በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከወራቶች በፊት የተቀላቀለው ሰበታ ከተማ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት በርካታ ተጨዋቾችን እያስፈረመ ይገኛል፤ በአዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመመራት ወደ ውድድር የሚገባው ይኸው ቡድን በመጪው የውድድር ዘመን ላይ ስኬታማ ውጤትን ለማምጣት ያስፈረማቸው ተጨዋቾችም ከመከላከያ ተከላካዩን አዲሱ ተስፋዬን፣ አማካዮቹን ዳዊስ እስጢፋኖስና ሳሙኤል ታዬን እንደዚሁም ደግሞ አጥቂውን ፍፁም ገ/ማሪያምን ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኃይሉ አሰፋ /ቱሳ/ እና ሌሎችንም ተጨማሪ ተጨዋቾችን ሊያስፈርም ችሏል፡፡
የሰበታ ከተማን ፊርማ ካኖሩት ተጨዋቾች መካከል ለዛሬው በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ያናገርነው ተጨዋች በወላይታ ድቻና በመከላከያ ቡድን ውስጥ በነበረው ያለፉት ስድስት ዓመታት የተጨዋችነት ቆይታው በበርካታ ግጥሚያዎች ላይ በመሰለፍ የሚታወቀውና ምንአልባትም ደግሞ በብዙ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍም ከሚታወቁ በጣም ጥቂት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቹን አዲሱ ተስፋዬን ነውና በዝውውር መስኮቱ መከላከያን በመልቀቅ እንዴት ወደ ሰበታ ከተማ እንደመጣ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስተንለት ምላሹን ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- የክረምቱን የእረፍት ጊዜ የትና እንዴት እያሳለፍክ ነው?
አዲሱ፡- የእረፍት ጊዜዬን በአሁን ሰዓት በማሳለፍ ላይ የምገኘው እዚሁ በምኖርበት የአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከባለቤቴ ጋር ሲሆን በእዚህም ወቅት የጂምናዝዬም ልምምድ በመስራትና ከጤና ቡድን ተጨዋቾች ጋርም ኳስን እየተጫወትኩ ስገኝ ከአዲስ አበባ ውጪም የተወሰነውን ጊዜያቴን በትውልድ ሀገሬ አምቦ ጊንጪ ከቤተሰቦቼም ጋር አሳልፌያለሁ፡፡
ሊግ፡- መከላከያን ለአራት ዓመታት አገልግለህ ከክለቡ ጋር ተለያይተሃል፤ የቆይታ ጊዜያቶችህን እንዴት ነው የምትገልፃቸው?
አዲሱ፡- በመከላከያ ውስጥ የነበረኝ የእስካሁኑ የተጨዋችነት ቆይታዬ በአብዛኛው ጥሩ የሚባልና በጣምም የተደሰትኩበት ነው፤ በእዚሁ ክለብ ሳለውም ሁለት ጊዜ የጥሎ ማለፍና አንድ ጊዜ ደግሞ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለማንሳት ችያለሁና እነዚህን ስኬቶቼ መቼም ቢሆን የምረሳቸው አይደለም፡፡
ሊግ፡- በመከላከያ ቆይታህ በእዚህ ዓመት ብዙም መጫወት አልቻልክም፤ ምክንያቱ ምንድነው?
አዲሱ፡- አዎን፤ የእዚህ ዓመት የክለቡ ቆይታዬ እንዳለፉት ሶስት ዓመታቶች በቋሚ ተሰላፊነት የታጀበ አልነበረም፤ ዘንድሮ በአብዛኛው ተጠባባቂና ኦቨር ቤንች ሆኜም ነው ጊዜውን ያሳለፍኩት፡፡ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ለክለቤ ተሰልፌ ልጫወት ያልቻልኩትም በአሰልጣኙ ችግር ምክንያትና ባልተረጋጋ ቡድን ውስጥ ስለነበርኩም ነው፡፡
ሊግ፡- ለመከላከያ እየተሰለፍክ ያልተጫወትከው ጉዳት ስለነበረብህ ነው የሚል መረጃን ሰማን፤ የእውነት ነው?
አዲሱ፡- በፍፁም፤ የተወራው ወሬ ሁሉ ሃሰትና የተሳሳተም መረጃ ነው፤ ፈጣሪ ይመስገን፤ እኔ ጉዳት የለብኝም፤ ጥቂት የጉልበት ጉዳት የነበረብኝም ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፤ ያኔም ስጎዳ ጉልበቴን መታጠብ ካልሆነ በስተቀር ኦፕራሲዮን /ሰርጀሪ/ ያደረግኩበት ሁኔታ የለምና ቶሎ ድኜ ነው ለክለቤ ስጫወት የነበርኩት፤ ዘንድሮ ግን በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ለክለቤ ሳልጫወት የቀረሁት አሰልጣኛችን እኔን ሊያሳልፈኝ ስላልፈለገ ነው፡፡
ሊግ፡- መከላከያን በመልቀቅ ወደ ሰበታ ከተማ አምርተሃል፤ ይሄ እንዴት ነው የሆነው?
አዲሱ፡- ከመከላከያ በመለያየት ወደ አዲሱ ቡድኔ ሰበታ ከተማ ያመራሁት እንደ ሲኒየር ተጨዋችነቴ ቡድኑ በውል ማራዘሚያ ባቀረበልኝ ጥቅምና ደመወዝ ልንስማማ ስላልቻልን ነው፤ ያኔም ሰበታ ከተማዎች ለተጨዋቾች እንዲከፈል በተወሰነው እና ህጉን ባከበረ መልኩ ለእኔ ጥሩ ጥቅም ስለሰጡኝ ፊርማዬን ለእነሱ ላኖር ችያለው፤ ወደፊትም በክለቡ በሚኖረኝ ቆይታም ብዙ ጥቅምን አገኛለው ብዬም ስላሰብኩ ክለቡን የመጀመሪያ ምርጫዬም ለማድረግ ችያለው፡፡
ሊግ፡- ወደ ቅ/ጊዮርጊስ እንደዚሁም ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ቡናና ወደ ሌሎች የሀገራችን ቡድኖች ታመራለህ ተብለህ ስትጠበቅ ማረፊያህ ሰበታ ከተማ ሆኗል፤ ወደ ሌሎቹ ቡድኖች እንዴት ሳትገባ ቀረህ?
አዲሱ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትላልቅ በሚባሉት የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በዝውውር መስኮቱ ተፈልጌ ወደ እነሱ ሳላመራ የቀረሁት በእኔ ላይ በተከፈተው “እግሩ ጉዳተኛ ነው፤ የጉልበት ህመምም ችግር አለበት” በሚል በተናፈሰው የበሬ ወለደ አይነት የተሳሳተ መረጃ ነው፤ ወደ ሁለቱ ቡድኖች ልገባ ተቃርቤ ነበር ያም ሆኖ ግን እኔ ጤነኛ ሆኜ ህመም አለበት ተብሎ ስለተነገራቸው ብቻ በአረዳድና በመረጃ እጦት ችግር ምክንያት ወደ እነሱ ሳልገባ ቀርቻለውና በእኔ ላይ እንግዲህ የሆነው ይህ ነው፡፡
ሊግ፡- አሁን አንተ ጤነኛ ነኝ እያልክ ነው፤ ወደ ቅ/ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንዳታመራ ስላደረገክ የእግር ጉዳት አለበት የሚለውን የሰዎች መረጃን ስትሰማ ምን አልክ?
