Google search engine

“ዩ አር ኤንን በጥሩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ አሸንፈን ወደ ተከታዩ ዙር እናልፋለን” ወንድሜነህ ደረጄ /ኢትዮጵያ ቡና/

 

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ኡጋንዳ አምርቶ የ2-1 ሽንፈትን ማስተናገዱ ይታወቃል፤ ጨዋታው ለእናንተ ከባድ ነበር?

ወንድሜነህ፡- በፍፁም፤ ግቦቹ በአጋጣሚ ገቡብን እንጂ ግጥሚያው ለእኛ ከባድ አልነበረም፤ ለእዛ ማሳያውም ግቦቹን ካስተናገድን በኋላ ኳሱን በተለይም ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ከእነሱ በተሻለ መልኩ ተቆጣጥረን፣ ብልጫ ወስደንና ጫና ፈጥረንም ለመጫወት በመቻላችን ነው፤ ይህ ውጤት ለእኛ ፈጥሞ አይገባንም ነበር፤ ኳስ ሆነና ግን ልንቀበለው ችለናል፡፡

ሊግ፡- ውጤቱ አስቆጫችዋ!

ወንድሜነህ፡- በጣም፤ ምክንያቱም እኛ ላይ ከተቆጠረብን የአጋጣሚ ጎልና የእኛ ቡድን ደግሞ በሜዳ ላይ ይዞት ከቀረበው የኳስ ቁጥጥሩ ብልጫና ጫናም ፈጥሮ ከመጫወቱ አንፃር እንዴት አያስቆጨን? ያም ቢሆን ግን አሁን የቁጭት ስሜቱን ወደ ኋላ ረስተን ለመልሱ ጨዋታ በጥሩ መልኩ ተዘጋጅተናል፡፡

ሊግ፡- የኡጋንዳው ተጋጣሚያችሁ  ዩ አር ኤን እንዴት ያለ ቡድን ነው? ግቦቹንስ በምን መልኩ አስቆጠሩባችሁ?

ወንድሜነህ፡- ተጋጣሚያችንን እንደጠበቅነው ነበር ያገኘናቸው፤ ኳስ ለመጫወት ሙከራን ያደርጋሉ፤ በአብዛኛው የመስመር ጨዋታንም ይጠቀማሉ፤ በክሮስ ኳስም ጎል ለማግባት ነው ጥረትን የሚያደርጉት፤ እኛም ላይ የገቡት ግቦች በእዛ መልኩ የተቆጠሩ ናቸው፤ ያን አጨዋወታቸውንም በደንብ ስለተረዳን ለመልሱ ጨዋታ እኛ ከያዝነው እንቅስቃሴ ውጪ በዛ ላይም በደንብ ሰርተንበን መጥተናል፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና 2-0 ከተመራ በኋላ በዊሊያም ሰለሞን አማካኝነት ያስቆጠራት ግብ ውጤቱን አጥብቦ እንዲመጣ አድርጎታል፤ ይህቺ ግብ በምን መልኩ ተቆጠረች? ግቧስ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ያላት ዋጋ የቱን ያህል ነው?

ወንድሜነህ፡- ኢትዮጵያ ቡና ብቸኛዋንና አንዷን ግብ ለማስቆጠር የቻለበት መንገድ ኳሱን በጣም ተቆጣጥሮ ከመጫወቱ በተጨማሪ እነሱ ሜዳ ላይም በመግባት ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ስለቻለ ነው፤ ያቺ ግብም ለእኛ አሁን ላይ ካለን ጥሩ አቋምና በእነሱ ሜዳ ላይ ከመጫወታችን አኳያም ከፍተኛ ተነሳሽነትንም ነው ልትፈጥርልን የቻለችውና ያላት ዋጋ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናና የዩ አር ኤን የመልስ ጨዋታ በባህርዳር ስታድየም ይደረጋል፤ ይህ ጨዋታ ምን አይነት ፉክክር ይደረግበታል? ውጤቱን በተመለከተስ በእነሱ ሀገር አጥብባችሁ ከመምጣታችሁ አንፃር ወደ ቀጣዩ ዙር የምታልፉ ይመስልሃል?

ወንድሜነህ፡- አዎን፤ ለእዛ ፈፅሞ አንጠራጠርም፤ ዩ አር ኤንን በጥሩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ አሸንፈን ወደ ተከታዩ ዙር እናልፋለን፤ ይህን ለማለት የደፈርኩትም በመጀመሪያው የሜዳችን ውጪ ጨዋታ ላይ ጥሩ ስለነበርንና አስቀድሞ መጫወትም ነገሮችን ለማወቅ ጥቅምም ስላለው ነው፤

ይህ የመልስ ጨዋታ ደግሞ ከመጀመሪያው ግጥሚያችን በተሻለ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበትም አምናለው፤ ይህን የድል ውጤት ለማሳካትም ጎል ሳይቆጠርብን መውጣት እንዳለብንም ስለምናውቅ ባለ ድሉ እኛ እንሆናለን፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እናንተን ሲያበረታቱ ነበር፤ በድጋፋቸው እንዴት አገኘካቸው?

ወንድሜነህ፡- በጥሩ ሁኔታ ነው ሲደግፉን የነበሩት፤ ምክንያቱም እነሱ በእኛ እምነቱ አላቸውና፤ ከጨዋታው በኋላ  በሜዳ ላይ ባሳየነው ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴና ውጤቱንም አጥብበን በመጣንበት ሁኔታ  ከኛም ጋር ነው አብረው ሊጓዙ የቻሉትና ደስተኝነታቸውን እየገለፁልን ይገኛል፤ ምክንያቱም እነዚህ ደጋፊዎች ጨዋታውን በሚገባ ሊከታተሉ ችለዋል፤ ሌሎችም ደጋፊዎች ስለ አጨዋወታችን ሰምተውና አይተው ድጋፋቸውንም እየሰጡን ነው በመልሱ ጨዋታም  ቡድኑ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችልም  እየነገሩን ይገኛልና እኛ ደግሞ እነሱን ለማስደሰት በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡

ሊግ፡- በኡጋንዳው ጨዋታችሁ ቡድናችሁ ላይ እንደክፍተት የሚቆጠረው ነገር ምን ነበር?

ወንድሜነህ፡-  በዛ ደረጃ ያየሁት ነገር ምንም የለም፤ ከሜዳችን ውጪ ከመጫወታችን አኳያ  ብዙ የተሻሉ ነገሮች ናቸው የነበሩት፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ…..?

ወንድሜነህ፡- የአዲሱ ዓመትን እኛ የተቀበልነው በኡጋንዳ ሆነን ነው፤ በዓሉ በውጤት ቢታጀብልን ኖሮ የበለጠ ጥሩ ይሆንልን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ጨዋታው ላይ የተመዘገበው ውጤት መጥፎ የሚባል ስላልሆነ ለደጋፊዎቻችን በመልሱ ጨዋታ ደስታን ልንሰጣቸው ዝግጁ ነን፤ 2014 ለሀገራችን የሰላምና የፍቅር እንዲሆን በስፖርት ዘርፉም የአፍሪካ ዋንጫና ሌሎች ተሳትፎም ስላለብን የተሳካ ጊዜ እንዲሆንልን እመኛለው፤ ደጋፊዎቻችን ለሚሰጡን ድጋፍም ከፍተኛ ምስጋናው አለኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: