Google search engine

“ጋብቻዬ ያማረ ነበር፤ ቅ/ጊዮርጊስን በውጤት መካስ እፈልጋለሁ”ሀይደር ሸረፋ (ቅ.ጊዮርጊስ)

ደደቢት፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ጅማ ከነማና መቐለ 70 እንደርታ ቅዳሜ ዕለት ለተሞሸረው ሙሽራ ሀይደር ሸረፋ በእግር ኳሱ በምርጥ ብቃቱ ተጫውቶ ያሳለፈባቸውና ከዓመት ዓመትም ችሎታውን እያሻሻለ የመጣባቸው ክለቦች ናቸው።

ሀይደር ሸረፋ  በእነዚህ ክለቦች የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ጥሩ ጊዜያቶችን ቢያሳልፍም በተለይም ደግሞ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ካመራ በኋላ በኳስ ህይወቱ የአንድ ተጨዋች ትልቅ እልሙና ግቡ ከሚባሉት ስኬቶች መካከል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳትና ብሎም ደግሞ በዚሁ ክለብ ውስጥ ሆኖ ባስፃፈው ደማቅ ታሪኩ እስከ ብሄራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድሉን በማግኘቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስደስተው ቢችልም ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ካመራ በኋላ ግን በተለይ ዘንድሮ ቡድናቸው ባስመዘገበው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውጤት በከፍተኛ ሁኔታ ማዘኑን መከፋቱን የቡድኑ  የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሀይደር ሸረፋ በዚህ ሳምንት ውስጥ ከባለቤቱ ሀናን መሀመድ ጋር ከፈፀሙት የጋብቻና የጫጉላ ሽርሽር በኋላ የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አናግሮት ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቶታል።

የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን /የዋልያዎቹ የአማካይ ስፍራ ተጨዋችን ሀይደር ሸረፋን ሊግ ስፖርት በሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ዙሪያም ያናገረችው ሲሆን ስለ ጋብቻ ፕሮግራሙም ምን ይመስል እንደነበርና በሰርጉም ዙሪያ ምን እንደተሰማው ጥያቄ ቀርቦለት በቂ የሆነ ምላሽን ሰጥቷል። ሀይደር በቀጥታ ወደ ጥያቄዎቹ እናምራ፦

ሊግ፦ የትዳሩን ዓለም ተቀላቅለሃል፤ በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ?

ሀይደር፦  እንኳን አብሮ ደስ አለን፤ አመሰግናለው።

ሊግ፦ የጋብቻ ፕሮግራምህ ምን ይመስል ነበር? ሚዜዎችህስ እነማን ነበሩ?

ሀይደር፦  ቅዳሜ ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ/ም ከባለቤቴ ሀናን መሐመድ ጋር የፈፀምኩት የጋብቻ ስነ-ስርዓት በጣም ደስ የሚልና በህይወቴ ተሰምቶኝ የማያውቅም ከፍተኛ ደስታን ያገኘሁበት ነው። ይህ ጋብቻዬ ከመጀመሪያው አንስቶ እስኪጠናቀቅ ድረስም በአማረና በደመቀ መልኩ መካሄድ መቻሉም አስደስቶኛል። ከዚህ የሰርግ ስነ-ስርዓት በኋላም ለጫጉላ ሽርሽሩ ወደ ውቢቷ እና አረንጋዴ ወደ ሆነችው ሀገር  አርባምንጭ ከተማ በመጓዝና በጣሙን የሚወደድላትን ነፋሻማ አየሯን በመቀበል ጭምር በጣም ጥሩ ጊዜንም ለማሳለፍ ችለናልና ይሄ የሰርጌ ክንውን ሁኔታ ሁልጊዜም ከአህምሮዬ የማይወጣ ነው።

ስለ ሚዜዎቼ ሁኔታ በተመለከተ እንደ እኛ እምነት በበርካታ አብሮ አደግ ጓደኞቼና አንዳንዶቹም አብሬያቸው ኳስ በምጫወት ጓደኞቼ በመታጀብ ጭምርም  ነው የሰርግ ፕሮግራሜን ያከናወንኩት።

ሊግ፦ የሰርጉ ፕሮግራም የትና በምን መልኩስ ነበር የተከናወነው?

