Google search engine

“ይሄን ብርቅዬ ደጋፊ የምገልፅበት ቃላቶች የሉኝም” አቶ ዳዊት ውብሸት የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ የቦርድ አባል

 

በአለምሰገድ ሰይፉ

የፈረሰኞቹ የአየር ጤናው ደማቅ ድግስ

“የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” ብሏል
ብርቅዬው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፤ ዛሬ
ላይ ሆነን የታሪክ ላይብረሪዎቹ ስለ ገድለኛው
ክለብ ቅ/ጊዮርጊስ ሲያወሩ ከልባቸው ብቻ
ሳይሆን እንባ እየተናነቃቸው ነው፡፡ በእነርሱ
ዘንድ አይደለም በጥይት መመታት ራስን
አሳልፎ እስከሞት መስጠት ክብራቸው እንጂ
ፍራቻቸው አይደለም፡፡ ዘንድሮ ፈረሰኞቹ
በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል
የቤተሰብ ውይይትና ድግስ በየቦታው ማድረግ
ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ ይህ ከጊዜ ወደ
ጊዜ እንደአሸን እየፈላ ያለው አዲሱ የቅዱስ
ጊዮርጊስ ትውልድ የክለቡን ታሪክ አውቆ
በማንነቱ ይኮራ ዘንድ የትናንት የፈረሰኞቹ
የውጤት ሞግዚቶች ተመክሮአቸውን እያጋሩ
ነው፡፡ ባለፈው እሁድም እጅግ ደማቅ በሆነ
መልኩ ተጀምሮ በተጠናቀቀው የአየር ጤናው
የፈረሰኞቹ ድግስ ላይ ተገኝተን እንዘግብላቸው
ዘንድ በተደረገልን ጥሪ መሠረት በበሳል
ስፖርታዊ ትንተናው ተለይቶ የሚታወቀው
የብስራት ኤፍ.ኤም ስፖርት ዋና አዘጋጅ
መንሱር አብዱልቀኒና ተባባሪ አዘጋጁ ዘላለም
እንዲሁም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አለምሰገድ
ሰይፉ በስፍራው ደርሰናል፡-
ድባቡ
ገና በጠዋቱ የአየር ጤና መንደር ቀውጢ
ሆናለች፡፡ በእግር ከሚጎርፈውና በበርካታ ባሶች
እየመጡ ከሚራገፉት ደጋፊዎች በተጨማሪ
በሞተር አጀብ የሚመጡ ደጋፊዎች ብዛት
ለቁጥር ይታክታል፡፡ ጆሮ በሚበሳው
ሞንታርቦ የሚለቀቀው የክለቡ ዜማ ደግሞ
ደጋፊዎቹን ከቁጥጥር ውጪ አድርጓቸዋል፡
፡ የአየር ጤናው ቤተሰባዊ ውይይትና ድግስ

የመጀመሪያ ገፅታው ይሄን ይመስላል፡፡
የተባረከ ትውልድ
ለመፍጠር የቀደሙትን
ታላላቆች ማክበር
አንድ ብር ከሀምሳ በማትሞላ ወርሃዊ
ደመወዝ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሉ ደምተው
ዛሬም ድረስ የክለባቸው ናፍቆት ያልወጣላቸው
የያኔው ትውልዶች ዛሬን ቆም ብለው ሲያዩት
የክለቡ እንዲህ በደጋፊ ሀብት መጥለቅለቁ
በእንባ ሲቃ እንዲታጠቡ ያደርጋቸዋል፡፡
“አስተዋሽ የለንም እንዴ?” ብለው እንዳይፀፀቱ
ዛሬ የክለቡ ተተኪ ትውልዶች የማይዘነጋ
ውለታቸውን እያስመለከቷቸው ነው፡፡
በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ዘመን በጥሩ
የኳስ ክህሎት ለሚወዱት ክለባቸው ከአንዴም
ሶስቴ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ የሰሩት አቶ
እንዳለ ፈይሳ ከ8 ያላነሱ ሞተረኞች እቤታቸው
ሲደርሱ መደንገጣቸው፣ በኋላ ላይ ደግሞ
በደስታ ማንባታቸውም አልቀረም፡፡ እነዚህ
በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የደመቁ ወጣቶች አቶ
እንዳለ ቤት ድረስ በመሄድ “ለዛሬ ማንነታችን
የእርሶ የትናንት አሻራ አለበት” በማለት
በከፍተኛ የሞተር አጀብ አየር ጤና ድረስ
አመጧቸው፡፡ እሳቸውም አሉ “ከዚህ በኋላ
ብሞት እንኳን አይቆጨኝም፡፡”
“ወጣቱ አመራር አደራህን
ተረከብ”
እጅግ በተቀናጀ ሁኔታ ሂደቱን እየመሩ
ያሉት የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ቀጣይ
ጉዟቸው በወጣትነት ዕድሜ የክለቡን ታላቅ

