Google search engine


“ጥሩ ብንጫወትም ውጤታችን እኛን አይገልፀንም”
“ጎል የማስቆጠር ችግራችን እየጎዳን ይገኛል”ፍፁም ዓለሙ /ባህርዳር ከተማ/

በመሸሻ ወልዴ


ብዙዎች “ስስ” ብለው የሚጠሩት እና ባሳለፈው የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወቱም ካለው ምርጥ የጨዋታ ብቃት በመነሳት የበርካቶችን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች አድናቆትን ሊያገኝ የቻለው የባህር ዳር ከተማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች እና አሁን ደግሞ ለብሔራዊ ቡድናችን ለመመረጥ የቻለው ፍፁም ዓለሙ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቡድናቸው ተሳትፎ ዙሪያ እና ስለራሱ አቋም እንደዚሁም ደግሞ ሌሎችንም አጠር ያሉ ጥያቄዎችን የሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አቅርቦለት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፤ መልካም ንባብ፡፡


ሊግ፡- በተደጋጋሚ ጊዜ “ስስ” ብለው ሲጠሩህ ሰማን….ቅፅል ስምህ ነው?
ፍፁም፡- አዎን፤ በዛ ስም ነው ብዙዎች የሚጠሩኝ፡፡

ሊግ፡- ግን ለምን ተባልክ?
ፍፁም፡- አላወቅኩትም፤ ምንአልባት ግን አሁን ሳይሆን ያኔ ቀጫጫ ነህ ለማለት ብለው ስሙን ያወጡልኝ ይመስለኛል፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎህ በርካታ አድናቂዎች እንዳሉህ እየተመለከትንም እየሰማንም ይገኛል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አለክ?
ፍፁም፡- እንዲህ ያሉ አድናቆቶችን ማግኘት መቻል በጣም መታደል ነው፤ የበለጠ ተግተህ እና ጠንክረህ እንድትሰራም ያደርግሃል፡፡ በዚህ ዙሪያ ለሚሰጡኝ አድናቆቶችም ሆነ ማበረታቻዎች ደግሞ የስፖርት አፍቃሪውንም ሆነ የቡድናችንን ደጋፊዎች ላመሰግናቸው እወዳለው፤ ለአድናቆታቸውም ፈጣሪ ያክብርልኝ ነው የምለው፡፡

ሊግ፡- የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ጨምሮ ከዛ በፊትም በነበሩት የውድድር ዓመታቶች በሜዳ ላይ ጥሩ ብቃት እንዳለህ እያሳየ ነው፤ የዘንድሮው አቋምህ ካለፉት ይለያል?
ፍፁም፡- አዎን፤ ያለኝን ብቃት አሁን ላይ ገና ከጅማሬው ሳየው በብዙ ነገሮች ላይ መሻሻሌን እየተመለከትኩ ነው፤ በእዚህ ደረጃ ላይ ለመገኘቴም ጠንክሬ መስራቴም በጣም ጠቅሞኛል፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ አሁን በያዝኩት ነገር ላይ በመቀጠል እና ተሽዬም በመገኘት የበለጠ ምርጥ ችሎታዬን የማሳይ ይሆናል፡፡

ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎህም ላይ ሆነህ ከዚህ በፊት ካለህ ብቃት አኳያ ማሻሻል አለብኝ ብለህ የምታስበው ነገር ምንድን ነው?
ፍፁም፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ በአብዛኛው ጥሩ ነገሮች ቢኖሩኝም የራሴ ድክመት ከምላቸው እና በጣም ደግሞ ማሻሻል ካሉብኝ ነገሮች ውስጥ ልጠቅሰው የምፈልገው በእንቅስቃሴ ደረጃ ያለ አግባብ የምባክነው ነገር አለ፤ በአብዛኛው ኢኮኖሚካሊ የሆነ ፉትቦልንም አይደለም የምጫወተው እና እዚህ ላይ ለራሴ የቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወት ስል ጠንክሬ እየሰራሁበት ነው የምገኘው፡፡

