Google search engine

ጆሳምቢን ከ400 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለዳኞች የትጥቅ ስጦታ አበረከተ

የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር የፕሪምየር ሊጉ ዳኞችና የውድድር ታዛቢዎች ስልጠናና ግምገማ ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ
ሆቴል ተካሄደ፡፡ በዕለቱ የፕሪምየር ሊጉ ወንድና ሴት ዳኞች የጨዋታ ኮሚሽነሮችና የፌዴሬሽኑ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
ዳኞቹና የጨዋታ ኮሚሽነሮች በምድብ በምድብ ተከፋፍለው ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በውድድር ዓመቱ ያጋጠሟቸውን ችግሮችና
መፍትሄያቸውን እንዲሁም በሁለተኛው ዙር መደረግ ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በዝግ ውይይት አድርገዋል፡፡ በቡድን ከተደረገው ውይይት
በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የዳኞች
ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በመገኘት ከዳኞችና ከጨዋታ ኮሚሽነሮቹ ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አንዳንድ ዳኞች በአፅንኦት እንደገለፁት በተለይ በክልል በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ከሚፈጠረው የፀጥታ ችግር ባሻገር የየክልሉ የፀጥታ
ኃይሎች ፍትሃዊ ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ለክልላቸው ሰዎች ወገንተኝነታቸውን ስለሚያሳዩ የሚፈጠሩት ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ እንዳያገኙ
እንቅፋት ፈጥሯል በማለት ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ጨዋታዎችን ዳኝተው ከጨረሱ በኋላ አበላቸው በጊዜ ስለማይከፈላቸው በእጅጉ
እየተጉላሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ አሁን በአዲስ መልክ የተመረጠው የፌዴሬሽኑ አመራር የዳኞችንና የኮሚሽነሮችን ችግር
ቀርፎ ወደተሻለ ነገር ለመጓዝ የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ከላይ በተነሱትና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
እንደ አቶ ዮሴፍ ገለፃ ከሆነ በዘንድሮው የውድድር ዘመን አንደኛው ዙር ተሳትፎን በተመለከተ ከፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ጋር ውይይት አድርገው
እንደነበርና ከ16ቱ ክለቦች ውስጥ ከአንዱ ክለብ በስተቀር 15ቱም ክለቦች የዘንድሮው አንደኛው ዙር የዳኞችና የኮሚሽነሮች አሰራር ጥሩ
እንደነበር ምስክርነት ሰጥተዋል ካሉ በኋላ ይህ ማለት ግን መቶ ፐርሰንት ስኬታማ ነበር ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ መነሻነት በሁለተኛው ዙር
የተሻለና ፍትሃዊ ዳኝነት ለማየት እንድንችል ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል በማለት ተናግረዋል፡፡
አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ አክለው እንደገለፁት ተወዳዳሪ ክለቦች ከእኛ ፍትሃዊ ዳኝነት እንደሚፈልጉ ሁሉ እኛም ለክለቦቹ አስረግጠን የነገርናቸው
ነገር አለ፡፡ “እንደሚወራውና እንደሚባለው አንዳንድ ዳኞችና የውድድር ኮሚሽነሮች በሙስና ስለሚጠረጠሩ እባካችሁ ክለቦች በተቻለ አቅም
ማንም ዳኛና የውድድር ታዛቢ ወደ እናንተ ክልል ሲመጡ አልጋ እንዳትይዙላቸው፤ አበልም እንዳትሰጧቸው፡፡ ምክንያቱም እኛ የምንከፍላቸው
አበል በቂ ነው በማለት በተቻለ አቅም የሙስና አሰራር ክፍተቱን ለመድፈን እንችል ዘንድ ክለቦቹ እንዲያግዙን ነግረናቸዋል” ብለዋል፡፡
በዕለቱ የነበረው የግምገማና የስልጠና ሂደት በተሻለ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን በዚሁ መድረክ ላይም ሁሌም ከኢትዮጵያ ስፖርት ጎን ቀድሞ
በመሰለፍ የሚታወቀው የጆሳምቢን ትሬዲንግ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በግሉ ከ400 ሺህ ብር በላይ በማውጣት ለሁሉም
የፕሪምየር ሊጉ ዳኞች ዘመናዊ ትጥቅ ከውጭ ሀገር በማስመጣት በዛኑ ዕለት ለአርቢትሮቹ ያበረከቱ ሲሆን ዳኞቹም በበጎ ፈቃደኝነት
በመነሳሳት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ስላደረጉላቸው ድጋፍ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: