በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብን ከአዳማ ከተማ በመምጣት ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ምርጥ የሚባል የጨዋታ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው እና በቡድኑም የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው
የሊጉን የኮከብ ተጨዋችነት ክብርን ሊጎናፀፍ የቻለው ሱራፌል ዳኛቸው በዘንድሮ የውድድር ዘመንም ጥሩ ብቃቱን በማሳየት ቡድኑን ለድል ለማብቃት መዘጋጀቱን እየተናገረ ይገኛል፡፡የፋሲል
ከነማውን የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሊግ ስፖርት በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግራው ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የ2013 አዲስ ዓመት አቀባበሉ
“የአዲሱን ዓመት የተቀበልኩት በአማረ እና በጥሩ መልኩ ነው፤ ከቤተሰቦቼ ጋር በመሆንም ነው የዓመቱን ጅማሬ እና የዓመት በዓሉንም ጭምር ልቀበል የቻልኩት፤ ይህን ዓመት ስቀበልም
ሀገራችን የሰላም፣ የተረጋጋች፣የደስታ፣ የፍቅር እና የጤና እንድትሆንልን ከመመኘት ባሻገር ሁላችንም ደግሞ በየተሰማራንበት ሙያም የተሳካ እና ቆንጆ የሚባል ጊዜንም እንድናሳልፍም ነው
በድጋሚ ልመኝም የቻልኩት”፡፡
የ2012 አዲስ ዓመትን እንዴት እንዳሳለፈ
“ያሳለፍነው ዓመት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰው አስቸጋሪ ነበር፤ በተለይ ደግሞ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ እኛ ኢትዮጵያኖች ብቻ ሳንሆን ዓለም ጭምር ከስራ መስክ ጋር በተያያዘ
ከምንወደው ሙያና ስራችን በመራቅ ያሳለፍንበት ጊዜ ስለነበር ልንፈተንበት ችለናል፤ ከዛ ውጪ በፖለቲካው የተነሳም ሀገር ሰላም ያልሆነችበት ወቅትም ስለነበር ይሄ ሁሉ አልፎና ተረጋግቶ
የአዲሱ ዓመትላይም ኮቪድ ጠፍቶ እና በፖለቲካውም የነበረውም ሽኩቻ ቀርቶ የዓምናውን ጥሩ ጊዜ ያላሳለፍንበትን ሁኔታ ፈጣሪያችን እንዲያስቀርልን ከፍተኛ ምኞቴን እየገለፅኩኝ ነው”፡፡
የኮቪድ 19 መግባትን ተከትሎ ጥሬ ስጋን አትብሉ ተብሎ በመመሪያ ደረጃ ተነግሮ ነበር፤ አትዋሽ አንተ አልበላህም….?
“ለምን እዋሻለሁ፤ በደንብ አድርጌ ነው የበላሁት፡፡ ጥሬ ስጋን ከምነግርህ በላይ ነው በጣም የምወደው፤ ለፋሲል ከነማ ስጫወት ጎንደር ካለው የፆም ቀን ረቡዕ እና ዐርብ ካልሆነ በስተቀር
