Google search engine

“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እስካሁን አለማንሳቴ  ይቆጨኛል” “ወደ ቀድሞው ብቃቴ  መመለስና  አዳማ ከነማን ጠንካራ ተፎካካሪ ማድረግ ምኞቴ ነው” አሜ መሐመድ /አዳማ  ከነማ/

 

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ  ፕሪምየር  ሊግ ሻምፒዮና  ትናንት በተደረገው ጨዋታ  አዳማ ከነማ  ከፋሲል ከነማ  ጋር ተጫውቶ  1-1 ሊለያይ ችሏል፤    ለአዳማ ከነማ  ቀዳሚ  ያደረገችውን  ግብ  አሜ መሐመድ  ሲያስቆጥር   ለፋሲል  ከነማ  ደግሞ   ኦኪኪ አፉላቢ  ሊያስቆጥር  በቅቷል፡፡

አዳማ  ከነማ  ግጥሚያውን  በአቻ ውጤት ባጠናቀቀበት   ጨዋታ   ደረጃውን   ወደ    ዳሽ    በማምጣት ያሻሻለ ሲሆን  ቀጣዩን  ፍልሚያም በመርታት  ወደ  ላይ ከፍ ለማለት መዘጋጀቱንም  የቡድኑ  የአጥቂ  ስፍራ  ተጨዋች አሜ መሐመድ  ለሊግ   ስፖርት ጋዜጣ   አዘጋጅ ጋዜጠኛ  መሸሻ ወልዴ  /G.BOYS/  አስተያየቱን   ሰጥቷል፡፡

የአዳማ  ከነማው  የአጥቂ  ስፍራ  ተጨዋች   አሜ  መሐመድ   ስለ  ቤትኪንግ  ፕሪምየር   ሊግ  ተሳትፎአቸው    እና   ስለ  ራሱ  እንደዚሁም  ደግሞ  በሌሎች  ተያያዥ  ጉዳዮች   ዙሪያ  ሊግ ስፖርት  አናግራው  የሚከተለውን ምላሽ  ሰጥቷቷል፡፡

ሊግ፦  በቤትኪንግ  ፕሪምየር  ሊጉ  ከፋሲል  ከነማ  ጋር  አቻ ልትለያዩ ችላችዋል፤  ግጥሚያው  እንዴት  ነበር?

አሜ፦  በመጀመሪያው  አጋማሽ እኛ  ጥሩ  ነበርን፤  ከእነሱም  በተሻለ  የኳስ ብልጫን  ወስደንም ተጫውተናል፤  ውጤቱ  ለእኛም  ለእነሱም  አስፈላጊ  ስለነበረም እንደነበረን  የኳስ ብልጫም  ብዙ ጎል ማግባት እንችልም ነበር፤  ወደ  ሁለተኛው   አጋማሽ   ስናመራ ደግሞ  እኛ ወደ  ኋላ ባፈገፈገ  መልኩ በመጫወታችን እነሱ ሲጫኑን  ነበር፤  በረጅምና በቆመ ኳስ  ላይም  በመጠቀም  ወደፊትም   ስለተጫወቱ  ግጥሚያው   በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ  ችሏል፡፡

ሊግ፦  የአቻ  ውጤቱ  ለሁለታችሁም  ፌር ነው?

አሜ፦    እኛ  ካገኘነው  የግብ  እድል  አንፃር  መጀመሪያ  ላይ   ግጥሚያውን  መጨረስ  እንችል  ነበር፤  ያም ሆኖ ግን  የኳስ  ነገር ሆነና  ፍልሚያችን  በአቻ ውጤት  ሊጠናቀቅ በቅቷል፡፡

ሊግ፦  በድሬዳዋ  ከተማ  ላይ ያላችሁ  የውድድር  አጀማመር  ምን  ይመስላል?

አሜ፦  በመጀመሪያው ግጥሚያ  ድሬዳዋ ከተማን ድል  አድርገን  ነበር፤ ከዛም  ከኢትዮጵያ  ቡናና  ከፋሲል  ከነማ  ጋር  አቻ  ተለያየን፤  ይህን   ቆይታችንን  ስመለከትም  ከሐዋሳ  መልስ  ያሉብንን ችግሮች   እያስተካከልን   መምጣታችንንም  አሳይቶናልና   ይሄን  ነው  ለማስቀጠል  የምፈልገው፡፡

ሊግ፦  ቤትኪንግ  ፕሪምየር ሊጉ ሲጠናቀቅ የቱ ስፍራ  ላይ  ነው  የምናገኛችሁ?

