የዛሬው እንግዳችን ገና ወጣት ተጨዋች ነው፤ተወልዶ ያደገው በመካኒሳ አቦ ቤተክርስቲያን አካባቢ ወይንም ደግሞ በቀበሌ 13 ውስጥ ነው፤ ወላጅ አባቱ አቶ ኑር ናስር ሲባሉ ወላጅ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ በሽወርቅ አሰፋ ተብለው ይጠራሉ፤ ተጨዋቹ መሐመድ ኑር ይባላል፤ ስድስት ወንድሞችና አንድ እህት አለው፤ የኳስ ጅማሬው እንደ ማንኛውም እግር ኳስ ተጨዋች በአካባቢው በሚገኝ እድር ሜዳ ላይ በሕፃንነት እድሜው ነበር ለመጫወት የቻለው፤ ሜዳው ስያሜውን ያገኘውም አጠገቡ ጋር እድር ቤት ስላለና አሁን ላይ ለልማት በሚል ብዙዎች ተደራጅተው ስራ በሚሰሩበት አካባቢ ያለ ስፍራም ስለሆነ ነው፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ጅማ አባጅፋርን በመቀላቀል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመጫወት ዝግጁ የሆነው መሐመድ ኑር ባሳለፈው የኳስ ህይወቱ ለኢትዮጵያ መድን ስፖርት ክለብ በከፍተኛው ሊግ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ይህ ተጨዋች እያሳየ ያለው ብቃትም ወደፊት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደርሰዋል ተብሎም ግምት ተሰጥቶታል፤ መሐመድ ኑር በመድን ክለብ ቆይታው ለክለቡ ጎሎችን ከማስቆጠር ባሻገር ለጓደኞቹም የተመቻቹ ኳሶችን በማቀበልም ብዙዎች አድናቆታቸውን የቸሩት ተጨዋች ሲሆን በክለቡ ገና የአንድ ዓመት ቀሪ ውል እያለውም ነበር ከቡድኑ ጋር በስምምነት በመለያየትና እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብርም በመመለስ አዲሱን ክለብ ሊቀላቀል የቻለው፤ መሐመድን በዝውውሩ መስኮት በርካታ ክለቦች ዓይናቸውን ቢጥሉበትም እንደዚሁም ደግሞ እንደ ቅ/ጊዮርጊስ ያለ ትልቅ ክለብም ተጨዋቹን ወስዶ ቢመለከተውም መጨረሻ ላይ ሳይስማሙ በመቅረታቸው ተጨዋቹ የመሰለፍ እድልን ያስገኝልኛል ወዳለው ክለብ ጅማ አባጅፋር በማምራት አሁን ላይ የክለቡ ህጋዊ ተጨዋች ለመሆን ችሏል፤ መሐመድ ወደ ጅማ አባጅፋር ካመራ በኋላም በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በቂ የመሰለፍ እድል እየተሰጠው በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ውድድር ላይ ለቡድኑ ሶስት የሚደርሱ ጎሎችን አስቆጥሯል፤ በአንድ ጨዋታም ላይ የግጥሚያው ኮከብ ተብሎ የ12 ሺብርና የአዋርድ የዋንጫ ሽልማትንም ሊያገኝ ችሏል፤ ከጅማ አባጅፋሩ አዲስ ፈራሚ ተጨዋች ጋር የሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ስለ ኳስ ተጨዋችነት ህይወቱና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ተሳትፎው በምን መልኩ ለመቅረብ እንደተዘጋጀ ያናገረው ሲሆን ይኸው ወጣት ተጨዋችም ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
በልጅነት ዕድሜው በሰፈር ደረጃ ስለተጫወተበት የመጀመሪያው ክለቡና በወቅቱ ስላጋጠማቸው ሁኔታ
