Google search engine

“ኢትዮጵያ ቡናን ብወደውም ወደ ባህርዳር ከተማ ያቀናሁት የተሻለ ነገር በማግኘቴ ነው” “ለብሄራዊ ቡድን የተመረጥኩት እንደጠበቅኩት ነው” “በዘመኔ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫዬን  አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ” ዱሬሳ ሹቤሳ /ባህርዳር ከተማ/

“ኢትዮጵያ ቡናን ብወደውም ወደ ባህርዳር ከተማ ያቀናሁት የተሻለ ነገር በማግኘቴ ነው”

“ለብሄራዊ ቡድን የተመረጥኩት እንደጠበቅኩት ነው”

“በዘመኔ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫዬን  አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ”

ዱሬሳ ሹቤሳ /ባህርዳር ከተማ/

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ  የውድድር ተሳትፎው ምንም እንኳን የተጫወተበት ክለቡ ሰበታ ከተማ ከሊጉ ቢወርድም በግሉ ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ አሳይቷል፤  በጣም ፈጣን ነው፤ ፍጥነቱንና የኳስ ብቃቱን አክሎበት የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮችን ሲያስቸግርም ተመልክተናል።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ  ለሰበታ ከተማ በመጫወት ጥሩ የውድድር ጊዜን ያሳለፈው ዱሬሳ ሹቤሳ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ባህርዳር ከተማን በመቀላቀል ከክለቡ ጋር የፕሪ ሲዝን ዝግጅቱን መስራት ጀምሯል። ዱሬሳ በእዚሁ ቡድን የተጨዋችነት ዘመን ቆይታውም በዘመኑ የመጀመሪያውን የሊጉ ዋንጫ እንደሚያነሳም ይናገራል።

ዱሬሳ ይህን አስመልክቶ ሲናገርም  “አሁን የተዘዋወርኩበት ክለብ በወጣት ተጨዋቾች የተገነባና ጥሩ  የተጨዋቾች ስብስብን  የያዘ  ቡድን ነው ያለን፤ ጥሩም አሰልጣኝ አለን። ከእዚህ መነሻነትም  የሊጉ ዋንጫ ስለናፈቀኝ በዘመኔ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫዬን  አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ” ሲል ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።

ሊግ ስፖርት ጋዜጣ ከሰበታ ከተማ  ወደ ባህርዳር ከተማ በዝውውር መስኮቱ ካመራው ዱሬሳ ሹቤሳ ጋር  በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ያደረገው ቆይታም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት።

ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ ከልብ አመሰግናለሁ?

ዱሬሳ፦ እኔንም እናንተ በዝግጅት ክፍላችሁ ስም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ።

ሊግ፦ ባህርዳር ከተማን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት የቅድሚያ ምርጫህ አድርገህ ልትቀላቀል ችለሃል፤ ወደእዛ እንዴት ልታመራ ቻልክ?

ዱሬሳ፦ የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት  ቅድሚያ ላመራ የነበርኩት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ነበር፤ ክለቡንም እወደዋለሁኝ፤ ለእነሱ እንድጫወትላቸውም መጀመሪያም በወሬ ደረጃ አናገሩኝ። በኋላም ላይ በአካል አግኝተው ሊያወሩኝ ቢችሉም በአንድ አንድ ጥቅሞች ላይ  ለመስማማት ባለመቻላችንና  ሌላው  እኔን አጥብቆ የሚፈልገኝ ባህርዳር ከተማ ደግሞ የተሻለ ጥቅም ስላቀረበልኝ ወደ እነሱ  በማምራት ለክለቡ ለመጫወት ፊርማዬን አኑሪያለሁ።

ሊግ፦ ወደ ባህርዳር  ከተማ በማምራትህ የተፈጠረብህ ስሜት ምን ይመስላል?

ዱሬሳ፦ በእውነቱ ወደ ቡድኑ ስጓዝ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ምክንያቱም ይሄ ክለብ ሊጉ ላይ ካሉት  አሪፍና  የተሻሉ ቡድኖች መካከል  አንዱ ስለነበርም ነው፤ ከእዛ ውጪም  አሰልጣኙን በጣም የማከብረው፣ የምወደው   የቀድሞ አሰልጣኜ  ስለነበርና ከእሱም ጋር ለመስራት ፈቃደኛም ስለሆንኩ እንደገናም ደግሞ አሰልጣኙም የእኔን ጉድለት ይሞላልኛል  ብዬ ስላሰብኩና የኳስ ህይወቴንም በተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስን ስላሰብኩም ለቡድኑ ለመጫወት በመፈረሜ ደስተኛ ነኝ።

ሊግ፦ የአዲሱ ቡድንህ የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት ምን ይመስላል?

ዱሬሳ፦ አሁን ዝግጅት መስራት ከጀመርን  የሳምንታት ጊዜን አስቆጥረናል። በጣም ጥሩና ጠንካራ  ዝግጅትንም እየሰራን  ይገኛል። ጥሩ ቡድንም ነው ያለን፤ በመንፈስም በፊዚካሊም ጥሩ ነን። ከፈጣሪ እርዳታም ጋር  ጥሩ ውጤትን  ለማምጣት ተዘጋጅተናል።

ሊግ፦ በስኳዳችሁ የያዛችሁት የተጨዋቾች ስብስብ ምን ይመስላል?

ዱሬሳ፦ በጣም ጥሩ እና የተሟላ የተጨዋቾች ስብስብ ነው ያለን፤ ወጣቶች እንደዚሁም ልምድ ያላቸው ልጆችም አለን። በውድድር ዘመኑም  ዘንድሮ  በጣም አቅም ያላቸው ተጨዋቾች ስላሉንም  ጥሩ ጊዜን እንደ  ቡድንም እንደ ግልም እናሳልፋለን ብዬም አስባለሁ።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር  ሊጉ  ምን ውጤትን ስለማምጣት እያሰባችሁ ነው?

ዱሬሳ፦ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ  በግሌ ጥሩ ውጤትን ማለትም የሊጉ ዋንጫ የናፈቀኝ ስለሆነ  በዘመኔ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫዬን  አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ። እንደ ቡድን ደግሞ ዋንኛው እልማችን በሊጉ  ከ1-3 ባለው ደረጃ ላይ ሆነን ሊጉን ማጠናቀቅና በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ያ ካልተሳካም በኮንፌዴሬሽን ካፑ ላይ ስለመሳተፍም በማሰብ ላይም ነው የምንገኘው።

ሊግ፦ የዓምናው ቡድንህ  ከቤትኪንግ ፕሪምየር  ሊጉ ወርዷል፤  እንደ አንድ የቡድኑ ተጨዋች በውስጥህ ምን ስሜት ነበር የተፈጠረብህ?

ዱሬሳ፦ ሰበታ ከተማ ከሊጉ ሲወርድ በጣም ነበር ያዘንኩት፤ በተጨዋችነት ዘመኔም  እንዲህ ያለ ነገር  በድጋሚ ይፈጠራል ብዬም  አላስብም። በውድድር ዘመኑ በጣም ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያቶችን  ነበር  ያሳለፍኩት።  ይህ ቡድን ለእኔ ባለውለታዬ እና ጥሩ ነገሮችን ያደረገልኝ  ስለነበር ከሊጉ ስንወርድ ሀዘኔ ከፍተኛም ነበር።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ  ለሰበታ ከተማ መውረድ በምክንያትነት የሚጠቀሰው ነገር ምንድን ነው ?

ዱሬሳ፦ አንድ ቡድን ሁሌም በአንድ ተጨዋች እና በአስራ አንድ ተጨዋች ብቻ  አይሰራም፤  ለእኛ ክለብ ከሊጉ  መውረድ  በዋናነት ምክንያት የነበረው ነገር ከተጨዋቾች ምርጫ አንስቶ የአስተዳደር /የማኔጅመንት/ ችግር ስለነበረብን ነው። በተለይም ደግሞ ቀደም ሲል የነበረውን ቡድን ማለትም 13 የሚደርሱ ልጆችን ለቅቀንና ቡድኑን አፍርሰን  አዲስ ቡድንን ለመገንባት በመቻላችንም የተረጋጋ ነገር እንዳይኖረንና በፋይናንስ ረገድም አሁንም ድረስ የአራት እና የስድስት ወራት ደመወዝ ያልተሰጠን ተጨዋቾች ስላለንም እነዚህ ነገሮች በጣም ሊጎዱን ችለዋል። በህይወቴ  በመውረዳችን  በጣም ልፀፀት የቻልኩበትም ጊዜያት ነው።

ሊግ፦ የውድድር ዘመኑ ለአንተ እንደ ግል ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል?

