“ጥሩ ቡድን አለን፤ ሊጉንም እስከ 5ኛ ደረጃ ይዘን እናጠናቅቃለን”
ወንድሜነህ ደረጄ /ባህር ዳር ከተማ/
የባህር ዳር ከተማው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ወንድሜነህ ደረጄ የአሁን ሰአት ላይ በሊጉ ኳስን ተቆጣጥረው ከሚጫወቱ ጥቂት ተጨዋቾች መካከል ስሙ የሚጠቀስ ሲሆን ይህ ብልጠት የተካለበት የመከላከል እና የተረጋጋ አጨዋዋቱም በብዙዎች ዘንድ እየተወደደለት ይገኛል፡፡
የባህር ዳር ከተማ ክለብ በሊጉ ተሳትፎው ላይ አበረታች ውጤትን እያስመዘገበ በመጣበት የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይም ወጣቱ ተጨዋች ለኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን እስከመመረጥ ደረጃ ያደረሰው ሲሆን ተጨዋቹን በክለቡ የሊጉ የውድድር ተሳትፎ ዙሪያና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርበንለት ምላሹን ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- ሲዳማ ቡናን አንተ ባልተሰለፍክበት ጨዋታ ድል አድርጋችኋል፤ ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው?
ወንድሜነህ፡- የባህር ዳርና የሲዳማ ቡና ጨዋታ በእኛ ቡድን አሸናፊነት ቢጠናቀቅም በሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ በእሁዱ ጨዋታ ለኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ግልጋሎትን ሰጥቼ ከመመለሴና በድካምም ላይ ስለነበርኩ ለቡድኑ ተሰልፌ ለመጫወት ባልችልም ግጥሚያውን ለመመልከት እንደቻልኩት ቡድናችን የኳስ ብልጫን ወስዶ ተጫውቷል፡፡ ሲዳማዎችም ጠንካራነታቸው እና ጥሩ ቡድንነታቸውን ያሳዩበት ፍልሚያ ሆኖ ግጥሚያው ተጠናቋል፡፡
ሊግ፡- ባህር ዳር ከተማ በሲዳማ ቡና ላይ የተጎናፀፈው የድል ውጤት ለእናንተ ተጨዋቾች ምን ስሜትን ፈጥሮባችኋል?
ወንድሜነህ፡- ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነው የፈጠረልን፤ ይሄ ደስታ ምርጦቹን ደጋፊዎቻችንንም ጮቤ እንዲረግጡ ያስቻላቸው ስለሆነ ይሄ ስኬት ወደፊትም ይቀጥላል፤ በፕሪምየር ሊጉ ሲዳማ ቡናን ስናሸንፍ በዋናነት እንድንደሰት ያደረገን ተጋጣሚያችን ጠንካራና ለዋንጫ የሚፎካከር ክለብ ከመሆኑ አኳያ ነው፤ እኛም ለዋንጫው ወደሚፍካከሩት ክለቦች በነጥብ እንድንጠጋቸው ያደረገን ግጥሚያም ስለሆነ ሁሉም ነገር ጥሩ ሊሆንልን ችሏል፡፡ ከዛ ውጭም የቀጣይ ጨዋታችንን የምናደርገው ከሃዋሳ ከተማም ጋር ከሜዳችን ውጪ ስለሆነም ይሄን ግጥሚያ ማሸነፋችን ለተነሳሽነታችንም የሚጠቅመን ሆኗል፡፡
ሊግ፡- ባህር ዳር ከተማ በሊጉ አሁን እያስመዘገበ ካለው ውጤት አኳያ የአመቱ መጨረሻ ላይ ራሳችሁን በምን ደረጃ ላይ ነው የምታስቀምጡት?
ወንድሜነህ፡- ባህር ዳር ከተማ የሊጉን ውድድር ሲጀምር ከያዛቸው ወጣት ተጨዋቾች አኳያ እንደዚሁም ለሊጉም አዲስ ከመሆኑ አንፃር ራሳችንን ያስቀመጥነው ወይንም ደግሞ ትኩረት አድርገን ስንሰራ የነበረው በሊጉ መቆየቱ ላይ ነው፤ ከጥቂት የጨዋታ ቆይታ በኋላ ግን አሁን የምንጫወትበት የፕሪምየር ሊግ ውድድር ከአምናው የከፍተኛ ሊግ /ሱፐር ሊግ/ ውድድር አንፃር ቀላል ሆኖ ስለተመለከትነው የዘንድሮውን ውድድር ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የምናጠናቅቀው ከ1-5 ባለው ደረጃ ላይ ሆነን ነው፡፡
ሊግ፡- በሳምንቱ መጨረሻ ሐዋሳ ከተማን ትገጥማላችሁ፤ ጨዋታውን በምን መልኩ እየጠበቃችሁት ነው፤ ማንስ የጨዋታው አሸናፊ ይሆናል?