ኃላፊነት እንዲሸከም አደራ የተጣለበትን የቅ/
ጊዮርጊስ ክለብ የቦርድ አባል የሆነውን አቶ
ዳዊት ውብሸትን ተመሳሳይ በሆነ መንገድ
ወደ ድግሱ ስፍራ አጅቦ ማድረስ ነበር፡፡ ይህ
ለርሱ ታላቅ የቤት ስራ ነው፡፡ ዘመነኛው
ትኩስ ትውልድ በክለቡ ህልውና ፈፅሞ
አይደራደርም፡፡ እናም ያለአንዳች ማንቀላፋት
ሌት ተቀን ካልሰራ ሂደቱ የከፋ ነው፡፡ እሱም
አለ “ዛሬ ደጋፊው ትልቅ የሆነ የቤት ስራ ነው
የሰጠኝ፡፡ በፍፁምም አላንቀላፋም” በማለት
አቶ ዳዊት ውብሸት ለደጋፊው ቃል ገባላቸው፡፡
የክብር እንግዶቹ
በዕድሜ ቅይጥ ለሆነው ደጋፊ የዛሬን
ብቻ ሳይሆን የትናንቱን አድካሚ ጉዞ ማወቅ
ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ይህ አንጋፋ
ክለብ ዛሬ 83ኛ አመቱን የደፈነው ነገሮች
ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነውለት አይደለምና!
እናም የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ ካስትሮ
ሳንጃው እንግዶቹን በሚገባ አስተዋወቀ፡፡
ለቅ/ጊዮርጊስ ሲል እግሩን በጥይት ተመትቶ
ዛሬም ድረስ ከነጥይቱ አብሮ እየኖረ የሚገኘው
መሀመድ ቱርክ፣ በኢትዮጵያ የስፖርት አባት
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የስልጠና ቅኝት
ከክለቡ ጋር የሶስት ዋንጫዎችን ውጤት
ማሳካት የቻለው እንዳለ ፈይሳ፣ በሁሉም
ኢትዮጵያውያን ዘንድ የታተመ ፍቅርና
አክብሮትን የተጎናፀፈው የኢንስትራክተር
መንግስቱ ወርቁ ልጅ ዳዊት መንግስቱና
በቅርቡ በቅ/ጊዮርጊስ የቦርድ አመራር ውስጥ
በመካተት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው
አቶ ዳዊት ውብሸት ናቸው፡፡
ፍቅር እስከመቃብር
አሁን ጊዜው ደርሶ የቀደመ የክለቡን

ጣፋጭ ታሪክ ልንኮመኩም ነው፡፡ ሞት
ባያስፈራቸውም ዛሬ በሕይወት ኖረው እንደዚህ
እንደአሸን የፈላውን ደጋፊ በማየታቸው
ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፡፡ አቶ እንዳለ
ፈይሳ ከምን እንደሚጀምሩ አያውቁትም፡፡ ግን
ከምንም በላይ አንድ አነጋገራቸው ቀልቤን
ገዛው፡፡ “ያኔ ጊዮርጊስ ገብቶ ለመጫወት
ገንዘብ መናፈቅ ሳይሆን ወደክለቡ እንድንገባ
ፈጣሪን በፀሎት መጠየቅ ነበር” አሉ፡፡ ደጋፊው
በጭብጨባ አዳራሹን አናጋው፡፡ ኳስ ስሜት
ነው፡፡ ስሜት ደግሞ እምነት፤ እነዚህ የትናንት
ሰዎች ስለጊዮርጊስ ክለብ ታላቅነት ቢያወሩ
ቢያወሩ ስለማይጠግቡና ሰው የሚያምናቸው
ስለማይመስላቸው በመሀላ ሁሉ ቢያረጋግጡ
ደስተኞች ናቸው፡፡ “እኛ ያኔ የክለባችንን
ጨዋታ ለማየት በአጥር ላይ ተንጠልጥለናል፤
ወድቀናልም፡፡ ይህ ዛሬ እናንተ የተረከባችሁት
ክለብ በዋዛና ፈዛዛ የመጣ አይደለም፡፡ ብዙ
ዋጋና ደም ተከፍሎበታል” በማለት የተተኪው
ትውልድ የዘመን ቅብብሎሽ ጠንካራ መሠረት
ይጥል ዘንድ አደራ ብለዋል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን እንድትደግፉ
ከመጠጥ ጋር ቀላቅለው
የሚሰጧችሁ ነገር አለ እንዴ?
አቶ እንዳለ ተመስጠው ነው የሚያወሩት፡
፡ ቢልላቸው ሲናገሩ የሚተናነቃቸውን እንባ
ዝርግፍ አድርገው በማውረድ እፎይ ቢሉ
የሚመርጡ ይመስላል፡፡ ፈታኝ ስለነበረው
ወቅት ሲናገሩ “ቅ/ጊዮርጊስ ዛሬም በፈተና
ውስጥ ያለ ክለብ ነው፡፡ ያኔ ብዙሃኑ
ይህን ቡድን መደገፋቸው በጊዜው ለነበሩት
ኃላፊዎች የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ እናም
በሆነው ባልሆነው ምክንያት እየፈለጉ

