Google search engine

“ወደ አፍሪካ ዋንጫውም የማናልፍበት ምንም ምክንያት የለም” “ሩዋንዳን በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት አሸንፈን ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን የማላውቀው አይነት የደስታ ስሜትን ፈጥሮብኛል” ጋቶች ፓኖም

“ወደ አፍሪካ ዋንጫውም የማናልፍበት ምንም ምክንያት የለም”

“ሩዋንዳን በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት አሸንፈን ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን የማላውቀው አይነት የደስታ ስሜትን ፈጥሮብኛል”

ጋቶች ፓኖም

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ ሩዋንዳን በማሸነፍ  በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ችሏል።

ዋልያዎቹ  ከሩዋንዳ ጋር ባደረጉት ሁለት ጨዋታዎች የመጀመሪያውን በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ላይ በማድረግ ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን ቀጣዩን ጨዋታ ደግሞ ወደ ሩዋንዳ በመጓዝ ዳዋ ሆቴሳ ባስቆጠረው የቅጣት ምት ግብ ለሶስተኛ ጊዜ ሊያልፍ በቅቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ቻን አፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን አስመልክቶና ስለ ቀጣይ ጊዜ  የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎአቸው የቡድኑን ተጨዋች ዳዋ ሆቴሳን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አነጋግሮት ተከታዩን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል።

ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግናለን?

ጋቶች፦ እናንተም  አክብራችሁ  የጋዜጣችሁ እንግዳ አድርጋችሁኝ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናችኋለሁ።

ሊግ፦ ሩዋንዳን በማሸነፍ ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ችላችኋል፤ የደስታ ስሜቱ ምን ይመስል ነበር?

ጋቶች፦ በእዛን ዕለት ጨዋታ ቡድናችን  ለአልጄሪያው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የተሰማኝ የደስታ ስሜት ከፍ ያለ ነበር።  ምክንያቱም ይህ ውድድር የአፍሪካ ታላላቅ ሀገራት የሚሳተፉበት እና እኛ ደግሞ በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ የምንሳተፍበት  በመሆኑም  የደስታው መጠን እጥፍ ድርብም አይነት  ስሜት ነው የሆነልን።

ሊግ፦ ከሩዋንዳ ጋር ስትጫወቱ የመጀመሪያውን ጨዋታ አቻ መለያየታችሁን ተከትሎ የሁለተኛው ግጥሚያ ከባድ ሊሆንባችሁ እንደሚችል ተገምቶ ነበር፤ እናንተ ግን ድሉን አሳካችሁት?

ጋቶች፦ ግጥሚያው ከባድ ሊሆንብን  እንደሚችልማ መጀመሪያውኑም እናውቅ ነበር። ያም ሆኖ ግን  ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ እንደምናልፍም እርግጠኞች ነበርንና ያንን ነው ለማሳካት የቻልነው። ጠንካራ በነበረው ግጥሚያችንም  ስላለፍን በጣምም ነው ደስ ያለን።

ሊግ፦ ወደ ቻን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፋችሁ ዋናው ጥንካሬያችሁ የነበረው ምንድን ነው ?

ጋቶች፦ ያለን የቡድን መንፈስ ጠንካራ መሆንና ከእዛም በተጨማሪ ደግሞ  እንደ ቡድን  በጋራ ለመንቀሳቀስ መቻላችን ሌላው ደግሞ በአራቱ ግጥሚያዎቻችን ላይ በመከላከሉ ረገድ  ጥሩ ስለሆንና  ጎል ያልተቆጠረብንም በመሆኑና  ስድስት ግብም  ማስቆጠር  በመቻላችን  ያ ለውጤታማነታችን ረድቶናል።

ሊግ፦ ለቻን  አፍሪካ ዋንጫ ወደ አልጄሪያ  ስታመሩ ምን ውጤት ከዋልያዎቹ ይጠበቅ?

ጋቶች፦ ከእዚህ ቀደም በነበረን የሁለት ጊዜው የውድድር ተሳትፎ ከምድባችን ማለፍ አልቻልንም ነበር፤ አሁን ግን ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍ ዋናው እልማችን ነው፤ ያንን እንደምናሳካውም  እርግጠኛ ነኝ።

ሊግ፦ በቻን ላይ የነበረው የዋልያዎቹ ስብስብ በአንተ አንደበት እንዴት እና በምን መልኩ ይገለፃል?

