Google search engine

“የመድንን የቀድሞ ስምና ዝና ለመመለስ ቆርጠን ተነስተናል” “በባህርዳር የነበረንን ምርጥ ስኬት በሌሎች ከተማዎች ላይም ለመድገም ተዘጋጅተናል” “እንደ ቡድን መጫወታችን ነው ከፍ ወዳለው ማማ እየወሰደን የሚገኘው” ዮናስ ገረመው /ኢትዮጵያ መድን/

“የመድንን የቀድሞ ስምና ዝና ለመመለስ ቆርጠን ተነስተናል”

“በባህርዳር የነበረንን ምርጥ ስኬት በሌሎች ከተማዎች ላይም ለመድገም ተዘጋጅተናል”

“እንደ  ቡድን መጫወታችን ነው  ከፍ ወዳለው ማማ እየወሰደን የሚገኘው”

ዮናስ ገረመው /ኢትዮጵያ መድን/

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከአመታት ቆይታ በኋላ ዳግም የተቀላቀለው ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ጅማሬ አስከፊ ሽንፈትን ቢጎናፀፍም በተከታታይ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ላይ በመቶ ፐርሰንት የማሸነፍ ሪከርድ ሊጓዝ በመቻሉ እንደ ቅ/ጊዮርጊስ ሁሉ በመሪነቱ የማማ ስፍራ ላይ ሊቀመጥ ችሏል።

ኢትዮጵያ መድን በሊጉ የአምስተኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ መቻልን ረትቶ በእኩል 12 ነጥብ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በነጥብ የተስተካከለ ሲሆን የሚበለጠው በግብ ክፍያ ብቻ ነው። የእዚህን ቡድን የዘንድሮ  የውድድር ጅማሬና ስለ ቀጣይ ጊዜ ጉዞው እንደዚሁም ደግሞ ሌሎችን ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት ለክለቡ ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት ላይ የሚገኘውንና በሊጉ ታሪክም ከተለያዩ ክለቦች ጋር ማለትም ከጅማ አባጅፋርና ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር ዋንጫ ያነሳውን ዮናስ ገረመውን /ሀላባ/  የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጠይቆት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶታል፤ ተከታተሉት።

ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ በመሆንህ  እናመሰግንሃለን?

ዮናስ፦ እኔም አመሰግናችኋለሁ።

ሊግ፦ ከቅ/ጊዮርጊስ የሰፋ ግብ ሽንፈት በኋላ አራት ተከታታይ ድሎችን ለማስመዝገብ ችላችኋል፤ የእዚህ የለውጥ ሚስጥር ምንድን ነው?

ዮናስ፦ ያን ያህል የተጋነነ ሚስጥር  አለው ብለን አናስብም፤ ወደ ተከታታይ ድሎች ለመምጣት የቻልነው ከመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈታችን ለመማር በመቻላችን ነው፤ ያ ጨዋታ ለእኛ በተለይም ደግሞ በግል ደረጃ ስንጫወት ያለብን ችግር ነበርና በእዛ ላይ ጠንክረን እንድንሰራ አድርጎናል፤ ሲቀጥል  ደግሞ ክለባችን እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቲምም ስለሚጫወት በክለቦች ላይ የበላይነትን ወስደን ልናሸንፋቸው እና ወደ ሊጉ መሪው ማማም ላይ በነጥብ እንድንስተካከለው አስችሎናል።

ሊግ፦ በቅ/ጊዮርጊስ በሰፊ ግብ በተሸነፋችሁበት ዕለት በቡድናችሁ ውስጥ ምን አይነት ስሜት ነበር የተፈጠረው?

ዮናስ፦ ያን ግጥሚያ ያደረግነው ብዙም የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ሳናደርግ ነበር፤ ከጌም ርቀንም የተጫወትንበት ነው። ሽንፈቱን በእግር ኳስ ሊያጋጥም የሚችል አይነት ብለን ስለወሰድነው እና ደግሞም በቡድናችንም እንደምንተማመንም ስለምናውቅና አሰልጣኙም ብዙ ጊዜ የሚሰራው እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቲም የሚጫወት ቡድን ስለሆነና በተከታታይ ጨዋታዎች ላይም ለውጦች ሊኖሩን እንደሚችሉም ስለተረዳን በመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት በስሜት ደረጃ ያህን ያህል የተጎዳንበት ሁኔታ የለም።

ሊግ፦ በፕሪምየር ሊጉ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ሁለቱ ታሪካዊ ክለቦች ኢትዮጵያ መድንና መቻል ተገናኝተው ግጥሚያው በእናንተ አሸናፊነት ተጠናቋል፤ በጨዋታው ዙሪያ ምን ትላለህ?

ዮናስ፦ የገጠምነው ቡድን በጣም አሪፍ እና ጥሩ የሆነውን ነው።  ይህ ጨዋታ ውጤቱ ለእኛም ሆነ ለተጋጣሚያችን በጣም አስፈላጊ የሆነ ስለነበር  ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክርም ተደርጎበታል፤ ያም ሆኖ ግን በጨዋታ ፍላጎት የተሻለ የነበረውና እንደ ቡድን ሲንቀሳቀስ የነበረውም ክለብ ግጥሚያውን ለማሸነፍ ችሏል።

ሊግ፦ የኢትዮጵያ መድን የተጨዋቾች ስብስብን በተመለከተ ምን አልክ?

