Google search engine

“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከአፍ ከአፍችን ላይ የተነጠቅንበት አጋጣሚ ቢኖርም ወደፊት ብዙ ድሎች ይኖሩናል”ጋዲሳ መብራቴ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከአፍ ከአፍችን ላይ የተነጠቅንበት አጋጣሚ ቢኖርም ወደፊት ብዙ ድሎች ይኖሩናል”


“በሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም በችሎታው እንደ ታፈሰ ሰለሞን አይነት የሚያዝናናኝ ተጨዋች ማንም አይኖርም”
ጋዲሳ መብራቴ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

በመሸሻ ወልዴ


የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ከመቀላቀሉ በፊት ለኒያላ፣ ለደደቢት እና ለሐዋሳ ከተማ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ተመርጦ የነበረበት ጊዜም አይረሳም፤ በእግር ኳስ ችሎታው ሜዳ ላይ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የብዙዎቹን ትኩረት የሚስበው እና በአጨዋወቱም አድናቆት ያገኘው ጋዲሳ መብራቴ በኮቪድ 19 ምክንያት የእግር ኳሱ ከቆመ በኋላ ለወራቶች ከኳስ በመራቁ ስለፈጠረበት ስሜት፣ በጨዋታ ዘመኑ ለእሱ ቀዳሚና ጥሩ ስለሚላቸው ግጥሚያዎች እና ጎል፣ በአሁን ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስን ስለሚመለከት ጥያቄና ሌሎች መሰል ነገሮችን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አንስቶለት ምላሽን ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 የእግር ኳስ ውድድሮች ለወራቶች ቆመዋል፤ አሁን ላይ ደግሞ በአንድአንድ ሀገራቶች ተጀምሯል፤ ለእዚህን ያህል ጊዜ ያለኳስ መቆየት መቻል ምን ስሜትን ፈጥሮብሃል? ስለ ኳሱ መጀመርስ ምን የምትለው ይኖርሃል?
ጋዲሳ፡- የእውነት ለመናገር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ እና አነጋጋሪም ሆኖ ከቀጠለ በኋላ በአሁን ሰዓት ላይ የቆመው እግር ኳስ መጀመር መቻሉ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ በእኛ ሀገር ደግሞ አሁንም ኳሱ እንደቆመ እና ለመጪው ዓመትም እንደተላለፈ ነው፤ ስለዚህም ከኳስ መራቅ በጣም ከባድ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ኳስ ለእኛ ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን ለተመልካቹ፣ ለደጋፊው እና ለህብረተሰቡም የሚናፍቅ አይነት ስፖርት ስለሆነ ያለ ኳስ ለእዚህን ያህል ጊዜ ለመራቅ በመቻሌ በጣም ደብሮኛል፤ የእግር ኳሳችን ዳግም መጀመርም በጣም ናፍቆኛል፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ለእንደዚህን ያህል ጊዜ ከሜዳ ርቀህ ታውቃለህ?
ጋዲሳ፡- በፍፁም፤ ለእኛ እሱ ነው እንደውም አንደኛ ከባድ ያደረገብን ነገር፤ ሌላ ጊዜ የሊጉ ውድድር ሲያልቅ የምናርፈው ለአንድ ወር ወይንም ደግሞ ለአንድ ወር ከ15 ቀን ነው፤ ከዛ ወደ ዝግጅት እንገባለንና ይሄን ያህል ጊዜ ያለ ኳስ ከሜዳ ርቄ እረፍት ያደረግኩበት ወቅት ገጥሞኝ አያውቅም፤ ሁኔታው አዲስም ነው የሆነብኝ፡፡
ሊግ፡- ከኮቪድ 19 በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሃቸው እነማንን ነበር? በጣም የናፈቁህስ?