“የመጀመሪያ የሰፈር ክለቤ ራዕይ ይባላል፤ በአሰልጣኝ ኤፍሬም አማካኝነትም ነበር እየሰለጠንን በተስፋ ሜዳ ላይ ኳስን እንጫወት የነበርነው፤ በእዚህ ቡድን ቆይታችንም ከማይረሱኝ አጋጣሚዎች ውስጥ በአንድ ወቅት በአልማዝዬ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ባዘጋጀው የቶርናመንት ውድድር ላይ በመሳተፍ በአስኮ የታዳጊዎች ቡድን የተሸነፍንበትን ጨዋታ ነው፤ በእዚህ ጨዋታ ልንሸነፍ ብንችልም እኔም ሆንኩ ሌሎቹ ተጨዋቾቻችን ጥሩ ለመጫወት የቻሉበት አጋጣሚም ነው”፡፡
በቤተሰቡ አካባቢ እግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ስላጋጠመው ሁኔታ
“ያኔ እግር ኳስን እንድጫወት ፈፅሞ አይፈቀድልኝም ነበር፤ ለእዚህም ምክንያት ነበረው፤ የእኔ ወንድም የሆነው አልፋሪድ አንዴ ኳስ ሲጫወት ዓይኑ በኳስ ተመቶ ተጎድቶ ነበር፤ በዛ ጉዳቱም እዚህ ሀገር መታከም እንደማይችልና ወደ አሜሪካኗ ዋሽንግተን ከተማም ሄዶ መታከም እንዳለበት ስለተነገረ ከእሱ ውጪ ደግሞ ሌሎቹ ወንድሞቼ ውስጥም አብዱላኪምና ሰሚርም እጃቸውን የተጎዱበት አጋጣሚም ስለነበር ከዛ መነሻነት ነው እኔ በኳስ ተጫውቼና ተደስቼ በምመጣበት ሰዓት ከእንግዲህ ወዲያ እንዳትጫወት በሚል እገረፍ ስለነበር ኳሱን እንዳልጫወት እከለከል የነበርኩት፤ ያም ሆኖ ግን የእኔን ኳስ መጫወት ከቤተሰብ አባላቶች ውስጥ እናቴ በጣም ትፈልገውም ነበርና በኋላ ላይ መጫወቱን ቀጠልኩበት”፡፡
ኢትዮጵያ መድን አንተን ለእዚህ ደረጃ ያበቃ ትልቅ ክለብ ነው፤ ስለ ቡድኑ ምን ማለት ትችላለህ?
“የእውነት ነው ኢትዮጵያ መድን ለዛሬ ማንነቴ ትልቁን አስተዋፅኦ ያደረገልኝ ክለብ ነው፤ የኳስን ምንነት በዚህ ቡድን ቆይታዬ ከተተኪው ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በሚገባ ጠንቅቄ አውቄበታለው፤ በእዚህ ቡድን ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት ላይም ካሰለጠኑኝ አሰልጣኞች ውስጥ ከካሊድ መሐመድ ስለ ኳስ ቴክኒክ፣ ከአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ /ድሬ/ ሀላፊነትን፣ ከአሰልጣኝ ሀሰን በሽር ድፍረትና ወንድነትን፣ ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ ከአጥቂ ጎል የሚጠበቅ በመሆኑ አንድ አጥቂ ለአንድ ቡድን ምን ማድረግ እንዳለበትና ከአሰልጣኝ በፀሎት ደግሞ ብዙ ነገሮችን በተለይም ደግሞ የራስ መተማመንን ቀላል በሆነ መልኩ እንዳዳብር የተማርኩበት ሁኔታዎች ስላሉ መድንንንም ሆነ እነዚህን አሰልጣኞቼን ፈፅሞ አልረሳቸውም፤ በእዚህ አጋጣሚም አመሰግናቸዋለውም”፡፡
ኢትዮጵያ መድን አሁንም በከፍተኛው ሊግ ስለመቆየቱ
“ኢትዮጵያ መድን እንደ ትልቅ ክለብነቱና ምንም አይነት የፋይናንስ ችግርም ሳይኖርበት አሁንም ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ሳይቀላቀል ከፍተኛው ሊግ ላይ መቆየቱን ሳይ በጣም ነው የሚቆጨኝ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታቶች ለማለፍ ጫፍ ላይ ደርሰን ነበር እድሉን ያጣነው፤ ዘንድሮ ደግሞ ማለፍ እየቻልን ባለማለፋችን እስከ ማልቀስ ደረጃም ደርሻለው፤ መድን ላይ አሁን ባልኖርም አንድ ቀን ግን ሊጉን ቢቀላቀል በጣም ነው ደስ የሚለኝ”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለጅማ አባጅፋር ለመጫወት ፊርማህን አኑረሃል፤ መጀመሪያ ግን ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ነበር ያመራከው….?
