በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለድሬዳዋ ከተማ በመጫወት ላይ የሚገኘው ጋዲሳ መብራቴ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአቸው የሚጫወቱት ከሊጉ ላለመውረድ ሳይሆን ለደረጃ ተፎካካሪነት እንደሆነ ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር እንደሆነ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ታሪክ በጥሩ የጨዋታ ብቃቱ የሚታወቀው ጋዲሳ መብራቴ ስለ ክለባቸው፣ ስለ ራሱና መሰል በሆኑ ጥያቄዎች ዙሪያ ከጋዜጣችን ጋር ያደረገው ቆይታም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት።
ከውድድር ስፍራ ርቆ ዳግም ስለመመለሱና ስለተሰማው ስሜት
“ከሜዳ የራቅኩበት የተለየ ምክንያት የለውም፤ ላለመሰለፌም የአሰልጣኝ ውሳኔ ስለሆነ ተቀብዬዋለሁ። ሌላው ደግሞ ጉዳትም ነበረብኝና ወደ ሜዳ ዳግም በመመለስ የመጨረሻዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ለመጫወት ችያለሁ። ከእዚህ በኋላም በሙሉ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ ዕድሉ ይኖረኛል”።
ስለ 13 ሳምንታት የሊጉ ቆይታችሁ
“ባህርዳር ላይ ቡድናችን ጥሩ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ቀድሞ ጎል እየተቆጠረብን ውጤትን ያጣንበት ጊዜ ነበር። ከእዛ መልስ ደግሞ ወደ ሜዳችን ድሬዳዋ ከተማ ባመራንበት ጊዜ ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴን አሳይተን በሜዳችንና በደጋፊያችን ፊት በመጫወት ውጤትን ይዘን ልንወጣ ችለናል”።
የድሬዳዋ ከተማ ጠንካራና ክፍተት ጎኑ
“ጥንካሬያችን አንድነታችን እና ህብረታችን ነው፤ በልምምድ ስፍራና በካምፕ አካባቢ ያለው የቡድን መንፈስም ጥሩ መሆኑም ቡድናችንን ከሌላው ጊዜ ለየት እንዲል አድርጎታል። በክፍተት ጎን ደረጃ የሚገለፀው ደግሞ ቀድሞ ጎል የሚገባብን ነገር ነው። ጠንካራ ጎናችን ግን በጣም ይበዛል”።
የአምናው ቡድን ላለመውረድ ስለመጫወቱና የዘንድሮ ክለባቸውን በተመለከተ
“አምና ብዙ ክፍተቶች ነበሩብን፤ የተለያዪ አሰልጣኞችም ተቀያይረውብናል። እነዚህ ባለሙያዎችም የየራሳቸው የጨዋታ ታክቲክ ያላቸው ስለሆኑና ተጨዋቾቹንም ለመላመድ የተቸገሩበት ሁኔታ ስለነበር የመፈረካከስ ሁኔታ አጋጥሞናል። ሌላው ጉዳትም ነበር። ዘንድሮ ግን ሁሉም ተጨዋች ጠንክሮ በመስራት ላይ ያለና ተስፋ የሚጣልባቸው ልጆች ስላሉ ከእዛ ውጪም አሰልጣኙ ወጣትና ጥሩ የማሰራት ብቃት ያለው ስለሆነም የዘንድሮ ቡድናችን አሁን ላይ ላለመውረድ ስለ መጫወት የሚያስብ ተጨዋች ማንም የለም”።
የእዚህ ዓመት የክለባቸው እቅድ
“ማንኛውም ቡድን የሚዘጋጀው ከእዛ ውጪም ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን የሚሰበስበው ዋንጫ ለማንሳት ነው። ያ ባይሆን እንኳን በደረጃው ሰንጠረዥ እስከ አራትና አምስተኛ ደረጃ ሆነን ሊጉን ለመፈፀም እየተዘጋጀንም ይገኛል”።
እስካሁን ካደረጉት ፍልሚያ ያስቆጫቸው ጨዋታና የተደሰቱበት ግጥሚያ
“ነጥብ የጣልንባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ያስቆጫሉ፤ በተለይም ደግሞ በደረጃው ሰንጠረዥ ከላይ እንድንቀ
መጥ በሚያስችለን ከወላይታ ድቻ ጋርና ከአዳማ ከተማ ጋር በነበሩን ጨዋታዎች ላይ ነጥብ የጣልንባቸው ያስቆጩናል፤ በውድድሩ ላይ ቡድናችን የተደሰተባቸው ግጥሚያዎች ደግሞ ያሸነፍንባቸው ናቸው። በተለይም ከመድንና ከመብራት ሀይል ጋር ስንጫወት እየተመራን ድል ያደረግንበት ስለሆኑና በሜዳችን ስንጫወት ደግሞ ግጥሚያውን የምንረታበት ሁኔታ የተለየም ስለሆነ ስሜቱ በተለየ መልኩ ይገለፃል። “።
ስለ አሰልጣኛቸው ዮርዳኖስ አባይ
