመጠየቅ እና ያላደረገውም ቀሪ ጨዋታ እያለ ምንም ነገር ሳይመለስለት መቅረቱ የሚያሳዝን ነው፤ ለቡድናችንም ውሳኔ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ሆነን እንኳን ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች ልምምዳችን የእሁድ ቀንን ጨምረንም ሳናቋርጥ እንሰራ የነበረበት እና ምንም አይነት ምላሽንም ሳናገኝ የቆየንበት የውድድር ዓመት ነበርና የእዚህ ዓመትን አጠቃላይ ውድድር እንደ ፕሪምየር ሊግ ሆኖም ያላገኘሁት ነበር፡፡
ሊግ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ በነበረህ ያለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታህ ለክለቤ የሚጠበቅብኝን ግልጋሎት ሰጥቻለሁ ብለህ ታስባለህ? ስለቀጣዩ ጊዜስ የኳስ ህይወትህ ምን ትላለህ?
ታደለ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በተቀላቀልኩበት የመጀመሪያው ዓመት የውድድር ዘመን ተሳትፎዬ ላይ ጉዳት ለቡድኔ እንደፈለግኩት እንድጫወትና የሚጠበቅብኝንም ጥቅም እንዳልሰጥ ቢያደርግልኝም ታክሜ ከመጣሁ በኋላ ግን ዘንድሮ በነበረው የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ ገና ከጉዳት እንደመምጣቴ ለመሰለፍ ብዙ ቻሌንጆች ቢኖርብኝም በኋላ ላይ በሜዳ ላይ በከፈልኩት መስዋዕትነት ወደቋሚ ተሰላፊነት በማምራት ከእኔ የሚጠበቀውን ጥሩ የሆነ ግልጋሎትን ለቡድኔ ለመስጠት ችያለሁ፤ በተለይ ደግሞ ወደ መጨረሻዎቹ በርካታ ግጥሚያዎቻችን አካባቢም በራሴ አቋም ላይ ከፍተኛ መሻሻልን አሳይቻለው ብዬም አምናለው፡፡
ስለቀጣይ ጊዜው የኳስ ህይወቴን በተመለከተ የአሁን ሰአት ላይ ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ የሆንኩና ወደ ቀድሞ ብቃቴም የተመለስኩበት ሁኔታ ላይ ስላለው የመጪው ዓመት የውድድር ተሳትፎዬ ላይ ደግሞ ራሴን በከፍተኛ ደረጃ እና ብቃት ላይ ማስቀመጥን ስለምፈልግ ከወዲሁ የተለያዩ የሜዳ ላይና የጂም ስራዎችን በመስራት ከወዲሁም በጥሩ መልኩ እየተዘጋጀሁ ነው የምገኘውና ጥሩ ችሎታ ያለውን ታደለን ነው በአዲሱ የውድድር ዘመን ላይ የምትመለከቱት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች መሆንህን እንዴት ነው የምትመለከተው?
ታደለ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች መሆን መቻል ኳሱን የምትዝናናበት ስፖርት ከመሆኑ ባሻገር በዋናነት ደግሞ ስራህም ነውና ሁሌም ኳስ ተጨዋችነትህን እንደ ፕሮፌሽንህ ሆነህ ነው ልትመለከተው የሚገባው፤ እኔም ኳስ ተጨዋችነቴን የምገልፀው በእዚህ መልኩ ነው፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታንም በጣም ነው የምወደው፤ ከእግር ኳስ መለየትም ለእኔ በጣም ከባድ ነው፤ ስራዬን በማክበርም ጭምር ነው በመጪው ጊዜያትም በተከታታይነት ኳስን የምጫወተውና እስካሁን ለእዚህ ደረጃ ላበቃኝ ፈጣሪዬም ምስጋናዬን ላቀርብለት እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ያለህ የውል ዘመን ተጠናቅቋል? እዛው ትቀጥላለህ? ወይንስ ወደሌላ ቡድን ታመራለህ?
ታደለ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ያለኝ የውል ጊዜዬ ተጠናቋል፤ እንደዛም ሆኖ ግን ውሌን ብጨርስም አሁንም መጫወት የምፈልገው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ነው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለእኔ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን አድርጎልኛል፤ ክለቡን በቀጣይነት መጥቀምና ማገልገል እንደዚሁም ደግሞ ውጤታማም ማድረግ እፈልጋለሁና በቡድኑ ስለሚኖረኝ ቆይታ የክለቡን ውሳኔ እየጠበቅኩ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- በግብፅ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ተከታትለሃል? ያንን ከተመለከትክ በኋላ ምን አልክ?