“በኢትዮጵያ መድን ቆይታዬ የአንድ ዓመት የውል ጊዜ እየቀረኝ መጀመሪያ ሊወስደኝ የነበረው ክለብ እንዳልከው ቅ/ጊዮርጊስ ነበር፤ ወደዛ አምርቼ የቀናት የዝግጅት ጊዜ ልምምድንም ሰርቻለው፤ ያም ሆኖ ግን ከክለቡ ጋር በነበረኝ አጠር ያለ ቆይታ ምክንያቱን በማላውቀው ሁኔታዎች ልንስማማና ልንግባባ ስላልቻልን ወደ ጅማ አባጅፋር ቡድን አምርቼ ፊርማዬና ለማኖር ችያለው”፡፡
ወደ ጅማ አባጅፋር ለማምራት የቻልክበት ዋናው ምክንያትስ?
“ወደዚህ ቡድን ከማምራቴ በፊት ሌሎች አማራጮች ነበሩኝ፤ ያም ሆኖ ግን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እኔን ወደ ቡድኑ ከጠራኝ በኋላ በችሎታዬ ላይ እምነትን በማሳደሩ፤ ወጣት ተጨዋች በመሆኔም ደግሞ በእዚህ ሰዓት ካለኝ ብቃት አንፃር መጫወትን እንጂ መቀመጥን ፈፅሞ የማልፈልግ መሆኔንም በማወቁ ምንም ሳልግደረደር ነው ወደ ቡድኑ ያመራሁት”፡፡
በ15ኛው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ላይ ለጅማ አባጅፋር ጥሩ በመንቀሳቀስ 3 ጎሎችንም ለማስቆጠር ችለሃል፤ ይህ ብቃትህ በቤትኪንጉም ይቀጥላል?
“ለዛ ፈፅሞ አልጠራጠርም፤ በሲቲ ካፑ ተሳትፎአችን መጀመሪያ ላይ እንደምንጫወት አላወቅንም ነበር፤ ወደ ውድድሩ ስንገባ ግን ተሳትፎአችን እኛን ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹን ቡድኖች በጣም የጠቀማቸው ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ በዚህ ውድድር ላይ ክለባችን ያለበትን አቋም በደንብ አውቆበታል፤ እኔም እንደ አንድ የቡድኑ አጥቂ ዓላህ ረድቶኝም ጎሎችን ላስቆጥርበት ችያለውና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉም ላይ ይህን ብቃቴን ነው ዳግም ነው የማሳየው”፡፡
ከሌላኛው የቡድኑ አጋሩ ዳዊት ፍቃዱ ጋር እየፈጠሩት ስላለው ጥምረት
“ዳዊት ጥሩ አጥቂ ነው፤ ተግባብተክም የምትጫወተው ነው፤ በመድን አብረን ሆነን የፊት መስመሩን አሳምረነዋል፤ ይሄ ጥምረታችን በድጋሚ አሁንም በጅማ አባጅፋር ክለብ ውስጥ ይቀጥላልና ለቡድኑ ጥሩ ነገር ለመስራት ተዘጋጅተናል”፡፡
ጅማ አባጅፋር በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ምን ውጤትን ለማምጣት እንደተዘጋጀ
“ይሄ ቡድን ላለመውረድ የተጫወተበት ጊዜ ዘንድሮ እንደሚያከትም እርግጠኛ ነኝ፤ አሁን ላይ ጠንካራ ቡድንን እና ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብን ይዟል፤ ቤትኪንጉን የምንወዳደረውም ጥሩ የሚባል ውጤትን ለማምጣት ነው”፡፡
ስለ ወደፊት ግቡና እልሙ
“በኳስ ህይወቴ የእኔ ዋንኛ እልምና ግብ ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ሊጉ ላይ ተጫውቼ ወደ ውጪ ሀገር በመውጣት በፕሮፌሽናል ደረጃ መጫወት ነው፤ ከዛ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጥም ሀገሬን መጥቀምም እፈልጋለው”፡፡
በመጨረሻ…
“በእግር ኳሱ አሁን ላይ ለመጣሁበት መንገድ በቅድሚያ ፈጣሪዬን ዓላ እኔን ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች እና ቤተሰቦቼን ማመስገን እፈልጋለው፤ ከዛ ባሻገር ማለት የምፈልገው ዘንድሮ የተሻለ የውድድር ዘመንን እንደምንመለከት ነው”፡፡