ከልምምድ በኋላ ጥሬ ስጋን ነው የምመገበው፤ በአጠቃላይጥሬ ስጋን መብላት በጣም ያስደስተኛል፤ በቀዳሚነት የምመርጠው ምግቤም ነው”፡፡
ባለቤትህም እንደ አንተ ጥሬ ስጋን ትወድ እንደሆነ
“እሷ በእዛ ዙሪያ የእኔ ተቃራኒ ነች፤ እኔ ጥሬ ስጋን በፍቅር እንደምወድ ሁሉ እሷ ደግሞ አትወድም፤ የእሷ ምግብ ፒዛ እና በርገርም ነው፤ በተለይ ፒዛን በጣም ትወዳለች”፡፡
በኮቪድ ከእግር ኳስ መራቁን ተከትሎ የሰውነት ኪሎ መጨመርን አሳይቶ እንደሆነ
“ኪሎ አልጨመርኩም፤ እንደዚሁም ደግሞ አልወፈርኩም፤ ከእዛ ይልቅ አሁን ላይ በእኔ ላይ ያየሁት ለውጥ ቢኖር የፊት ለውጥ ነው፤ ይኸውም ምንድን ነው? በስራ ላይ /በልምምድ ላይ/
የነበረው ሱራፌል እና አሁን በቤቱ ውስጥ ያለው ሱራፌል ልዩነት የታየበት መሆኑ ነው፤ በፊት በልምምድ ላይ በነበርኩበት ሰዓት ፀሐይ እና ብርድ ስለሚፈራራቅብኝ ፊቴ ይጠቁር ነበር፤ አሁን ላይ
ደግሞ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ የማሳልፍበት ሁኔታ ስላለና ልምምዴንም የምሰራው እዛም በመሆኑ እንደዚሁም ደግሞ ባለቤቴ በፊት ውጪ ከምመገብበት
በሚሻል ሁኔታ እና ለእኔም በሚስማማ መልኩም በቂ የሆነ ምግብ እና ፍሬሽ የሆነ ጁስንም በቤት ውስጥ ሰርታ ስለምታዘጋጅልኝ ፊቴ ጠራ ሊልም ችሏል፤ ከዛ ውጪም የ10ኛ ወር ዕድሜ
ያስቆጠረች ልጅን ካስገኘችልኝ ውዷ ባለቤቴ ጋርም ሆኜ ልምምዴን በቤት ውስጥ በጥሩ ሁኔታ እየሰራው ያለበት ሁኔታ ስላለና አሁን ደግሞ በኮሮናው ምክንያት ተከልክሎ የነበረው
የጂምናዝየም ስራ ሊፈቀድ ስለቻለም እዛ እየተለማመድኩ ያለሁበት ሁኔታም ስላለና የእኔ ሰውነት ደግሞ በተፈጥሮ የመወፈር ነገርንም ስለማያሳይ በአሁን ሰዓት በጥሩ ሁኔታ ላይም ነው
የምገኘው”፡፡
ከኮቪድ መግባት በኋላ በአካል ማግኘት ፈልጎ ስላላገኘው እና በጣም ስለናፈቀው ነገር
“የእውነት እና የምር ለመናገር አሁን ላይ በጣም የናፈቀኝ ነገር ቢኖር ከሰዎች ይልቅ እግር ኳሱ ነው፤ ከዛ በኋላ ደግሞ ለብዙ ወራቶች ያላገኘዋቸው የስራ ባልደረቦቼ፣ የክለባችን ደጋፊዎች
እና ደጋፊዎቻችን በስታድየም ውስጥ የሚያሰሙት የድጋፍ ድምፅ ሌላው የናፈቁኝ ነገሮች ናቸው”፡፡
በፋሲል ከነማ ባለው እና በአዳማ ከተማ ክለብ በነበረው ቆይታ ምርጡን የጨዋታ ጊዜ የት እንዳሳለፈ
“በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ደስተኛ ሆኜ ባሳልፍም ለእኔ ራሴን የተመለከትኩበት እና አቅሜንም አውጥቼ እንድጫወት ያደረገኝ ክለብ ቢኖር ፋሲል ከነማ ነው፤ በፋሲል
ከነማ ቆይታዬ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከማግኘት ባሻገር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ኮከብ ተጨዋች ተብዬም ሽልማትን ያገኘሁበት ወቅትም ስለነበር
ምርጡን ጊዜም ላሳልፍበትም በቅቻለሁ”፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ፣ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ለመሰልጠን ችለሃል፤ ለአንተ ከሶስቱ ምርጥ ስለሆነው
አሰልጣኝ
“ሶስቱም አሰልጣኞች የየራሳቸው የማሰልጠን ብቃት /ኳሊቲ/ አላቸው፤ ከእነሱ መሀል አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እኔን በኃላፊነት በመራኝ ሰዓት በአካል ብቃቱ በኩል ብቁ /ፊት/ እንድሆንና
በፊት ኳስን ስጫወት የምንቀሳቀሰው ኳስን ሳገኝ ብቻ ነበርና ከዛ በኋላ ግን የነበረብኝን ኳስ የመንጠቅ ችግር እንዳስተካክል ያደረገበት መንገድ የሚደንቅ ነው፤ ሌላው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ
ለመልሶ ማጥቃት /ካውነተር አታክ/ አጨዋወት ያለው እምነት ከፍ ያለ ስለሆነ ያን አጨዋወት እንድለምድ አድርጎኛል፤ የአሁኑ አሰልጣኛችን ስዩም ከበደም የሚከተለው የአጨዋወት
ፍልስፍና ልክ ከቀድሞ አሰልጣኛችን ውበቱ አባተ ጋርም የሚመሳሰል አይነት በመሆኑም ከሁሉም ጥሩ ነገሮችን ማግኘቴን ብቻ ብጠቅስ ለእኔ በቂዬ ነው ብዬ ነው የማስበው”፡፡
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ስላጠለቀው የማልያ ቁጥር
“የአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ ነበር የተጫወትኩትና በተስፋው ቡድን እያለው 19 ቁጥርን በዋናው ቡድን ደረጃ ስጫወት ደግሞ 80 ቁጥርን ነበር አጥልቄ የተጫወትኩት”፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስላስቆጠረው የመጀመሪያ ግቡ
“የመጀመሪያዋ የሊግ ግቤ አዳማ ከተማ ወላይታ ድቻን 3-1 ሲያሸንፍያስቆጠርኳት ናት፤ ግቧንም ያኔ በ2008 ዓ/ም ላይ በ80 ቁጥር መለያዬ ያገባዋትም ነበረችና ከማሊያው ሰፋ ማለት
አንፃርና ከእኔም አነስ ያለ ሰውነት አኳያ የማሊያው ቁጥር አይከብደውም እንዴ የተባለበትን ጊዜ ፈፅሞ የማልረሳውም ነበርና ከዛ በኋላም ነው በ80 ቁጥር ማሊያው ከእኔ ሰውነት ጋር
አብሮ አይሄድም በሚል ብዙ ሲባል ከርሞመጀመሪያ 14 ቁጥርን ቀጥሎ ደግሞ የ7 ቁጥርን ማሊያን በኋላ ላይ ልለብሰው የቻልኩት”፡፡
የ“7” ቁጥርን መለያን ለአዳማ ከተማ አጥልቀህ ስትጫወት ፈልገህ ሳይሆን ተገደህ መሆኑን ሰማን…ስለለበስክበት ምክንያት አንድ ነገር ብትለን?
