test
Google search engine

“ፋሲል ከነማ ምርጥ የውድድር ዘመንን አሳልፏል፤ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎውም የሚያድግ ውጤትን ያስመዘግባል” ሽመክት ጉግሳ /ፋሲል ከነማ/

በመሸሻ ወልዴ

በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሐዋሳ ከተማን በማሸነፍ ሻምፒዮና የሆነው ፋሲል ከነማ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ የታንዛኒያውን አዛም ክለብ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ ላይ ይፋለማል፤ ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎው ጠንካራና ጥሩ ቡድንን ይዞ በመቅረብ በቡዙዎቹ ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳቱን ተከትሎና በእዚህ ዓመት ስላሳለፈው የውድድር ዘመን ተሳትፎው እንደዚሁም በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ስለሚኖረው ተካፍሎና ሌሎችን ጥያቄዎች ለቡድኑ ስኬታማ ተጨዋች ሽመክት ጉግሳ አንስተንለት ተጨዋቹ ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ እሁድ ዕለት ባደረገው ጨዋታ ሐዋሳ ከተማን አሸንፎ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስቷል፤ የእዚያን ዕለት ደስታችሁ ልዩ ነበር፤ ያ የሆነበት የተለየ ምክንያት አለው?
ሽመክት፡- አዎን፤ ምን መሰለህ የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያጣነው በትንሽ ስህተት እና ስፖርታዊም ባልሆነ መልኩ ነው፤ በዛም በጣም አዝነናል፤ ያም ሆኖ ግን አጠቃላይ የእዚህ ዓመት የውድድር ተሳትፎአችንን ያለምንም ዋንጫ ማጠናቀቅ በክለባችን ውስጥ የሚፈጥረውን አስደሳች ያልሆነ ስሜት አስቀድመን ስለምናውቅ እና ፋሲል ደግሞ ዘንድሮ ይዞት እንደቀረበው ጥሩና ጠንካራ ቡድን አንፃር እንደዚሁም ደጋፊዎቻችንም በየሜዳው እየዞሩ እኛን ለመደገፍ ከከፈሉት መስዋትነት አኳያ ቢያንስ ይሄን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ማግኘት የግዳችን ስለነበር ነው የውድድሩ ሻምፒዮና ከሆንን በኋላ ደስታችንን በልዩ እና አስደሳች በሆነ መልኩ ልንገልፅ የቻልነውና ቡድናችን ያገኘው ድል ለእኛም ሆነ ለምርጦቹ ደጋፊዎቻችን በአቻነቱ ወደር የማይገኝለትም ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን እንጂ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አልቻላችሁም፤ የዘንድሮው የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ ለማን ነበር የሚገባው?
ሽመክት፡- ለእኛ ነዋ! ዋንጫውንም ለማንሳት እንችል ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የመጨረሻው ቀን ላይ ከስሁል ሽረ ጋር ባደረግና ጨዋታ እግር ኳሳዊ ያልሆኑ ነገሮች በሜዳ ላይ ስለተንፀባረቁና በስታዲየሙ ውስጥም ከሚታየው ጥሩ ያልሆነ ድባብ አኳያም ግጥሚያውንም በኳስ እንቅስቃሴ ደረጃ ማሸነፍ መቻልም ከባድ ስለሆነብን ጨዋታውን በአቻ ውጤት በማጠናቀቃችንና በሜዳው ላይ ግጥሚያውን ያደረገው መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ተጋጣሚውን ስላሸነፈ ቡድናችን ከኳስ በወጣ ሁኔታ የዋንጫው ባለቤት ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የእዚህ ዓመት ላይ ያሳለፈውን የውድድር ጊዜ እንዴት ነው የምትገልፀው?
