Google search engine

“የፋይናንስ ችግራችን ከተፈታና ደመወዛችን ከተከፈለን ሊጉ ላይ መቆየት የምንችል ይመስለኛል” የአብስራ ተስፋዬ /ደደቢት/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የደደቢቱ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች የአብስራ ተስፋዬ በሊጉ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ብቃቱን
እያሳየ ሲገኝ ተጨዋቹ ከስፖርት ቤተሰቡ ጥሩ አድናቆት ከማግኘቱ አንፃር በክለባቸው የሊጉ ተሳትፎ፣ ወቅታዊ
አቋም እና በራሱም የቡድኑ ቆይታ ዙሪያ አናግረነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የደደቢት የውጤት ማጣት ምስጢር

“በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአችን ክለባችን ውጤት ሊያጣ የቻለው በቅድሚያ ልምድ ያላቸው
/ሲኒየር/ ተጨዋቾች በስኳዳችን ስለሌለን፣ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ችግር ስላለብን ከዚያ ውጪም                                                                                            በአንድአንድ ጨዋታዎቻችን ላይ የዳኝነት ጫናም ስለሚደርስብን እና እንደዚሁም ደግሞ ጎል ማስቆጠሩም ላይ
ከፍተኛ ክፍተቶች ስለነበሩብን እነዚህ ዘንድሮ ላጣናቸው ውጤቶች ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል”፡፡

ውጤታማው እና ጠንካራው የሊጉ ክለብ አሁን ላይ በወራጅ ቀጠናው ላይ ስለመገኘቱ

“ደደቢት በከዚህ ቀደም የሊግ ተሳትፎው በጠንካራነቱ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን የወራጅ ቀጠናው
ላይ መገኘቱ ለእኛ በጣም ከባድ ነገር ነው የሆነብን፤ የክለቡን የቅርብ ጊዜ ውጤት ብትመለከት እንኳን
አምናና ካቻምና ጥሩ ነበር፤ ዘንድሮ ግን ይሄንን ማስቀጠል አልቻልንምና በእዚህ ዓመት ያጋጠመን የውጤት
ማጣት በጣም ያሳዘነን፣ ያስከፋን እና ነገሮቹ ሁሉ የሚያም ሆኖም አግኝተነዋል”፡፡

ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ልምምድ ስለማቆማችሁ

“አዎን፤ ይሄ እውነት ነው፤ የቡድኑ ተጨዋቾች ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከረቡዕ ዕለት አንስቶ
/ያነጋገርነው ሐሙስ ነው/ ልምምድን አቁመናል፤ ልምምዳችንን ልንሰራ ያልቻልነውም የሶስት ወራቶች
ደመወዝ ሊከፈለን ስላልቻለም ነው፤ ይህ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶም ጥያቄያችንን ለክለቡ ስንጠይቅ
ደመወዛችሁን በቅርቡ ታገኛላችሁ ጠብቁ በሚል ምላሽ ይሰጠን ስለነበር አሁን ግን ገንዘቡን እስኪሰጡን ድረስ
ልምምድን አቁመናል”፡፡

ደደቢት በሊጉ የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ በወራጅ ቀጠናው ላይ ይገኛል፤ ክለባችሁ ሊጉ ላይ ይቆያል? ወይንስ
ይወርዳል?

“የዘንድሮው የሊጉ ውድድር ላይ ክለባችን ምንም እንኳን በተደጋጋሚ በደረሰበት ሽንፈት በወራጅ ቀጠናው ላይ
ቢገኝም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ግን ብዙዎቹን ቡድኖች በኳስ ቁጥጥር በልጦ እና ጥሩ ተጫውቶም ነው
ከሜዳ የሚወጣው፤ የሁለተኛው ዙር ላይም ጥሩ መሻሻልን አሳይቶ ውጤት ማምጣት ጀምሮም ታይቷል፤ ያም
ሆኖ ግን የአሁን ሰአት ላይ የሊጉ ውድድር ሊጠናቀቅ 10 ጨዋታዎች በቀሩበት ጊዜ ቡድናችን ውስጥ
የተከሰተው የፋይናንስ ችግር እኛን ልምምድ እስክናቆም ያደረሰን በመሆኑ በሊጉ ላይ የመቆየት እድላችን
በጣም ጠባብ ነው የሚሆነውና አሁን ላይ ክለቡ ከሊጉ ይወርዳል አይወርድም ብሎ ለመናገር በጣም
የሚከብድ ነው የሚሆነው”፡፡

ደደቢትን ከሚገኝበት ደረጃ አሁን ላይ ከሊጉ እንዳይወርድ ማድረግ ይቻላል?