“የአዳማ ከተማ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ላይ የ7 ቁጥርን መለያ ልለብስ የቻልኩት የእውነት ነው ፈልጌ ሳይሆን ተገድጄ ነበር፤ ይሄን ማሊያ ያደርግ የነበረው የክለባችን ምርጡ ተጨዋች
እና በኋላ ላይ አንዱ ዓይኑን በጉዳት ያጣውና ከቡድኑም በእዚህ መልኩ የተለየውታከለ አለማየሁ ነበር፤ ከዛም 2009 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ የሲቲ ካፕ
ጨዋታ ላይየቡድናችን አሰልጣኝ የነበረው አሸናፊ በቀለ “ከዚህ በኋላ የታከለ ምትክ አንተ ነህ፤ የእሱን 7 ቁጥርም ለብሰህ ትጫወታለህ፤ ታከለ በሜዳ ላይ እንዳለም ህዝቡ እንዲያውቅም
እፈልጋለሁ” ብሎኝ ሲነግረኝ የእሱን ቁጥር ለብሼ ወደ ሜዳ ለመግባት ፈራሁ፤ ምክንያቱም ታከለን በችሎታው በጣም የማደንቀው፣ የማከብረው፣ በጣም ጎበዝ እና ብዙም ኳሊቲ ያለው
ትልቅ ተጨዋች ነበርና አሁን በውጪው ዓለም ልክ የሄነሪን ማልያ ኦባሚያንግ ከዛ ባፊት ደግሞ ቲዎ ዋልኮት ለብሰው እንደተጫወቱት ሁሉ እኛም ክለብ ጋር ሰው እንደ እሱ ብዙ ነገርን በአንዴ
ስለሚጠብቅብህ ነው ራሴን ዝቅ በማድረግ ራስህን ዝቅ ስታደርግ ደግሞ ፈጣሪ ከፍ ያደርግሃልና በዛ መልኩ ነው አይሆንም የእሱን ማሊያ አለብስም ብዬ ለአሰልጣኛችን የነገርኩት፤
ወዲያውም አሰልጣኝ አሸናፊ አሰልጣኙ እኔ ነኝ ወይንስ አንተ በሚል ቃል ከተናገረኝ በኋላ የቡድናችን ተጨዋቾች ደስተኛ ባይሆኑም ከዛን ጊዜ አንስቶ በክለቡ ቆይታዬ ተገድጄ መለያውን አድርጌ
ልጫወት ቻልኩ”፡፡
በፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ቆይታህ ተወዳጅ ሆነሃል፤ የክለቡ ምልክት ነህ ማለት ይቻላል?
“በፍፁም፤ እኔ የቡድኑ ምልክት ተጨዋች አይደለሁም፤ ፋሲል ከነማ ብዙ ታሪክን ሰርተው ያለፉ ተጨዋቾች ተጫውተው ያሳለፉበት ክለብ ነው፤ እነ አብዱራህማን ሙባረክን /ግሪዳውን/
መጥቀስ ይቻላል፤ ከዛ ውጪ ደግሞ በክለቡ ብዙ ቆይታ ባያደርግም በችሎታው በጣም የማደንቀው ዳዊት እስጢፋኖስም የተጫወተበት ቡድንም ነውና ራሴን በዛ ደረጃ የምገልፅ አይነት
ተጨዋች አይደለሁም፤ ከዛም በመነሳት በቡድኑ ቆይታዬ በጣም የተረዳሁት እና ልናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር “የፋሲል ከነማ ትልቁ ምልክት ዓርማው እንጂ እኔ እንዳልሆንኩ ነው”፡፡
ለፋሲል ከነማ ገብተህ ስትጫወት በአዳማ ከተማ የለበስከውን 7 ቁጥር ቀይረህ 10 ቁጥርን ነው ለማጥለቅ የቻልከው፤ ለምን መቀየር ፈለግክ?
“ከአዳማ ከተማ ወደ ፋሲል ከነማ ዝውውርን ባደርግኩበት ጊዜ ቀድሜ እለብስ የነበረውን 7 ቁጥር በመቀየር 10 ቁጥርን ላደርግ የቻልኩት ፋሲል ውስጥ ለቡድኑ ለ7 ዓመታት ያህል
የተጫወተ ፍፁም የሚባል ሲኒየር ተጨዋች ስለነበር የ7 ቁጥሩን እሱ ይለብስ ስለነበር ነው፤ ከዛ በኋላም 10 ቁጥርን ያጠልቅ የነበረው ራምኬል ሎክ ከቡድኑ ሲለቅ ደግሞ ይሄንኑ ማሊያ