ዮናስ፦ ወጣትም ሲኒየር ተጨዋቾችም የተሰባሰቡበት ቡድን ነው ያለን። ኳሱን በህብረትም ነው የምንጫወተው። አቅም ያላቸው እና ብዙ ነገሮችንም መስራት የሚችሉ ልጆችም አሉንና በስብስብ ደረጃ ከሌሎቹ ጋር ያን ያህል የተራራቀ ልዩነት የለንም።

ሊግ፦ በፕሪምየር ሊጉ  እንደ ቅ/ጊዮርጊስ ሁሉ እናንተም በእኩል 12 ነጥብ በመሪው ማማ ላይ ተቀምጣችኋል? የምትበለጡት በግብ ክፍያ ብቻ ነው። በቀጣይነት በምን መልኩ እንጠብቃችሁ?

ዮናስ፦ አሁን ላይ በእዚህ መልኩ ጠብቁን አንልም፤ የእኛ ዋናው ዓላማ ከፊት ፊት ያሉብንን ጨዋታዎች እያሸነፍን መሄድ ነው። የተሻለ ቦታ ላይ መገኘትን እንፈልጋለን፤ ለእዛም ስንል ስራችንን ጠንክረን ስለመስራት ብቻም ነው የምናስበው።

ሊግ፦ ኢትዮጵያ መድን ታሪካዊ ቡድን ነው፤ ስለዚህ ክለብ የምታውቀው ነገር አለ?

ዮናስ፦ ከእዚህ በፊት ስለነበረው ከሆነ ክለቡን  ሊወርድ አካባቢ  በተወሰነ መልኩ ነው በአካል  ያየሁት።  ከእዛ በፊት ስለነበረው ከሆነ  ደግሞ ከተለያዩ አካላቶች እንደሰማሁት ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች የወጡበት፣ ትልቅ እና ታሪካዊ ቡድንም እንደነበረ ነው። ይህን ሳውቅ እንደዚህ ላለ ቡድን ለመጫወት በመቻሌ ራሴን እንደ ዕድለኛ ነው የምቆጥረው። ለእዚህ ታሪካዊ ክለብም እንደ ቀድሞ የቡድኑ ተጨዋቾች እኔም ሆንኩ ሌሎቹ የክለብ አጋር ጓደኞቼ አንድ ነገርን ሰርተን ማለፍም እንፈልጋለን።

ሊግ፦ በኢትዮጵያ መድን ውስጥ ጥሩ የጨዋታ ጅማሬን እያሳየህ ነው፤ ከእዚህ ቀደም ከነበረህ ብቃት አንፃር እንደ አዲስ እያንሰራራው ነው ትላለህ? ስላሳለፍከው የኳስ ህይወትስ ምን አልክ?

ዮናስ፦ አዎን፤ እያንሰራራው ነው። ሀሳቤ የተሻለ ተጨዋች መሆን ነው። ያን ለማግኘት ደግሞ ጠንክሬ እሰራለሁ።

ሊግ፦ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ለሁለት ጊዜያት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ቻልክ? ከእዚህ በኋላስ ስለ ሌላ ድል ምን እያሰብክ ነው?

ዮናስ፦ ያላገኛዋቸው ዋንጫዎች እና ክብሮች አሉ፤ እነሱን ማሳካት እፈልጋለሁ። ሌላው ደግሞ ሶስተኛ የሊግ ዋንጫንም  ማግኘት እፈልጋለሁ።

ሊግ፦ በሊጉ የአሰልጣኝነት ቆይታው ውጤታማ ከሆነውና አሁን ላይ  ኢትዮጵያ መድንን እያሰለጠነ ካለው ገብረመድህን ሀይሌ ጋር በተደጋጋሚ የመስራት ዕድሉ ገጥሞሃልና ስለ እሱ ምን ማለት ትፈልጋለህ?

ዮናስ፦  ስለ እሱ እኔ ባልናገር እንኳን  ስራው ምስክር ነው።  ያው ገብሬ ስኬታማ የሆነው በግለሰብ የሚያምን ሳይሆን እንደ ቡድን የሚያሰለጥንና የሚያጫውት አሰልጣኝ ስለሆነ ነው። እሱ ሁሌም አዳዲስ እና  እያንዳንዱ ተጨዋች በኳስ ችሎታው ሊለወጥበት የሚችልን ስልጠናንም  ይሰጥሃልና  ከእሱ ጋር ስለሰራው ስለ ጎበዝ አሰልጣኝነቱ ነው ለመናገር የምፈልገው።

ሊግ፦ የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ መድን  ምን ውጤትን ማምጣት ሰንቋል?

ዮናስ፦ ከወዲሁ እንዲህ ያለ ውጤት ይኖረናል አልልህም፤ ዘንድሮ ክለቡ ከከፍተኛ ሊግ ነው የመጣው። ቡድኑን ጥሩ ተፎካካሪ እናደርገዋለን ። በመቀጠል ደግሞ ወደ ተሻለ ማለትም ወደ ዋንጫው ፉክክር ውስጥ ለመግባት እንጫወታለን።

ሊግ፦ የባህርዳር የአምስት ሳምንት ቆይታ ተጠናቋል፤ ለኢትዮጵያ መድን እንዴት አለፈ?

ዮናስ፦ ለእኛ ለመድኖች  ጥሩ ጊዜን  ያሳለፍንበት ነው፤ ምክንያቱም ወደዚህ የመጣነው ጥሩ ውጤት ለማምጣትም ነበርና ያን አሳክተነዋል።

ሊግ፦ አንድ ነገር በልና እናጠቃል?

ዮናስ፦ ፈጣሪ ይመስገን፤ በሰላም አስጀምሮ በሰላም ላስጨረሰን አምላክ ክብርና ምስጋና ይግባው።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P