ሀይደር፦ በእኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባህል መሰረት ማለትም የኒካ ፕሮግራሜ የተካሄደው ባልዬው ወደ ሴቷ ቤት በመሄድ ነውና በባለቤቴ ቤት ነበር ሰርጌ ሊከናወን  የቻለው።

ሊግ፦ እስኪ ጋብቻ የፈፀምክላትን ባለቤትህን አስተዋውቀን? እሷ እንዴትስ ትገለፃለች?

ሀይደር፦ ባለቤቴ ሀናን መሀመድ ትባላለች። የአንድ  አካባቢ ልጆችና አስቀድመንም የምንተዋወቅ ጓደኛማማቾችም ነን። እሷን በተመለከተ ከእኔ አጠቃላይ ህይወትም ሆነ የኳሱ ህይወትም  ጀርባ ብዙ ነገሮችን እያደረገችልኝ ያለች አስተዋይና ቆንጅዬ ሚስቴም ስለሆነች በዛ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የአባቴና የእናቴ ዱሀም እሷን ከዓላም ስላስገኘልኝ ለፈጣሪዬ ዓላም ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለው።

ሊግ፦ አንተ ኳስ ተጨዋች ነህ፤ እሷስ ኳስ ላይ እንዴት ነች?

ሀይደር፦ ስለ ኳስ የምታውቅልህ ነገር የለም፤ አይታም አታውቅም። ምንም አይነት እውቀቱም የላትም። ስታዲየምም ገብታ አታውቅም። ብቻ በሀይላይት ደረጃ ስለ እኔ ከምትሰማውና ከምትመለከተው ነገር በመነሳት   ኳስ ተጨዋችነቴን ብቻ በመረዳት በጥሎ ማለፍም ይሁን በአንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ ውጤት አጥተን በምከፋ ሰዓት እንዲህ አትሁን በርታ ነገም ሌላ ቀን ነው ታሸንፋላችሁ በሚል የምታፅናናኝ ጊዜያቶችም አሉና በዛ ደረጃ የምትገለፅ ባለቤት ነው ያለኝ።

ሊግ፦ አሁን ትዳሩን ገባህበት፤ ጣህሙ እንዴት ይገለፃል?

ሀይደር፦ የእውነት ገና ጀማሪ ተጣማሪ ብሆንም ትዳር ደስ የሚል ነገር ነው። ከወዲሁ ጣፋጭ ሁኔታዎችንም እየተመለከትኩበት ነው። በተለይም ደግሞ ስፖርተኛ ስትሆን የእግር ኳስ ጨዋታን ከክልል ክልል እየተዘዋወርክ የምታደርገው ጨዋታም ስለሆነና ከዛሬ ነገም ብዙ ነገሮችንም የምታውቅበት ሁኔታ ስላለ የትዳርን ጥሩነት በመረዳት ላይ ነው የምገኘው።

ሊግ፦ ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ እየተዘጋጀ ከሚገኘው የብሔራዊ ቡድናችን ጋር የነበረህን ልምምድ ትተህ ነው ጋብቻህን ያደረግከው ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?

ሀይደር፦  ይሄ የሰርግ ፕሮግራሜ ቀን የተቆረጠው የብሄራዊ ቡድን የተጨዋቾች ምርጫ ይፋ ከመደረጉ በፊት ነው። ይኸው ጥሪ ሲደረግልኝም ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር መልካም ግንኙነቱ ስላለኝ ይህን ሁኔታዬን አሳውቄአለሁ። እሱም ከጋና ጋር ለሚኖረን ጨዋታ ብዙም ጊዜ እንደሌለ ነግሮኝና እኔም ካለኝ ፕሮግራም  ጋርም ተነስቶ በስምምነት ይሄ ጨዋታ እንዲያልፈኝም አድርጓል።

ሊግ፦ በቢኒ ትሬዲንግ የጀመረው የኳስ ህይወትህ እስከ ቅ/ጊዮርጊስና እስከ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተጨዋችነት ደረጃ ዘልቆ ተጉዟል፤ በዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?