ለማጥለቅ ቻልኩ፤ 10 ቁጥርን በጣም እወደዋለሁኝ፤ ይህን ማሊያ የማደንቀው ዳዊት እስጢፋኖስም አጥልቆት የተጫወተበት መለያ በመሆኑም እኔም ማድረጌ የሚያስደስተኝም ነው”፡፡
ለፋሲል ከነማ ስትጫወት ከአድናቂዎችህ ስለተሰጠህ ስጦታ እና ሙገሳ
“በፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ቆይታዬ ከአድናቂዎቼም ሆነ ከደጋፊዎቻችን ብዙ ስጦታዎችን አግኝቻለው፤ ከሁሉ ስጦታ ደግሞ ለእኔ ትልቁ ስጦታ ከአንዲት እንስት የቡድኑ ደጋፊ በፍሬም ተሰርቶና
ታሽጎ ልክ ወደቤትህ እንደገባህ ክፈተው ብላኝ የሰጠችኝ የኪዳነ ምህረት ምስል ለእኔ ልዩ የደስታ ስሜትን ነው የፈጠረብኝ፤ ምክንያቱም የእኔ የውልደት ቀን ሰኔ 16 ቀን ነው፤ ይሄ ቀን ደግሞ
የኪዳነምህረት በመሆኑና የስጦታ ምስሉም ከእኔ የውልደት ቀን ጋር በመገናኘቱም ነበር በኋላ ላይ ልጅቷን እስከማክበርና እስከማመስገን ደረጃም ላይ የደረስኩት፤ ከዛ ውጪ ሌላ ከተሰጡኝ
ስጦታዎች መካከል የማስታውሰውና ስጦታውን ለሰጠኝም ሰው የማመሰግነው በ2010 የፕሪምየር ሊጉ ውድድራችን በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታችን ሐዋሳ ከተማን ጎንደር ላይ ገጥመን
ነበር፤ እነሱን 3-1 ለማሸነፍም ችለን ነበር፤ በዛ ጨዋታ ላይ ታዲያ ለክለቡ 3ኛ ለእኔ ደግሞ የመጀመሪያዬ የሆነችና ከብዙዎችም ሰዎች ጋር እንድተዋወቅባት ያደረገች ምርጥ የቺፕ ግብን
አስቆጥሬ ነበርና ግቧን ካስቆጠርኩ በኋላ ማሊያዬን አውልቄ ስሮጥ የሚያሳይ ፎቶ በባነር መልክ ተሰርቶ ተሰጥቶኝ ነበርና ይሄን የሚያምር ስጦታውን ፈፅሞ አልረሳሁም፤ ስጦታውን እኔም
በጣም ለምወዳት እናቴም ሰጥቻትም በቤቷ ውስጥ ልሰቅለውም ችላለች፤ ሌላው በአድናቆት ደረጃ የሚሰጡኝ ሙገሳዎች ብዙ ቢሆንም ከአድናቆት ባሻገር ደግሞ ጉድለትህን የሚነግሩህ
ሰዎችና ጓደኞችም አሉና እነሱንም በአግባቡ እየተቀበልኳቸው ነው ያለሁት፤ ለምክራቸውም ምስጋናን አቀርባለው፤ በተለይ በችሎታ አንተ ጎበዝ ነህ፤ ጥሩ ነገርም አለህ፤ ግን ስሜታዊ
ትሆናለህ ይሉኛል፤ ያው ኳስ ስሜታዊ የሚያደርግ ስፖርት ቢሆንም ለመጪው ጊዜ ስሜታዊነቴን አስተካክዬና አንድአንዴም ከዳኞች ጋርም ያሉብኝን ጭቅጭቆች አስተካክዬ ለመምጣት ራሴን
እያዘጋጀው ነው”፡፡
ከፋሲል ከነማ ጋር ዘንድሮ ሊያሳካው ስለሚፈልገው ድል
“በእዚህ ቡድን የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ እስካሁን የጥሎ ማለፍና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫዎችን ለማግኘት ችያለሁ፤ ከዛ ውጪም የኮከብ ተጨዋችነት ክብርንም ልጎናፀፍ በቅቻለሁ፤
በእነዚህ ስኬቶቼም በጣምም ደስተኛ ነኝ አሁን የቀረኝ ድል ደግሞ የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ ነውና ይሄን ስኬት በእዚህ ዓመት የማሳካው ነው የሚሆነው”
የእግር ኳስን ሜዳ ገብተህ በምትጫወትበት ሰዓት በተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ማርክ የመደረግ ነገር አለ፤ ያኔ ትበሳጫለህ?