ሊግ፡- ሁለገብ ተጨዋችነት አንተን ይገልፅሃል?
ፍፁም፡- ከወገብ በላይ ከሆነ አዎን፤ እዛ ላይ ጥሩ ተክኜበታለው፡፡

ሊግ፡- ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ ቻልክ፤ ስለ ስሜቱ ብትገልፅልኝ?
ፍፁም፡- ለብሔራዊ ቡድን በመመረጤ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ምክንያቱም ሀገርን ወክሎ መጫወት የማንኛውም ተጨዋች ከፍተኛ ፍላጎት ነውና ስለዚህም ይሄን ያገኘሁትን እድል በአግባቡ ልጠቀምበት በሚገባ ተዘጋጅቻለው፡፡

ሊግ፡- ባህርዳር ከተማ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የአዲስ አበባንም ሆነ የጅማ ጨዋታዎቹን አጠናቆ ለባህር ዳሩ ውድድር እያሟሟቀ ይገኛል፤ የሁለቱን ከተሞች ተሳትፎአችሁን እንዴት መዘናችሁት?
ፍፁም፡- አዲስ አበባ ላይ በነበረን የውድድር ቆይታችን ቡድናችን ጥሩ እና ምርጥም ነበር፤ አዝናኝ እግር ኳስንም ይጫወት ነበር፤ ወደ ጅማ ካመራን በኋላ ግን ቡድናችንን ትንሽ የውጤት መበላሸት ስላጋጠመው በምንፈልገው መልኩ ሆኖ አላገኘነውም፤ አሁን ላይ ይሄን ችግር ስላወቅነው ለባህርዳሩ ተሳትፎአችን ያሉብንን ችግሮችና ክፍተቶቻችንን አስተካክለን በመምጣት ጥሩ ቡድን ይዘን ለመምጣት እንሞክራለን፡፡

ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁ እንደ ቡድን ያላችሁ ጥንካሬና ክፍተት ጎን ምንድን ነው?
ፍፁም፡- ጠንካራው ጎናችን በተደጋጋሚ ጊዜ ጎል ጋር እንደርሳለን፤ ይሄ ጥሩ ሆኖ ሳለ እንደምናገኛቸው እድሎች ደግሞ ብዙ ጎሎችን አናገባም፤ እዚህ ላይ ችግር አለብን፤ አለማግባታችን ሊጎዳንም ችሏል፤ በክፍተት ደረጃ ሌላ ላነሳው የምፈልገው ነገር ቢኖር ደግሞ በቀላሉ ጎልን የማስተናገድ ነገር ይታይብናልና እነዚህ ከላይ የተገለፁት ቀላል የሚባሉ ክፍተቶቻችን በፍጥነት ሊታረሙ ይገባል፡፡

ሊግ፡- ባህርዳር ከተማን እንደ እቅድ የት ደረጃ ላይ ልታስቀምጡት አስባችኋል?
ፍፁም፡- የእዚህ ዓመት የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን መወዳደር ስንጀምር የእኛ የመጀመሪያው እቅዳችን የነበረው ሊጉን በደረጃ ተፎካካሪ ውስጥ ሆኖ እንዲጨርስ ማድረግ መቻል ነው፤ አሁን ላይ ያለንበትን ደረጃ እና ውጤት ሳየው ግን ሊጉ እኛን በሚመጥነን ደረጃ ላይ አይደለም ያስቀመጠን፤ እኛ የጠበቅነው ከእዚህ በተሻለ ደረጃ ላይ መቀመጥ ነበር፤ ስለዚህም በቀጣይ ጊዜ ውጤት ከማምጣት አንፃር ቡድናችን ብዙ ነገሮችን ሊሰራ ይገባዋል፡፡

