Google search engine

“ፋሲል ከነማን በቀላሉ ማቆም የማይታሰብ ነው” በዛብህ መላዮ /ፋሲል ከነማ/

 

 

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ፋሲል ከነማ በመቶ ፐርሰንት የማሸነፍ ሪከርድ እየመራው ይገኛል፤ የቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በዛብህ መላዮም የኮከብ ግብ አግቢነት መሪነቱን ከቡድን አጋሩ ፍቃዱ ዓለሙ ጋርና ከሲዳማ ቡናው የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች

ይገዙ ቦጋለ ጋር በጋራ በመሆን የቅድሚያው ደረጃ ላይ ሊቀመጡ ችለዋል፡፡

የዓምናው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ ሊጉ በብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት በተቋረጠበት ወቅት ለተጨዋቾቹ እረፍት ሰጥቶ ቢገኝም አንድአንዶቹ ተጨዋቾች ግን በሊጉ ላይ ባሳዩት ጥሩ ብቃት ዳግም ለዋልያዎቹ የመመረጥ ዕድልና በማግኘት ልምምዳቸውን በተጠናከረ መልኩ እየሰሩም ነው፤ ከእነዚህም ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውና በሊጉም የውድድር ተሳትፎው ለፋሲል ከነማ ውጤት ማማር ጥሩ አስተዋፅኦውን እያደረጉ ከሚገኙት ተጨዋቾች ውስጥ ስሙ በጉልዕ የሚጠቀሰውን በዛብህ መላዮን ሊግ ስፖርት በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የቡድናቸው ተሳትፎ እና በሌሎችም ጥያቄዎች ዙሪያ አናግራው ተጨዋቹ ተከታዩን ምላሽ  በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡

የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ እና በዛብህ መላዮም ያደረጉት ቆይታም ይህንን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ሶስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በመቶ ፐርሰንት ሪከርድ እየመራ ይገኛል፤ ውጤቱን እንደጠበቃችሁት ነው ያገኛችሁት?

በዛብህ፡- አዎን፤ ምክንያቱም ቡድናችን የዓምናው ሻምፒዮና ነው፤ ስለዚህም የአጋጣሚ ቡድን እንዳንባል ይህንን ስኬት ማስቀጠል ይኖርብናል፡፡ ለዛ ደግሞ እያንዳንዶቹን ጨዋታዎች ከወዲሁ በማሸነፍ ነጥቦችን መሰብሰብ የግድ ይኖርብናልና ለዛም ነው ግጥሚያዎቹን እያሸነፍን በመጓዝ ላይ የምንገኘው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ድልን የተጎናፀፈባቸው ያለፉትን ሶስት ጨዋታዎቹን እንዴት ተመለከትካቸው?

በዛብህ፡- በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ የቡድናችንን አቋም እንደተመለከትኩት ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ከፍተኛ መሻሻሎችን እያሳየን በመምጣት ላይ መሆናችንን ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከጨዋታው ውጪ በሶስቱም ጨዋታዎች ላይ 9 ነጥብን ማስመዝገብ መቻላችን ትልቅ ስኬት ነውና ይሄ እያስደሰተን ያለ ነው፡፡

ሊግ፡- ካለፉት ሶስት የድል ጨዋታዎቻችሁ ምርጡን ግጥሚያ ጥቀስ ብትባል ለእናንተ የትኛው ቅድሚያውን ይወስዳል?

በዛብህ፡- ጅማ አባጅፋርን በሰፊ ግብ ያሸነፍንበት ጨዋታ ነዋ! ይሄ ጨዋታ ሶስተኛው ፍልሚያችን ነበር፤ የሁለታችን ቡድኖች ጨዋታ ከሜዳ አንፃር ኳስን ይዞ ለመጫወት መረጋጋት እንዳይኖረን ቢያደርግም እኛ ግን ቶሎ ቶሎ ወደ እነሱ ግብ ክልል እንደርስ ስለነበር ያ የሰፊ ግብ ውጤትን አስገኝቶልናልና ይህ ጨዋታ ቀዳሚ ምርጫዬ ነበር፡፡

ሊግ፡- ከጅማ አባጅፋር ጋር ስትጫወቱ በሰፊ ግብ ለማሸነፋችሁ ምን ረዳችሁ፤ የተጋጣሚያችሁ አቋምስ ምን መልክ ነበረው?