“ብዙ ጊዜ የእግር ኳስን ስጫወት ማርክ የማልደረግበት ቀን የለም፤ በእዚህ በኩል ታዲያ በጣም የተበሳጨሁበት ወቅት ቢኖር አንዴ መቐለ ላይ ከስዑል ሽረ ጋር ስንጫወት በእነሱ 3 እና 4
ተጨዋቾች መሀል ተከብቤና ማርክ ተደርጌም እየመቱኝ በምንጫወትበት ሰዓት ምንም አይነት እንቅስቃሴን እንዳላደርግ ስላገዱኝ በብስጭት ወደ አሰልጣኛችን ስዩም ከበደ ጋር ሄጄ
ሊያጫውቱኝ አልቻሉምና ቀይረኝ እስከማለት ደረጃ ደርሻለሁ፤ ያን ስነግረው ጠራኝና ምንም ችግር የለውም አትበሳጭ ለእኛ የአንተ ወደዚህ እና ወደዛ ማለት ብቻ ይበቃናል፤ አንተን እነሱ ማርክ
ሊያደርጉ ሲመጡ ሌሎቹ ተጨዋቾቻችን ነፃ እየሆኑ ነውና ለቡድኑ ትልቅ ስራን እየሰራክ ነው፤ አንተ በመኖርህ ብቻ ተጠቃሚም መሆን ይቻላልም ብሎ በእግር ኳሱ ላይ ጥሩ ግንዛቤው
እንዲኖረኝም አድርጓል”፡፡
የእግር ኳስን ስትጫወት አንተን ለማበሳጨትም ሆነ በሌላ ምክንያት ኳስ አትችልም ያለህ ተጨዋች አጋጥሞህ ያውቃል?
“በፍፁም፤ የሚሳደቡ ተጨዋቾች ግን አጋጥመውኛል፤ ያኔ ሲሰድቡኝም እኔም ስሜታዊ ሆኜም አናድጄ ምላሼን እሰጣችኋለሁ”፡፡
የእግር ኳስን በተቃራኒነት ስትገጥሙትና ስታሸንፉት ደስ የሚልህ ክለብ
“ቅዱስ ጊዮርጊስን ነዋ! ምክንያቱም እነሱን ማሸነፍ ማለት ለሌሎች ግጥሚያዎችከፍተኛ ተነሳሽነትን ስለሚፈጥሩልህ”፡፡
በፕሪምየር ሊጉ በተቃራኒነት ከገጠምካቸው ቡድኖች ውስጥ በጣም ያስቸገሩህ እና የሚከብዱህ
“የመጀመሪያው አስቸጋሪው ክለብ ወደ ሱፐር ሊጉ /ከፍተኛው ሊግ/ የወረደው ደቡብ ፖሊስ ነው፤ ሌላው ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ የሚወዳደረው ኢትዮጵያ ቡና ነው፤ እነዚህ ሁለት ቡድኖች
የሚያስቸግሩትም የሚከብዱትም ግብ ገብቶባቸው ሁሉ ኳስን ይዘው ስለሚጫወቱ ነው፤ ኳስ የሚይዝ ቡድን ብዙ ጊዜ ለተጋጣሚ አስቸጋሪ ነውና ሁለቱ ናቸው እስካሁን የከበዱኝ”፡፡
የእግር ኳስን ልጅ ሆኖ ሲጫወት ስላገኘው ልዩ ሽልማት
“ያኔ በምኖርበት ቦታ ለመርቲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ኳስን እጫወት ነበር፤ በምጫወትበት ጊዜም የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች ተብዬ የብራዚሉን ካካ መለያ ልሸለም በቅቻለሁ”፡፡
የእግር ኳስን በልጅነት ዕድሜው ሲጫወት ግጥሚያዎችን በምን አስይዘው ይጫወቱ እንደነበር
“የመጀመሪያው ፉትቦል የሚባል ማስቲካ ነበር በእሱ የተለያዩ ተጨዋቾችን ምስል የያዘ ተለጣፊ ነገር ነበርና በእሱ ነው፤ በኋላ ላይ ደግሞ በገንዘብ መጫወት ጀመርን”፡፡
የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ነጭናጫ ነበርክ?