ወንድሜነህ፡- ከሐዋሳ ከተማ ጋር የሚኖረን ጨዋታ እነሱ በወላይታ ድቻ ተሸንፈው ከመምጣታቸው አኳያና ግጥሚያቸውንም በሜዳቸው ስለሚያደርጉ ጨዋታው ለእኛ ቀላል አይሆንልንም፤ ያን ስላወቅንም ለግጥሚያው በጥሩ መልኩ ተዘጋጅተናል፤ የጨዋታው አሸናፊም ቡድናችን ይሆናል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ከተጫወትክ በኋላ የእረፍት ጊዜህን የት ታሳልፋለህ?
ወንድሜነህ፡- ብዙ ጊዜ በካምፕ ውስጥ ነው የማሳልፈው፤ ሙዚቃ እሰማለሁ፤ ፊልምም አያለሁ፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ወደ ጣና ሃይቅ በመሄድ መንፈሴን አድሳለሁ፡፡
ሊግ፡- የትውልድ አካባቢህን እንዴት ትገልፀዋለህ?
ወንድሜነህ፡- የእኔ የትውልድ ስፍራና ቦታ መሳለሚያ እህል በረንዳ በሚገኘው የአህያ በር አካባቢ ነው፤ ይሄ ቦታም ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት እና ከዛ ውጪም ብዙ የእግር ኳስ ተጨዋቾችም የወጡበት ስፍራ ስለሆነ እኔም ከዚህ ቦታ ተነስቼም በእግር ኳሱ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ ብሄራዊ ቡድን ደረጃ በመመረጥ እንድጫወት የጥርጊያውን በር የከፈተልኝ አካባቢ ስለሆነ ሰፈሬን የምገልፀው በልዩ ፍቅር ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ አሁን ለደረስክበት ደረጃ የወላጅ እናትህ ድጋፍ እና ምክር ከሁሉም የላቀ እና ልዩም ነው ይባላል፤ በዚህ ላይ ምላሽህን ብትሰጥበት?
ወንድሜነህ፡- የእውነት ነው፤ ለወላጅ እናቴ እኔ ብቸኛዋ ልጅዋ ስለሆንኩኝ ብዙ ለፍታ እና ጠላም ሸጣ ነው ያሳደገችኝ፤ ከእሷም ጋር ነው የምኖረው፤ እናቴ ለ20 ዓመታትም እኔን ጠላ በመሸጥ ስታሳድገኝም ለእኔ የዋለችው ውለታ በጣም ከፍ ያለም ስለነበር ለዚህ የዛሬ ደረጃ እንድበቃም አድርጋኛለች፤ ከእዚህ ውለታዋ በመነሳትም አሁን ላይ እኔ የምኖረው ለእሷ ለእናቴ ነው፤ እናቴ ልጅ ሆኜ ኳስን እንድጫወት አትፈልግም ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን የእኔን ስሜትና ፍላጎት አየችና የደረስኩበትም ደረጃ በአበረታችነቱ የሚጠቀስ ሲሆን ጊዜ በብዙ ነገር ትደግፈኝና ታበረታታኝም ነበር እኔም አሁን ላይ ጥሩ ደረጃ ስደርስላት ጊዜ ጠላ መሸጡን አቁማ የእኔን ስኬት በምክሯ የበለጠ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እየጣረች ነውና እናቴን በዚህ አጋጣሚ ለእኔ ጀግናዬ እንደሆነች መግለፅ እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ላይ ጠንካራ እና ደካማ ጎንህ ምንድነው?
ወንድሜነህ፡- ጠንካራ ጎኔ ፍጥነት አለኝ፤ ኳስን ይዤ እጫወታለሁ ተረጋግቼም ነው የምጫወተው፤ ብልጠትም አለኝ፤ ደካማ ጎኔ ደግሞ የረጅም ኳስ ላይ ፐርፌክት አይደለሁም በአካል ብቃቱም ፊዚካሊ ላይ የሚቀረኝ ነገር አለና በደካማ ጎኖቼ ላይ በግሌ በመለማመድ ጭምር አቋሜን ሙሉ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ኳስን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ እየተጫወትክ ነው፤ ይሄ የመጨረሻ ግብህ ነው?