በዛብህ፡- ጅማ አባጅፋሮች ከእኛ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከሉ ረገድ በጣም ጠንከር ብለውብን ነበር፤ መከላከሉም ላይ የሰው ቁጥር ነበራቸው፤ በዛም ጎሎችን ለማስቆጠርም ተቸግረን ነበር፤ ግብ ካገባን በኋላ ግን ቦታውን እየለቀቁ ወደ እኛ ሲመጡ እነዛን ክፍተት ለመጠቀም ቻልንና አጠቃናቸው፤ ግቦችንም አስቆጥረን አሸነፍናቸው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ አሁን ላይ በምርጥ ብቃቱ ላይ ይገኛል?

በዛብህ፡- ቡድናችን የውድድሩ ጅማሬ ላይ ስለሆነ ገና ምርጥ ብቃቱን እያሳየ አይደለም፤ ያም ሆኖ ግን ከላይ እንደገለፅኩትም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሸሻልን ነው፤ ሊጉ ከተቋረጠበት ሲቀጥል አቋማችንን ሙሉ ለሙሉ በማስተካከል በጣም ጠንካራ የሆነውን ፋሲል ከነማን በሜዳ ላይ እናስመለክታለን፡፡

ሊግ፡- በቤቴኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ፋሲል ከነማ ዋንጫውን በድጋሚ ያነሳል?

በዛብህ፡- ለዚህ ምንም ጥርጣሬ አይግባህ፤ እንደ እቅድ ያስቀመጥነውም ይህን ድል ለሁለተኛ ጊዜ መቀዳጀት መቻል ነው፤ እልማችንም ይሳካል፡፡

ሊግ፡- ለፋሲል ከነማ ዋንጫውን ማንሳት ላይ የትኞቹ ቡድኖች ጠንካራ ተፎካካሪ ወይንም ደግሞ ስጋት ይሆኑበታል?

በዛብህ፡- ዘንድሮ ደካማ የምትለው ቡድን ማንም የለም፤ በቀጣይነትም እየተጠናከሩም ነው የሚመጡት፤ ከዚህም በመነሳት አሁን እንደተመለከትኳቸው ለእኛ በዋንጫው ፉክክሩ ላይ ስጋት ሊሆኑብን ይችላሉ ብዬ የምጠቅሳቸው ቡድኖች ቅ/ጊዮርጊስን፣ ባህርዳር ከተማን፣ ሲዳማ ቡናን፣ ድሬዳዋ ከተማን፣ ሐዋሳ ከተማንና አዳማ ከተማን ነው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ላይ ዘንድሮ የተለየ ነገርን ተመልክተሃል?

በዛብህ፡- እስካሁን በፍፁም፤ እንደ ዓምናው ነው የ90 ደቂቃ ጨዋታችንን እንደ ቡድን በመጫወት ውጤት እያስመዘገብን የምንገኘው፤ በአንድ ጨዋታ ላይ ደግሞ ጥሩ የሆነ ቡድን ያሸንፋልና እኛም በዛ መልኩ ግጥሚያዎችን አሸንፈናል፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንጉ ሀያ ለሚደርሱ ቀናቶች ተቋርጣል፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?

በዛብህ፡- የእዚህ ውድድር መቋረጥ መቻል የሚጠቅማቸው ቡድኖች አሉ፤ ለምሳሌ ውጤትን ያጡ ቡድኖች ከአንድ ሳምንት የቡድናቸው እረፍት በኋላ ወደ ዝግጅት ሲመለሱ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎቻቸው ላይ ምን አይነት ክፍተት እንደነበረባቸው  ራሳቸውን በደንብ ተመልክተው እንዲመጡና ጉዳት የነበረባቸውም የአንድ አንድ ክለብ ተጨዋቾችና የእኛን ቡድን ጨምሮም ተጨዋቾቻን ከህመማቸው አገግመው ለመምጣት እንዲችሉም ስለሚያደርጋቸው መቋረጡ ጥቅም አለው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በሶስተኛ ጨዋታው የሱራፌልን ግልጋሎት በጉዳት አላገኘም ነበር፤ የእሱ አለመኖር ይጎዳል?

