Google search engine

“ጎል ባስቆጠርኩበት የቅ/ጊዮርጊሱ ጨዋታ በቋሚ ተሰላፊነት ያልተጫወትኩት በምግብ መመረዝ ታምሜ ስለነበር ነው”
ዳዋ ሆጤሳ /ሀዲያ ሆሳዕና/

በመሸሻ ወልዴ


በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛው ሳምንት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ወደ ሜዳ ተቀይሮ በገባው በዳዋ ሆጤሳ የቅጣት ምት ጎል 1-0 ለመምራት ቢችልም የሀዲያው የተከላካይ መስመር ተጨዋች ቴዎድሮስ በቀለ ለግብ ጠባቂያቸው በግንባሩ ለማቀበል ወደ ኋላ የላከውን ኳስ የቅ/ጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛ አግኝቷት እና ኳሷን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሯት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡


ሀዲያ ሆሳዕና ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታውን በአቻ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ ስለ ሁለቱ ፍልሚያ፣ ጨዋታውን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ስለመጀመሩ፣ ስላስቆጠራት ጎል፣ ስለተመለከተው ቢጫ ካርድ፣ ከሰበታ ከተማ ጋር ሲጫወቱ ስለሳታት የፍፁም ቅጣት ምት እና ስለ ቡድናቸው ቀጣይ ጉዞ ለክለቡ ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት ላይ የሚገኘውን ዳዋ ሆጤሳን የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጥያቄዎችን አቅርቦለት ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ እንዲያነቡትም ጋብዘንዎታል፡፡


ከቅ/ጊዮርጊስ አቻ ስለተለያዩበት ጨዋታ እና ስለ ውጤቱ


“ቅ/ጊዮርጊስ የሊጉ ትልቅ ቡድንና ብዙ ዋንጫዎችን ያገኘም ሆኖ ነው ከእነሱ ጋር ባደረግነው ጨዋታ አቻ ልንለያይ የቻልነው፤ ወደ ጨዋታው ስንመጣ እኛም ሆንን እነሱ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎቻችን ነጥብ ጥለንና በጥሩም ሙድ ላይ ባልነበርንበት ሁኔታ ነው ተገናኝተን የግጥሚያው አሸናፊ ለመሆን የተጫወትነው፤ ውጤቱን ሁለታችንም እንፈልገው ስለነበር በጣም ጠንካራና እልህ የተቀላቀለበት ጨዋታንም ነበር ያካሄድነው በመጨረሻ ግን በአቻ ውጤት ግጥሚያው ተጠናቋል፤ ስለ ውጤቱ እንዲህ ብዬ መናገርምአልፈልግም”፡፡


ከቅ/ጊዮርጊስ በነበራቸው እና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ግጥሚያውን ተጠባባቂ ሆኖ ስለመጀመሩ

“በቤንች ወንበር ላይ ተቀምጬ የነበረው ከምግብ መመረዝ ጋር በተያያዘ ትንሽ አሞኝ ስለነበርና ገናም ከአልጋዬ ላይ ተነስቼ እንድጫወት ተፈልጎ ስለነበር እንጂ ከሌላ ችግር ጋር የተያያዘ አልነበረም፤ በኋላ ላይም ተቀይሬ ወደ ሜዳ ገባውና ለክለቤ ጥሩ የቅጣት ምትን አስቆጠርኩ”፡፡


በቅ/ጊዮርጊስ ላይ ግብ ሲያስቆጥር ስላሳየው የደስታ አገላለፅ


“በከፍተኛ ስሜት ላይ ሆኜ ደስታዬን እንደዛ ባለ መልኩ ለመግለፅ የቻልኩት የተለየ ምክንያት ኖሮኝ ሳይሆን ለጨዋታው የገባሁት ከህመም በመምጣቴ እና ለቡድኔም ተቀይሬ ስገባ አንድ ጥሩ ነገርን መስራት አለብኝ ብዬ ስላሰብኩና ያም ስለተሳካልኝ ነው”፡፡