ወንድሜነህ፡- በፍፁም፤ አሁን ላይ በሊግ ደረጃ ኳስን እየተጫወትኩ ነው፤ ለኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድንም ተመርጬ ተጫውቻለሁ፤ ይሄን ሳይ አገርን ወክሎ መጫወት የሚሰጠውን ደስታ ስላየሁት ቀጣይ ግቦቼ ጠንክሬ በመጫወት በዋናው ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተካትቼ የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማድረግ እና ውጤት ማምጣት ከዛም የፕሮፌሽናል ተጨዋች ሆኜም በመጫወት የአገሬን ስም ማስጠራት እፈልጋለውና እነዚህ ግቦቼ ናቸው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለክለብህ በመከላከሉ ላይ በምታሳየው የጨዋታ እንቅስቃሴ ምላጭ ብለው ሲጠሩ ሰማን፣ ስሙን ማን ነው ያወጣልህ? ለምንስ ተባልክ?
ወንድሜነህ፡- ምላጭ የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣልኝ ለሱሉልታ ከነማ ክለብ በምጫወትበት ሰዓት የቡድናችን ወጌሻ የነበረው ኢሳያስ ነው፤ ይሄ ወጌሻ አሁንም በምጫወትበት የባህርዳር ከነማ ክለብ ይገኛልና ስሙን ያወጣልኝ የኳስ አነጣጠቄን እና ብልጠቴን በማየት ነው፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ደጋፊዎች ግልፃቸው?
ወንድሜነህ፡- የባህር ዳር ደጋፊዎችን ክለባችን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከመግባቱ ጀምሮ ባውቃቸውም እነሱን መግለፅ በጣም ይከብዳል፤ የከፍተኛ ሊግ ላይ ይሰጡት በነበረው ድጋፍ እንዲህ አይነት ምርጥ ደጋፊ የለምም ተብሎ ተነግሮላቸዋል፡፡ አሁን ደግም ይህንን ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል እኛን ተጨዋቾች በሚገባ እያበረታቱን ይገኛልና እናመሰግናቸዋለን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን በማሊ በሰፊ ግብ ተሸንፏል፤ የግቡ መጠን ሰፋ፤ የሽንፈቱ ምክንያት ምን ነበር? ጨዋታውስ ምን ይመስል ነበር?
ወንድሜነህ፡- ከማሊ ጋር በሜዳቸው ባደረግነው ጨዋታ ከነበረን ጥሩ እንቅስቃሴ አንፃርና በጨዋታውም ከእነሱ ተሽለን ከመገኘታችን አኳያ እነሱ እኛን ያሸነፉበት ውጤት በፍፁም አይገባንም፡፡ በጨዋታው የተሸነፍነው ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶብን እና በኋላም ላይ ዳኛው በሚወስናቸው አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑ ውሳኔዎች በቡድናችን ላይ የመረበሽ ነገርን ሊፈጠር በመቻሉ ነው፤ ከነአን ማርክነህም በኋላ ላይ በቀይ ካርድ ወጥቶብን በጎዶሎ ልጅ ልንጫወት መቻላችንም ለሽንፈታችን ዋንኛ ምክንያቶች ነበሩና ከማሊ ጋር የነበረን ጨዋታ ቢያንስ በጠባብ 1-0 በሆነ ውጤት ብቻ መሸነፍ ነበረብን፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….
ወንድሜነህ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ በአጭር ዓመታት የተጨዋችነት ጊዜዬ ውስጥ የአሁን ሰአት ላይ ከአካባቢዬም ሆነ ከሌላ ስፍራዎች ብዙ ተጨዋቾች ያላገኙትን ሀገር ወክሎ የመጫወት እድል በማግኘቴ ጥሩ እርምጃን ተራምጃለሁ ብዬ አስባለው፤ ወደፊት ደግሞ በብሄራዊ ቡድን ደረጃም በመመረጥና በቋሚነትም ተሰልፌ ለመጫወት ራሴን በሚገባ እያዘጋጀሁት ስለሆነ ለእዚህ ደረጃ እንድበቃ እኔን በመምከርና በማሰልጠን ድጋፍ ያደረጉልኝን ከአሰልጣኞች መካከል በፕሮጀክት ደረጃ ለመርካቶ ዩኒየን ስጫወት ያሰለጠነኝን ተሻለ ምንዳዬን ከእሱ በመቀጠል ደግሞ ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ እንድገባ ያስቻሉኝን አሰልጣኝ ማቲያስ ከበደ እዮብ ማለ /አሞካቺ/ እና ሙሉጌታን እንደዚሁም ደግሞ አሰልጣኝ ታደሰ ጥላሁን እና የባህር ዳር ከነማው አሰልጣኝን ጳውሎስ ጌታቸው ማንጎ ጥሩ ነገር ያደረጉልኝ ስለሆነ እነሱን እና የሰፈሬ ጓደኞቼን እንደዚሁም እናቴን ማመስገን እፈልጋለው፡፡