የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂው እና አጓጊው ጨዋታ
ኢትዮጵያ ቡና Vs ፋሲል ከነማ
ቀን፡- ቅዳሜ ጥር 27/2013
ሰዓት 4፡00
በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና የሁለተኛው ዙር የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከትናንትናው ዕለት አንስቶ መካሄድ የጀመረ ሲሆን ቀጣይ ጨዋታዎቹ ደግሞ ዛሬና ነገ ይደረጋሉ፤ በዛሬው ዕለት ከሚካሄዱት ጨዋታዎች መካከልም የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት የቀኑ 4 ሰዓት ላይ ጨዋታ ወሳኝና ተጠባቂም ሆኗል፤ የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ አሸናፊም ወይ የነጥብ ልዩነቱን ያሰፋዋል አልያም ያጠበዋል ተብሎም ስለሚጠበቅ ግጥሚያው በሁለቱም ቡድን ተጨዋቾችና ደጋፊዎቻቸው ዙሪያም ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በ32 ነጥብ እየመራ ባለው ፋሲል ከነማ እና በ5 ነጥብ ልዩነት ተበልጦ እየተከተለ በሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና መካከል ስለሚደረገው የዛሬ ጨዋታ፣ ስለ ራሳቸው እና ስለ ቡድኖቻቸው አስመልክተን ከሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ በአማካይ ስፍራ ላይ በጥሩ መልኩ የሚጫወቱትን የኢትዮጵያ ቡናውን ሬድዋን ናስርን እና የፋሲል ከነማውን በዛብህ መላዮን አናግረናቸዋል፤ ተጨዋቾቹም ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡
ስለ ኳስ ጅማሬው እና አስተዳደጉ
“እግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት በአካባቢያችን በሚገኘው የጉቶ ሜዳ ላይ ነው፤ እዛም ነበር ከጠዋት አንስቶ እስከ ማታ ድረስ በሰፈር ደረጃ በመጫወት እና ቀጥሎ ደግሞ በአሰልጣኝ በቀለ አማካኝነት ተኮትኩቼ በማደግ የኳስ ጉዞዬን ያስቀጠልኩት፡፡ አስተዳደጌን በተመለከተ አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፍኩት ኳስን ከመጫወት ጋር ነው፤ በተለይ ደግሞ ከትምህርት ቤት መልስ ከእነ ዩኒፎርሜ እጫወት የነበረበትን ጊዜ መቼም ቢሆን አልረሳሁም”፡፡
በሕፃንነትህ ዕድሜህ የእግር ኳስን ስትጫወት ለአንተ አርአያ ስለነበረው ተጨዋች
“ጉቶ ሜዳ በርካታ ተጨዋቾችን ያፈራ አካባቢ ነው፤ ኳስን በዛን ወቅት ስንጫወትም በቅድሚያ ሰፈሩ ያፈራቸውን ትላልቅ ተጨዋቾችንም ነበር ለምሳሌ እንደ እነ ደረጄ /ሊቴ/ እና ዳዊት ቀለምወርቅን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ስንመለከት የነበረው፤ እነሱ ሁሌም ያበረታቱናል፤ እንደዛም ሆኖ ግን ኳስን ሲጫወት በደንብ ተመልክቼው አርአያ ያደረግኩት ተጨዋች ታላቅ ወንድሜን ጅብሪል ናስርን ነው፤ እሱ ያኔ አስገራሚ የኳስ ችሎታ ነበረው፤ እሱን መመልከቴም ነው ይበልጥ ወደ ኳሱም እንድሳብ ያደረገኝ፤ ከእሱ ውጪ ሌላ ወንድሜ አቡበከር ናስርም ጥሩ ችሎታ ነበረው እና እነሱ ናቸው ተምሳሌቶቼ”፡፡
የእግር ኳስን ተጫወት፤ አትጫወት በሚል ቤተሰብ ጋር ስለነበረው አመለካከት እና ስላሉት ወንድም እና እህቶቹ
“በቤተሰባችን ውስጥ ሁለት ወንድሞች እና አንድ እህት ነው ያለኝ፤ ስለ ወንድሞቼም ከላይ ገልጬያለው፤ እህቴን በተመለከተ ደግሞ ልጅ ሆና በሰፈር ደረጃ ትጫወት ነበር፤ አሁን ትታለች፤ ቤተሰብ ጋር ኳስ ከመጫወቴ ጋር በተያያዘ ስላለው አመለካከት የእኛ ቤተሰብ ጋር እንዲህ የሚል ነገር የለም፤ እንድንጫወትም፤ እንድንማርም ይፈልጋሉ፤ ያለምንም ጫናም ነው ኳስን ስንጫወትም የነበርነው”፡፡
ስለ መጀመሪያ ክለቡ እና ወደ ቡድኑም ስለገባበት መንገድ