አሜ፦ የእኛ እቅድ ጥሩ  ተፎካካሪ  ሆኖ ሊጉን  በደረጃ ውስጥ  ማጠናቀቅ ነው፡፡ ለዛም ለመብቃት  ጠንክረን እንሰራለን፡፡

ሊግ፦  በቤትኪንግ  ፕሪምየር   ሊግ  የዘንድሮ ፍልሚያችሁ  የየቱ ጨዋታ ውጤት  ያስቆጫችዋል?

አሜ፦ የሚቆጨኝ  አቻ  መውጣት  ሳይገባን  የወጣንባቸውን   ፍልሚያዎች ናቸው፤ ከእነዛ መካከልም  በተለይም ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር  ስንጫወት ብዙ  ኳስ  ስተን  ማሸነፍ  የምንችልበትን ጨዋታ  አቻ  መለያየታችን  በጣሙን  ያበሳጨኛል፡፡

ሊግ፦  አዳማ  ከነማ  ምርጥ  ቡድን  ነው?

አሜ፦  አዎን፤  በየቦታውም  ምርጥና ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብም  አለን፡፡

ሊግ፦  በፋሲል  ከነማ  ላይ  ጎል ማስቆጠር ችለሃል፤   በእዚህ ዙሪያ  የምትለው ነገር ካለ?

አሜ፦  ወደ ድሬዳዋ ከተማ ከመጣን ጀምሮ  ጥሩ ብቃቴን በማሳየት ላይ እገኛለው፤  በእዚሁ ከተማ ቆይታዬም   በፋሲል ከነማ  ላይ  የመጀመሪያ ጎሌን ለማስቆጠርም  በቅቻለሁ፤  ከግብ ስትርቅ  ብዙ ጫና አለው፤   እንደ አጥቂነቴም ወደፊት  ከእኔ  የሚጠበቅብኝን ብዙ  ጎሎችንም  ማስቆጠር  አለብኝና ያን  ማሳካት ይኖርብኛል፡፡

ሊግ፦  በውድድር  ዘመኑ  ቡድናቸው  ስላላቸው ጥንካሬና  ክፍተት?

አሜ፦  እስካሁን 6  ገብቶብናል፤  ብዙ  ጎል  የማይቆጠርብን   መሆኑ  እኛን  ጠንካራ  አድርጎናል፡፡ ክፍተታችን  ደግሞ  በፊት  መስመሩ ላይ  ተደጋጋሚ ጎሎችን  ማስቆጠር መቻል ነው፤  ይሄን  ችግር  ለማስተካከል መዘጋጀት  አለብን፡፡

ሊግ፦  በእግር ኳስ ጨዋታ  ዘመንህ  ምርጡ  የጨዋታ  ጊዜ  የት  እያለህ ያለው ነው?

አሜ፦ በጅማ አባ ቡና  እዛ  በነበርኩበት ሰዓት  ክለቡን ከሱፐር ሊግ ወደ  ፕሪምየር  ሊግ  እንዲሸጋገር አስችየው ነበር፤  ከዛ ውጪ የውድድር ዘመኑም ኮከብ ግብ አግቢ ተብዬ ስለተሸለምኩና  ለወጣትና  ለዋናው ብሄራዊ ቡድንም ስለተመረጥኩ  ያ  ጊዜ  ምርጥ  የሚባል  ነው፡፡

ሊግ፦  ጥሩና  ምርጥ  ጊዜ   ያሳለፍክበት  ወቅትስ?

አሜ፦  እሱ በወልቂጤ ከተማ  በነበርኩበት  ጊዜ  አምና ላይ  ነበር፤ ቡድናችን መጀመሪያ ላይ  ጥሩ ቢሆንም  በኋላ ላይ አቋሙ እየወረደ በመምጣቱ እና  አንድ ነጥብ ብቻም  በሁለተኛው ዙር ላይ ሊያገኝ በመቻሉ ይሄ ጥሩ ጊዜን ያላሳለፍኩበት ነው፡፡

ሊግ፦ ወደ  ቅዱስ ጊዮርጊስም አምርተህ ነበር፤ በእዛ  የነበረክስ ቆይታ?

አሜ፦  ያኔ  ክለቡን የተቀላቀልኩት  ሻምፒዮና ሆነው ከመጡ በኋላ ነበር፤ በቆይታዬም በአፍሪካ ቻምፒዮንስ  ሊግና በኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ  ልሳተፍም ችያለው፤  እኔ የገባሁበት  ዓመት ላይም ጅማ አባጅፋር ዋንጫውን ያንሳ እንጂ ድሉ ለእኛ ይገባንም ነበር፤   በቅ/ጊዮርጊስ ቆይታዬ  አንዳንዴ  በመጠነኛ ጉዳት  ከሜዳ የራቅኩበት ወቅት ቢኖርም  በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡

ሊግ፦  ወደ ካሜሮኑ  የአፍሪካ  ዋንጫ ተሳትፎአችን እናምራ  የዋልያዎቹ  ተሳትፎ እንዴት  ይገለፃል?