“አዎን፤ ያ የመጣውም መሸነፍን ካለመፈለግ ነው፤ ይሄ ባህሪዬ አሁንም አልፎ አልፎ ይታይብኛል”፡፡
የእግር ኳስን በትልቅ ደረጃ መጫወት እየቻለ ያሰበበት ስፍራ ባለመድረሱ የሚያስቆጭህ ተጨዋች
“ሁለት ናቸው፤ አንዱ ለአዳማ ከተማ ይጫወት የነበረው እና በጣም የማደንቀው አንድ ዓይኑንም በአደጋ ያጣው ታከለ አለማየሁ ሲሆን ሌላው ደግሞ በተወለድኩበት መርቲ ጃጁ ኳስን በአጥቂ
ስፍራ ላይ ሆኖ ሲጫወት በጉልበት ህመም ምክንያት በኳሱ ሳይሳካለት የቀረው እዲ አበራ ሌላ የምጠቅሰው ተጨዋች ነው”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጨዋች ብትባልም፤ ዋንጫውን ግን ለማንሳት አልቻልክም….አያናድድም?
“በደንብ ያናድዳል እንጂ፤ ለዛም ነው ይሄን የሊግ ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳትም ጠንክሬ እየሰራሁኝ ያለሁት፤ በተለይ በእዚህ ኮቪድ ወቅት ሰፊ የእረፍት ወቅትም ነበርና በቀን
ሁለቴም ነው ያለ እረፍት ቤቴ ሆኜና ጂም በመስራትም የአዲሱን የውድድር ዘመን እየተጠባበቅኩ ያለሁት”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ተጨዋችነትን ክብር ለሁለት ጊዜያት ያሳኩ ተጨዋቾች አሉና የእነሱን ሪከርድ ለመጋራት ስለምታደርገው ጥረት
“የፕሪምየር ሊጉ የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማትን በፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ስለሚገባኝ ማግኘት ችዬ ነበር፤ ይሄ ኮከብነትም በእዚህ ብቻ እንዲቆም
አልፈልግምና ተከታታይ የሆኑ ስኬቶችን ማግኘት እፈልጋለው፤ አሁን ላይ ኮከብ ተጨዋችነትን እያለምኩ ያለሁትም ለሁለት ጊዜ ለሁለት ጊዜ ያገኙትን ተጨዋቾች ሪከርድ ለመጋራት ብቻ ሳይሆን
እነሱን አልፌም ለመሄድም ጭምር ነውና ያን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው”፡፡
የእግር ኳስን ተጫውተህ ስታበቃ ወደፊት አሰልጣኝ የመሆን እቅድ አለ?
“በፍፁም”፡፡
የእግር ኳስን ተጫውተህ ስታበቃ ታዲያ ምን ስለመሆን ነው እያሰብክ ያለኸው?
“በንግድ ውስጥ ስለመሰማራት ነዋ! ምክንያቱም ባለቤቴ በዛ ውስጥ ነው ያለችው፤ ከእሷ ጋርም ከወዲሁ ብዙ ነገሮችንም እየተነጋገርን እንገኛለንና ነጋዴ ነው የምሆነው”፡፡
የእግር ኳስ ማቆሚያ እንዲሆን የምትመኘው ክለብ
“አሁን ላይ እሱን አላውቅም፤ ፈጣሪ ብሎ ግን ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ማቆሚያዬ ቡድን ቢሆን በጣም ነው ደስ የሚለኝ”፡፡
የአውሮፓ ብዙዋን ሊጎች ተጀምረዋል፤ እየተከታተልክ ከሆንክ ምን ትላለህ?
