Google search engine

“የድሬዳዋ ከተማን ውጤት እናሻሽላለን፤ በአበረታች ደረጃም ላይ እናስቀምጣለን” ገናናው ረጋሳ /ድሬዳዋ ከተማ/

 በመሸሻ ወልዴ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው የምስራቁን ክልል በመወከል እየተወዳደረ የሚገኘው የድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የሁለተኛው ዙር ላይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣና ሊጉንም ከ4ኛ እስከ 7ኛ ባለው ደረጃ ላይ ሆኖ እንደሚያጠናቅቅ የቡድኑ ተጨዋች ገናናው ረጋሳ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው ዙር ባደረጋቸው የእስከአሁን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ እና በደቡብ ፖሊስ በመሸነፍ ሶስት ነጥብን ያስመዘገበ ሲሆን በአጠቃላይ የሊጉ ውድድርም በአሁን ሰዓት 18 ነጥብን ይዞ በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤  ይህን በተመለከተ እና በኳስ ህይወቱ ዙሪያ ከክለቡ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን ገናናው ረጋሳን አናግረነው ምላሹን ሰጥቶናል፡፡

ሊግ፡- የእግር ኳስ አጀማመርህ ምን ይመስላል? የትስ ተወልደህ አደግክ?

ገናናው፡- የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኳስ ተጨዋች በሰፈር ደረጃ ልጅ ሆኜ በመጫወት ነው፤ የተወለድኩት እና ያደግኩት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ጨርቆስ አካባቢ በአሁኑ አጠራር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው፡፡

ሊግ፡- በቤተሰባችሁ ውስጥ ስንት ወንድም እና እህት አለ? የእግር ኳስ ተጨዋቹስ አንተ ብቻ ነህ?

ገናናው፡- አዎን፤ ከቤተሰባችን ውስጥ ስፖርተኛው እኔ ብቻ ነኝ፤ አምስት ወንድሞችም አሉኝ፤ እህት ደግሞ የለኝም፡፡

ሊግ፡- የልጅነት ዕድሜ ላይ ኳስን መጫወት ስትጀምር ማንን አድንቀህ ነው ያደግከው?

ገናናው፡- የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊ ሆኜ ከማደጌ አኳያ ልጅ ሆኜ የእግር ኳስን ስጫወት ቀልቤን ስበውት ያደነቅኳቸው ተጨዋቾች ሁሉንም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ቢሆንም በተናጠል ግን  ወላጅ አባቴ ሁሌም ስታዲየም ይዞኝ ሲገባ በዋናነት ያደነቅኩት ተጨዋች ቢኖር በእሱ ቦታ ላይ የምጫወት ባልሆንም ተከላካዩን ደጉ ደበበን  ነው፤ ደጉን ላደንቅ የቻልኩትም የእሱ አጨዋወት እና በስራው ላይ ያለው ታታሪነትም ደስ ይለኝ ስለነበር ነውና በዛ ላደንቀው ችያለው፡፡

ሊግ፡- በክለብ ደረጃ የእግር ኳስን እንዴት መጫወት ጀመርክ? የት የት ክለብስ ገብተህ ተጫወትክ?

ገናናው፡- የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ገብቼ ለመጫወት የቻልኩት በአካባቢያችን ተቋቁሞ ለነበረ እና ራዕይ ለሚባል የቸርች ቡድን ነው፤ ወደዚህ ቡድንም ገብቼ ልጫወት የቻልኩትም የቡድኑ አሰልጣኝ  በነበረው አቤል አማካኝነት ነው፤ አቤል  የእኔን ጥሩ ችሎታ ተመልክቶ እና አድንቆኝም ነው  ሊጠራኝ የቻለው፤  እሱ ያኔ ወደ ዋናው ቡድንም አሳድጎኝ ሊያጫውተኝ ችሏል፤ በክለቡ ቆይታዬም የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ አጠናቅቄና የራዕይ ቡድንንም ለቅቄ ስለነበር በመቀጠል የገባሁበት ክለብ  የቡና የተስፋ ቡድን ነው፤ እኔን የጠራኝ አሰልጣኙም  ኤፍሬም ደምሴ /ቤቢ/ ነበርና ለቡና ተስፋ ቡድን ሄጄ  ተጫወትኩ፡፡ እዛም ጥሩ እንቅስቃሴን ስላሳየው  በአሰልጣኝ ዮሃንስ  ሳህሌ ይመራ ለነበረው የኢትዮጵያ u-17 ቡድን ልመረጥ እና በስኪመር ስፍራም ልጫወት ቻልኩ፤ በመቀጠልም በታዳጊ ቡድን ያሳየሁት እንቅስቃሴ ጥሩ በመሆኑም ወደ ቡና የዋናው ቡድን ለማደግም ቻልኩ፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና የነበረህ ቆይታህ እንዴት ይገለፃል? ከቡና በኋላስ የት ገብተህ ተጫወትክ?