በዛብህ፡- የሱራፌል አለመኖር ግጥሚያን አሸነፍክም አላሸነፍክም የሚያስቀርብህ ነገር አለ፤ ብዙ ጊዜ እሱ ሲኖር በቡድኑ ሪትም ውስጥ የቆየ ተጨዋች በመሆኑ የኳስ ቁጥጥራችን መጠንም ሆነ የማጥቃት ሀይላችን ይጨምራል፤ ስለዚህም ሱሬ አስፈላጊው የቡድናችን ተጨዋች ነው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሶስት ግቦችን ከወዲሁ በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢነቱን ከሚመሩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሆነሃል፤ የአንተን የሚለየው ደግሞ አማካይ ሆነህ ግቦችን እያስቆጠርክ መሆኑ ነው?

በዛብህ፡- ጎሎችን ማስቆጠር ከአጥቂዎች ብቻ አይጠበቅም፤ ያም ስለሆነ ነው ለጎል የቀረበ ተጨዋች ሁሌም ቢሆን ጎልን ማስቆጠር ይችላልና እኔም ያንን ነው እውን እያደርግኩ ያለሁት፤ በከዚህ ቀደም የኳስ ህይወቴ ብዙ ጊዜ 16 ከ50 ውስጥ የመገኘት ልዩ ብቃት አለኝ፤ የጎል እድሎችንም በተደጋጋሚ ጊዜም እፈጥራለው፤ በወላይታ ድቻ እያለውም በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስልጠናም ከሚያሰራኝ ስራዎች አኳያ ሌሎች ግቦችን ያስቆጠርኩበት አጋጣሚም አለና ይሄ የግብ ማስቆጠር ብቃቴ ለእኔ ብዙም አዲስ አይደለም፡፡

ሊግ፡- ጅማ አባጅፋርን ባሸነፋችሁበት ጨዋታ ሁለት የድል ጎሎችን ስታስቆጥር የተፈጠረብህ የደስታ ስሜት ለየት ይል ነበር፤ ምክንያቱ ምንድን ነው? ከዚህ በፊትም በአንድ ሌላ ግጥሚያ ላይ ሁለት ግቦችን ያስቆጠርክበት ጨዋታም ነበር፤ ታስታውሰዋለህ?

በዛብህ፡- በአንድ ጨዋታ ላይ የድል ግቦችን ማስቆጠር መቻል ሁሌም ቢሆን ከፍተኛ ደስታን ይሰጣልና እኔም ዘንድሮ ለክለቤ በማስቆጥራቸው ግቦች ከወዲሁ እየተደሰትኩ ነው፤ ጎሎቹን ስታገባ ደስታክን ልዩ የሚያደርገው ነገር ደግሞ ግጥሚያዎቹን ቡድንህ ሲያሸንፍም ነውና የእኔንም ደስታ የተለየ ያደረገው ይሄ እና በአንድ ጨዋታም ሁለት ግቦችን ያስቆጠርኩት ከረጅም ጊዜ በኋላም ይኸውም በቅ/ጊዮርጊስ ላይ ካስቆጠርኩ በኋላ በመሆኑም ነው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ጅማሬ ጨዋታዎች ከቡድናችሁ ተጨዋቾች ውስጥ የቱን ተጨዋች ለየት ባለ እንቅስቃሴው ተመለከትከው?

በዛብህ፡- በአጨዋወቱ ለየት ያለብኝና ከፍተኛ አድናቆትን እየሰጠሁት ያለው ተጨዋች በረከት ደስታን ነው፤ ይሄ ተጨዋቻችን ዓምና እንደመጣ አካባቢ በእንቅስቃሴው በኩል ተቸግሮ ነበር፤ አሁን ግን እኛ ፋሲሎች በእሱ ብዙ እየተጠቀምን ነው፤ የበረከት ጥሩ ተጨዋችነትም የሚጀምረው ከልምምድ ወቅት አንስቶም ነው፤ ለዛም ነው በክለባችን ውስጥ ለውጤታችን ማማር ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ጎናችን የምትለው ምንድን ነው?