“የእኔ የመጀመሪያ ክለቤ አዲስ አበባ ከነማ ነው፤ ወደእዛም ያመራሁት እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ለሆናቸው የታዳጊ ቡድን ለመጫወት የሙከራ እድል ነበርና ያን አሳክቼ ነው የገባሁት፤ በእዛም ቡድን ቆይታን አደረግኩ፤ ለ20 ዓመት በታች ቡድንም በማደግ ቡድኑ ውስጥ ኖርኩ በዛን ጊዜ ቆይታዎቼም ብዙም የመጫወት ዕድሉን ባላገኝም በኋላ ላይ በቢጫ ትሴራ እስከ ዋናው ቡድን ደረጃ ልዘልቅ እና ልጫወትም የምችልበትን ዕድል ለማግኘት ስለቻልኩ ጥሩ ተነሳሽነት ተፈጠረብኝ፤ ከእዚህ ቡድን ቆይታዬ በኋላም ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቀልኩ”፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ቡና ማምራቱ እና ክለቡን ሲቀላቀል ስለተሰማው ስሜት
“ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀልኩበት መንገድ በጣም የሚገርም እና ሌሎች ቡድኖችም ከዚህ ክለብ ብዙ ትምህርትን ሊወስዱበት የሚገባ ነገር ነው፤ ቡና ትልቅ ቡድን ሆኖ በአሰልጣኙ ካሳዬ አራጌ አማካኝነት ለተጨዋቾች የሙከራ ዕድልን ይሰጥ ነበር፤ ይህ ሙከራ እግር ኳሱ ላይ ብዙ ለማይታወቁ ተጨዋቾች መሰጠት መቻሉም ቡድኑንም አሰልጣኙንም እንዲያስመሰግናቸውም ያደርጋቸዋል፤ እኔም ወደዚህ ቡድን ሙከራ ታደርጋለህ ተብዬ በአሰልጣኝ ይገዙ አማካኝነት ሲነገረኝ ያልጠበቅኩት ነበርና በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ይገዙ እኔን በአዲስ አበባ ከነማ ተተኪው ቡድን ውስጥ አሰልጥኖኛል፤ አጨዋወቴን ስለሚያውቅ አንተ ካሳዬ ለሚፈልገው እንቅስቃሴ ትሆናለህ ብሎ ወደ እሱ ላከኝ እኔም በሙከራው ብቁ ሆንኩና ለቡድኑ ተያዝኩ፤ ቀጥሎም ፊርማዬን ሳኖር ይበልጥ ተደሰትኩ የቡና አገባቤም ይሄን ነው የሚመስለው”፡፡
ለኢትዮጵያ ቡና በቋሚ ተሰላፊነት እየተጫወተ ስለመሆኑ
“በቅድሚያ ወደዚህ ታላቅ ቡድን መምጣቴ እና ቡድኑን መቀላቀሌ እኔን በጣም ደስተኛ አድርጎኛል፤ ይሄን ካልኩ ካሳለፍነው ዓመት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ተቀይሬ በምገባባቸው ጨዋታዎች ላይም ሆነ በቋሚ ተሰላፊነት የምጫወትባቸው ጨዋታዎች ላይ እድሉን ለማግኘት መቻሌ እድለኛ እንድሆንም አድርጎኛልና ይሄን ቋሚ ተሰላፊነቴን ዳግምም የማስቀጥለውም ይሆናል”፡፡
በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ስላለው ወቅታዊ አቋሙ
“በእዚህ ቡድን ቆይታዬ አሁን ላይ ያለኝ አቋም ጥሩ ነው፤ እንደ ቡድን ስለምንጫወት እና አሰልጣኛችንም የሚሰጠን የጨዋታ ታክቲክም ከእኛ ጋር ስለሄደም ነው ለእኔ ጥሩነቴንም እያሳየኝ የሚገኘው”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና እየተከተለ ያለው አጨዋወት ተመችቶሃል?
“በጣም፤ ቀለል ያለም ነው፤ ከዛ ውጪም በረኛችን ጭምር እንደተጨዋችም ሆኖ ስለሚጫወት ያለ ድካምም ጥሩ እየተንቀሳቀስንበትም ነውና ይሄ ደስ ይላል”፡፡
ለሶስት ጊዜያት ያህል ሀትሪክ ስለሰራው እና የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ስላለው የቡድኑ ተጨዋች እና ወንድሙ አቡበከር ናስር
“ስለ እሱ እኔ ወንድሙ ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተውለታል፤ አቡኪ በችሎታው ከብዙዎቹ የሀገራችን ተጨዋቾች ይለያል፤ ሲጫወት በጣም እለኸኛ ነው፤ በብቃቱ ሁሉንምያሟላ በሳል ተጨዋች እና ፈጣን የሆነ አህምሮም ያለው ነው፤ ከዚህ በኋላም ያሰበው ደረጃ ላይ ለመድረስ ጠንክሮ መስራትም ይጠበቅበታል”፡፡
አቡኩ! አቡኪ! አቡኪ! የሚለው ስም በተደጋጋሚ ጊዜ ሲጠራና ሲወደስ የእኔስ ስም ለምን እንደ እሱ ጎልቶ አይጠራም በሚል የቅናት ስሜት አላደረብህም….?
