“ፋሲልን አሸንፈን የነጥብ ልዩነቱን እናጠባለን፤ ያለመድኩትን ጎል ማስቆጠር አሁን ስለጀመርኩት ተደስቻለው”
አቤል እንዳለ /ቅ/ጊዮርጊስ/
ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታዎቹን በነገው ዕለት በይፋ ሲከፍት በከፍተኛ ጉጉት ከሚጠበቁት ግጥሚያዎች መካከል አንዱ ፋሲል ከነማ ከቅ/ጊዮርጊስ የሚያደርጉት የ9 ሰዓቱ ፍልሚያ ነው፤ ይሄም ጨዋታ በባህርዳሩ ኢንተርናሽናል ስታድየም ሲከናወንም ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር በሁለቱ ቡድኖች መካከል ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቅ/ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርጉት ይኸው ጨዋታ ሁለቱን ቡድኖች በነጥብ የሚያራርቅ አለያም ደግሞ የሚያቀራረብ ይሆናል ተብሎ ግምት የተሰጠው ሲሆን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ አስመልክቶና ከቡድናቸው ጋር በተያያዘ ጉዳይ ዙሪያ ከቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋቾች መካከል የአሁን ሰዓት ላይ ለቡድኑ ጥሩ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውንና ግቦችንም እያስቆጠረ ያለውን አቤል እንዳለን አናግረነው በሚከተለው መልኩ ምላሽን ሰጥቶናል፡፡
ወልቂጤ ከተማን ስላሸነፉበት የ1ኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ
“አሪፍ እና ጥሩ ጨዋታ ነበር፤ ቀድሞም ግብ ተቆጠረብን፤ የምንዘናጋው ነገር አሁንም አብሮን አለ፤ በጨዋታው ጥሩ ጎናችን ሊባል የሚችለው በዚህ ፍልሚያ ላይ ብቻ ሳይሆን ባለፈው ጨዋታም ላይ ጎሎችን እያስቆጠርን መምጣታችን ነው፤ ግን መዘናጋት ጎል እንዲቆጠርብንም አድርጓልና ይሄን ችግር ልንቀርፈው ይገባል”፡፡
ከቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ጋር ስለሚያደርጉት የነገው ተጠባቂ ጨዋታ
“ይሄ የሁለታችን ቡድኖች ጨዋታ የእውነትም እኛ ወደ ሻምፒዮናነቱ ለምናደርገው ጉዞ በነጥብ የሚያቃርበን ለእነሱ ደግሞ መሪነታቸውን አጠናክረው ለመጓዝ የሚያስችላቸው ስለሆነ ተጠባቂነቱ ትክክል ነው፤ በጨዋታው ላይ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚኖርም እርግጠኛ ነኝ”፡፡
የጨዋታው አሸናፊ ማን እንደሚሆን
“ቅ/ጊዮርጊስ በወቅታዊ አቋሙ በተለይም ደግሞ ከፍተኛ ተነሳሽነትን በማሳየት በኩል በአሁን ሰዓት ከፋሲል ከነማ በሚሻልበት ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ የነገው ጨዋታ ባለድል የምንሆነው እኛ ነን፤ ይሄን ጨዋታ አሸንፈንም ከመሪው ቡድን ፋሲል ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነትንም እናጠበዋለን፡፡
ለቅ/ጊዮርጊስ በተከታታይ ጨዋታዎች ጎሎችን እያስቆጠረ ስለመሆኑ
“ግቦችን በማስቆጠሬ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ያለመድኩትም ነበር፤ እኔ የምታወቀው ለጓደኞቼ ኳስን መስጠት /አሲስት/ ማድረግ ነበር፤ አሁን ግን ግብ ማስቆጠር ስለጀመርኩ በራስ መተማመኔ ጨምሮልኛል፤ ይሄ መሆን መቻሉ ደግሞ ሌሎችን ግቦችም ለማስቆጠር እንድሞክር ያደርገኛል”፡፡