ጋዲሳ፡- ኮቪድ ወደ ሀገራችን ከገባ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አግኝቻቸው የነበሩት ሰዎች የቡድኔ ተጨዋቾች ነበሩ፤ ያኔ በደብረዘይት ከተማም ላይ ነው ለአንድ ሳምንት ያህል ልምምድ ስንሰራም የተገናኘነውና እነሱ ናቸው በጣም የናፈቁኝ፤ ከእነሱ ውጪም የቡድናችን ደጋፊዎች እና አመራሮቻችንም ናፍቀውኛል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ጨዋታውስ አልናፈቀህም?
ጋዲሳ፡- ስለ እግር ኳሱ አሁን ላይ እያወራከኝ ራሱ በጣም ይናፍቀኛል፤ ኳሷን ለእዚህን ያህል ጊዜ ሳትነካት መቆየትም ከባድ ነው፤ በዛ ላይ ኳስን እንዳትጫወትም ሜዳዎች ሁሉ ዝግ ስለሆኑም ሁሉም ነገርም አስቸጋሪ ነው የሚሆንብህ እና እንደ ኳስ የሚናፍቅ ነገር ምንም የለም፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ጊዜ ስፖርተኛውም ሆነ ሌላው የማህበረሰቡ አካል ቤተሰቦቹን በሰፊው ለማግኘት ችሏል፤ አንተን ተንተርሶስ አንድ ነገር ብትል?
ጋዲሳ፡- የእውነት ነው በተለይ የእግር ኳስ ጨዋታው ሙያችን ለሆነው ስፖርተኞች አሁን ላይ ነው ቤተሰቦቻችንን በሰፊው ያገኘነው፤ ከእነሱም ጋር በምንገናኝበት ሰዓት ብዙ ነገሮችንም እያወቅንም ነው ያለው፤ ይሄ መሆን መቻሉ የሚያስደስት ነገር ነው፤ ምክንያቱም ከቤተሰብ ጋር ስትገናኝ በመወያየት ምን ምን ነገሮችን መስራት እንዳለብህ ታውቃለህ፤ እቅዶችንም ትነድፋለህና ሰፊውን ጊዜ ከእነሱ ጋር ማሳለፋችንን በአንድ ጎኑ ስትመለከተው እንደ ጥሩ ጎኑ ነው የምወስደው፡፡
ሊግ፡- ብዙዎቹ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ትዳርን መስርተው እየኖሩ ይገኛል፤ አንተስ የውሃ አጣጪህን አላገኘኸም?
ጋዲሳ፡- /የማያባራ ሳቅ ከሳቀ በኋላ/ የሳቅኩት ውሃ አጣጪ በሚለው ጥያቄ ነው፤ እሷን አሁን ላይ አግኝቻታለው ማለት ይቻላል፤ በጣም ጥሩ የሆነች ጓደኛ አለችኝ፤ እንደ ፕሮጀክት ለወደፊቱ ህይወታችን በማሰብ አንድ አንድ ነገሮችንም ከወዲሁ መነጋገር ጀምረናል፤ ቆይታችንንም ፈጣሪ ያዝልቅልንም ነው የምለው፡፡
ሊግ፡- በቤት ውስጥ አሁን ላይ የእረፍት ጊዜህን በምታሳልፍበት ወቅት ምን ምን ስራዎችን እየሰራ ነው የምትገኘው?
ጋዲሳ፡- አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ወደ ቤተሰቦቼ ከመጣሁበት ወቅት አንስቶ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን አላቆምኩም ነበርና እነዛን ነው አመቺ በሆነው ግቢያችን ውስጥ ስሰራ የነበረው፤ ምክንያቱም ስፖርት የሚቀጥል እና ነገም ጀምረው ልትባል የምትችለው አይነት ስለሆነ በእዚህ ነው የግድ ሰውነትን መጠበቅ መቻል ስላለብህ ጊዜውን ሳሳልፍ የነበረው፤ ከቤተሰቦቼ ጋር እጫወታለው፤ ተከታታይ ፊልሞችንም አያለው፤ መፅሀፎችንም አንድ አንዴ አነባለው፤ ከዛ በተጨማሪም ኮቪድን ታሳቢ በማድረግ በአካባቢያችን ሐዋሳ ላይ ከማህበረሰቡ እና ከቀበሌም ጋር አንድ አንድ የበጎ አድራጎት ስራዎችንም ለመስራት ችያለው፤ አሁን ላይ ደግሞ የእግር ኳስ ጨዋታዎች በአንድ አንድ ሀገራት ስለተጀመሩም የእነሱን ጨዋታዎች እመለከታለው፡፡


ሊግ፡- እንደ ስፖርተኛነትህ አሁን ላይ ከኳሱ ከመራቅህ አንፃር አመጋገብህ ተቀይሯል? ሰውነትህስ በእዚህ ጊዜ ጨም ሯል?