ዱሬሳ፦ እንደ ግል ፈጣሪ ይመስገን ጥሩ  ጊዜያቶችን ለማሳለፍ  ችያለሁ። ከእዛ የበለጡ ነገሮችን እንዳልሰራ ያደረጉኝ ነገሮች ደግሞ አሉ።  እነዛ ነገሮች ሳይሳኩልኝ ስለቀሩ ደግሞ በጣም አዝኛለሁ።

ሊግ፦ በሰበታ ቆይታህ ጥሩ ጊዜን ባሳልፍም የበለጠ እንዳልሰራ  ያደረጉኝ ነገሮች ደግሞ አሉ ብለሃል። እነዛ ምንድን ናቸው ?

ዱሬሳ፦ በሰበታ ቆይታዬ ብዙ ነገሮችን እንዳልሰራ ካደረጉኝ ምክንያቶች ውስጥ የአስተዳደር ችግሩን ከላይ ገልጫለሁ፤ ከእዛ ውጪም በግል ጉዳይ  የቤተሰብ ችግር ነበር። እነዚሁ ሁኔታዎች  ተፅህኖን ያመጣሉ። በተለይም ደግሞ ደመወዝ እየተከፈለን ስላልነበርም ልምምዶችን እስቀማቋረጥ ደርሰን  በአህምሮ ደረጃ ዝግጁ እንዳንሆንም  ተፅህኖን ፈጥረውብናል። ልምምዶችን  በግልም ነበር የምንሰራው እና በእኔም ሆነ በቡድኔ አባላቶች ላይ ከባድ ጊዜን እንድናሳልፍ አድርጎናል፤ ያም ሆኖ ግን በመጨረሻ እነዚህን አጋጣሚዎች እንደ ግል ታግዬም ቢሆን የተሻለ ነገሮችን ለመስራትም  ሞክሬያለሁ።

ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን እንደ አጠቃላይ በምን መልኩ አገኘኸው?

ዱሬሳ፦ በቅድሚያ የእኛን ቡድን የውድድር ተሳትፎ በተመለከተ በጉዞአችን በጣም ብዙ ችግሮች ነበሩብን። እነዚህ ነገሮች ካልተስተካከሉ ኳሱ ላያድግም ይችላል። በእዛ አካባቢ የሚገኙ አቅም ያላቸው ተጨዋቾች ብዙ ነበሩ። ዛሬ ላይ ቡድኑ ከሊጉ ሲወርድ  እነዚህን ልጆች ማንም የሚያስታውሳቸው ሰውም የለም። እንደዚህ አይነት ቡድኖች ደግሞ ትውልድን የሚገሉ ስለሆኑም ነገሮችን ከጅምሩ ነው ማስተካከል የሚገባው። ለምን? የአገራችን እግር ኳስ አሁን ላይ እያደገ እና የተሻለ እየሆነ ነው የመጣው። ከእዛ አንፃርም መንግስትም የተሻለ ነገርን ማሰብም ይኖርበታል።  ወደ ፉትቦሉም ኳሱን

የሚያውቁ ሰዎች ሊመጡበትም ይገባል። ይህን ካልኩ ወደ ውድድሩ  ሳመራ ደግሞ  ሊጉ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ አሸናፊውሞ አንዱ ወራጅም ሳይታወቅ የተደረገ ስለነበር  በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ነው የተጠናቀቀው። የሚገርም ፉክክርም ተደርጎበታል። ምንም እንኳን  አሸናፊው ቡድን በመጨረሻው ቀን ቢታወቅም ቅ/ጊዮርጊስ የሊጉ ሻምፒዮና እንደሚሆን ግን  ከአምስት ጨዋታዎች በፊት አውቅም ነበር። በኳስ ህይወቴ እንዲህ ያለ ፉክክርን ተመልክቼ አላውቅም። በጣም ደስ ይላል። የሀገራችን እግር ኳስ እንዳደገ አንደኛው ማሳያም የውድድሩ ሻምፒዮና እንደከዚህ በፊቱ ሊጉ ሳይጠናቀቅ ሳይሆን በመጨረሻው ቀን ላይ መታወቅ መቻሉም ነው።

ሊግ፦ በአንተ አመለካከት ዘንድሮ  የትኛው ተጨዋች ጎልቶ ሊወጣ ችሏል?