ሀይደር፦ የእውነት ነው፤ ኳስን መጫወት የጀመርኩት የአሁኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በሆኑትና ያኔም የ10 ዓመት ልጅ በነበርኩበት ሰዓት እሳቸው አቋቁመውት በነበሩት የቢኒ ትሬዲንግ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ነው።  ይህ የፕሮጀክት ቡድንም እኔን ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገልኝም ነው። የፕሮጀክቱ  ባለቤት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ያኔ የእኛን ስሜት በጠበቀ መልኩ ከኳሱ ውጪ ትምህርታችንንም በጥሩ ሁኔታ እንድንከታተልም ያደርገን ነበርና የእሱ ውለታ የማይረሳ ነው። በዚሁ ቡድን ቆይታዬ ሌላው ልጠቅሰው የምፈልገው ሰው አሰልጣኛችንን አፈወርቅ ጉርሙን ነው። እሱ እኛን አሰባስቦ ከአቶ ዮሴፍ ጋር ብዙ ስራን ሰርቷል። በጥሩ ሁኔታም ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች በሆናቸው የህፃናት ቡድን ውስጥ አሰልጥኖኝ አልፏልና አቶ ዮሴፍንና አቶ አፈወርቅን ከዓላ በታች ሁሌም የማመሰግናቸው ነው፤ ያ ምርጥ ጊዜም የማይረሳኝ ነው።

ሊግ፦ አሁን ላይ ለቅ/ጊዮርጊስ እየተጫወትክ ይገኛል፤ በኳሱ በመጣህበት መንገድና  ባሳለፍካቸው የኳስ ህይወቶችህ ደስተኛ ነህ?

ሀይደር፦  አዎን! በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ኳስን ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ  በቢኒ-ትሬዲንግ  ፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ስጫወት ለጥሩ ደረጃ እንደምበቃ አውቅም ነበርና ከዛ በኋላም ወደ ክለብ ተጨዋችነት ከተሻገርኩ በኋላም ከዓመት ዓመት በችሎታዬ ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችንና ለውጦችን እየተመለከትኩበት ስለሆነም ያ አስደስቶኛል።

በዚሁ የኳሱ ቆይታዬ ሌላው በጣም ያስደሰተኝ ጉዳይ ደግሞ በመቐለ 70 እንደርታ ቡድን ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት ማንኛውም የእግር ኳስ ተጨዋች በጨዋታ ዘመኑ የሚመኘውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከዚሁ ቡድን ጋር ላነሳ ስለቻልኩና ለወደፊቱም የምናገረው ታሪክ ስላለኝም ይህ  ሌላው ያስደሰተኝ ጉዳይ ነው።

ሊግ፦ ሀይደርን በኳስ ህይወቱ ምን አስከፍቶታል?

ሀይደር፦  እኔን ያስከፋኝ ያሳዘነኝም በኳስ ህይወቴ ልክ ሰሞኑን እንደፈፀምኩት የአማረ የጋብቻ ስነ-ስርዓት ሁሉ  ጥሩ ጊዜን አሳልፌ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ከመጣው በኋላ ግን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አለመቻሌ ነው። አምና እንኳን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ሊጉ በመቋረጡ ምንም አላልኩም ነበር። ዘንድሮ ግን ይህን የሊግ ዋንጫ በስኬታማነቱ ከሚታወቀውና ድልን ከለመደው ከዚህ ቡድን ጋር  የሻምፒዮናነትን ክብርን መጎናፀፍ ፈልጌ ነበርና ያ ሊሳካልኝ አልቻለም። ይህ የሻምፒዮናነት ድልን ከዚሁ ቡድን  ጋር ማግኘትን እፈልጋለው ያኔም አሁን  በኳሱ  ያለኝ  የደስታ ጊዜ ሙሉ  ይሆንልኛልም።

ሊግ፦ የቅ/ጊዮርጊስ ቆይታህ እንደ መቐለ 70 እንደርታ በስኬት የታጀበ አልነበረምና የውጤት ማጣት ሚስጥራችሁ ምን ነበር?