የመሪነቱን ግብ ካስቆጠራችሁ በኋላ ደስታችሁ ወዲያውኑ ስለመብረዱ


“የእውነት ነው፤ እኔ ባስቆጠርኩት ጎል በመደሰት ላይ በነበርንበት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነው የትኩረት ማጣት ችግር አጋጥሞን እነሱ የአቻነቷን ግብ አስቆጥረውብን ደስታችንን ሊነጥቁን የቻሉት፤ እንዲህ ያሉ ነገሮች በእግር ኳሱ ውስጥ የሚያጋጥሙ ናቸው፤ ጎሎችን አንተ ስታስቆጥር ወይንም ደግሞ በአንተ ቡድን ላይ ጎል ሲቆጠር ስህተቶች ይኖራሉ፤ ካልተሳሳትክ እንዲህ ያሉ ነገሮች አይፈጠሩምና ዋናው ነገር ከእዚህ ተምረህ በቀጣይ ጨዋታዎቻችን ላይ ጥሩ ሆነን ስለመቅረብ ነው ማሰብ የሚገባን”፡፡


ለክለቡ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር አድርጎት ስለነበረው ጥረት


“በቅ/ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከመስመር ላይ የተሰጠኝን የጎንዮሽ ኳስ ለዓለም ብርሃኑ በቀላሉ ያዘብኝ እንጂ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረትን አድርጌ ነበር፤ ነገር ግን ኳሷን ለመቀበል የተገኘሁበት የቦታ አቋቋም /ፖዚሽን/ ፊት ለፊት ስላልነበርና ቦታው ስለጠበበብኝ እንደዚሁም ደግሞ ከአጠገቤ ደስታ ደሙም ስለነበር ጎል ሳትሆን ቀርታለች”፡፡


በጨዋታው ላይ ስለተመለከተው ቢጫ ካርድ


“ኳሷን ለማግኘት በነበረው ጥረት በእነሱ ተጨዋች ላይ እኔ ፋውል አልሰራውም ነበር፤ ሁለታችንም አምሳ አምሳ ነበር ኳሷን ለማግኘት ዕድሉ የነበረን፤ ዳኛው እዛ ላይ ተሳስቷል፤ ስሜታዊ ሆኜና በእዛ ተበሳጭቼ ቅዋሜ በማሳየቴ ነው የቢጫ ካርድን የተመለከትኩት እንጂ ዝም ብል ኖሮ ቢጫ ካርዱን አላይም ነበር”፡፡


ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ከፋይናንስ ችግር ጋር በተያያዘ ደመወዝ ሳይከፈላቸው እና ለተወሰነ ቀንም ልምምድ ሳይሰሩ ተጫውተው ሜዳ ላይ ብርቱ ፉክክር ስለማድረጋቸው


“በእዛ መልኩ ግጥሚያውን ለማሸነፍ የተጫወትነው የተለየ ነገር ኖሮን አይደለም፤ ክለባችን አሁንምየፋይናንስ ችግር አለበት፤ ይሄ ችግር ይስተካከላል ብዬም አምናለው፤ እስከዛው ድረስ ግን አንድ ቡድን ወደ ሜዳ እስከገባ ድረስ የሚችለውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፤ አሸናፊ ስትሆንም ነገ ብዙዎች ስለ አንተ የሚናገሩት ነገር ይኖራል፤ ያለበለዚያ ግን ደመወዝ ስላልተከፈለን በሚል ከአቅም በታች ከተጫወትክ ጣቶች ሁሉ አንተ ላይ የሚቀሰሩብህም ይሆናል፤ በዛ ላይ አሁን የአገራችን የሊግ ውድድር በዲ.ኤስ.ቲቪም እየታየ ነው፤ ራሳችንን ለሌላ መድረክ ማለትም ወደ ውጪ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወጥቶ ለመጫወትም የምናሳይበት ነገር እና ስለ ገፅታችንም መጨነቅ ስላለብንም ነው በእዛን ቀን ጨዋታ ላይ ግጥሚያውን በአቻ ውጤት ብናጠናቅቅም በከፍተኛ ፍላጎትና ወኔ ላይ ሆነን ልንጫወት የቻልነው”፡፡


ከሰበታ ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ቡድናቸው ለድል የሚበቃበትን የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው እሱ መትቶ በመሳቱ በክለቡ አካባቢ የተፈጠረበት ችግር ካለ


“ምንም የተፈጠረ ችግር የለም፤ በኳስ ህይወቴ ፔናሊቲ ስስት የመጀመሪያዬ ነው፤ ከዚህ በፊት ለናሽናል ሲሚንትም ሆነ ለአዳማ ከተማ ስጫወት የመጀመሪያ መቺም እኔ ነበርኩና አልሳትኩም፤ ዘንድሮ ግን ሳትኩ፤ ይሄ በኳስ ያጋጥማል፤ በዕለቱ በመሳቴም ተበሳጭቻለው”፡፡


በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የአቻ ውጤትን በተከታታይ ጨዋታዎች ስለማስመዝገባቸው እና በቀጣይ ጊዜ ስለሚኖራቸው የውድድሩ ተሳትፎ


“ባለፉት ጨዋታዎቻችን በተለይ ደግሞ ወደ ጅማ ከመጣን በኋላ ተከታታይ የሆኑ የአቻ ውጤቶችን እያስመዘገብን ያለነው ጎል ጋር የመድረስ ችግር እያጋጠመን በመሆኑ ነው፤ በእዚህ መልኩ መጓዝም ይጎዳል፤ አዲስ አበባ ላይ በነበረን ጨዋታ በተደጋጋሚ ጊዜ ጎል ጋር እንደርስ ነበር፤ አሁን ይሄን አጥተነዋል፤ ስለዚህም ይሄን ችግራችንን በማስተካከል በባህር ዳር ከተማ ለሚካሄደው የሚቀጥሉት ጨዋታዎች እና ለአጠቃላዩም የሁለተኛው ዙር የሊጉ ተሳትፎአችን ቡድናችንን ወደነበረው ጥንካሬው እና አሸናፊነቱ በፍጥነት ልንመልሰው የግድ ይለናል”፡፡


ለሀዲያ ሆሳዕና ጎሎችን ስለማስቆጠር መቻል


“ሁሌም ቢሆን ከአንድ አጥቂ ጎል ይጠበቃል፤ በተለይ ደግሞ ጥሩ ሜዳ ስታገኝ ጎል የማስቆጠር ፍላጎትህ ይጨምራል፤ በጅማ በነበረን ቆይታ ከሜዳው ምቹ አለመሆንና ወደ ተቃራኒ ቡድንም ጎል ጋር ለመድረስ ከነበረብን ችግር የተነሳ እንደጠበቅኩት ጎሎችን እያስቆጠርኩ አይደለውም፤ ወደ ባህር ዳር ስናመራ ግን ሜዳው ለጨዋታ በጣም አመቺ ስለሆኑ ለክለቤ ተጨማሪ የሆኑ ግቦችን የማስቆጥር ይሆናል”፡፡


ፋሲል ከነማ በአዲስ አበባ ቆይታችሁ እናንተ ይዛችሁት የነበረውን መሪነት ስለመጨበጡ እና አካሄዱ አስግቷችሁ እንደሆነ


“እኛን ምንም የሚያሰጋን ነገር የለም፤ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድሩ እኮ ገና ብዙ ጨዋታዎች የሚቀሩት ነው፤ በእኛና በፋሲል መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ብዙ የሚራራቅ አይደለም፤ የሁለት ጨዋታዎች ልዩነት ነው፤ እነሱ ላይ መድረስ እንችላለን፤ ዋናው ነገር ጠንክረን መስራት ነው፤ በቀጣይ ጊዜ የሊጉ ጨዋታዎቻችንም የተሻሉ የሚባሉ ውጤቶችን እናስመዘግባለን”፡፡


ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመመረጥ ጋር በተያያዘ


“በእዚህ ዙሪያ ከዚህ በፊት ብዙ ነገሮችን ስላልኩ አሁን ደግሜ እንዲህ ማለት አልፈልግም፤ ያም ሆኖ ግን አሁንም ሀገሬን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎቱ ስላለኝ በተጠራሁበት ጊዜ ከእኔ የሚጠበቅብኝን ነገር አደርጋለው”፡፡


ስለ ግል ህይወቱ እና ስለባለቤቱ


“ከባለቤቴ እና ከልጅነቴም ዕድሜ ጀምሮ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ከነበረችው ውብዓለም አበራ ጋር በፈፀምኩት ጋብቻ የትዳር ዓለሙን ተቀላቅዬ ደስ የሚል እና ጥሩ የሆነ ኑሮን እየኖርኩኝ ነው ያለሁት፤ የሶስት ዓመት ወንድ ልጅም አለን፤ ባለቤቴን በተመለከተ ለእኔ ብዙ ነገሮችን ያደረገችልኝና ሁሉ ነገሬ የሆነች ናት፤ ሁሌም ታበረታታኛለች፤ ስከፋም ስደሰትም ከጎኔ ነችና ላመሰግናት እወዳለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P