አሜ፦ አሪፍ ነበሩ፤  ጥሩ  እንቅስቃሴንም አድርገዋል፡፡ የኳስ ነገር ሆነና  ውጤት አጣን እንጂ  ከእነሱ ጋር ያለን  ልዩነት  ይሄን ያህልም አይደለም፤  የዋልያዎቹ  ዋናው ችግር የነበረው በመጀመሪያው ግጥሚያ  ቡድኑ አዲስ ስለሆነ  ለመደናገጥ በመቻላቸው ነው፡፡

ሊግ፦  በቀጣይነት  ወደ  ዋልያዎቹ ስብስብ ስለመቀላቀል ምን ታስባለህ?

አሜ፦  ያን እድል ዳግም ለማግኘት ጠንክሬ መስራት አለብኝ፤  ፈጣሪ ሲፈቅድም የቡድኑ ተጨዋች መሆኔ የማይቀር ነው፡፡

ሊግ፦  አሜ  ሲገለፅ?

አሜ፦  ሰዎችን ብዙ  እቀርባለው፤  እናደዳለውም፡፡  መበለጥን ደግሞ  ፈፅሞ አልወድም፡፡

ሊግ፦  ወደ  ትዳር  ህይወትህ  እናምራ?  እሷ ማን ትባላለች? እንዴትስ ትገለፃለች?

አሜ፦  አሁን ላይ   ትዳርን  ከመሰረትኩ ሶስት ዓመት ሆኖኛል፡፡  ባለቤቴም   ነጃት  ጃፋር  ትባላለች፡፡  በጅማ ከተማ ላይም ነው ያገኘዋት፡፡  ባለቤቴ ለእኔ ሁሉም  ነገሬ ናት፤ በሁሉም ነገር ከጎኔም ናት ከእሷ  የሁለት  ዓመት እድሜ ያለው ዊልዳን  አሜ የሚባል ልጅም አለኝና በእዛ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሊግ፦  በእግር  ኳስ  ተጨዋችነት  ዘመንህ   አላሳካሁትም የምትለው  ነገር  ምንድን ነው?

አሜ፦ የፕሪምየር ሊግ  ሻምፒዮና  አለመሆን መቻሌን  ነው፤   ያን  ለአንድ  ቀን  ባሳካው በጣም ደስ ይለኛል፡፡

ሊግ፦  በቤትኪንግ  ፕሪምየር ሊጉ  ለአዳማ ከነማ ፈታኝ  የሆነበት ክለብ ማን ነው?

አሜ፦  በጣም የፈተነን ክለብ የለም፤ ብዙ ቡድኖች አምሳ አምሳ ነው  እኛን የፈተኑን፡፡

ሊግ፦  በቤትኪንግ  ፕሪምየር  ሊጉ  ምርጥ ብቃቱን  ያሳየ  ተጨዋች ማን  ነው?

አሜ፦  የቅዱስ ጊዮርጊሱ  አቤል ያለው  በጥሩ ብቃት ላይ ስለሚገኝ እሱ ነው ቀዳሚው ምርጫዬ፡፡

ሊግ፦  ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን  በምን  መልኩ  አገኘከው?

አሜ፦  የዘንድሮ  ውድድር  ጥሩ  ነው፤  ከአምናውም  ተሻሽሏል፡፡

ሊግ፦  አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በአንተ አንደበት ሲገለፅ?

አሜ፦  ጥሩ አሰልጣኝ ነው፤  እንደ ወንድምና አባትም ነው፤  በቅ/ጊዮርጊስ ቤትም ስላሰራኝ ስለ መልካምነቱም  አውቀዋለው፡፡

ሊግ፦ በክለባችሁ ከሚገኙ ተጨዋቾች ውስጥ  አስቂኙ ማን ነው?

አሜ፦  አብዲሳ  ጀማል፡፡

ሊግ፦  ዝምተኛውስ?

አሜ፦ እዮባ፡፡

ሊግ፦ በመጨረሻ……?

አሜ፦  አዳማ ከነማን አሁን ወደ አሸናፊነት ማምጣት አለብን፤  በደረጃ ውስጥም ገብተን ለሁለተኛው ዙርም  ልንዘጋጅ ይገባናል፡፡ ከዛ ውጪ  እኔም ጠንክሬ በመስራት ቡድኔን መጥቀምም እፈልጋለው፡፡   ሌላ ማለት  የምፈልገው  በጣም የምወዳትንና  የማፈቅራትን  ባለቤቴን ለምታደርግልኝ ነገር  ሁሉ  ማመስገንም እፈልጋለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P