ጋዲሳ፡- በፍፁም፤ ሰውነቴ አልጨ መረም፤ የተለየ አመጋገብ የምመገብበት ሁኔታም የለም፤ የእኔ ሰውነት ደግሞ በተፈጥሮ አይጨምርም፤ ጥቂት ቢጨምር እንኳን ያን ወዲያው በስፖርት ስለማጠፋ ውም እንደበፊቱም ነው አሁንም ድረስ የምመገበው፡፡
ሊግ፡- ለኒያላ፣ ለደደቢት እና ለሐዋሳ ከተማ ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ አሁን ደግሞ ለቅ/ጊዮርጊስ እየተጫወትክ ይገኛል፤ በእነዚህ ክለቦች ባደረግከው ቆይታ የአ ንተ የምንጊዜውም ምርጡ እና መቼም የማትረሳው ጨዋታ የቱን ነው?
ጋዲሳ፡- በቀዳሚነት ደረጃ ላይ የማስቀምጠው ምርጡ ጨዋታዬ በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት ከኤሌክትሪክ ጋር ያደረግነውን የሜዳችን ላይ ፍልሚያን ነው፤ ይህን ጨዋታ የመጀመሪያ ተመራጭ እና መቼም እንዳልረሳው ያደረገኝም በአሰልጣኛችን አዲሴ ካሳ የሚመራው ቡድናችን ከተሸነፈ ከፕሪምየር ሊጉ በሚወርድበት አጣብቂኝ ደረጃ ውስጥ የሚገባበት እና ደጋፊዎቻችንም እያለቀሱ ባለበት ሰዓት አንድ ለአንድ እያለን ዳንሄል ደርቤ ያቀበለውን ኳስ አመለ ሚሊኪያስ ጨርፏት ተመስገን ተክሌ ባለቀ ሰዓት ግብ አስቆጥሮልን ልንተርፍ የቻልንበት ጨዋታ ስለሆነ ይሄን ግጥሚያ ነው የምጠቅሰው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ካስቆጠርካቸው ግቦች ውስጥ ቁጥር አንዷ እና ምርጧስ?
ጋዲሳ፡- ሁለት ናቸው፤ የመጀመሪያዋ ለሐዋሳ ከተማ ስጫወት መከላከያ ላይ ያስቆጠርኳት ስትሆን ሌላዋ ደግሞ ለአሁኑ ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በምጫወትበት ሰዓት በድሬዳዋ ከተማ ላይ ያገባዋት የቅጣት ምት ግብ ናት፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በቀልደኝነቱ የሚያስቅህ እና ደስታንም ፈጥሮልህ የሚያዝናና ተጨዋች?
ጋዲሳ፡- ያለምንም ጥርጥር ታፈሰ ሰለሞን ነዋ! እሱ በሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም በችሎታው ጭምር የሚያዝናናኝ ተጨዋች ነው፤ በሁሉም ነገርም እንደ እሱ የሚያዝናናኝ ተጨዋችም ማንም አይኖርም፡፡
ሊግ፡- ታፈሰ ይለያል ማለት ነው?
