Google search engine

“ጤነኛ ልሁን እንጂ ሁሌም ለቅ/ጊዮርጊስ በርካታ የድል ጎሎችን አስቆጥርለታለሁ” ሳልሀዲን ሰኢድ /ቅ.ጊዮርጊስ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ 7 ክለቦች ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ዛሬና ነገ ይጫወታሉ
የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በሚደረጉት አራት ግጥሚያዎች የሚጠናቀቁ ሲሆን በእዚሁም መሰረት ዛሬ ቅዳሜ በ8 ሰአት መከላከያ ከወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት እና በ10 ሰአት ደግሞ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
የእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ውጤትም ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያልፉትን ሁለት ቡድኖችም ያሳውቃል፡፡ በእስካሁኑ ጨዋታ መከላከያ ብዙ ጎል አገባ በሚለው ህግ በ4 ነጥብ እና በ1 ግብ ምድቡን ሲመራ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብና ጎል ተከታዩን ስፍራ ይዟል፡፡ ቅ/ጊዮርገስ በ3 ነጥብና በ1 ጎል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወልቂጤ ከተማ ያለምንም ነጥብ 3 የግብ እዳ ኖሮበት የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፍበት እድሉ አክትሟል፡፡
ከሌላው ምድብ ደግሞ ሰበታ ከተማ በ4 ነጥብና በአንድ ግብ ምድቡን ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት በተመሳሳይ ሶስት ነጥብና ያለምንም ግብ ተከታዩን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ፤ ኤሌክትሪክም በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ስፍራ ይዞ ይገኛል፤ በእዚሁም መሰረት ነገ በሚደረጉት የ8 ሰዓቱ የወልዋሎ አዲግራትና የሰበታ ከተማ እንደዚሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና የኤሌክትሪክ ጨዋታ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግበው ቡድን የግማሽ ፍፃሜውን ይቀላቀላል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ጨዋታዎችን አስመልክተን ከየክለቡ ተጨዋቾች ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ በሚከተለው መልኩ ይቀርባል፡፡


ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልቂጤ ከተማን በአንተ ሁለት ጎሎች 3ለ1 ለማሸነፍ ችሏል፤ ጨዋታውን እንዴት አገኘኸው?
ሳላህዲን፡- የወልቂጤ ከተማን የተፋለምንበት የረቡዕ ዕለት ጨዋታ ለእኛ በጣም አስቸጋሪ እና ፈታኝ የነበረብን ሲሆን በአጠቃላይም ለቡድናችን ይህ ግጥሚያ ብቻ ሳይሆን ሰሞኑን ስናከናውናቸው ከነበሩት የወዳጅነት ጨዋታዎች አንስቶም ስንቸገርበት የነበረ ነው፤ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለውም የቡድኑ አሰልጣኝ አዲስ ከመሆኑ አኳያ ከእሱ የአጨዋወት ፍልስፍና ጋር ለመላመድና ለመዋሃድም ጊዜ የሚያስፈልገን ሆኖ ሳለ ደጋፊው ግን ቡድኑ ውጤትና ድል የለመደ ከመሆኑ አንፃር የመታገስ ነገር ስለማይታይበት ይህ አስቸጋሪ ሆኖብን ቆጥቷል፤ ቢሆንም ግን የአሁኑ የረቡዕ ጣፋጭ ድል ለቡድናችን ጥሩ መነሳሻ ይሆንልናል ብለን እያሰብን ነው የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመመራት አንሰራርቶ ባሸነፈበት ጨዋታ ጠንካራ ጎኑ ምን ነበር? ደካማ ጎኑስ?
ሳላህዲን፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ላይ የቡድናችን ደካማ ጎን የነበረው ባለፈው ግጥሚያ ሽንፈትን አስተናግደን ስለነበር ጫና ነበረብን፤ ያም ሆኖ ግን ቀጣዩን ጨዋታ በማሸነፋችን አሁን ላይ ደግሞ ከጫና ተላቀን በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ሌላው ወደ ጠንካራው ጎናችን ስናመራ ቡድናችን ጎል ተቆጥሮበት እና ተመርቶ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ተስፋ የማይቆርጥ ቡድን መሆኑ ነው፡፡ ለእዚህም ነው እኔ ተቀይሬ ከገባሁ በኋላም ከቡድኔ አጋር ጓደኞቼ ጋር በቡድን ስራ ውስጥ በመሳተፍ እና በተጋጣሚያችንም ላይ ጫናን ፈጥረን በመጨረሻም ጣፋጩን ድል ልንጎናፀፍ የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ በወልቂጤ ከተማ ላይ ያስቆጠርኳቸው ሁለት የድል ግቦችም ሆኑ በሜዳ ላይ የነበረህ የጨዋታ እንቅስቃሴ አሁን ላይ ወደ ጥሩ አቋምህ መምጣትህን ያመላከተ ነው፤ ራስህን አሁን ላይ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ሳላህዲን፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በተጨዋችነት እያገለገልኩ ባለሁበት የአሁን ሰአት ላይ እኔን ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝ ነገር ቢኖር የጤንነቴ ጉዳይ ነው፡፡ ጤነኛ ከሆንኩ ከቡድን ጓደኞቼ ጋር ሁሌም ቢሆን ጥሩ ነገርን ሰርተን ክለባችንን ውጤታማ ለማድረግ እንጥራለን፡፡ እኔም ጠኔኛ ልሁን እንጂ ለክለቤ ሁሌም ቢሆን በርካታ የድል ጎሎችንም አስቆጥርለታለው፤ ዋናው እና ቀዳሚው ሃሳቤም ጤነኛ መሆን መቻልም ነው፡፡
ሊግ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያስቆጠርካቸው ሁለት ጎሎች በተለይ ደግሞ ከሩቅ መጥተህ ያገባኸው የመጀመሪያው ጎል የከዚህ በፊቱን እያስታወሱ ብዙዎቹ እንዲወያዩብህ አድርገሃል፤ ስለጎሎቹ ምን ትላለህ?