ሀይደር፡- በቅ/ጊዮርጊስ ያለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታዬ እንደ መቐለ 70 እንደርታ ተጨዋችነቴ በነበሩት የውድድር ጊዜያቶች ከስኬት ጋር ልዛመድ ያልቻልኩበት ዋናው ምክንያት በመጀመሪያው ዓመት ላይ ኮቪድ ሊጉን ስላቋረጠው በዛ ዙሪያ ብዙም ነገርን ባልል እመርጣለው፤ የዘንድሮ የውድድር ቆይታችን ላይ ግን ቡድናችን ውጤትን ሊያጣ የቻለበት ዋናው ምክንያት ብዬ የማስበው ቅ/ጊዮርጊስ የሀገሪቱ ትልቅና ከዚህ ቀደም ደግሞ ብዙ ድሎችንም የተጎናፀፈ ክለብ በመሆኑ ከዛም ባሻገር በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የሚጫወት ቡድን ስለሆነም ወደ ክለቡ የሚመጡት ተጨዋቾች ላይ በእዚህ ቡድን ውስጥ ከሚፈለገው ውጤታማነት በመነሳት ጫናን የመሸከምና የመቋቋም ችግሩ ስላለባቸው ይህ ሁኔታ ነው ውጤት እንዳይቀናን እያደረገ ያለው፤ ስለዚህም ቅ/ጊዮርጊስ ላጣው ውጤት ጥፋተኞቹ የእኛ ተጨዋቾቹ ችግርም ነውና በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የሀዘን ስሜት ተሰምቶኛል፡፡

ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ቆይታህ ባለመድከው መልኩ ሀትሪክ ለመስራት ችለሃል፤ ከዚህ በመነሳት ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ?

ሀይደር፡- የእውነት  ነው በተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ የእኔ አብዛኛው ስራ የነበረው ሜዳ አካልዬ በመጫወት ከባላጋር ተጨዋቾች ላይ ኳሶችን ነጥቆ መጫወትና ለአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾችም የተመቻቹ ኳሶችን ማቀበል መቻል ነበር፤ በዛ መልኩ እየተጫወትኩ አልፎ አልፎ አንድ አንድ ጎሎችንም ያስቆጠርኩበት ጊዜያቶች ነበሩ፤ ያም ሆኖ ግን በእዚህ ዓመት የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ የመጨረሻ ጨዋታችንን ከወልቂጤ ከተማ ጋር ባደረግንበትና በአሸነፍንበት ጨዋታ ላይ የሆልዲንግ ሚናው ተሰጥቶኝ ሀትሪክ በመስራት ሶስት ግቦችን ለቡድኔ ለማስቆጠር በመቻሌ በራሴ ላይ ከፍተኛ አግራሞትን ነው የፈጠረብኝ፤ ጎሎችን ማስቆጠር መቻልም ምን ያህል ከፍተኛ የደስታ ስሜትን እንደሚፈጥርም የተረዳሁበት ሁኔታም ስለነበር አጋጣሚዎቹ በቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቴም ሌሎችን ተጨማሪ ጎሎችን እንዳስቆጥር ከፍተኛ ተነሳሽነትንም የሚፈጥርልኝ ነው፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካጣ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጪው ዓመት ተሳትፎ ይህን ድል ክለባችሁ ይጎናፀፋል? ወይንስ ለአምስተኛ ዓመታት ድሉን ያጣል?

ሀይደር፡- አሁንማ በፍፁም የውጤት ማጣቱ ሊደገም አይገባም፤ ቅ/ጊዮርጊስ እኮ ድል የለመደ ቡድን ነው፤ እስካሁን ያጣው ውጤትም ያስቆጫል፤ ከዋንጫ ውጪ የሶስተኛና የሁለተኛ ደረጃ ውጤት እንኳን ለክለቡ ፈፅሞ አይገባውምም፤ ባለፉት ተከታታይ ዓመታቶች ክለባችን ከስኬት ርቋል፤ በዚህ ደጋፊዎቹ፣ አመራሮቹና የቡድኑ አጠቃላይ አባላቶችም በጣሙን አዝነዋል፤ እኔ ወደ ቡድኑ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ ያለውን የውጤት ማጣት ስመለከት በራሱ ይህ ክለብ አሁን በሚገኝበት ደረጃ ፈፅሞ ሊቀመጥ የማይገባው ቡድን እንደሆነ ስላወቅኩኝም የመጪው ዓመት ላይ ለሚኖረን የውድድር ተሳትፎ ራሳችንን በሚገባ ፈትሸን በዝግጅት ወቅትም በጣም ጠንክረን ሰርተን መጥተን ክለቡ ወደሚታወቅበት የውጤታማነት ታሪኩ ልንመልሰው ይገባል፤ ደግሞም ከቀጣዩ ዓመታቶች ጀምሮም ይህን እውን እናደርገዋለን፡፡

ሊግ፡- በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ሀገራችን ከአስተናጋጇ ሀገር ካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ተደልድላለች፤ የእዚህን ዕጣ መውጣት ስትመለከትና ስትሰማ ምን አልክ?