ገናናው፡- በኢትዮጵያ ቡና የነበረኝ ቆይታ በተስፋ ቡድኑ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ያን ያህል ነበር፤ ከተስፋው ቡድን ጋር  ግን ጥሩ ቆይታው ነበረኝ፤ ለዛም ነው ለታዳጊም ቡድን ልመረጥ እና ወደዋናው ቡድንም ለማደግ የቻልኩት፤ ያም ሆኖ ግን በዋናው ቡድን ላይ ትላልቅ እና ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ስለነበሩና በቋሚ ተሰላፊነትም ብዙም የመጫወት እድሉን ስላላገኘው የዋናው ቡድን ቆይታዬ ያንን ያህል የሚነገርለት አልነበረምና ቡናን የለቀቅኩት የመጫወት እድሉን ላገኝ ባለመቻሌ ነው፡፡

ከቡና ቆይታዬ በኋላ ደግሞ ቀጥዬ የተጫወትኩበት ክለብ  ቢኖር ባህር ዳር ከተማ ነው፤ ወደዛ ከማምራቴ በፊት ግን በአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ አማካኝነት ለደደቢት እንድጫወት ተጠርቼ የነበረ ቢሆንም ወደ ቡድኑ ላመራ ከጫፍ ስደርስ ዩሃንስ ራሱ ደደቢት ከያዛቸው ትላልቅ እና ልምድ ካላቸው ተጨዋቾች አንፃር ጊዜህን እዚሁ ቆይተህ ከምታሳልፍና ከምትቀመጥ  በሱፐር ሊግ ራስህን ለምን ፈተነከው አትመጣም ብሎኝ  አሰልጣኝ ዩሃንስ ወደ ባህርዳር ከተማ ልኮኝ ነበርና እዛ  ለባህር ዳር ከተማ ለ1 አመት ተጫወትኩ፤ በኋላም በአሰልጣኝ አስራት አባተ መራጭነት ወደ አዲስ አበባ ከነማ ክለብ ለመግባት እና  ወደ ቡድኑም ለማምራት ቻልኩ፡፡ ለአዲስ አበባም ለአንድ አመት ከተጫወትኩ በኋላ ሌላ የተቀላቀልኩት ቡድን በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ መራጭነት ለድሬዳዋ ከነማ ክለብ ነውና  የአሁን ሰአት ላይ አሰልጣኙ ከእኛ ጋር ባይኖርም በአሰልጣኝ ስምኦን አባይ በሚመራው ቡድን ውስጥ እየተጫወትኩ ነው የምገኘው፡፡  

ሊግ፡- በእግር ኳሱ ያሳለፍካቸውን ያለፉት ጊዜያቶች እንዴት ነው የምትገልፃቸው?  ደስተኛ ነበርክ?

ገናናው፡- የእግር ኳስ ተጨዋቾች የሚያሳልፏቸው ያለፉት የህይወት ጉዞዎች ብዙ ፈተናዎች ያሉት ቢሆንም እኔ ግን በኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ደስተኛ ልሆን የቻልኩትም ወደፊት አንድ ነገርን አገኛለው ብዬም ስለማስብ ነው፡፡ ኳስን በምጫወትበት የአሁን ሰዓት አንድ ነገር ሀፕን ቢያደርግብኝ ራሱ ነገን ሌላ ቀንም ብዬ የማስብ አይነት ሰው ስለሆንኩም ደስተኛ ሆኜ ነው ኳስን እየተጫወትኩ የምገኘው፡፡

የኢትዮጵያ ቡናን እድሉ በያዘበት ሰአት ከ20 አመት በታች ላለው የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ተመርጬ እና ተጫውቼ ከሀገር ውጪ ደርሼ ነው የመጣሁት በሌሎቹም የኢትዮጵያ ተተኪ ቡድኖች ውስጥም በአሰልጣኝ ግርማም በአሰልጣኝ ዩሃንስም አብርሃምም ሲሰለጥኑ ለሀገሬ ተመርቼ የተጫወትኩ ስለሆነ በኳሱ ህይወቴ ደስተኛ ነኝ፡፡  

ሊግ፡- የእግር ኳሱ ላይ ማሻሻል አለብኝ የምትለው ነገር ምንድነው?