ደጋፊውን ያሳድዱ ነበር፡፡ ሆኖም ከዛ አልፎ
የወራሪውን ጠላት ክንድ ያንበረከከው ታላቁ
ክለባችን መቼም ቢሆን እጅ ሰጥቶ አያውቅም፡
፡ አንዴ ምንም ባልተፈጠረበት ሁኔታ አንድ
ጓደኛችንን አሰሩት፡፡ እሱም የፈለገ ነገር ቢመጣ
በቅ/ጊዮርጊስ እንደማይደራደር ነገራቸው፡፡
በኋላ የጣቢያው መርማሪ ተስፋ በመቁረጥ
ለመሆኑ ሁላችሁም ይሄን ክለብ ብቻ
እንድትደግፉ ከመመጥ ጋር ቀላቅለው የሆነ
ነገር ይሰጧችኋል እንዴ? በማለት እስረኛውን
ፈታው፡፡ እናም ይኸው የዛሬውም ትውልድ
ያለአንዳች ጎትጓች በፍቅር ብቻ ተማርኮ
ያገኘውን ክለብ ሊጠብቀውና ሊንከባከበው
ይገባል” በማለት የያኔውን አስደማሚ እውነታ
አወጉን፡፡
ከ1963 እስከ ዛሬ ከጥይት ጋር
ይህን ታሪክ ሳታይ አትሙት ያላት
ነፍስ፤ የምር የክለብ ፍቅር ማለት እዚህ
ድረስ ይዘልቃል እንዴ? የአረብ ዝርያ
ያለው መሀመድ ቱርክ በጥይት የተመታው
የሶማሌን ውጊያ ተቀላቅሎ አይደለም፡
፡ ይልቁንስ ዛሬ ድረስ ለዘመናት ሰውነቱ
ውስጥ ተሰንቅራ የምትገኘው ጥይት
የገባችው ለጊዮርጊስ ሲል ነው፡፡ እናም ዛሬ
ድረስ የጥይቱ ስሜት ሲሰማው ያኔ ለብሶ
የተጫወተለት ክለብ የማልያ ፍቅር ነው
የሚታወሰው፡፡ እንደአነጋገሩ ከሆነ እንኳንም
በጥይት ተመታው አይነት ነው፡፡ ፈገግታ
የማይለየውና ጊዮርጊስ ሲወሳ ሁሌም አብሮ
የሚዘከረው መሐመድ ቱርክ እግር ኳስን
ሳይጠግብ ከውድድር ዓለም የተገለለ ቢሆንም
በጊዜው ለክለቡ የሰጠው ግልጋሎት ግን ታሪክ
የሚዘነጋው አይደለም፡፡
ልክ እንደእንዳለ ሁሉ መሐመድ ቱርክም
ለጊዮርጊስ ሲል ብዙ ፈተናዎችን ተቀብሏል፡
፡ ያለውን ብቃት በማየት ለሌላ ክለብ ተሰልፎ
እንዲጫወት ለማስገደድ በማሰብ እስር ቤት
ተወርውሯል፡፡ ይሄን ገጠመኝ ሲያወራ እንዲህ
ይላል “ለሌላ ክለብ እንድጫወት የተደረገብኝ
ጉትጎታ አልሳካ ሲላቸው ማታ እቤት ቁጭ
ብዬ እራቴን ልታደም ስል ወታደሮች በሬን
አንኳኩተው መጡ፡፡ እንዴ በዚህ ሰዓት ምን
ፈልጋችሁ ነው? ስላቸው አይ ለሆነ ጉዳይ
ፈልገንህ ነው በማለት ወደማላውቀው ስፍራ
ወሰዱኝ፡፡ ከዛ የሆነ ደብዛዛ ቤት ውስጥ በር
ከፈቱና እዚህ ግባ አሉኝ፡፡ ስገባ የሆነ ሰው
መሬቱ ላይ ተኝቷል፡፡ ቀረብ ብዬ ስመለከተው
ስዩም አባተ ነው፡፡ በጣም ደንግጬ እዚህ
ምን ልታደርግ መጣህ? ስለው ከጊዮርጊስ
ወጥተህ እኛ ለምንፈልገው ክለብ ተጫወት
ሲሉኝ እምቢ ስላልኳቸው ነው በኃይል
ሊያስገድዱኝ ያመጡኝ አለኝ፤ የእኔም ሁኔታ
ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ነገርኩትና
ከፈለጉ ይግደሉን እንጂ አናደርገውም በማለት