ሳላህዲን፡- የእግር ኳስን ለመጫወት ወደ ሜዳ ስትገባ የአንተ ዋንኛ ዓላማ ሊሆን የሚገባው ግጥሚያውን ማሸነፍ መቻል ነው፤ ለእዛ ደግሞ ጎል ማስቆጠር የግድ ይልሃልና እኔም በውጤታማነቱ የሚታወቀው ቡድኔ የጨዋታው አሸናፊ እንዲሆን በጣሙን ከመፈለግ አኳያ እና በከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜትም ወደ ሜዳ በመግባት ሁለት ጥሩ ጥሩ ግቦችን ለማስቆጠር የቻልኩት፤ የመጀመሪያው ጎሌ የእውነትም ለበርካታ አመታት ለቀድሞ ቡድኔ ሙገርና ለአሁኑ ክለቤም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳስቆጥራቸው የነበሩ ናቸውና በእለቱ ጨዋታ ቡድናችን አሸናፊ በመሆኑ ከመደሰቴ ባሻገር ግቦቹንም በጥሩ መልኩ ነው የምገልፃቸው፡፡
ሊግ፡- ወልቂጤ ከተማዎች የጨዋታው ተጋጣሚያችሁ ነበሩና እነሱን እንዴት ተመለከትካቸው?
ሳላህዲን፡- ወልቂጤ ከተማን ከታችኛው ሊግ እንደመምጣቱ ስንመለከተው በጣም ጥሩ ቡድን ነው፤ የውድድር ዓመቱንም በጥሩ ውጤት የሚያጠናቅቁ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ከተማ /ሲቲ ካፕ/ ዋንጫ የውድድር ተሳትፎው ላይ ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ባህር ዳር ከተማን ማሸነፍ መቻል ሙሉ ለሙሉ ያሳልፈዋል፤ ይህን የምታሳኩ ይመስልሃል?
ሳላህዲን፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሁሌም ቢሆን አንድ ግጥሚያን ለማድረግ ወደ ሜዳ ስትገባ ወደ ተከታዩ ዙር አለፍክም አላለፍክም ጨዋታውን የግድ እንድታሸንፍላቸው ስለሚፈልጉ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለብንን የዛሬውን ጨዋታ በድል አድራጊነት ለማጠናቀቅ በሁሉም መልኩ ተዘጋጅተናል፤ ደግሞም ጨዋታውን እናሸንፋለን፡፡
ሊግ፡- ሳላህዲን ሰይድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጎል ማስቆጠር ጀምሯል፤ ከእዚህ በኋላስ….? ቡድናችሁስ ዘንድሮ እንዴት ይጠበቅ?
ሳላህዲን፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታ በመጀመሪያ አሁን ላይ የውድድር አመቱን ጤነኛ ሆኜ ነው መጨረስ የምፈልገው፤ በእዚህ ክለብ ውስጥ ጉዳቶች በተደጋጋሚ በእኔም ሆነ በወሳኝ ተጨዋቾች ላይ የሚደርሱበት ሁኔታ ስላለ ደጋፊው ትዕግስት ሊያደርግ ይገባልና ያ ከሆነ እንደዚሁም ደግሞ እኔ ጤነኛ ልሁን እንጂ በእዚህ አመት ለቡድኔ ሌሎች ጎሎችንም በማስቆጠር የውድድር ዓመቱን በጥሩ ብቃቴ የማሳልፍ ነው የሚመስለኝ፡፡ ከዛ ውጪም ክለባችን አሁን ላይ ባልተለመደ ሁኔታ የሊጉን ዋንጫ ካጣ የሁለት አመታትንም አስቆጥሯልና ዘንድሮ ይህ ሳይደገም ወደምንታወቅበት አስፈሪ ቡድንነትና ውጤታማነት የምንመለስ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ ባደረገው ፍልሚያ የጨዋታው ኮከብ /ማን ኦፍ ዘ ማች/ ተብለህ ተሸልመሃል፤ የተፈጠረብህ ስሜት ምን ይመስላል?
ሳላህዲን፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልቂጤ ከተማን ባሸነፈበት ግጥሚያ ተቀይሬ በመግባት ሁለት የድል ጎሎችን ለክለቤ በማስቆጠሬና ጥሩም በመንቀሳቀሴ የጨዋታው ኮከብ ተብዬ ስሸለም በውስጤ የተፈጠረብኝ የደስታ ስሜት በጣም ከፍ ያለ እና ለእኔም የቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ሌሎች ተጨማሪ ጥሩ ነገሮች እንድሰራም መነሳሳትን የሚፈጥርልኝ ነው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ሳላህዲን፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወልቂጤ ከተማን ባሸነፍንበት የረቡዕ ዕለት ጨዋታ ትዕግስትን አድርገው ቡድናችንን በጥሩ ሁኔታ ነበር ሲደግፉ የነበረው በስተመጨረሻም እኛ ባገኘነው ድል ተደስተውም ሲጨፍሩ ታይተዋል፤ እነዚህ ደጋፊዎችም ልዩ ናቸውና ያስቆጠርኳቸውን ሁለት የድል ጎሎች ማስታወሻነት ለእነሱ ማበርከት እፈልጋለሁኝ፡፡
ፎቶ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኢንስፔክተር የኔነህ በቀለ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ለቡድኑ ሁለት የድል ጎሎችን ላስቆጠረው እና የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ለተሸለመው ሳላህዲን ሰይድ ሽልማት ሲያበረክቱለት ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P