አዲሱ፡- የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች ምንም አይነት የእግር ጉዳትም ሆነ የህመም ስሜት ሳይኖርብኝ በሰሙት የተሳሳተ መረጃ መሰረት ብቻ እኔን የክለባቸው ተጨዋች ሳያደርጉኝ ስለቀሩበት ሁኔታ በአንድ ጎኑ ሳስበው ቢያስከፋኝም፤ በብዙ ጎኑ ሳየው ደግሞ ወደ እነሱ አለማምራቴን በበጎነት እየተመለከትኩት ነው፤ አሁን እኔ በመልካም ጤንነት ላይ የምገኝ ተጨዋች ነኝ፤ ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶም ሆነ በዘንድሮ የውድድር ዘመን የመሰለፍ ዕድሉን ባገኘሁባቸው ጨዋታዎች ላይ የጭቃም የዝናብም ግጥሚያዎችን ማድረግ ችያለው፤ ከሰበታ ከተማ ጋር በሚኖረኝ የቀጣይ ዓመት የተጨዋችነት ቆይታዬም ለቡድኔ እንደ አዲስ ሆኜ በመምጣትና ውጤታማም ግልጋሎትን በማበርከት በእኔ ላይ ትክክለኛ ያልሆኑ ወሬዎችን ያስወሩብኝን ሰዎች አፍ የማሲዝበት የውድድር ዘመን ይሆንልኛል ብዬ ጊዜውን እየጠበቅኩት ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- በሰበታ ከተማ ምን አይነት የውድድር ዘመንን የምታሳልፍ ይመስልሃል?
አዲሱ፡- የሰበታ ከተማ ክለብ ውስጥ በሚኖረኝ የ2012 የውድድር ዘመን ቆይታ የራሴን ችሎታ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ብቃት ላይ ለማስገኘት፤ እንደዚሁም ደግሞ ለጥሩ ስምና ዝና ለማብቃትና የቀድሞ ማንነቴንም ለማሳየት ከፍተኛ ጥረትን እያደረግኩ ነው የምገኘው፤ ከዛ ውጪም ጉዳተኛ ሳልሆን ጉዳተኛ ነው በሚል እየተወራብኝ ያለውንም ነገር በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጥሩ በመጫወት ወሬውን መሰረተ-ቢስ እንደሆነ የማስመሰክርበት የውድድር ዘመን ይሆንልኛል ብዬም እያሰብኩ ነው ያለሁት፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ባሳለፍካቸው ጊዜያቶች ደስተኛ ነህ?
አዲሱ፡- አዎን፤ በአብዛኛዎቹ ዓመታት ጥሩና መልካም የሚባሉ የውድድር ጊዜያቶችን አሳልፌያለው፤ ዘንድሮ ብቻ ግን የተረጋጋ የኳስ ቆይታ ስላልነበረኝና ከሐዋሳ ከተማ ጋር በተደረገውና 5ለ2 በተሸነፍንበት ጨዋታም በቀይ ካርድ መውጣቴን ተከትሎ ከመቐለ 70 እንደርታና ከባህር ዳር ከተማ ጋር የነበሩት ጨዋታዎች ላይ ባለመሰለፌ በቅጣት ላይ የነበርኩ ተጨዋች ሆኜ በጉዳት ነው ለክለቡ ያልተጫወተው በሚል በእኔ ላይ የተሳሳተ መረጃ እንዲወሩ መንገዶች የተከፈቱበትም ጊዜ ነበርና ይሄ ዓመት እኔን ብዙ ነገር ያሳጣኝ ቢሆንም አስተምሮኝ ያለፈም ዓመት ነውና በአዲሱ ዓመት ራሴን በልዩ ብቃት አቅርቤም እመጣለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ምን አተረፍክ?
አዲሱ፡- ብዙ ነገሮችን፤ ኳስ ተጨዋች መሆኔ ከብዙ ሰዎች ጋር አስተዋውቆኛል፤ ጥሩ ጓደኞችን አሰልጣኞችን እና የስራ ባልደረቦችንም እንዳፈራ አድርጎኛልና ኳስን ህይወቴ ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሊግ፡- በወላይታ ዲቻ እንደዚሁም ደግሞ በመከላከያ ክለብ ውስጥ የነበረህ ቆይታ ከብቃት አንፃር ጥሩ እና አበረታች የሚባል ነው፤ ይህንን ተከትሎ ከአድናቂዎችህ የሚደርሱ አስተያየቶች አሉ?