በአቋማችን ፀናን፡፡ እናም እናንተም የዛሬ
ትውልዶች ይህ በደምና በሞት መስዋዕትነት
የተገኘን ክለብ በአደራ መጠበቅ አለባችሁ”
በማለት ደጋፊውን በጩኸት እንዲናጋ
አደረጉት፡፡
“ዳዊት አንላቀቅም
ስለክለባችን መፃኢ ሁኔታ
ንገረን”
ከዚህ አሰፈሪ ማዕበል ለመዳን ጥያቄን
መመለስ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተፈተሸ
ነገር ይናፈቃል፡፡ ደጋፊው የቦርድ አመራሩ
እንዲህ ወደታች ወርዶ ጥያቄያቸውን
ለማድመጥ በመምጣቱ የተሰማቸውን
ደስታ በከፍተኛ ጭብጨባ ነው የገለፁት፡
፡ እናስ አቶ ዳዊት እጅህ ከምን? እንዲህ
ሲል ይመልሳል “የእውነት እኔ በዚህ ደረጃ
ደጋፊውን አልጠበቅኩም፤ ምን ያክል ለክለቡ
ኃያል ፍቅር እንዳላችሁ ማሳያ ነው፡፡ እኛ
ያኔ ስናቅድ ሙሉ ስታዲየሙን ለመሙላት
የተወሰነ ነገር ብንሰራ ብለን አቅደን ነበር፡
፡ እናንተ ግን ከእኛ እቅድ ቀድማችሁ ያቺን
ክፍተት በመድፈን መላ ስታዲየሙ የቅ/
ጊዮርጊስ ልጆች እንዲሆኑ አስቻላችሁን፡፡
እውነት እላችኋለሁ ይህንን ብርቅዬ ደጋፊ
ልገልፅ የምችልበት ቃላቶች የሉኝም፡፡ እናንተ
ልዩ ናችሁ፡፡ እኛ ደግሞ እዚህ ወንበር ላይ
የተቀመጥነው ቦታውን ለማሞቅ ሳይሆን
የእናንተን ጥያቄ ለመመለስና ክለባችንን
በሁለት እግሩ ለማቆም ነው፡፡ ደግሞም
እናደርገዋለን፡፡ እኔ ወደዚህ ክለብ ስመጣ
ለለውጥ ነው፡፡ አለዚያ መስራት ካልቻልኩ
መልቀቅ ነው ያለብኝ፤ አይዟችሁ እጅ ለእጅ
ተያይዘን የምትወዱትን ክለብ እናሳድገዋለን”
በማለት ቆፍጠን ያለ ምላሽ ሰጠ፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ በቀጣዮቹ
ጊዜያቶች ምን ያስባል?
እንደ አቶ ዳዊት ገለፃ ከምንም በላይ
ክለቡን መለወጥ ከተፈለገ አሁን ያለው የክለቡ
ይዘትና ቅርፅ መቀየር መቻል አለበት፡፡ ይሄን
አካሄድ ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ ከሀገር
ውስጥ እንደሞዴል የምንወስደው አንዳችም
ነገር ስለሌለ ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት
በመዘዋወር ዘመናዊው የክለብ አደረጃጀት ምን
እንደሚመስል ለማጥናት እየሞከርን ነው፡፡
በአጠቃላይ የክለቡን አሰራር ማዘመን ስንችል
ለውጡም በሂደት እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡
በተለይ ደግሞ ስፖንሰርን በተመለከተ ሁሌም
እኛን የሚደግፉ አጋሮች የሚሰጡት ድጋፍ
በእገዛና በመልካም ፈቃደኝነት ላይ ብቻ