በዛብህ፡- እንደ ቡድን በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ በኩል መጫወት መቻላችንን ነዋ! ይሄም ነው ውጤታማ እያደረገን የሚገኘው፤ ሌላው አንድ አንድ ተጨዋቾቻችንን በጉዳት ስናጣም ሆነ ተቀይረው በሚወጡበት ወቅት ከስር ያደጉት ወጣት ተጨዋቾቻችን የእነሱን ስፍራ በመተካት የሚሸፍኑበት ብቃትም አላቸውና ያም ነው እየጠቀመን ያለው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማን ባለፉት ሶስት ጨዋታዎቹ እንደተመለከትከው በተለይ ምን ነገሮች ላይ ማስተካከል ይኖርበታል?

በዛብህ፡- የማጥቃት ስራው ላይ ብዙ ጎልቶ የታየው በሶስተኛው ሳምንት ጨዋታው ላይ ነበር፤ ያን እንቅስቃሴ ማስቀጠል ይኖርበታል፤ ያኔም ክፍተቱ ሙሉ ለሙሉ ይደፈናል፡፡

ሊግ፡- ሐዋሳ ከተማ ተመቸችህ?

በዛብህ፡- በጣም፤ ምርጥ ከተማ ነች፡፡

ሊግ፡- የሐዋሳ ከተማ ዩንቨርስቲ ሜዳስ?

በዛብህ፡- ስለ እሱ እንኳን ተወው፤ ስታዲየሙ ጥሩ ሆኖ ሳለ ሜዳው ግን በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ይህንንም ሊያውቅ የሚችለው ሜዳውን የተጫወተበት እና የተራመደበት ብቻ ነው፤ የሚያውቀውም ያውቀዋል፤ ሳሩ ደረቅ ነው፤ ፓስ ለማድረግ ተቸግረንበታል፤ ወድቀህ ለመነሳትም ይከብዳል፤ ይሄ በመሆኑም የውድድሩ አዘጋጅ አካላቶች ከወዲሁ ለዚሁ ሜዳ መፍትሄ በማበጀት ጥሩ እግር ኳስ እንዲካሄድበት ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡

ሊግ፡- ከቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ተሳትፎ ውስጥ በተለየ መልኩ የወደድከው ነገር?

በዛብህ፡- ውድድሩ ለእኛ ሀገር ተጨዋቾች ብዙ ነገሮችን ይዞልን መምጣቱን ብናውቅም የዘንድሮን ለየት የሚያደርገው ደግሞ የተጨዋቾች ቅያሪ ላይ ከሶስት መደበኛ ተቀያሪዎች ውጪ አራተኛውና አምስተኛው ተቀያሪዎች በተለይ ለታዳጊ ተጨዋቾች የተሰጠ በመሆኑ ይሄ እድል ለእነሱ መምጣቱና የመጫወት አጋጣሚዎችንም እንዲጠቀሙበት የሚያደርጋቸው በመሆኑ ይሄ የተፈጠረው ሁኔታ አስደስቶኛል፡፡

ሊግ፡- ለዋልያዎቹ ከተጠሩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሆነሃል?

በዛብህ፡- አዎን፤ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጥሩ የውድድር ጊዜን እያሳለፍኩ ስለሆንኩ ነው ጥሪው የደረሰኝ፤ ለቡድኑ በመጠራቴም ደስ ብሎኛል፤ ሀገሬን መጥቀምና ማገልገልም እፈልጋለው፡፡

ሊግ፡- ስናጠቃልል?

በዛብህ፡- በመጀመሪያ አሁን ላይ ሀገራችን ሰላሟን ያጣች በመሆኑ ፈጣሪ ሁሉንም ነገር አስተካክሎ ወደምንታወቅበት ፍቅራችንና ደስታችን እንደዚሁም ደግሞ መዋደዳችን እንዲመልሰን በፀሎት ልንለምነው ይገባል፤ ይህን ካልኩ በኳሱ ህይወቴ ዛሬ ለምገኝበት ደረጃ የረዱኝን ቅድሚያውን የፈጠረኝ አምላኬ ይወስዳል፤ ቤተሰቦቼ እና አንድ ልጅን ከወዲሁ ያስገኘችልኝን ባለቤቴ ቅድስት አመነን እንደዚሁም በተለየ ሁኔታ የምመለከታት እናቴን፤ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞችና ከጎኔ የሆኑት ሁሉ ብዙ ነገሮች አድርገውልኛልና እነሱን ማመስገን እፈልጋለውኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P