የፋሲል ከነማ ስኬታማው የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች ሽመክት ጉግሳ የቡድናቸውን የዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና መሆናቸውን አስመልክቶ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት።
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ስለመሆናቸው
“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ለሁለት ጊዜ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ደግሞ ለአንድ ጊዜ ከዚህ ቀደም ከተጫወትኩበት የደደበት እና የአሁኑ ቡድኔ የፋሲል ከነማ ክለብ ጋር ላነሳ ችያለሁ። በዚህ ዓመት ላይ ደግሞ ይኸው ቡዙዎች ተጨዋቾች የሚመኙትን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አስቀድሞ የጥሎ ማለፍና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ካነሳሁበት ክለቤ ጋር ገና የሊጉ ጨዋታዎች ሊጠናቀቁ የአራት ሳምንታት በቀረበት ጊዜ ይህን ድል ልጎናፀፍ በቅቻለሁ እና እየተሰማኝ ያለው የደስታ ስሜት ከፍተኛ ነው”።
ለፋሲል ከነማ ቤትኪንጉን ዋንጫ ማንሳቱ ይገባዋል ተብሏል፤ ለዚህ ድል ስለበቁበት መንገድ
“እንደተባለው የእውነትም ድሉ ይገባናል፤ ካሳለፍነው ጥሩ የውድድር ዘመን አኳያ እንደሁም ስኬቱ ባይገባን ነው የሚገርመው።
በዚህ የውድድር ዘመን ፋሲል ለሻምፒዮንነት የበቃው ከመሬት ተነስቶ አይደለም። ብዙ ጥሮና ለፍቶም ነው ድሉን የተቀዳጀው። በዚህ ሂደት ውስጥ እነዚህን እንድናሳካም ሀሜት ነገሮች በክለባችን ውስጥ አለመኖሩና ለሁሉም ለሚያጋጥሙን ችግሮችና ነገሮች ፊት ለፊት መነጋገራችን ሊጠቅመን ችሏል። እኛ ክለብ ውስጥ ባይገርምህ የሙጂብ፣ የሱራፌል፣ የያሬድ፣ የበዛብህ፣ የአምሳሉ እና የመሳሰሉት ተጨዋቾች ጓደኛ ሆኜ ከሁሉም ጋር ተከባብረን ነው ስራን የምንሰራው። ጥሩ ቡድን አለን። ሁሉም ነገር እኛ ጋር በስርዓትም ነው የሚሄደው። በተለይ ደግሞ ከቡና ጋር በነበረን የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ላይ የደረሰብን ሽንፈት እኛን አንገጫግጮን ስለነበር ያ ግጥሚያ ስላነቃንም ነው ሌላ ሽንፈትን ሳናስተናግድ ለዚህ ድል ልንበቃ የቻልነውና ፈጣሪን አመሰግነዋለሁ”።
የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳታችሁን ተከትሎ ከዚህ በኋላ የሚኖሯችሁን ጨዋታዎች በምን መልኩ ልታደርጉ እንደተዘጋጃችሁ
“በእግር ኳስ ዓለም አንድ አንዴ ሻምፒዮናነቱን አስቀድሞ ያረጋገጠ ቡድን በፊት እንደሚጠበቅበት አይነት አቋምና ብቃት በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ላያሳይ ወይንም ደግሞ ምንአልባት ለሌላ ቡድን ጥቅም ተብሎ ከአቅም በታች ሊጫወት ይችል ይሆናል። እኛ ፋሲሎች ጋር እንዲህ ያለ ለእግር ኳሱ ነቀርሳ የሆኑ ነገሮችን በቀሪዎቹ ጨዋታዎቻችን ላይ በፍፁም አናደርግም። ይሄን ደግሞ ባለፈው ከወልቂጤ ከተማ ጋር በነበረን ጨዋታ ላይም አሳይተናል። ከዚህ በኋላም
ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ከሚኖረን ጨዋታም ጀምሮ አሁንም ቢሆን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አነሳን ብለን ለማንም ተጋጣሚያችን ከአቅም በታች እየቀለድን አንጫወትም፤ ፋሲል ከነማ ዋንጫን አገኘሁ ብሎ ብቻ የሚቆም ቡድን አይደለም ቀሪዎቹን ግጥሚያዎች በመርታት ከፍተኛ ውጤትን ማስመዝገብ ይፈልጋል። ከዛ ውጪ ከፍተኛ ግብ አግቢያችን ሙጂብ ቃሲምም ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥሮ ለኮከብ ግብ አግቢነቱ እንዲፎካከር እንፈልጋለን። ሌላው ደግሞ ሁሉም ሰው በኳስ የተፈጠረ ቤተሰብ አለው። በዚህ ዕድሜ ሽልማቶችን ማግኘትም የሁሉም ፍላጎትም ስለሆነ ኳሱን ያለምንም መዘናጋት ለወጣት ተጨዋቾቻችን ጭምርም ነው ጥሩ ነገርን እንዲጠቀሙ በመፈለግ እና ለእነሱ ልምዳችንን ጭምር በማካፈል እየተጫወትንና ደስታችንንም እያጣጣምን የምንገኘው። ይህን ካልኩ ሌላ ልጨምረው የምፈልገው አንድ ነገር በእግር ኳሳችን ላይ መላቀቅ በፍፁም እንዳይኖርም ነውና ከዚህ በኋላ በሚኖሩት ግጥሚያዎች እኛ የምንለው ልክ እንደኛው ስኬት ሁሉ ሁሉም ቡድን በእግር ኳሱ የልፋቱን ማግኘት አለበትም ነው”።
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የሜዳ ላይ ብቃቱ ከሌላው ጊዜ አኳያ ምርጥ ስለመሆኑ
“የእውነት ነው። የከዚህ በፊቱ ብቃቴ ጥሩ እንደሆነ ባውቅም የዘንድሮ ደግሞ ለየት ብሎብኛል። ሶስት ግቦችን በውድድር ዘመኑ ላይ አስቆጥሬያለሁ። 13 አሲስቶችን ደግሞ አድርጌያለሁ። ከዛ ውጪም በዚህ ዓመት ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችን እንዳሳየውም ተረድቻለሁ። ይህ ሁሉ የሆነውም ጠንክሬ በመስራቴ ነው”።
ለወላይታ ድቻ ከሚጫወቱት ወንድሞቹ ጋር ስለሜዳ ላይ ብቃታቸው ያወሩ እንደሆነ
“አዎን፤ ከእነሱ ጋር ልክ እንደክለባችን ተጨዋቾች እና ጓደኞቼ ነው የማወራቸው፤ ባለን ብቃት ላይም በደንብ እንነጋገራለን፡፡ ለምሳሌ አንዱ ኳስ የሚይዝ ከሆነ ምን ሰዓት ላይ ኳስን መያዝ እንዳለበት እነገረዋለው፤ እኔም ላይ ክፍተቶች ካዩብኝ ጨዋታዎቹ በዲ ኤስ ቲቪ የሚተላለፉ በመሆናቸው ይነግሩኛል”፡፡
ስለ ቁጠኝነቱ
“ይሄ መሸነፍን ካለመፈለግ አብሮኝ የመጣና ያደገብኝ ነው፤ ለዛም ነው በሜዳ ላይ ስቆጣ የምስተዋለው”፡፡
በመጨረሻ
“ለፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ ለክለቡ አጠቃላይ አባላትና ለቤተሰቦቼ የዘንድሮውን ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማሸነፍ በመቻላችን በቅድሚያ እንኳን ደስ አላችሁ ማለትን እፈልጋለው፤ ይሄ ዋንጫ ብዙ መስዋትነትን በመክፈል ከዚህ ቀደም ያጣነውን ዋንጫ የካሰልን ነው፤ ድሉም በጣም አስደስቶናል፤ ከጎናችን ለነበራችሁ ደጋፊዎቻችንም ሁሉ ከፍተኛ ምስጋናን ላቀርብላችሁም እፈልጋለውኝ”፡፡