ገናናው፡- በኢትዮጵያ የአጭር ዓመት የተጨዋችነት ቆይታዬ ላይ   በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የእግር ኳስን የተጫወትኩት ገና ዘንድሮ በመሆኑና ወደፊት ደግሞ ከእኔ የሚጠበቁት ነገሮች ብዙ ስላሉ ማሻሻል አለብኝ ብዬ የማስባቸው ነገሮች በርካታ ናቸው፤ በኳሱ አሁን ላይ ያለኝን ብቃት ማሻሻል እፈልጋለው፤ ራሴንም ለውጪ ገበያ ማቅረብ እና ችሎታዬንም ከፍ ባለ ደረጃ ላይ በማስቀመጥ እንደዚሁም ደግሞ  ብቃቴንም በማሳደግ በጥሩ ደረጃ ላይ መገኘትንና የሀገሬንም ስም በኳሱ ማስጠራት እፈልጋለው እና ይሄንን ለማሳካት ጠንክሬ ነው የምሰራው፡፡

ሊግ፡- የእግር ኳስን በምን በምን ቦታ ላይ ተጫውተህ አሳለፍክ?

ገናናው፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆኜ ጀምሮ ስጫወት ያልተጫወትኩባቸው ቦታዎች የሉም፤ መጀመሪያ በሰፈር ደረጃ ግብ ጠባቂ እንድሆንላቸው ብዙዎች ስለሚጠሩኝ በዛ ቦታ እጫወት ነበር፤ በመቀጠል ደግሞ   የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ሆንኩ፡፡ በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሚመራው  የታዳጊ ቡድን ውስጥ ደግሞ  በስኪመር ስፍራ ላይ ተጫወትኩኝ፡፡  ከዛ ውጪም  በሊብሮ ስፍራ እንደዚሁም በቀኝ ፉልባክ የመስመር አጥቂ ሆኜ ተጫውቻለው፤ በድሬዳዋ ከተማ ቡድንም አሰልጣኝ ስምኦን አባይ በተለያየ ስፍራ እያፈራረቀም የሚያጫውተኝ ጊዜም አለና በአጠቃላይ ሁለገብ ተጨዋች ነኝ ማለት እችላለው፡፡  

ሊግ፡- የድሬዳዋ ከተማን የመጀመሪያው ዙር የሊግ ተሳትፎ እንዴት አገኘኸው?

ገናናው፡-  ድሬዳዋ ከተማ በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሚመራበት ሰአት የውድድሩ ጅማሬ ላይ ለውጤት የሚተጋ ጥሩ ቡድን ሰርቶ፣  ቡድኑንም በወጣት ገንብቶ እና በመከላከሉና በማጥቃቱም ረገድ ጠንካራ ቡድንን ለመገንባት ጥረትን ማድረግ  ቢጀምርም የተጨዋቾች የልምድ ማጣት እና ውጤት በሚጠፋ ሰዓትም የደጋፊዎች ጫና እኛን በምንፈልገው መልኩ እንዳንጫወት ስላደረገን ውጤታችን እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፤ እሱ ከለቀቀም በኋላ ቡድናችን በሚፈልገው መልኩ ውጤትን እያመጣም አይደለምና ሁለተኛው ዙር ላይ ግን የተሻለ ነገር ይኖረናል፡፡

ሊግ፡- ድሬዳዋን በዋናነት ያጋጠመው የውጤት ማጣት ችግር ምን ነበር?

ገናናው፡- ድሬዳዋ ከነማ በመጀመሪያ ደረጃ  በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነው፤ ይሄ ቡድንም ጥሩና የተሳካ ውጤት ለማምጣትም ጊዜን ይፈልጋልና የእኛ ቡድንን በመጀመሪያው ዙር ወጤት ያሳጡት ዋና ችግሮች የልምድ ማጣት እና ውጤት ሲጠፋም  ደጋፊው የሚያሳድርብን ጫና በቀጣዮቹ ግጥሚያዎች ተረጋግተን እንድንጫወት ስለማያደርገን ነው፤ ሌላው የክለባችን ችግር  የአጨራረስም ነው፤ በሜዳችን ስንጫወት የጎል ማስቆጠር እድሎችን እያገኘን እነዛን አንጠቀምም፤ በሜዳችንም ብዙ ነጥቦችን ይዘን የማንወጣ ስለሆንን እነዚህ ጎድተውናል፡፡  

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ክለባችሁን  በሁለተኛው ዙር እንዴት እንጠብቀው?