ዱሬሳ፦ የዓመቱ ጥሩ ተጨዋች ነበር ብዬ ስሙን የምጠራው ተጨዋች በረከት ደስታን ነው። የተሻለ ነገርንም በሊጉ ላይ አሳይቷል። ከእሱ ውጪ ሌላ የምጠራቸው ተጨዋቾች ደግሞ ከነሃን ማርክነህንና ጋቶች ፓኖምን ነው።

ሊግ፦ የአዲሱ ሲዝን ውድድር  ከወዲሁ አጓጉቶሃል?

ዱሬሳ፦ በጣም፤  ምክንያቱም ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር ለክለባችን የተሻለ ነገርን  ለመስራትም በመዘጋጀት ላይ ስለሆንኩ  ነው።

ሊግ፦ አዲስ ዓመት ሲመጣ ሁሌ ከፊትህ ድቅን የሚልብህ ነገር ምንድን ነው?

ዱሬሳ፦ በአብዛኛው የእንቁጣጣሽ በዓል አከባበርን በደስታ ስለማሳለፍ እና  ትምህርት ቤትም የሚከፈትበት ጊዜ ስለሆነ ወደዛ ስለመሄድ  ነው የማስበው። ከእዛ ውጪም አዲስ ልብስ ስለመልበስ፣ አዲስ ጫማም ስለማድረግና በወደፊት ህይወቴ ላይም አዲስ ተስፋን ስለመሰነቅም  ከፊቴ ይመጡብኛል። አሁንም አዲስ ዓመት ሊገባ የተቃረበበት ጊዜ ስለሆነም በኳስ ህይወቴ ፕላን አድርጌ የተዘጋጀሁበት ሁኔታም አለ።

ሊግ፦ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመመረጥ ጥሪው ደርሶሃል፤ ያን ጠብቀህ ነበር?

ዱሬሳ፦ ካለኝና ከነበረኝ አቅም አንፃር ለዋልያዎቹ እንደምመረጥ  በጣም ጠብቄ ነበር። ከእዚህ ቀደምም በነበረው ቡድን ውስጥ ተመርጬም እንደነበር የሚታወስ ነው።

ሊግ፦ ለብሄራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም ለመጀመሪያ ጊዜ ስትመረጥ ስሜትህ ምን ይመስል ነበር?

ዱሬሳ፦ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመረጠው  የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ነው የነበርኩበት። ያኔ ስመረጥም በጣም ነው ደስ ያለኝ። ምክንያቱም የምትጫወተው ሀገርህን ወክለህም ነውና በውስጥህ የተለየ ደስታ ነው የሚፈጠርብህ። አሁንም በድጋሚ ያን የመመረጥ ዕድል ስላገኘው ደስተኛ ነኝ። የተሰጠኝንም እድል ታሪክ መስራትም ስለምፈልግ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር በአግባቡ እጠቀምበታለሁ ብዬም ነው የማስበው።

ሊግ፦ እናጠቃል….?

ዱሬሳ፦ ማንኛውም ሰው በተሰማራበት ሙያ ጠንክሮ ከሰራ  ፈጣሪም ይረዳዋልና  የተሻለ ደረጃ ላይ ይደርሳል።  ከእዛ ውጪ ሁሌም ለስራ ታማኝ መሆንም ከትልቅ ግብ ላይ እንድትገኝ ያደርግሃል። ሌላው ቤተሰብህን እንደዚሁም ደግሞ ባለሙያን ማክበርና የተሻለን ነገርንም ማሰብ ጥሩ ነው። በህይወትህ አጋጣሚም  ትችት ሊያጋጥምህ ስለሚችልም ያን ተረድተህ እና አገናዝበህ በአግባቡ ልትመልስም ይገባል። ይህን ካልኩ በኳስ ህይወቴ የዛሬ ደረጃ ላይ እንድደርስ ከልጅነት ዕድሜ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች እና የአሁኑ አሰልጣኜን ኢንስትራክተር አብርሃም  መብራቱን እንደዚሁም የዋልያዎቹን አሰልጣኝ ውበቱ አባተንም ለማመስገን እፈልጋለውኝ።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P