“ሊጎቹን አዎን እየተከታተልኩ ነው፤ ተመልካች ባለመኖሩ ግን ደብዘዝ ያለ ነው፤ ተጨዋቾቹ ደግሞ በአብዛኛው ብቁ /ፊት/ ናቸው”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግስ ያለተመልካች ከተጀመረ ምን መልክ ይኖረዋል?
“ከአውሮፓዎቹ ሊጎች የበለጠ ደብዘዝ ይላላ፤ ያ ደግሞ ለእኛ ሀገር ስላልተለመደም ብዙም አይመችም”፡፡
ስለ ባለቤቱ እና ስለ ትዳር ህይወቱ
“ከባለቤቴ ሜሮን ሰለሞን ጋር የመሰረትኩት ትዳር በጥሩ ሁኔታ እየሄደልኝ ነው፤ ከእሷ ጋር አሜን ሱራፌልም የተባለች አሁን 10ኛ ወር ላይ የደረሰች ልጅም ለማፍራት ችለናል፤ ባለቤቴን
በተመለከተ በጣም ጥሩ ሰው ነች፤ ከሚገባው በላይ የማፈቅራት እና የምወዳትም ነች፤ እንደ እናቴና እንደቤተሰቦቼም ነው የማያትና ሁሌም በተለይ ደግሞ አሁን ኮሮና ከገባበት ጊዜ ጀምሮ
ከአጠገቤ ሳትለይ አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረገችልኝ ነችና በጣሙን ላመሰግናት እፈልጋለሁ”፡፡
በመጨረሻ
“ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና እንዲሆንልንና የኮቪድ 19 ወረርሽኝም ጠፍቶ ሁሉም በደስታ ዓመቱን እንዲያሳልፍ እንደዚሁም ደግሞ እኔም ከአምናው እና
ከካቻምናው በበለጠ መልኩ ክለቤ ፋሲል ከነማ ውስጥ ጥሩ ነገርን ሰርቼ በርካታ የስኬት ሽልማቶችን ማግኘት ዋንኛው እቅዴ ነው፤ ከእዚህ ሌላ መናገር የምፈልገው በእኔ የእግር ኳስ
ተጨዋችነት ህይወት እዚህ ደረጃ ለመድረሴ ከጎኔ ለሆኑ ሁሉ ቤተሰቦቼን ጨምሮ ታላቅ ምስጋና አለኝ”፡፡
በኮቪድ 19 የሊጉ ውድድር ከተቋረጠበት ጊዜ አንስቶ ሱራፌል ስላሳለፋቸው ጊዜያቶች
የተመለከታቸው ፊልሞች፡- መኒስት ኢንቱ ዘ ባድ ላንድ የተባሉትን ተከታታይ ፊልሞች
ያነበባቸው መፅሐፎች፡- ምንም የሉም
ለብዙ ጊዜያት ስልክ የተደዋወለው፡- ከባለቤቱ ጋር /በተለይ ቤተሰቦቿ ጋር ያደረች እንደሆነ/
ኮቪድ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ስለገዛቸው የሳኒታይዘሮች እና የአልኮሎች ብዛት፡- 3 ሊትር ሳኒታይዘር እና 1 ሊትር አልኮል
ከመኖሪያ ስፍራው በተደጋጋሚ ጊዜ ስለሄደበት ሌላ ቦታ፡- ከናዝሬት አንድ ጊዜ በክለቡ ጉዳይ ወደ ጎንደር ከመሄዱ ውጪ የትም አልሄደም
በየቀኑ ለብዙ ሰዓት ስለተኛው እንቅልፍ፡- ቀን ቀን ለ2 ሰዓት ማታ ማታ ደግሞ ለ12 ሰዓት /ይኸውም ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 4 ሰዓት/