Google search engine

“ፋሲል ከነማን ማሸነፋችን አያስገርምም” ኤልያስ አህመድ /አዲስ አበባ ከተማ/

 

በእግር ኳስ ተጨዋችነት የእስካሁን ጉዞው ወደተለያዩ ቡድኖች ተጉዞ  ሊጫወት ችሏል፤ ልደታ ክፍለ ከተማ፣ የልደታው ኒያላ፣ ሐረር ሲቲ፣ ሰበታ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር፣ ወላይታ ድቻና በግማሽ ዓመት ዓምና መጥቶ የተጫወተበት አዳማ ከተማ ደግሞ የእሱ የቅድሚያ ክለቦች ናቸው፤ ኤልያስ አህመድ ይባላል፤ በአሁን ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በመቀላቀል ከፋሲል ከነማ ጋር ተደርጎ በነበረው  የመጀመሪያ ጨዋታው ላይ ለቡድኑ የድል ጎልን ከማስቆጠር ባሻገር ጥሩ የውድድር ጅማሬንም በማሳየት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን አሳይቷል፤ ከዚህ ተጨዋች ጋር ሊግ ስፖርት በኳስ ህይወቱና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎአቸው ዙሪያ አጠር ያለ ቆይታን አድርገን ምላሹን ሰጥቶናል፡፡

ስለ ውልደቱ፣ እድገቱ እና የኳስ ጨዋታ አጀማመሩ

“ተወልጄ ያደግኩት ልደታ ክፍለ ከተማ አካባቢ በሚገኘው ብሪሞ ሜዳ ነው፤ እዛም ነው የእግር ኳስን ከልጅነቴ ዕድሜዬ አንስቶ  መጫወት የጀመርኩት”፡፡

በልጅነት ዕድሜው እግር ኳስን መጫወት ሲጀምር በቤተሰቡ አካባቢ ስለነበረው ፍላጎት

“ወላጅ አባቴ በቦክስ ስፖርት ውስጥ ያሳለፈ ተወዳዳሪ ነበር፤  ስለ ስፖርት ጥቅምንም  ብዙ ነገር ያውቃል፤ ከዛም የተነሳ ነው ኳስን እንድጫወት በመፈለግ እሱም ሆነ እናቴ ኳስን እንድጫወት ፈቅደውልኝ  በዛ በኩል በምንም ነገርሳልቸገር ወደምወደው ሙያ ውስጥመጥቼ ኳሱን ልጫወት የቻልኩት”፡፡

በቤተሰባቸው ውስጥ ብቸኛው ስፖርተኛ እሱ ብቻ እንደሆነ

“አዎን፤ አንድ ወንድምና ሁለት እህቶች ቢኖረኝም ብቸኛው ስፖርተኛውና ኳስ ተጨዋቹ እኔ ነኝ”፡፡

የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ

“ምንአልባት ልሆን የምችለው ወደ ንግዱ ዓለም ተሰማርቼ ነጋዴ መሆን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን  ፈጣሪ አንተ ኳስ ተጨዋች ነው መሆን ያለብህ ስላለኝ በዛው ሙያ ላይ ልሰማራ ችያለው”፡፡

በልጅነት ዕድሜው ከሀገር ውስጥና ከባህርማዶ  ስላደነቃቸው ተጨዋቾችና ስለሚደግፈው ቡድን

“ከውጪ የብራዚሉ ሮናልዲኒዮ ጎቾ አድናቂ ሆኜ ነው ያደግኩት ከሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ደግሞ የሳላህዲን ሰይድ አድናቂ ነበርኩ፤ የምደግፈው ቡድን ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድን ነው”፡፡

የእግር ኳስን ስለተጫወተበት የመጀመሪያ ክለቡ

“በፕሮጀክት ደረጃ እግር ኳስን ተጫውቼ ከመጣው በኋላ ለመጀመሪያ  ጊዜ በክለብ ደረጃ የተጫወትኩት በአሰልጣኝ ብዙአየሁ ዋዳና በረዳቱ እስጢፋኖስ ይሰለጥን በነበረው የልደታ ክፍለ ከተማ ክለብ ውስጥ ነው፤ ያኔም በከፍተኛው ሊግ ላይ ነበር ለመጫወት የቻልኩት”፡፡

በእግር ኳስ ተጨዋችነት የተለያዩ ክለቦች ውስጥ ገብቶ ሲያሳልፍ እስካሁን ስለመጣበት መንገድ

“በእግር ኳሱ የመጣሁበት መንገድ ጥሩ ነው፤ የምወደውን ኳስም እየተጫወትኩትም ስለሆነ ተከፍቼ አላውቅም”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ክለባቸው ስላለው የውድድር አጀማመር

“የፕሪ-ሲዝኑ የዝግጅት ወቅታችን ጠባብ ከመሆኑና ወደ አቋም መለኪያ ግጥሚያውም በስምንት እና በ10 ቀን ልምምድ ከመግባታችን አንፃር አሁን ላይ ቡድናችን እያስመዘገበ የሚገኘውን ውጤት ስንመለከተው ጅማሬያችን አሪፍ ነው፤ የሊጉን ውድድር ስንጀምር አዲስ ቡድን ከመሆናችን አኳያ በደንብ አልተቀናጀንም ነበር፤ ለእዛም ነው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈቶች ያጋጠሙን በሶስተኛው ጨዋታ ላይና አሁን ደግሞ ከእረፍት በመጣንበት የአራተኛው ጨዋታችን ላይ ባለብን ክፍተት ላይ ሰርተን ስለመጣንና በአቋም ደረጃም ልንስተካከል ስለቻልን ሁለቱን ትላልቅ የሀገሪቱን ቡድኖች መከላከያንና ፋሲል ከነማን ልናሸንፋቸው ችለናል”፡፡