ታደለ፡- የአፍሪካ ዋንጫውን ሁሉንም ጨዋታዎች ባልከታተልም በአልጀሪያና በሴኔጋል መካከል የተደረገውን የፍፃሜ ግጥሚያ እንደዚሁም ሌሎች የተመለከትኳቸውም ጥቂት ጨዋታዎች አሉ፤ ይህን ሳይ በሜዳ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ አንፃር እና እንደ ማዳጋስካርን የመሳሰሉት ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ውድድር ላይ ተካፋይ መሆናቸውን ሳስብ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በእዚህ መድረክ ላይ አለመሳተፍ መቻሉ በጣም እንድቆጭ ነው ያደረገኝ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከእዚህ በፊት በነበሩት የማጣሪያ ግጥሚያዎች ላይ ጠንካራ ከሚባሉት እንደ እነ አልጀሪያ ከመሳሰሉት ሀገራት ጋር በሜዳው ላይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ብርቱ ፉክክርን ያደረገበት ሁኔታ ቢኖርም ለአፍሪካ ዋንጫ የሚመደብበት ምደብ ከባድ መሆኑ ብቻ እንዳያልፍ አድርጎታል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድሉ ከባድ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ማለትም ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው ላይ እነ ኬንያን የመሳሰሉት ሀገራት ባሉበት ምድብ ውስጥ ማለፍ እየቻልን ለጨዋታዎቹ ጥንቃቄ ባለማድረጋችን እና ጥንቃቄ ማድረግ የምንጀምረውም ከሁለት የማጣሪያ ጨዋታ በኋላ መሆኑ እነዚህ ዋጋ እያስከፈሉን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዳናልፍ አድርጎናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2021 በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኮትዲቩዋር፤ ከማዳጋስካር እና ከኒጀር ጋር ተደልድሏል፤ አሁንስ ለአፍሪካ ዋንጫው ማለፍ የምንችል ይመስልሃል?
ታደለ፡- ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፍ የሚቻለው በእግር ኳሱ ላይ በትኩረት እና በጥንቃቄ ስትሰራ እንጂ በግምት በመንቀሳቀስ አይደለምና ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍን ካሰብን ሁሉን ነገር አሁን ላይና ከወዲሁም ነው መጀመር ያለብን፤ የምድባችን ተወዳዳሪ ከሆኑት ሀገራት መካከል ጠንካራውን ኮትዲቯር እንተውና ማዳጋስካርን ከዚህ ቀደም በደርሶ መልስ ጨዋታ አግኝተን አሸንፈናታል፤ ከኒጀር ጋርም ተሸናንፈናል፤ አሁን ላይ ግን እንደ ማዳጋስካር የመሳሰሉት ሀገራት እግር ኳሳቸው ላይ እንደበፊቱ አይደለምን በዛ በኩል ጥንቃቄ ወስደን ልንጫወት ይገባል፤ ማዳጋስካር በግብፁ የአፍሪካ ዋንጫ የውድድር ተሳትፎዋ ላይ እንደ እነ ናይጄሪያን የመሳሰሉትን ሀገራት ለማሸነፍ ችላለችና እኛ በፊት የነበሩትን ነገሮች ወደ ኋላ ረስተን እንደዚሁም ደግሞ ከሶስቱ ሀገራት ጋር ለሚኖረን እያንዳንዱ ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን መጫወት ከቻልን ስለተጋጣሚዎቻችንም ወቅታዊ አቋምም በሚገባ ልንረዳ ከቻልን ለአፍሪካ ዋንጫው የማናልፍበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
ሊግ፡- አሁን የእረፍት ጊዜ ነው፤ ታደለ በእዚህን ወቅት ምን ያደርጋል?
ታደለ፡- የአርባምንጭ ተወላጅ እንደመሆኔና ብዙ ስፖርቶችም በእዚሁ ክልል ስላሉ የክረምቱን የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው ዓሳ በመብላትና ለአዲሱ የውድድር ዓመት የሚያዘጋጀንን ተጨማሪ የሜዳ ላይና የጂም ልምምዶችንም እዛ ከሚገኙ ተጨዋቾች ጋር እየተጠራራን በመስራትም ጭምር ነው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ታደለ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከተፈለገ በቅድሚያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ወሳኔዎች ተአማኒነትን እያጡ እና ቆራጥም ሊሆኑ ስላልቻሉ በእዚህ ደረጃ ፌዴሬሽኑ ማንንም ከማንም ባለማበላለጥ እውነተኛ እና ትክክለኛ ስራዎችን ሊሰራ ይገባዋል፤ ወደ ክለቦች ስናመራም ደጋፊዎቻቸውን ወደ ስፖርቱ ሜዳ ሲያመሩ ኳሱን እንጂ ፖለቲካዊ የሆኑ ነገሮችን እንዳያራምዱ ይህም ማለት ኳሱ ላይ ፖለቲካው ስለገባ እግር ኳሱ ላይ ትልቅ አደጋ እንዳያስከተል በመንገርና በማሳወቅ ሊያስተምሯቸው ይገባል፤ ወደ ደጋፊው ጋር ስንሄድ ደግሞ ለሃገራችን የስፖርት እድገት የምናስብ ከሆነ ደጋፊው ኳስን ተመልክቶ፤ በኳስ ተዝናንቶ ወደቤቱ ስለመሄድ ብቻ እንዲያስብ እንጂ ስለብሄርተኝነት እና ስለ ጎሳ እንዳያንፀባርቅና ከዛ ነገር መውጣት እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል፤ መንግስት ጋርም ስንሄድ ከፖለቲካ የፀዳ እና ንፁህ የሆነ ውድድርን እንድናከናውን ትልቅ ስራን ሊሰራም ይገባዋልና በዚህ ላይ ስለ ኳሱ እና ስለ ሀገራችን የሚያስቡ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ወደ ስፖርቱ ኃላፊነት የሚመጡበትን መንገድ ሊፈጥር ይገባዋል፡፡
በመሸሻ ወልዴ