ሊግ፡- የጅማ አባጅፋር ወቅታዊ አቋም ምን ይመስላል?
አክሊሉ፡- የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ክለባችን በአሁን ሰዓት ያለው አቋም ጥሩ እና ለተጋጣሚ ቡድኖቻችንም በጣም አስፈሪ ሆነን የቀረብንበት ነው፤ ይሄ አስፈሪነታችንም እስከ ሊጉ የመጨረሻ ሳምንታት ድረስ የሚቀጥልም ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ጅማሬ ላይ በውጤትም በእንቅስቃሴም ጥሩ አልነበራችሁም፤ ምክንያቱ ምን ነበር? አሁን ላይ ደግሞ መሻሻልን“ አሳይታችኋል፤ የለውጥ ሚስጥሩ ምንድን ነው?
አክሊሉ፡- የመጀመሪያው ዙር ላይ ክለባችን ላጣቸው ውጤቶች በምክንያትነት የማቀርባቸው ችግሮች ብዙ የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የኢንተርናሽናል የጨዋታ ተሳትፎም ነበረንና በጊዜው የሀገር ውስጥም የሊግ ውድድርን እናደርግ ስለነበር የውድድር መደራረቦች፣ የተጨዋቾች የደምወዝ ክፍያ በጊዜው አለመከፈሉ እና እንደዚሁም ደግሞክለባችን በአዲስ መልክም የተሰራ ስለነበርና ስኬታማ መሆኑም ላይ ጊዜ ስለሚያስፈልግ እነዚህ ውጤትን አሳጥተውናል፡፡
ጅማ አባጅፋር የሁለተኛው ዙር ላይ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ከመጀመሪያው ዙር መሻሻልን በማሳየትስኬትን እያስመዘገበ ሊመጣ የቻለውየክለቡ አመራሮች ወደ እኛ ተጨዋቾች በመምጣት እና በመቅረብም እየሰሩ ስለነበር ይሄ ግንኙነት መፈጠር መቻሉ ለዛሬው ለምንገኝበት የውጤት ደረጃ ሊረዳን ችሏል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው ውድድር በምን ውጤት ታጠናቅቃላችሁ?
አክሊሉ፡- የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአቸን ላይ ቡድናችን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እያሳየ ከመጣው መሻሻል አኳያ የዘንድሮውን የሊግ ውድድር የምናጠናቅቀው የደረጃ ፉክክር ውስጥ መግባትን ነው፤ ይሄንንም እውን እንደምደርገውም አምናለሁ፡፡
ሊግ፡- የጅማ አባጅፋር ውስጥ ያለህ ቆይታ ምን ይመስላል? ለቡድኑስ የቱን ያህል ግልጋሎትን ሰጥተከዋል?
አክሊሉ፡- ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀልኩት ዘንድሮ ቢሆንም በቡድኑ ያለኝ ቆይታ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፤ በቆይታዬምክለቡንበሚገባ እየጠቀምኩትም ነው የሚገኘው፤ በተለይ ደግሞ በአሰልጣኞቼ የተሰጠኝን የጨዋታ ሚና በአግባቡም በመወጣት ላይ ስለሆንኩም ራሴንም በሚገባ ተመልክቼበታለሁ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ላይ ባለህ አቋም ራስህን በምን ደረጃ ላይ ታስቀምጠዋለህ? የብቃቴስ ጫፍ ላይ ነኝ ትላለህ?
አክሊሉ፡- በፍፁም፤ በኳሱ ገና የብቃቴ ጫፍ ላይ አልደረስኩም፤ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በአሁን ሰአት የምገኝበት አቋም እና ደረጃዬ ጥሩ ቢሆንልኝም በእዚህ ደረጃ ላይ ብቻ መገኘቴ ግን ለእኔ በቂ አይሆንልኝም፤ ስለዚህም ከእዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ አቋሜ ላይ የማስተካክላቸው ነገሮች አሉና ጠንክሬ እየሰራው ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሐዋሳ ከተማን ነገ እሁድ ትፋለማላችሁ፤ ስለጨዋታው ምን ትላለህ? ማንስ የግጥሚያው አሸናፊ ይሆናል?