“አዎን፤ ለምን አይቻልም! ክለባችን ያለበትን የፋይናንስ ችግር
የሚፈታ ከሆነ፤ ለቡድኑም ተጨዋቾች ደመወዛቸውን በፍጥነት የሚሰጥ ከሆነ አሁን ላይ በወራጅ ቀጠናው
አካባቢ ከሚገኙት ክለቦች ጋር በነጥብ ብዙም ስላልራቅን እርግጠኛ የምንሆነው ደደቢትን ከወራጅነት
እናተርፈዋለን፤ ይሄን ለማለት ያስቻለኝ ዋንኞቹ ጉዳዮችም በሜዳችን ላይ ተከታታይ ጨዋታዎች ስላሉም ነውና
እነሱን አሸንፈን ሊጉ ላይ እንቆያለን”፡፡

የፕሪምየር ሊግ ፉክክሩን በተመለከተ

“መቐለ 70 እንደርታ በመምራት ላይ የሚገኘው የፕሪምየር ሊጉ ውድድር በአሁን ሰዓት ጥሩ ፉክክር
እየተደረገበት ነው፤ ጨዋታው ገና አላለቀም፤ እያንዳንዱ ቡድንም 10 ጨዋታዎች ይቀሩታል፤ ለዋንጫው
ፉክክር መቐለን የሚከተሉትም ቡድኖች በቅርቡ ይገኛሉና ውድድሩ አጓጊ ሆኗል”፡፡

የደደቢት ክለብ ውስጥ ያለውን የኳስ ሕይወት የት ደረጃ ላይ ለማድረስ እንደሚፈልግ እና ስለ ቡድኑ ቆይታው
“በደደቢት ክለብ ውስጥ ባለኝ የእግር ኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ የነበርኩ ቢሆንም አሁን አሁን ላይ ግን
በተሸናፊው ቡድን ውስጥ መጫወት መቻል ያለህን አቅም ሙሉ ለሙሉ አውጥተህ እንድትጫወት አያደርግምና
እዚህ ላይ ብዙ ነገሮች ያስከፉኛል፤ በእስከአሁን ቆይታዬ ግን ለቡድኑ በማበረክተው ጥሩ የሜዳ ላይ አስተዋፅኦ
ብዙ አድናቆቶችን አግኝቼበታለውና ለወደፊቱ በእነዚህ ነገሮች በመበረታታት ራሴን በኳሱ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ
ማስቀመጥ እፈልጋለው፤ እነዚህም የፕሮፌሽናል ተጨዋች መሆን፣ ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወት
እና በታላላቅ ክለቦች ውስጥም ገብቶ መጫወት ነውና እነዚህን ለማሳካት ጠንክሬ እሰራለው”፡፡

 

የደደቢት ጥንካሬና ድክመት

“የደደቢት ጥንካሬ ተጋጣሚዎቹን በኳስ ቁጥጥር መብለጡ ብቻ ነው፤ ድክመታችን ደግሞ ወደ ማጥቃቱ ላይ
ስናመራ ጎል ማስቆጠር ላይ የአጨራረስ ችግር አለብን፤ ይሄ ችግር ግን አሁን ሁለተኛው ዙር ላይ እየተሻሻለ
መጥቷል”፡፡

በእግር ኳስ ማሻሻል የሚፈልገው

“የሊግ ውድድሩ ላይ ዓምና ጎል ማስቆጠር አልቻልኩም ነበር፤ ዘንድሮ ግን ሁለት አስቆጠርኩ ወደፊት ደግሞ
ብዙ ጎሎች እንዲኖሩኝ ስለምፈልግ እነዚህን ጎል የማስቆጠር ችግሬን ማሻሻል እፈልጋለው”፡፡
ከባህር ማዶ የሚያደንቀው ክለብና የሚወደው ቡድን
“የባርሴሎና ደጋፊ ስሆን ከተጨዋቾች አንድሬስ ኢንዬስታን አደንቃለው”፡፡

በመጨረሻ….

“በእግር ኳስ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ለረዳኝ ፈጣሪዬ፤ ቤተሰቦቼ እና የቡድን አጋሬ ተጨዋቾች እንደዚሁም
በሜዳ ላይ በማሳየው አበረታች ብቃት አድናቆት ለሚሰጡኝ ሁሉ ምስጋናን ማቅረብ እፈልጋለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P