ጋዲሳ፡- አዎን፤ ከእኔ ጋር በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ አብረን ተጫውተናል፤ በጣም ከመቀራረባችን የተነሳም ምርጥ ጓደኛ ሆነንም አሳልፈናል፤ እሱን የሚለዩት ነገሮች በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ከሰዎች ጋር ወዲያው ተግባብቶ በቀልዱ ደስታን የሚፈጥርልህ ነገር እና ሌላው ደግሞ ሜዳ ላይ ባለው ድንቅ የእግር ኳስ ብቃቱ ራሱን ተመልካቹንና አንተንም አዝናንቶ ኳስን ወደካት እንድትጫወት የሚያደርግበት መንገድ አለና ያ እሱን በደምብ ይገልፁታል፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት አሁን ላይ የቅርብ ጓደኛህ ማን ነው?
ጋዲሳ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ አብረውኝ እየተጫወቱ ያሉት አስቻለው ታመነ እና ጌታነህ ከበደ፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ተመልክተህ ካደመጥካቸው ውስጥ በጣም ያስገረመ ነገር አለ?
ጋዲሳ፡- አዎን፤ ጉዳዩ ያስገረመኝ ብቻ ሳይሆን ያሳዘነኝም ጭምር ነው፡፡ እኔ፣ አስቻለው፣ አዳነ እና አንድ አንድ ሰዎች ሆነን ሐዋሳ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ከቀይ መስቀሎች ጋር በመተባበር ለህብረተሰቡ ትምህርት እየሰጠን ነበር፤ ያኔ እኔና አስቻለው በተመደብንበት አንድ የገበያ ቦታ ላይ ስለ ኮቪድ ህዝቡ ግንዛቤው አልነበረውምና አንድ ላይ ተቀራርቦና ተሰባስቦ በነበረበት ሰዓት በአጋጣሚ አስቻለው ማይኩን ይዞ ለህዝቡ አትቀራረቡ፣ ተራራቁ፣ እጃችሁንም በሳሙና ታጠቡ ኸረ በጣም ጥንቃቄ አድርጉ እያለ በሚናገርበት ሰዓት አንዱ እልፍ ሲል ምን ቢል ጥሩ ነው “ቤታችን እንድንቀመጥ ብሩ ስጡን ነው” ያለውና በእዚህ አባባሉ እንድስቅ ቢያደርገኝም መቼም ቢሆን ሁኔታውን አልረሳውም፤ የህብረተሰቡንም ግንዛቤ ማጣትም የተመለከትኩበት ስለሆነ ይሄ ሊታረም የሚገባውም ጉዳይ ነው፡፡
ሊግ፡- የቡድን አጋርህ ጌታነህ ከበደ የሚያስቀኝ እና የሚያዝናናኝ ተጨዋች ጋዲሳ ነው ብሏል፤ በዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ይኖርሃል?
ጋዲሳ፡- የእውነቱን ነው፤ ጌታነህ በልምምድ ሰዓት ላይም ሆነ በሰርቪስ ውስጥ ሁሌም እኔ በማደርጋቸው ነገሮች ሲስቅ እና ሲዝናና ነው የሚውለው፤ ከሐዋሳ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስመጣም ምን እሱን ብቻ በአዲሱ ቡድን ቆይታዬ በሰርቪስ በምንጓዝበት እና ዝምታም በሰፈነበት ሰዓት እኔ ነኝ እንዲህ ያለ ሁኔታን ያለመድኩት ነገር ስለነበር ሌሎቹንም የቡድናችን ተጨዋቾች ጭምር ሳዝናናቸው እና ደስታንም ስፈጥርላቸው የነበረው፤ ምክንያቱም እኔ በተፈጥሮዬ ማዘንና መተከዝን ፈፅሞ አልወድም፤ ሁሌም ደስተኛ ሆኜም ነው ጊዜዬን ማሳለፍ የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮና ውድድሮችም ከተቋረጡ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አንድአንድ ክለቦች ያልተቋረጠ ወርሃዊ ደመወዝን ለተጨዋቾች በመክፈል ላይ ይገኛሉ፤ ከዚሁ በተቃራኒም ለወራቶች የደመወዝ ክፍያንም ያልከፈሉ ቡድኖች አሉ፤ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋችነትህ በእዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?