አክሊሉ፡- ከሐዋሳ ከተማ ጋር የሚኖረን የእሁዱ ጨዋታ እነሱ ከተደጋጋሚ ሽንፈታቸው በኋላ በመምጣት የሚያደርጉትስለሆነ ለእኛ ግጥሚያው ቀላል አይሆንልንም፤ ይህ ጨዋታ ለእኛ ከበድ የሚልብን ቢሆንም በሜዳችን ላይ ከመጫወታችን አኳያ እና በሜዳችን ስንጫወትም በማሸነፉ በኩልም ጥሩ ሪከርድ ያለን በመሆኑም ይህንን ወደ ደረጃ ተፎካካሪነት የሚያስገባንን ጨዋታ እናሸንፋለን፡፡
ሊግ፡- የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፉክክርን እንዴት ተመለከትከው? ማንስ ዋንጫውን ያነሳል?
አክሊሉ፡- እውነት ለመናገር በእግር ኳስ ህይወቴ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎችን ፈፅሞ አላየሁም፤ የዘንድሮው የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በጣም ይለያል፤ በእግር ኳስ ተስፋ ያለመቁረጥን አይተንበታል፤ አንድ ነገርን አደርጋለው ብለህ ወደሜዳ የምትገባ ከሆነ ያን ማሳካት እንደምትችልም ልናይበት ችለናል፤ ለእኛም ሀገርም ብዙ ነገርን አስተምሮን አልፏል፡፡ የሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል ላልከው እኔ ምንም እንኳን የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊ ብሆንም በአቋሙ ያሳመነኝ ሊቨርፑል ዋንጫውን እንዲያነሳ ነው የምፈልገው፤ ዋንጫው ይገባቸዋልም፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ በጣም የተደሰትክበት እና የተከፋህበት አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
አክሊሉ፡- በዘንድሮው የውድድር ዘመን ላይ በጣም የተከፋሁት በደቡብ ፖሊስ ስንሸነፍ ሲሆን የተደሰትኩበት አጋጣሚ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን በጨዋታ ጭምር በልጠን ባሸነፍናቸው ጊዜ ነው፡፡
ሊግ፡- ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከወልዋሎ አዲግራት ጋር የነበራችሁን ጨዋታ እንዴት ነው የምትገልፀው?
አክሊሉ፡- ከወልዋሎ አዲግራት ጋር የነበረን ጨዋታ በሁለታችንም መካከል ማራኪ ፉክክር ቢታይበትም በእንቅስቃሴ ደረጃ እኛ ተሽለን ታይተንበታል፤ ያም ሆኖ ግን በትኩረት ማነስ እኛ ላይ ግብ ሊገባብን ቢችልም እኛም ጎል አስቆጥረን አቻ ለመለያየት ችለናል፡፡
ሊግ፡- የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎችን በሚመለከት ምን ትላለህ?
አክሊሉ፡- የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች ቡድናቸውን የሚወዱ እና ጥሩ ናቸው፤ ሁሌም ግጥሚያዎችን እንድናሸንፍ ደማቅ እና ድንቅ ድጋፋቸውን ይሰጡናልና እነሱን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ በተለይ አሁን ላይ ለምናመጣው ውጤት የእነሱ እገዛ በጣም ጠቅሞናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክርን እንዴት ትገልፀዋለህ?
አክሊሉ፡- የፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው ፉክክር በጣም ደስ ይላል፤ ከታች ያሉትም ነጥባቸው በአብዛኛው በጣም ስላልተራራቀ ወራጁ እስካሁን አለየም፤ የሊጉን ዋንጫም ማን እንደሚያነሳም መገመት ይከብዳልና ጥሩ ውድድር እየተካሄደ ይገኛል፡፡