“እሱ ወጣት አሰልጣኝ ነው፤ የሚሰጣቸው ልምምዶችም ጥሩ ናቸው። እኛ በአግባቡ ልምምዱንም እየሰራን ይገኛል። በስልጠናውም ሊለውእኔጠን የተዘጋጀ ባለሙያ ስለሆነና እስካሁን የመጣንበት መንገድም ጥሩ ስለሆነ አሰልጣኛችን ወደፊት ትልቅ ባለሙያ እንደሚሆን እምነታችን ነው”።
በሊጉ የውድድር ተሳትፎ ጥሩ ችሎታ የነበረ ተጨዋች ስለ መሆንህንና ያን ስም ስለማጣትህ
“በእኔ የኳስ ህይወት ዙሪያ ብዙ ነገሮች ተነስተዋል። በተለይም ደግሞ ከዲስፕሊን ጋር በተያያዘና በሌላ ነገሮችም ዙሪያ የተለየ ስም እንዲሰጥብህ ስለሚያደርግና ትኩረትም እንዲደረግብህ ስለሚያስችል ኳሱ ላይ ተፅህኖ ይፈጥርብሃል። አሁን ላይ ግን ይህ ሁኔታ ከእኔ ውስጥ ወጥቷል። በእዚህ ጉዳይ ዙሪያም ብዙዎች ምስክርነታቸውን ከመስጠት ባሻገር ባለኝ ነባራዊ ሁኔታም ደስተኞች ናቸው። ከእዛ ውጪም በጥሩ ጤንነት፣ ብቃትና በደስታ ላይ የምገኝ ተጨዋች ስለሆንኩም ከእዚህ በኋላ ራሴን ከፍ ባለ ደረጃ ላይ በማስቀመጥ የተሻለውን ድሬዳዋ ከተማን አልፎ ተርፎም ሀገርን የሚጠቅመውን የቀድሞውን ጥሩ ተጨዋች ጋዲሳን እንደማሳይ እርግጠኛ ነኝ”።
ባሳለፈው የኳስ ህይወት የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶት ያውቅ እንደሆነ
“አንዳንዴ በማወቅም ባለማወቅም አላስፈላጊ ነገሮች ውስጥ መግባት ስላለና ብዙ ህይወቶችንም ስላየው እዛ ነገር ውስጥ ባልገባው የምትልበት ጊዜ አለ። በተለይም ደግሞ ካለኝ ጥሩ የእግር ኳሱ ስም አኳያም በዲስፕሊን ስሜ ባይነሳ የምልበት ጊዜም አለና እንዲህ ያሉ ነገሮች ያስቆጩኛል። አሁን ላይ ግን የቡድኔን አሰልጣኝ ጨምሮ የቡድን አጋሮቼ አልፎ ተርፎም ብዙ ሰዎች በተስተካከለ መንገድ እንድጓዝ ምክራዊ ምስክርነታቸውንም እየሰጡን ስለሆኑና ስሜቴም የተነካበት ሁኔታ ስላለና አሁን ላይ ልምምዴን በጥሩ ሁኔታ እየሰራሁ ስለሆንኩም በቀጣይነት ራሴን በጥሩ መንገድ ላይ ታገኙኛላችሁ”።
በኳስ ህይወትህ የይቆጨኛል ስሜት ተሰምቶ ያውቅ እንደሆነ
“በጣም የሚቆጨኝ ባሳለፍነው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎአችን ላይ መገኘት እየተገባኝ ያን ዕድል በማጣቴ ነው። ቡድኑ ለውድድሩ ሲያልፍ ነበርኩበት ግን በዲስፕሊን በሚል ምክንያት ለውድድሩ ሳልሄድ ቀርቻለሁ። ያም ሆኖ ግን በቀጣይነት ይሄን ዕድል ዳግም እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ”።
ስለ ዘንድሮ የሊጉ ፉክክር
“በጣም አሪፍ ነው፤ የአንደኛው ዙር በእዚህ መልኩ ሄዶም አያውቅም። ዲ ኤስ ቲ ቪ ከመጣ በኋላም ክለቦች በተቀራረበ ነጥብ ላይም ነው የሚገኙት። ከአምናው የተሻለ ነገርን እየተመለከትንም ነው። ማን ዋንጫ እንደሚያነሳና ከሊጉ እንደሚወርድሞ አታውቅምና ሊጉ ጥሩ ውድድርን እያስመለከተን ነው የሚገኘው”።
ስለ ኳታሩ ዓለም ዋንጫ
“በውድድሩ ላይ የብራዚል ደጋፊ ነበርኩ። እነሱ ሲወድቁ የተሰማኝ ጥሩ ያልሆነ ስሜት ስለነበር ጨዋታዎችን መከታተሉ ላይ ብዙ አልነበርኩም። ያም ሆኖ ግን አርጀንቲና ሳትሆን ሊዮኔል ሜሲ የዓለም ዋንጫን እንድታነሳ እፈልግ ስለነበርኩ በእዛ ደስ ብሎኛል”።
ስላለፈው የገና በዓልና ስለ መጪው የጥምቀት በዓል
“የገና በዓልን ለሁለት ቀን እረፍት ተሰጥቶን ስለነበር ወደ ቤተሰብ ጋር ሩቅ በመሆኑ ባንሄድም በጥሩ ሁኔታ ነው ያሳለፍነው። በመጪው የጥምቀት በዓል ላይ ደግሞ በስራ ጭምር ጊዜውን በጥሩ ሁኔታ እንደምናሳልፍ እርግጠኛ ነኝ”።
በመጨረሻ
“መጪው የጥምቀት በዓል ነው፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ። ከእዛ ውጪ ደግሞ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በተጀመረው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ለሆኑት ተጨዋቾቻችንና የኮቺንግ ስታፍ አባላቶች መልካም ውጤት እንዲገጥማቸው እመኛለሁ”።