ጋዲሳ፡- ኮቪድ 19 ጊዜ ያመጣው ወረርሽኝ ሆኖ እንጂ ይህ ባይኖር ኖሮ ለስፖርተኛው ደመወዝን ያልከፈሉ ክለቦች ክፍያውን መፈፀማቸው የማይቀር ነበር፤ ስለዚህም እንዲህ ያሉ ቡድኖች ተጨዋቾች ያሉበትን ሁኔታ በመረዳት ይህም ማለት ትዳርን መስርቶ የሚኖር አለ፣ እናቱን፣ አባቱን፣ ወንድሙን፣ እህቱን፣ ልጆቹንና በአጠቃላይ ቤተሰቦቹን የሚረዳ አለና የክለብ አመራሮች ይህን ተረድተው እና እነሱን በማሰብ ክፍያቸውን ሊፈፅሙላቸው ይገባል፡፡ በእዚህ ዙሪያ የእውነቴን ነው የምልህ የእኛ ክለብ አመራሮች እንዲያ ያለ ነገር እንዲገጥመን በፍፁም ስለማይፈልጉ እና ስለማያስቡም በሚሰሩት በጎ ስራ ሁሉ በጣሙን እንዳመሰግናቸው አድርጎኛል፡፡ ስለዚህም ሌሎች ክለቦችም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለምንድን ነው ለተጨዋቾች ደመወዝ እየከፈለ ያለው የሚለውን ነገር ከግንዛቤ ውስጥ በመክተት ደመወዛቸውን ቢከፍሏቸው ጥሩ ነው፤ ተጨዋቾች አሁን ካሉበት ሁኔታ አኳያም ደመወዝ ሲከፍሏቸው ብሰማም በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ በአሁን ሰዓት ደመወዝ የማይከፍሉ ቡድኖች ከእኛ ቡድን ብዙ ትምህርት መውሰድ ይኖርባቸዋል እንጂ ዝም ብሎ ቁጭ ማለታቸው ተገቢ አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡ እንደውም በዚህ ሰዓት ነው ስፖርተኛው ምንድን ነው የሚያስፈልገው? ስፖርተኛውን እንዴት ነው መንከባከብ እና መደገፍ ያለብን? ጤንነታቸውስ እንዴት ነው? ወቅቱን እንዴት እና በምን መልኩስ እያሳለፉ ነው በሚል በመጠየቅ ከእኛ ክለብ ብዙ ትምህርታዊ ነገሮችን መውሰድም ያስፈልጋል፤ በእዚህ አጋጣሚ የእኛ ቡድን ውድድሩ ከተቋረጠ እና ወደ ቤተሰቦቻችንም ከመጣን ጊዜ ጀምሮ በቡድን መሪያችን አቶ ታፈሰ አማካኝነት በሳምንት ሶስትና አራት ቀናት እየተደወለልን እንዴት ሆናችሁ? ቤተሰብስ እንዴት ነው? በሚል እየተጠየቅን ይገኛል፤ ያ ራሱ ከደመወዝ ይበልጣል፤ አንተንም ያስደስትሃል፤ ራስህንም ቤተሰቦችህንም እንድትጠብቅም ያደርግሃል ስለ ቡድንህ እንድታስብም ያስችልሃልና በዚሁ አጋጣሚ እሳቸውን ላመሰግናቸው እወዳለው፤ እዚህ ላይ አንድ ልጨምር የምፈልገው ነገር ቢኖር የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑም በእዚህ ጉዳይ ላይ ተጨዋቾች ውል እስካላቸው ጊዜ ድረስ ደመወዝ የማይከፍሉ ክለቦች ለተጨዋቾች ደመወዛቸውን በፍጥነት እንዲከፍሏቸው ጣልቃ መግባትም አለበት እላለው፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ የቆመው እግር ኳስ ዳግም ወደ ነበረበት እንዲመለስ በአህምሮ እያሰላሰልክ ያለኸው ነገር ምንድን ነው?
