Google search engine

“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ አለን፤ ኢትዮጵያ ቡናንም  እናሸንፋለን”ሱራፌል ዳኛቸው /ፋሲል ከነማ/

“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ አለን፤ ኢትዮጵያ ቡናንም  እናሸንፋለን”

የሊጉን መሪ መቐለ 70 እንደርታን  ባለፈው እሁድ በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ፊት አስተናግዶ 1ለ0 ያሸነፈው ፋሲል ከነማ በአሁን ሰዓት ከመሪው ቡድን ጋር ያለውን  የነጥብ ልዩነት ወደ 7 ያጠበበ ሲሆን ይህ የውጤታማነት ጉዞውም የሊጉን ዋንጫ ሊያገኝ ወደ ሚችልበት የፉክክር ደረጃ ላይም  እንዲጓዝ  እያደረገውም ነው፡፡

የፋሲል ከነማ ክለብ በሊጉ ውድድር  ጠንካራ ከሚባሉት ክለቦች መካከል ስሙ የሚጠቀስ ሲሆን በዚህ  የውጤታማነት ጉዞም ላይ  ባለበት የአሁን ሰዓት ወሳኝ  የሚባለውን ግጥሚያ የፊታችን ሰኞ ከኢትዮጰያ ቡና ጋር ለማድረግም ዝግጁ ሆኗል፡፡

የፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡናን የሰኞ ጨዋታ አስመልክቶ እና የፋሲል ከነማን ወቅታዊ አቋም እንደዚሁ  ባለፈው እሁድ መቐለ 70 እንደርታን ድል  ባደረጉበት ጨዋታ ዙሪያ ለቡድኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ከሚያሳዩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ለሆነው  ሱራፌል ዳኛቸው ጥያቄን አቅርበንለት ተጨዋቹ ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቶናል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪውን መቐለ 70 እንደርታን ለማሸነፍ ስለቻሉበት ጥንካሬ

“ፋሲል ከነማ መቐለ 70 እንደርታን ለማሸነፍ የቻለበት ዋንኛው ጥንካሬው ተጋጣሚው ወደ ጎንደር ይዞት የመጣውን የጨዋታ ታክቲክ በሜዳው ላይ ባደረገው የጨዋታ እንቅስቃሴ በሚገባ ሊረዳው እና ጠንቅቆትም ሊያውቅ በመቻሉ ነው፤ መቐለ ከእኛ ጋር ባደረገው የእሁዱ ጨዋታ ወደ ሜዳችን የመጣው የአቻ ውጤትን በማስመዝገብ ነጥብ ሊያስጥለን ነበር፤ በጨዋታው አስራ አንዱም ተጨዋቾች የመከላከል አጨዋወትን መርጠውና በራቸውንም ዘግተው ነው ሲጫወቱ የነበሩት፤ ወደ እኛ የሚመጡት ሌሎች ታላላቅ ክለቦችም በራቸውን ዘግተው የሚጫወቱበት አጨዋወት ስላላቸው ያንን የተዘጋውን ቦታ በማስከፋት ከዚህ ቀደም እኛ ጨዋታዎችን ልናሸንፍ ችለናል፡፡ የመቐለ  70 እንደርታንም በእሁዱ ጨዋታ እኛ ያሸነፍንበት አንዱ ምክንያትም ይሄ ነበር፤ ከዛ ውጪም ሁላችንም የቡድናችን ተጨዋቾች ያለን አንድነት እና የጨዋታው የማጠናቀቂያ  ፊሽካም አልቢትሩ እስኪነፋ ድረስ ከፍተኛ ትግል አድርገን የምንጫወትበት ጠንካራ ጎን ስላለን ይሄ ባለድል አድርጎናል”፡፡