“ቅናት በጥሩ ነገር ሲሆን አሪፍ ነው፤ ስለዚህም እኔም እንደ እሱ ስሜን በተደጋጋሚ ጊዜ በጎላ መልኩ ለማስጠራት በቀጣዩ ጊዜ የቡድኔ ቆይታዬ ይበልጥ ጠንክሬ እሰራለው”፡፡
ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከሚመራው ፋሲል ከነማ ጋር ስለሚያደርጉት የነገው ጨዋታ እና ስለሚያስመዘግቡት ውጤት
“ይሄ ጨዋታ ለሁለታችን በጣም ወሳኝ ነው፤ እኛ ተጋጣሚያችንንም አካብደን ወደሜዳ አንገባም፤ በተለይ ይሄን ግጥሚያ እነሱ ካሸነፉ ወደ ሻምፒዮናው የሚያደርጉትን ጉዞ የበለጠ የሚያሳምርላቸው ስለሆነ ለእዚህ ጨዋታ እንደ ሌሎች ቡድኖች ግጥሚያዎቻችን ሁሉ ነጥቡ ስለሚያስፈልገን ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ በሚገባ ተዘጋጅተንበታል፤ ከግጥሚያው መጠናቀቅ በኋላም የጨዋታው ባለድል እኛ ሆነን እንደምንደሰትበትም አስባለውኝ”፡፡
ስለ ተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ
“ፋሲል ጥሩ ቡድን ነው፤ እንደ እኛ ኳስን ተቆጣጥሮም ይጫወታል”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ያሸንፍ እንደሆነ
“የምንጫወተው ታዲያ ለምንድነው? ሊጉ ገና 11 ጨዋታዎች ከፊቱ አሉት፤ ከውድድሩ መሪ ፋሲል ከነማ ጋር አሁን ያለን የነጥብ ልዩነት 5 ነው፤ “ፋሲልን በዛሬው ጨዋታ ለማሸነፍ የሚያስችል ሙሉ ብቃት አለን፤ ድል አድርገነውም የነጥብ ልዩነታችንን እናጠበዋለን ይሄን ዋንጫ ለማንሳትም እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስም ጠንክረን በመስራት እንጓዛለን”፡፡
ስለ ካሳዬ አራጌ እና ወጣት ተጨዋቾች ላይ ስላለው እምነት
“ስለ እሱ በቀላል ቃላት ብቻ ማውራት በቂ ነው ብዬ አላስብም፤ በጣም ጎበዝ የሆነ አሰልጣኝ ነው፤ ቡና የራሱ የሆነ አጨዋወት ሁሌም እንዲኖረው የሚያደርግ ታታሪ ባለሙያተኛም ነው፤ በዛ ላይ በጣም የተረጋጋ እና ስራውን በማስተዋልም የሚሰራ ነው፤ ከዛም በተጨማሪም በታዳጊ ወጣት ለተገነቡት የቡድኑ ተጨዋቾች ለሁሉም የመጫወት እድልን እየሰጠና አንዱን ከአንዱም ሳያበላልጥ ብቁ ተጨዋቾች ሆነውለት እንዲቀርቡም እያደረገም ነውና በዚህ ሊመሰገን ይገባል”፡፡
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በልምምድ ሜዳው እያሰለጠናቸው አብሯቸው ሲጫወት ስላለው የኳስ ችሎታ
“እሱ ሲጫወት እኔ ልደርስበት ባልችልም በልምምድ ሜዳው ላይ ስራን በሚያሰራን ሰዓት በመሀል ባልገባ አጨዋወት የእሱን ችሎታ በገራሚነት ነው የምታየው፤ አንድ አንዴም ከውጪ ሆነን በመመልከትም በአስገራሚ የአቀባበል ችሎታው እስከ መሳቅ ደረጃም ላይ እንደርሳለንና ምነው ያኔ ኖረን ሲጫወት ብናየው ጭምር በሚልም ልንመኝም ነው የቻልነው”፡፡
በመጨረሻ…
“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ የረዱኝን ሁሉ አመሰግናቸዋለውኝ፤ ቅድሚያውን ፈጣሪዬ ይወስዳል፤ ከዛ ቤተሰቦቼ በተለይ እናቴና አባቴ ብዙ ነገርን አድርገውልኛል፤ በመቀጠል ልጅ ሆኜ ያሰለጠነኝን በቀለን በአዲስ አበባ ከነማ ተተኪ ቡድን ውስጥ ያሰለጠነኝንና አሁንም ድረስ ስልክ በመደወል የሚያበረታታኝን ይገዙን፤ በዋናው ቡድን ያሰለጠነኝን እስማሄል አቡበከርን እና የአሁን የቡና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌንና ኮቺንግ ስታፉን ከልብ ለማሰግናችሁ እፈልጋለውኝ”፡፡