ጋዲሳ፡- የዓለማችን ትላልቅ ሀገራቶች አሁን ላይ ያውም በኮቪድ 19 በጣም ውጥረት ውስጥ በሆኑበት ሁኔታ የሊግ ውድድራቸውን ጀምረዋል፤ እንደ እኔ እምነት እና እንደ እኔም ተስፋ አሁን በኢትዮጵያ ያለውና የሚታየው ነገር ጥሩ በመሆኑ፣ ህብረተሰቡም ግንዛቤ እያገኘ በመሆኑ፣ በጤና ምርመራውም ከበሽታው የሚያገግመው ሰው በመብዛቱ እና ትላልቅ ከሚባሉት ሀገራት አኳያም ብዙም የሚያስከፋ ነገርንም ስላልተመለከትኩኝ ይህ ቫይረስ ከሀገራችን ጠፍቶ የሊግ ውድድራችን ይጀመራል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፤ ይህ እንዲሆንም ዋናው አሁን የምናደርገውን ጥንቃቄ አስቀጥሎ መጓዝ ነው፤ የጤና ባለሙያዎችም የሚነግሩንን ነገር ይዘን የምንጓዝ ከሆነም የምንናፍቀው የእግር ኳስ ጊዜው ይመጣልና ይሄን ነው እያሰላሰልኩ ያለሁት፡፡
ሊግ፡- ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገብተህም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማጣጣም አልቻልክም፤ ምንድን ነው የምታስበው?
ጋዲሳ፡- የእውነት ነው ይህንን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ለማንሳት ብዙ አጋጣሚዎች መጥተውልኝ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ይህንን ስኬት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከአፍ ከአፋችን ላይ ልንቀማ ስለቻልን ጣፋጩን ድል እስካሁን ድረስ ለማጣጣም አልቻልኩም፤ በእዚህ ዓመት ግን ቡድናችን ምንም እንኳን በአቋም ደረጃ የመውጣትና የመውረድ ሁኔታ ቢያሳይም ከመሪው ክለብ ጋር የነበረን የነጥብ ልዩነት ብዙ ስላልነበር እና የቡድናችን ስፕሪትም ጥሩ እየሆነ መጥቶ ስለነበር ክለባችን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮናነት የሚያመራበት እድሉ ነበረው፤ እንደ እኔ እምነትም ሊጉ ከቆመበት ይቀጥል ቢባልም ለመጀመሪያ ጊዜም ዋንጫውን የምስምበት እድሉ ይኖረኝም ነበር፡፡ ይህ ባይሳካም ወደፊት ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ብዙ ዋንጫዎችን ከክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ማንሳቴ የማይቀር ነው፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊግ ውድድሩ ተቋረጠ እንጂ ወደ ክለባችሁ ከታዳጊው ቡድን አዲሱ አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ መጥቶ ነበር፤ የስልጠና ጅማሬው ምን ይመስል ነበር?
ጋዲሳ፡- የሊግ ውድድሩ ከመቋረጡ በፊት በደብረ ዘይት በነበረን የአንድ ሳምንት ቆይታችን በአዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ ሲሰጠን የነበረው ልምምድ በጣም ጥሩ እና ስልጠናውም ዘመናዊ መልክን የያዘም ነበር፤ ከዛ ውጪም የአሰልጣኙ ቀረቤታም ሁላችንም የወደድነው ሆኖም ነው የአዲሱ ዘመን ውድድር እስኪጀመር ድረስ ልንለያይም የቻልነው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ አንድ አንድ ነገሮችን በልና እናጠቃል?
ጋዲሳ፡- ኮቪድ 19 ወደ ሀገራችን ከገባ በኋላ አሁን አሁን በአንድ አንድ ህብረተሰብ ዘንድ የሚሰሙት ነገሮች የእውነት በጣም ቅር ያሰኛሉ፤ አንድ አንዶቹም የሚያሳዝኑ እና ጭንቅላትንም የሚነኩ ናቸው፤ ሕፃናቶችን አስገድዶ መድፈርም ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ ነው፤ በዚህ ላይ መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ በየተሰማራበት ሙያ ላይ ሆኖ ድርጊቱን በከፍተኛ ሁኔታ በማውገዝ ይሄ ችግር እንዲቀረፍ ብዙ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P