ገናናው፡- ድሬዳዋ ከተማ የሁለተኛው ዙር የውድድር ተሳትፎው ላይ ቡድኑን ለማጠናከር እንደ እነ ምን ያህል ተሾመ (ቤቢ) እና ኤልያስ ማሞን የመሳሰሉ እና ለብሄራዊ ቡድንም ጭምር  የተጫወቱ ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸውን ልጆች የያዘበት አጋጣሚ ስላለ አሁን ካለንበት ደረጃ አንፃር ቡድናችንን ፈፅሞ በወራጅ ቀጠናው ላይ አላስበውም፤ ሊጉን መሪው ክለብ ርቆን ስለሄደ  ከአራተኛ እስከ 7ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ሆነን ነው የምንጨርሰው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን  በቅርቡ ማሸነፍ ችላችኋል፤ በደቡብ ፖሊስ ደግሞ ተሸነፋችሁ፤ አሁን ደግሞ መከላከያን ትገጥማላችሁ፤ እነዚህን  ጨዋታዎች እንዴት ትመለከታቸዋለህ?

ገናናው፡- የኢትዮጵያ ቡናን በቅርቡ ገጥመን ያሸነፍንበት ጨዋታ ለእኛ በጣም ጥሩ የሆነልን ነበር፤ ጨዋታውን አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ስተንና  በቡናም ላይ የበላይነትን ወስደን  ያሸነፍንበት ግጥሚያ ስለነበር በውጤቱ በጣም ደስ ብሎኛል፤ አሸናፊነቱም ይገባናል፡፡

የደቡብ ፖሊስ ጋር ስንጫወት ደግሞ ግጥሚያውን ምንም እንኳን የእነሱ ተከላካይ አበባው ቡታቆ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ እኛ ለማጥቃቱ አስበን ቦታችንን ነቅለን በሄድንበት ሰዓት በመልሶ ማጥቃት ጎል ተቆጥሮብን ለመሸነፍ ብንችልም ጥሩ ፉክክር ያደረግንበት ጨዋታ ነበር፤ ግጥሚያውን ቢያንስ አቻ ማጠናቀቅም ይገባን ነበር፡፡

የመከላከያ ጋር የሚኖረንን የነገው የሜዳችን ላይ ጨዋታን በተመለከተ ደግሞ ሁለታችንም የወራጅ ቀጠናው አካባቢ ስለምንገኝ ጨዋታው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ መቻል ለእኛ በጣም አስፈላጊያችን ስለሆነ ጨዋታውን በድል እንወጣለን፡፡

ሊግ፡- የውልደት  እና የእድገት ሰፈርህን እንዴት ነው የምትገልፀው?

ገናናው፡- ጨርቆስ የሚታወቀው የፍቅር ሰፈር በመሆን ነው፤ የአራዶችም ሰፈር ነው፤ በኳስም ይታወቃል እና የእዛ ሰፈር ልጅ በመሆኔ በጣም ደስ ይለኛል፡፡

ሊግ፡- የእግር ኳስን በመጫወትህ የቤተሰብ ተፅዕኖ ነበረብህ?

ገናናው፡- በፍፁም፤ ቤተሰቦቼ ኳስን እንድጫወት ሁሌም ነው የሚያበረታቱኝ፤ በተለይ ደግሞ አሁን በሕይወት የሌለው እና ዶክተር የሆነው አባቴ ኳስን ከመውደድ ባሸገር ራሱም ይጫወት ነበርና ብዙ ድጋፍ ነው ሲያደርግልኝ የነበረው እና እነሱን ሁሌም ነው የማመሰግናቸው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ….

ገናናው፡- የእግር ኳስ ተጨዋች እንድሆን እና ለዛሬም ደረጃ እንድበቃ ከፈጣሪ ቀጥሎ ከእኔ ጀርባ ብዙ አካላቶች አሉ፤ በመጀመሪያ የማመሰግነው ቤተሰቦቼን ነው፤ ከዛም የአባቴን ያህል በቀይ መስመር ይሰመርበትና አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ እንደወንድም እንደ ጓደኛና አባትም ሆኖ እየመከረኝ ለእዚህ አድርሶኛልና እሱንም አመሰግናለው፤ ወደፊትም ከእኔ ጎን እንደማይለይም አስባለው፤ ሌላው የማመሰግነው ባለቤቴን ነው፤ ዘንድሮ የማገባት ባለቤቴ ለእኔ ብዙ ነገር ነችና እሷም ትመስገን ሌሎችም ከእኔ ጎን የሆኑትን ሁሉ  አመሰግናለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P