የተመሰረተ ሳይሆን በዘመናዊ ቋንቋ ሰጥቶ
የመቀበል ባህልን ለማዳበር ይቻል ዘንድ
ተግተን እየሰራን ነው” ብሏል፡፡
የትጥቁ ናፍቆት
የብዙሃኑ ደጋፊ አንገብጋቢና ወቅታዊ
ጥያቄ ይህ ነበር፡፡ እናም በዚህ ዙሪያ የቦርድ
አመራሩ ምላሽ መስጠት ነበረባቸው፡፡ እንደ
አቶ ዳዊት ገለፃ በጊዜው መምጣት የነበረበት
ትጥቅ የዘገየው በወቅቱ በሀገራችን ተፈጥሮ
በነበረው አለመረጋጋትና የውጭ ምንዛሬ
እጦት መሆኑን ገልፀው አሁን ሁሉ ነገር
መስመር በመያዙ ከአንድ ሳምንት በኋላ
5 ሺህ ትጥቆችን ከሁለት ሳምንት በኋላ
ደግሞ 10 ሺህ የደጋፊዎች ማሊያ ከጣሊያኑ
ማክሮን በመረከብ በአጠቃላይ 15 ሺህ
ማሊያዎች ለደጋፊው እንደሚከፋፈል ቃል
ገብተውላቸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ከአሁን በፊት ክለቡ
ወደ ክልል ሲጓዝ ስፖርት ማህበሩ በቂ
ትራንስፖርት ያቀርብ እንደነበርና አሁን
ግን ይህ ሁኔታ ለምን እንደተቋረጠ
ይነገረን የሚል ጥያቄ ተነስቶ አቶ ዳዊት
ሲመልስ “ከአሁን በፊት ወደ ሃዋሳ ሲጓዙ
80 አውቶብሶችን አቅርበናል፡፡ አሁን ይሄን
ማድረግ ያልቻልነው ባስ የማዘጋጀቱ አቅም
አንሶን ሳይሆን ለእናንተ ደህንነት በማሰብ
ነው፡፡ እናንተ ጨዋታ ለማየት ክልል
ደርሳችሁ እስክትመለሱ ሁሉ ነገር የእኛ
ኃላፊነት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ
የፀጥታው ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ሴኪዩርድ
እስኪሆን ድረስ ክለባችሁን ለመደገፍ
ሄዳችሁ ጉዳት አጋጥሟችሁ ብትመጡ
በእጅጉ ያመናል፡፡ ምክንያቱ ይህ ብቻ ነው
እንጂ ወደፊት ጥያቄአችሁን ሙሉ ለሙሉ
እንደምንመልስ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ”
በማለት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን
ባለው ሁኔታ ክለቡ የመለማመጃ ሜዳውንና
ሆስቴሉን እንዲለቅ ስለተባለ ይህን ሁኔታ
ለማስተካከል ይቻለን ዘንድ ዘመናዊ ሆስቴል
እና የመለማመጃ ቦታ ለመስራት በእንቅስቃሴ
ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ ዳዊት ለእዚህ ስኬት
ደግሞ ሁለንተናቸውን ለቅ/ጊዮርጊስ አሳልፈው
በመስጠት ተለይተው የሚታወቁት የክለባችን
የቦርድ ሰብሳቢና ወንድማችን አቶ አብነት ገ/
መስቀል እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ በመሆኑ
ደጋፊዎቻችን በዚህ ረገድ ምንም አይነት
ስጋት ሊገባችሁ አይገባም በማለት ቃል
ገብተውና የክለቡ መዝሙር ተዘምሮ የዕለቱ
የአየር ጤና የፈረሰኞቹ የቤተሰብ ውይይትና
ድግስ ጥሩ በሆነ መልኩ ተቋጭቷል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P