ሀይደር፡- የዕጣ መውጣቱን ስነ-ስርዓት እንደተመለከትኩት ምድባችን ቀላል እንዳልሆነና ከአምስት ወር በኋላ ለሚካሄደው ውድድርም ከወዲሁ በጣም ጠንክረን መምጣት እንዳለብን ነው የተገነዘብኩት፤ በአሁን ሰዓት ቀላል የሚባል ምድብ የለም፤ አይደለም እኛ ምድብ ያሉት እነ ኬንያን የመሳሰሉ ቡድኖች ራሱ ከእኛ የሚሻሉ ናቸውና አዘጋጇን ሀገር ጨምሮ ከሎሎቹ የምድብ ተወዳዳሪዎቻችን ጋር በሚኖረን ጨዋታ ቡድናችን የራሱ የሆነና ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ሊጠቅመው የቻለም የአጨዋወት ሀሳብ ያለው በመሆኑ አሁን ላይ ከያዛቸው ወጣት ተጨዋቾችና ልምድ ካካበቱም ተጨዋቾች ጋር በማጣመር ጥሩ ውጤት ለማምጣት መታገል ነው ያለበት፤ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድላችንን የምናከብደውም የምናቀለውም እኛ ተጨዋቾች ነን፤ የያዝነውን አጨዋወት በማስቀጠል ጥሩ ውጤትም ልናመጣ ይገባል፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳስ ህይወትህ ቀጣይነት ከወዲሁ ምን ምን ነገሮችን ለማከናወን አቅደካል?

ሀይደር፡- አሁን ላይ የጫጉላ ሽርሽር ቆይታዬን ካጠናቀቅኩኝ በኋላ ቢሾፍቱ ወደሚገኘው የቡድናችን ልምምድ ለመቀላቀል ወደዛ ልጓዝ ነው፤ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ተከታታይ የውጤት ስኬቶችን ማስፃፍ እፈልጋለው፤ በዚህ ቡድን ያለኝ ቆይታም እንደ ሰርጌ ያማረና በውጤት የታጀበ እንዲሆንም እፈልጋለውና ይሄ ዋናው እልሜ ነው፤ ከዚህ ውጪ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ላይም ዋልያዎቹ ለሚያስመዘግቡት ውጤት የቡድኑ አንድ አካል ተመራጭ በመሆን የሀገሬ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብም ማድረግ እፈልጋለው፤ በኳሱ ከሀገር በመውጣት የመጫወት ራዕይም አለኝ፡፡

ሊግ፡- በእግር ኳሱ የተከፋክበት ጊዜ ተብለህ ብትጠየቅ ምላሽህ ምንድን ነው የሚሆነው?

ሀይደር፡- ብዙዎቹ የተደሰትኩባቸው ጊዜያቶች ቢሆኑም ሽንፈት ያስከፋኛል፤ በተለይም ደግሞ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ከመጣው በኋላ ክለቡ ሲሸነፍና ይሄን ቡድን ለሻምፒዮናነት ሳላበቃ ስለቀረው ቅር ብሎኛልና ቡድኑን ከአጋር ጓደኞቼ ጋር በውጤት የምክስበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡

ሊግ፡- አንድ ነገርን በልና ቃለ-ምልልሱን እናጠቃል?

ሀይደር፡- በእግር ኳሱ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ብዙ ሰዎች ከጀርባዬ አሉ፤ ሁሉንም ልጥራ ካልኩም ቦታም አይበቃክምና ከጎኔ የሆናችሁትን ሁሉ አላምዱሉላሂ ከልቤ ላመሰግናችሁ እወዳለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P