ኢትዮጵያ ቡናን ሰኞ ስለሚፋለሙበት ጨዋታና ስለቀጣይ ግጥሚያዎቻቸው

“ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚኖረን የሰኞው ጨዋታ ውጤቱ ለእነሱም ሆነ ወደ ዋንጫው ፉክክር ለመቃረብ በጣም እድሉ ላለው የእኛ ቡድን በጣም የሚያስፈልገን  ስለሆነ በሁለታችንም መካከል  የሚኖረው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት ቢሆንም የጨዋታው  አሸናፊ የምንሆነው ግን እኛ ፋሲሎች ነን፤ በቀጣይነት ስለምናደርጋቸው ጨዋታዎች ደግሞ ከወዲሁ ለመናገር የምፈልገው  በተለይ ከዚህ በኋላ ያሉንን የሜዳ ውጪ  ግጥሚያዎቻችን  ለእኛ በጣም ወሳኞች ስለሆኑ እነዚህን ጨዋታዎች በሜዳችን እንደምናደርጋቸው ግጥሚያዎች አጥቅተን በመጫወት ተጋጣሚዎቻችንን እናሸንፋቸዋለን”፡፡

መቐለ 70 እንደርታን ያሸነፋችሁበት ጨዋታ ለእናንተ  ወሳኝነቱ የቱን ያህል ነበር?

“ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎቻችን ውስጥ መቐለ 70 እንደርታን ያሸነፍንበት ጨዋታ ለእኛ በጣም ወሳኝ የነበረው ክለቡ የሊጉ መሪ ስለሆነና ከእነሱም ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት  በማጥበብ ወደ ዋንጫው ፉክክር ለመቃረብ እንድንችል እድሉን የፈጠረልንም ግጥሚያ ስለሆነ ነው፤ ከዛ ውጪም ውጤቱ በደጋፊዎቻችን ዘንድ በጣም ይፈለግም ስለነበር የጨዋታው ባለድል መሆናችን በጣሙን ሊያስደስተን ችሏል”፡፡

የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር አሁን ላይ ስትመለከተው

“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የከዚህ ቀደም አብዛኛዎቹን የውድድር ዓመታቶች ስመለከታቸው አንድ ቡድን ብቻ ማለትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለብቻው ይሄድና ዋንጫውን የሚያነሳበት እድሉ  ሰፊ ነበር፤ አሁን ግን ያ አካሄድ ተቀይሯል፤ በዘንድሮ ውድድርም ምንም እንኳን መቐለ 70 እንደርታ ተከታዮቹን እኛን በ7 እና ሌሎቹን ደግሞ ከስምንት ነጥብ በላይ በመምራት በቀዳሚ ደረጃ ላይ ቢገኝም ከሜዳው ውጪ ባለው ጠንካራ ግጥሚያዎች አኳያ   ብዙ ቡድኖች ማለትም 5 እና 6 የሚደርሱ ቡድኖችም ዋንጫውን የማንሳቱ እድሉ አላቸውና የዚህ ዓመት ፉክክሩ በእኔ እይታ ጥሩ የሚባል ነው”፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአሁን ሰአት ጥሩ እግር ኳስን እየተጫወተ ስላለው ቡድን

“በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የከዚህ ቀደም  እይታዬ ኳስን በመቆጣጠር ደረጃ ጥሩ እግር ኳስን ይጫወት የነበረው ቡድን ኢትዮጵያ ቡና ነበር፤ አሁን ላይ ግን ጥሩ የሚጫወተው ክለብ ፋሲል ከነማ ነው፡፡

ፋሲል ከነማ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ኳስን ይዞ ተቆጣጥሮና አጥቅቶም ስለሆነ ይሄ የቡድኑ አጨዋወት ከሌሎች ክለቦች እንዲለይ ያደርገዋል”፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን  ብዙ ጠብቀከው በውጤታማነቱ ያልተሳካለት ክለብ

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ነዋ! ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው አመት የሊጉን ዋንጫ ስላጣ ዘንድሮ አስፈሪ ቡድንን ይዞ ይመጣል ብዬ ጠብቄው ነበር፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ላይ ክለቡን ሳየው በውጤታማነት የሚታወቀውን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳ ላይ እየተመለከትነው አይደለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚህ በፊት የሚያደርጋቸውን የሜዳው ውጪ ግጥሚያዎችን ቢያንስ 1ለ0 አሸንፎ ወይንም ደግሞ አቻ ተለያይቶ ይመጣል እንጂ አይሸነፍም ነበር፤ ይሄ ሽንፈት ግን አሁን ላይ ስለታየ አስፈሪነቱ እንደበፊቱ አይደለምና ቡድኑ በውጤታማነቱ እየተሳካለት አይደለም”፡፡