አዲሱ፡- አዎን፤ ብዙዎቹ በሜዳ ላይ ከማሳየው እንቅስቃሴ በመነሳት በርታ፣ በያዝከውም ነገር ቀጥል፤ ወደፊት ደግሞ ትልቅ ቦታ ደርሰህ እንደምናይህ እርግጠኛ ነን በማለት አድናቆታቸውን ይገልፁልኛል፡፡ በምኖርበት ሠፈር ቤላ አካባቢም የሚገኙት አድናቂዎቼም አንተ ለምን ወደ ትልልቅ ክለቦች ገብተህ አትጫወትም በሚልም ለእኔ ያላቸውን ጥሩ ነገርም ስለሚገልፁልኝ ወደፊት ጊዜው ሁሉንም ነገር ሲፈታው ወደ እነዛ ክለቦች ገብቼ መጫወቴ አይቀርም፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በቀይ ካርድ ስንቴ ከሜዳ ወጣህ? በቀይ ስትወጣስ የተፈጠረብህ ስሜት ምን ነበር?
አዲሱ፡- በተጨዋችነት ዘመኔ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣሁት ሁለት ጊዜ ነው፤ አንዱ ከዓመት በፊት ቡድናችን የወራጅ ቀጠናው አካባቢ ሆኖ ሲጫወትና ክለባችን ባልተረጋጋበትና ጫና ውስጥ በነበረበት ሰዓት ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር የነበረን ጨዋታ ላይ ከአዳነ ግርማ ጋር ተጣልተን ሁለታችንም በቀይ ካርድ የወጣንበት ሲሆን አንዱ ደግሞ ዘንድሮ ከሐዋሳ ከተማ ጋር ባደረግነው ጨዋታ 5ለ2 ስንሸነፍ በቀይ የወጣሁበትና ይህንንም ተንተርሶ ቅጣት ተጥሎብኝ ከመቐለ 70 እንደርታና ከባህርዳር ከተማ ጋር በነበሩት ጨዋታዎች ላይ እኔ መሰለፍ የማልችል ተጨዋች ሆኜ እነዛን ጨዋታዎች በጉዳት የተነሳ መጫወት እንዳልቻልኩ እየተነገረ ያለበት ሁኔታ ነበርና ሁለቱንም ጊዜ በቀይ ካርድ መውጣቴ ዛሬ ላይ ይፀፅተኛል፤ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣት አንድን ቡድን ምንያህል እንደሚጎዳው የተመለከትኩበትም ነገር አለና በቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቴ እንደዚህ አይነት ከሜዳ በቀይ ካርድ መውጣትን የማላስተናግድ ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- መከላከያ ከፕሪምየር ሊጉ ወርዷል፤ ምንድን ነበር የተሰማህ?
አዲሱ፡- መከላከያ የሀገሪቱ ትልቅና ስም ያለው ቡድን ነው፤ በእዚህ ቡድን ውስጥ ተጫውቼ ክለቡ ዘንድሮ ወደታችኛው ሊግ መውረዱ እኔን እንደሌሎቹ ተጨዋቾች ሁሉ አንዱ የታሪኩ ተወቃሽ እና ትልቅ ጠባሳም ጥሎብኝ እንዲያልፍ አድርጓልና፤ ይሄ ይቆጨኛል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ አልቻልክም፤ አይቆጭህም?
አዲሱ፡- ሁሌም ነው እንጂ በጣም የሚቆጨኝ፤ በእዚህ የወጣትነት ዕድሜዬ መጫወት ካልቻልኩ መች ልጫወት ነው፤ ጥሩ ብቃቴን ባሳየሁበት ጊዜ ለመመረጥ አልቻልኩም፤ የእኛ ሀገር የብሔራዊ ቡድን የተጨዋቾች መስፈርትም ምን እንደሆነ ስለማይታወቅ ይህ ዕድሉ በተደጋጋሚ ጊዜ አምልጦኛል፤ ስለዚህም በአዲሱ ዓመት ራሴን በጥሩ ሁኔታ በማዘጋጀት ይህንን የመመረጥና ብሎም ደግሞ የመጫወት እድሎችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትን አድርጋለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ መሆን አልቻለም፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን ቢደረግ ጥሩ ነው ትላለህ?
አዲሱ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካም ሆነ በአለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ጥሩና ተከታታይ ውጤትን እንዲያመጣ ከተፈለገ መጀመሪያ መሰራት ባለው ነገር ላይ ልንሰራ ይገባል፤ ሌላው ቋሚ የሆነ ቡድንም ያስፈልገናል፤ እኛ ሃገር ላይ እየሆነ ያለው ግን ይሄ አይደለም፤ ለብሄራዊ ቡድን በተጨዋችነት ትጠራና ወዲያው ትመለሳለህ፡፡ ይሄ አሰራር ሊቀየር ይገባል፡፡ አንድን ተጨዋች ለብሄራዊ ቡድን ከጠራከው በኋላ ከምትመልሰው ለተጨዋቹ ልምድ እያገኘ የሚሄድበትን ነገር ብትፈጥርለት ጥሩ ነው፤ የብሄራዊ ቡድኑ ምርጫም የይድረስ ይድረስ ከሚሆን ብቃትን መነሻ ባደረገ መልኩ ቋሚ ብሄራዊ ቡድን ቢኖረን ለወደፊቱ የኳሱ እድገታችን መልካም ነው የሚመስለኝ፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ኳስን ሲጫወት ሜዳ ላይ ስሜታዊ ሆኖ ስለመጫወቱ…?
አዲሱ፡- አዎን፤ ይሄን ጓደኞቼም በተደጋጋሚ ጊዜ ነግረውኛል፤ ስሜታዊ ነህ፤ አግሬሲቭም ነህ፤ ራስህን ለጉዳት በሚያጋልጥ አጨዋወት ውስጥም ትገባለህ በሚል ለረጅም አመት ልጫወት በምችልበት እንቅስቃሴ ውስጥ እንድመጣም ይነግሩኛልና ይሄንን ወደፊት በስራዬ የማሻሽለው ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- ለእግር ኳስ ተጨዋቾች የሚከፈለው ወርኃዊ ደመወዝ ከ50 ሺ ብር እንዳይበልጥ በሚል በፌዴሬሽኑ ተወስኗል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
አዲሱ፡- የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ኳሳችን ያላደገበት ብዙ ችግሮች እንዳለ እያወቀና በእዛም ላይ መወያየት ሲገባው ዛሬ ላይ የተጨዋቾች ደመወዝ ይህንን ያህል መሆን አለበት በሚል በተጨዋቾች ላይ ከባድ ውሳኔን ፈርዶ ለመስማት መቻሌ በእውነቱ በጣም ነው ያዘንኩት፤ ውሳኔውም የአመራሮቹን ያለመብሰል ችግርና ከኳሱም ጋር ትውውቅ ያላቸው ያህል ስለማይመስለኝ በእዚህ ውሳኔ ተቀራርበን ብንነጋገርበት ጥሩ ነው፡፡
ሊግ፡- ለአንተ የኳስ ህይወት እዚህ ደረጃ መድረስ እነማንን ታመሰግናለህ?
አዲሱ፡- ቤተሰቦቼን ነው በዋናነት የማመሰግነው፤ ከዛ ውጪም ከልጅነቴ አንስቶ አሰልጥነውኝ ያለፉም ባለሙያዎች አሉ፤ ሌላዋ ደግሞ ውዷ ባለቤቴ ሀዊ ተስፋዬም ትገኛለች፤ በተለይ እሷ በእኔ ኳስ ህይወት ውስጥ ሀሳቦችን በማካፈል እና አሁን ወደገባሁበትም ክለብ ሰበታ ከተማ እንዳመራ ያማከረችኝም ስለሆነች ለእዚህ ለእሷና ለሌሎቹም ታላቅ ምስጋና ነው ያለኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
አዲሱ፡- የመከላከያ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ቆይታ በአብዛኛው ጥሩ ጊዜያቶችን ማሳለፌን ተናግሬያለው፤ ዘንድሮ ደግሞ በመጫወትና ባለመጫወት ያጣሁትና የቀሩብኝ ነገሮች ነበሩና በአዲሱ ቡድኔ ሰበታ ከተማ መጪውን ጊዜ ጠንክሬ ሰርቼ በመቅረብ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ቀድሞ የነበረኝን ጥሩ ስም ዳግም ለማስጠራት ከዛ ውጪም በታማኝነት ተጫውቼም አዲሱን ቡድኔ ለውጤት ለማብቃት ዝግጁ ነኝ፡፡