ሊግ፡- የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ተከታዮቹን ቡድኖች በ5 ነጥብ እና ከዛ በላይ ርቋቸው ሄዷል፤ ፋሲል ከነማ ላይ ይደረሳል?
ፍፁም፡- የሊግ ውድድሩ በርካታ ጨዋታዎች ናቸው እኮ ከፊቱ ያሉት ለምን አይደረስም፤ እዛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን በጣም ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ሊግ፡- ባህርዳር ከተማ ካደረጋቸው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ለአንተ ምርጡ እና የተቆጨኸባቸው ጨዋታዎች የትኞቹ ናቸው?
ሊግ፡- ብዙ ናቸው፤ ከፋሲል ከነማ፣ ከቅ/ጊዮርጊስ፣ ከኢትዮጵያ ቡና እና ከጅማ አባጅፋር ጋር ባደረግናቸው ግጥሚያዎች ጥሩ ተጫውተን ሳለን ነው የድል ውጤትን ይዘን ለመውጣት ከመፈለግ እና ከመጓጓት አኳያ የምንፈልገውን ስኬት ልናስመዘግብ ስላልቻልን ልቆጭ የቻልኩት፡፡

ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ምርጥ ቡድን አላችሁ? ስብስባችሁስ በምን መልኩ የሚገለፅ ነው?
ፍፁም፡- አዎን፤ ምርጥ ቡድን እንዳለን በጣም አምናለው፤ ስብስባችንን በተመለከተም ሁሉም የቡድናችን ተጨዋቾች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ናቸው፤ ኳስ የሚጫወት ቡድንም አለን፤ ባህር ዳር ላይ ደግሞ ሜዳው ለጨዋታ በጣም አመቺ ስለሆነ ከእስካሁኑ የተሻለውንና ጠንካራውን የባህርዳር ከተማ ቡድንን እናስመለክታለን፡፡

ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለአንተ ምርጥ ተጨዋቾች እነማን ናቸው?
ፍፁም፡- የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ታፈሰ ሰለሞንና አቡበከር ናስር የተለየ ብቃትን እያሳዩን ነው፤ ለእኔ ሁለቱ ምርጦች ናቸው፡፡
ሊግ፡- ከባህርማዶ ተጨዋቾች ውስጥ ማንን ነው የምታደንቀው? የምትደግፈው ቡድንስ?
ፍፁም፡- ከተጨዋቾች የማደንቀው ሊዮኔል ሜሲን ነው፤ የምደግፈው ቡድን ደግሞ የለኝም፤ ሁሌም ግን ጆሴፍ ጋርዲዮላ የሚይዛቸው ክለቦች በኳሱ ስለሚያዝናኑኝ እሱ የሚያሰለጥናቸው ቡድኖች አድናቂ ነኝ፡፡

ሊግ፡- ስለ ባለቤት እና ስለ ትዳር ህይወትህ ምን አልክ?
ፍፁም፡- ባለቤቴ ቅድስት ወልደ አምላክ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ ምርጧ ሴትና ስጦታም ናት፤ ከእሷ ጋር ጣፋጭ የሆነን የትዳር ህይወትንም እየመራን ይገኛል፤ ጠንካራ የሆነች ሴት ነች፤ ኳስን ያንን ያህል ብዙ ባትወድም ትከታተላለች፤ ዛሬ ለደረስኩበት የስኬት ደረጃም ከጎኔ ሁሌም አለች እና እሷንና ቤተሰቦቼን በጣም ነው የማመሰግናቸው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ፍፁም፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ አሁን ከምገኝበት ስፍራ በላቀ መልኩ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስን እያለምኩ ነው፤ ፈጣሪ ሲፈቅድ ከሀገር ወጥቶ መጫወትም ዋናው ምኞቴ ነው፤ ከዛ ባሻገር ቡድናችን ባህርዳር ከተማ በሜዳው በሚያደርገው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ጥሩ እና የተሻለ ውጤት በማምጣት ደረጃውን ከፍ የሚያደርግ እና የቀጣይ ጊዜ ጨዋታዎችም ውጤቱ ጥሩ እንደሚሆን የእርግጠኝነት ስሜቱ ይሰማኛል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P