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑን ፋሲል ከነማን ማሸነፋቸው አግራሞት ፈጥሮባቸው እንደሆነና ድሉ ይገባቸው እንደሆነ

“ፋሲል ከነማ ካለው ጥንካሬና የአምናም ሻምፒዮና ከመሆኑ የተነሳ የእኛ እነሱን ማሸነፍ ለብዙዎች አግራሞትን ፈጥሮባቸዋል፤ ለእኛ ግን የጨዋታው ዕለት እነሱን ማሸነፋችን ምንም አያስገርምም፤ እንደውም በዕለቱ ግጥሚያ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ያገኘናቸውን የግብ እድሎች ስላልተጠቀምንባቸው እንጂ ሶስትና አራት ግቦችንም በማስቆጠር ማሸነፍም እንችል ነበርና ያገኘነው የድል ውጤት ለእኛ በጣም የሚገባን ነው”፡፡

በፋሲል ከነማ ላይ የድል ጎልን በማስቆጠሩ ስለተፈጠረበት ስሜት

“በጣም ነበር ደስ ያለኝ፤ ምክንያቱም  ጎሏን ያስቆጠርኩት በአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ያለፉት ተከታታይ ሶስት ጨዋታዎች ላይ በጉዳት የተነሳ ለቡድኑ ተሰልፌ ስላልተጫወትኩና በእዚህ የመጀመሪያ ጨዋታዬ ላይም ትልቅ በሚባለው የፋሲል ከነማ ቡድን ላይ ጎሏን ስላስቆጠርኩ ነው፤ ይህቺ ግብ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አላት፤ ለቀጣይ ጨዋታዎቼም የራስ መተማመንን ይፈጥርልኛል”፡፡

ፋሲል ከነማን ስላሸነፉበት የጨዋታ ስልት

“ይህን ድል የተጎናፀፍንበት ምክንያት ሁላችንም ወጣት ተጨዋቾች ነን፣ ለሁሉም ክለቦችም እኩል ግምትን ሰጥተን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፤ ያን ስላወቅንና በአንድነት ሆነንም በከፍተኛ ሞራል ስለተጫወትን ግጥሚያውን ልንረታ ችለናል”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አዲስ አበባ ከተማ በክፍተት ደረጃ ምን ነገሮችን አሻሽሎ መምጣት ይኖርበታል

“አሁን ላይ ክለባችን እየተዋሀደና እየተቀናጀ ነው የሚገኘው፤ እንደዛም ሆኖ ግን ጎል ጋር ደርሰን የግብ ኳሶችን ያለመጠቀም ችግር አለና እዛ ላይ በደንብ ልንሰራበት ይገባል፤ ያኔም የተሻለ ቡድንም ነው የሚወጣን”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዘንድሮ  በምን ደረጃ ላይ ሆነው ያጠናቅቁ እንደሆነ

“አዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቹ ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ እያሳየ ይገኛል፤ ድልም ቀንቶታል፤ ይሄን ማስቀጠል ከቻልን በዘንድሮ ተሳትፎአችን ከ1-5 ባለው ደረጃ ውስጥ ሆነን ውድድሩን እናጠናቅቃለን”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል?

“እንደ ሌላው ጊዜ ይህን ዋንጫ አስቀድሞ ያነሳል ብለህ የምትገምተው ቡድን ዘንድሮ የለም፤ ከባድ ፉክክርም ነው እየተካሄደ የሚገኘው”፡፡

በእግር ኳሱ አሁን ስለሚገኝበት ደረጃና ስለ ወደፊት እቅዱ

“በእግር ኳሱ በምፈልገው ደረጃ ላይ ገና አልደረስኩም፤ ሙሉ አቅሜን አውጥቼም አልተጫወትኩም፤ ከዚህ መነሻነትም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ቆይታዬ ቡድኔን በጣም በሚጠቅም መልኩ በመጫወት ውጤታማ መሆንና ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን በመመረጥም ማገልገልን እፈልጋለው”፡፡

ከእግር ኳስ ውጪ የእረፍት ጊዜውን በምን መልኩ እንደሚያሳልፍ

“ከኳስ ውጪ ብዙውን ጊዜ ቤቴ ነው የማሳልፈው፤ እዛም ሆኜ ፊልሞችን አያለው፤ የሀይማኖት መፅሀፍን አነባለው፤ እንቅልፍን በመተኛትም በቂ እረፍትን አደርጋለው”፡፡

ባህሪይሁን በተመለከተ

“ዝምተኛ ነኝ፤ በጣም ከቀረብኩት ሰው ጋር ደግሞ በደንብ አወራለው”፡፡

በመጨረሻ….

“በምስጋና ልጨርስ በቅድሚያ ፈጣሪዬ ዓላ ሀገራችንን ሰላም እንዲያደርግልን እለምነዋለው፤ ለእዚህ ደረጃ ስላደረሰኝም ምስጋናዬን አቀርብለታለው፤ ከእሱ ሌላ የማመሰግናቸው ደግሞ ቤተሰቦቼን፣ አሰልጣኝ ቡዙአየው ዋዳን፣ አሰልጣኝ ጋሽ ከማል አህመድንና ሌሎች በእኔ ውስጥ ያለፉ አሰልጣኞችን ነው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P