ጋቶች፦ ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ እና  ኳስን መስርቶ መጫወት የሚችል ጥሩ ቡድን ነው ያለን።  ጥሩም ቡድን ስላለን  የውድድሩ ጊዜ ሲቃረብ ስኬታማ ውጤት እናስመዘግባለን።

ሊግ፦  ከቻን  የአፍሪካ ዋንጫ  ተሳትፎ ውጪ የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያም አለን፤ ከእነዛ ቀጣይ ውድድሮችስ ምን ውጤትን ትጠብቃለህ?

ጋቶች፦ ዋናው ነገር ጠንክሮ መስራት ነው፤  እዛ ላይ በደምብ አተኩረህ ከሰራ ለትልቅ የውድድር ደረጃ ላይ የማትደርስበት ምንም ምክንያት የለም። እስካሁን በነበሩት ሁለት ግጥሚያዎች ሁላችንም ቡድኖች ሶስት ነጥብ አለን። የራሳችንን ዕድል በራሳችን በመወሰን ስለምንጫወት የማናልፍበት ምክንያት የለም።

ሊግ፦  በአፍሪካ ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ  ግብፅን ለማሸነፍ ችለን ነበር። ከእዛ ቀደም በነበሩት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ እነሱ በተደጋጋሚ ጊዜ ያሸንፉን ነበርና የአሁኑ ድል ከምን የመጣ ነው?

ጋቶች፦ እንደ ተጨዋች ይህን የምገልፀው ኳሳችን በጣም እየተቀየረ  መምጣቱን ነው።  አሁን ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ የምታልፈውም ሆነ እንደ ግብፅ የመሳሰሉትን ሀገራት የምታሸንፈው በቀድሞ ስምህና ዝና ሳይሆን በወቅታዊ አቋምህ ነው።  ግብፅን ያሸነፍነው የተሻልን ስለነበርን ነው።   እኛም በእዚሁ ወቅታዊ አቋማችን  ነው  ስኬታማ እየሆንን ያለነው።

ሊግ፦ ዋልያዎቹ ላይ ከዚህ ቀደም  የነበረውን አቋምና አሁን ላይ ያለውን አቋም እንዴት ተመለከትከው?

ጋቶች፦ በፊት ላይ ከሜዳችን ውጪ ድክመት ነበረብን። በተለይ በስነ-ልቦናው ረገድ  አሁን ላይ ደግሞ በእዛ በኩል ጥሩ በመሆናችን ሁለቱንም ጨዋታዎቻችን ከሜዳችን ውጪ በመጫወት ጥሩ ውጤትን አስመዝግበናልና በእግር ኳሳችን ላይ ይሄ ትልቅ ለውጥ ይመስለኛል።

ሊግ፦  በእግር ኳሱ ላይ  ባለህ አቋም ራስህን የት ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ትፈልጋለህ?

ጋቶች፦ ዋናው ነገር ሁሌም እንደ ቡድንም እንደ ግልም ጠንክሬ ልምምዴን ስለምሰራ ያ ነው ለጥሩ ደረጃ እኔን የሚያደርሰኝ።

ሊግ፦ የሩዋንዳ አቻችሁን ስትረቱ  በሜዳ ላይ የነበረው ድባብ ምን ይመስል ነበር?

ጋቶች፦ በጣም ነበር ደስ የሚለው። በተለይም ኢትዮጵያኖች የሰጡን ድጋፍ የሚገርም ነበር። ሩዋንዳን ለማሸነፍ እንደምንችልም ከነበረው ድባብ አኳያ እናውቅም ነበር።

 

ሊግ፦  የአዲስ ዓመት ሊገባ ተቃርቧል፤  ይህን በምን መልኩ ልትቀበል ተዘጋጅተሃል?

ጋቶች፦ ሁሌም አዲስ ዓመት ዘመን ተሻጋሪ ነው። በወቅቱ የነበረው ጥሩም መጥፎም ነገር አልፎም ይሄዳል። አዲስ አመት ደግሞ አዲስ ተስፋንም እንድትሰንቅ ያደርግሃልና ጥሩ ነገሮችን ሁሌ ትጠብቃለህ።

ሊግ፦  በመጨረሻ ?

ጋቶች፦ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ2015 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ በዓሉ የፍቅር፣ የሰላም እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P