ፋሲል ከነማን ቀጣይ በሚኖረው ጨዋታ በምን መልኩ ሊጠቅመው እንደተዘጋጀ

“የፋሲል ከነማ  ክለብ በሊጉ ላይ  እያሳየ ካለው የዋንጫው ተፎካካሪነቱ አኳያ በቀጣይ ጨዋታዎች እኔ ልጠቅመው የተዘጋጀሁት በብዙ መልኩ ነው፤ ከእነዛ መካከልም አንዱ የቡድኑ የተጨዋችነት ቆይታዬ  ላይ ከወዲሁ የአቅሜን ሁሉ አውጥቼ በመጫወት ቡድኑን ወደ ዋንጫው ፉክክር ለሚያመራበት ጉዞው እየወሰድኩትም ነውና ይሄን ማድረጌ ያስደስተኛል ከዚህ በኋላም ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር በመሆንም በቀሪዎቹ ግጥሚያዎቻችን ክለቡን በጋራ  ሆነንም ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን”፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን በማሊ አቻው በሰፊ ግብ ተሸንፎ  ከማጣሪያው ውድድር ስለመውጣቱ

“ከማሊ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደረግነውን የመልስ ጨዋታ  በሰፊ ግብ ለመሸነፋችን የማቀርበው ምክንያት እንደ ሰበብ ሊቆጠርብኝ ቢችልም ዋና ዋና ጉዳዮቹን ግን እንደ ራሴ አመለካከት እና እይታ ማንም ምንም ቢል ከመናገር ወደኋላ አልልም፡፡

የማሊውን ጨዋታ አስመልክቶ ከወዲሁ ለማለትም የምፈልገው ከዚህ ቀደም በነበረኝ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎዬ ወደ ጅቡቲ የሄድኩበት እና የተጫወትኩ ቢሆንም የማሊ ጨዋታችን ላይ የነበረው ከፍተኛ የሙቀት መጠን እኛን በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሰን እንዳንጫወት ቸግሮን ነበር፤ ከማሊ በነበረን በዚሁ ጨዋታ አየሩ ከምነግርህ በላይ ይከብድ ነበር፤ የራስህንም ትንፋሽ ሁሉ ትሰማበትም ነበር፡፡ በዛ ላይ ቶሎ ቶሎ ትተነፍሳለህ አየሩም ያቀጥል  ነበርና በዚህ በኩል ተቸግረናል፤ ከዛ ውጪ የእለቱ ዳኛም ውሳኔዎች እኛን ጎድቶናል፤ የእለቱ ዳኛ ያን እለት ተገቢ ያልሆነ የፍፁም ቅጣት ምቶ ሰጥቶብናል በውሳኔ አሰጣጡም ደስተኛ ባልሆንበት ሰአት ስሜታዊ የመሆን ነገር እንዲፈጠርብንም አድርጓል፤ ከዛ ውጪ ከነዓን ማርክነህም በቀይ ካርድ ሲወጣ  የእኛ ቡድን ላይ ጫና ሊያድርብን ስለቻለ ይሄ በስነ-ልቦናው በኩል ይበልጥ  ጎድቶናል፡፡ የማሊ የኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ጋር በነበረን ጨዋታ  በሜዳ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ እኛ ኳስን ይዘንባቸው ስለነበር ህዝቡ ይቃወሟቸው ነበር፡፡  በእነዚህ ከላይ በገለፅኳዋቸው  ምክንያቶች ከመሸነፋችን ውጪ ሌሎች ምክንያቶችን በሜዳው ላይ ከነበረን ጥሩ እና እነሱን ከበለጥንባቸው የጨዋታ እንቅስቃሴዎች አንፃር ሌላ የምገልፀው ነገር አይኖርም”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P