ሽመክት፡- ፋሲል ከነማ የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ሊያሳልፍ የቻለው በአጨዋወቱ የብዙ ተመልካቾችን እና የደጋፊውን ቀልብና የኳስ ስሜት ከመግዛት ባሻገር እንቅስቃሴው ብዙዎችንም የሳበ ሲሆን ቡድኑ በርካታ አድናቂዎችም እንዲኖሩት አድርጓል፤ ይሄ ሁሉ ሊሆን የቻለውም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለቡድኑ ተጨዋቾች የሚሰጠው ስልጠና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን በማግኘቱና ከአጨዋወቱም ጋር ለመግባባት በመቻላቸው ይሄ የውድድር ዓመት ተሳትፎአችንን በጥሩ መልኩ እንድናጠናቅቅም አድርጎናል፤ ከዛ ውጪም ፋሲል ከነማ በእዚህ ዓመት ብዙ የለፋ፣ የጣረ እና በእያንዳንዱ ጨዋታም ውጤታማ ለመሆን ብዙ መስዋትነትንም የከፈለ ቡድን ቢሆንም የዋናው የሊግ ውድድር ላይ እግር ኳሳዊ ባልሆኑ ነገሮች ዋንጫን ልናጣ ብንችልም ፈጣሪ ደግሞ ለለፋ አካል የሚከለክለው አንዳችም ነገር ስለሌለ ለእኛ ያለምንም ስኬት አታጠናቅቁም በሚል የዘንድሮውን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንድናነሳ አድርጎናልና በእዚህ ደስተኛ ሆነን ክብርና ምስጋናን ለእሱ እንድንሰጥ አድርጎናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ያገኛሁት ሐዋሳ ከተማን በፍፁም ቅጣት ምት በማሸነፍ ነው፤ በዕለቱ ስለነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ፤ ስላመጣችሁት ውጤትና ስለተጋጣሚያችሁ ምን ትላለህ?
ሽመክት፡- የሐዋሳ ከተማ ክለብን የተፋለምንበት የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የፍፃሜ ጨዋታ የውድድሩ ሻምፒዮና ለመሆን በማሰብ በከፍተኛ ጉጉት ላይ ሆነን ያደረግነው ሲሆን በእለቱም የቢሾፍቱው ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ቡድናችን ከሚታወቅበት እና ከሚከተለው ኳስን መስርቶ እና ተቀባብሎ ከሚጫወትበት አጨዋወቱ አኳያ የሜዳው ለእንቅስቃሴ አመቺ አለመሆን ኳስን በምንፈልገው መልኩ እንድንጫወት እና በተጋጣሚያችንም ላይ የኳስ ብልጫን በጎላ መልኩ እንድንወስድም አላደረገንም፤ ከሐዋሳ ከነማ ጋር በነበረን ጨዋታ እኛ ከእነሱ ተሽለን የነበርነው ተደጋጋሚ የጎል ዕድሎችን በማግኘት ነው፤ እነዛንም ልንጠቀም ሳንችል ቀርተናል፤ ሐዋሳ ከነማን በዕለቱ ጨዋታ ጠንካራ ተፋላሚያችን ሆኖም ነው ያገኘነው፤ በመጨረሻ ግን ቡድናችን በእዚያን መልኩ ኳስን ተጫውቶ በመለያ ምት የውድድሩ ሻምፒዮን መሆኑ ለእኛ ጥሩና አስደሳችም የሆነልን ድል ነበር፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ሐዋሳ ከነማን በፍፁም ቅጣት ምት ማሸነፋችሁ ይታወሳል፤ የመለያ ምቱን ለመምታት ወደመምቻው ስፍራ ስታመራ አልፈራህም?
ሽመክት፡- እኔ አልፈራሁም፤ ስላልፈራሁም ነው ግቡን ያስቆጠርኩት፡፡
ሊግ፡- የፍፁም ቅጣት ምቱ ላይ ግን የሐዋሳ ከነማው ዳንኤል ደርቤ ያስቆጠራት የመለያ ምት ጎል እጅግ ምርጧ እና አስደሳች ተብላለች?
ሽመክት፡- የእውነት ነው የዳንኤል ጎል አስገራሚና ምርጧ ነበረች፤ የእኔ ደግሞ ተከታይና ሁለተኛዋ ምርጥ ግብ ነች፡፡ /ሳቅ/
ሊግ፡- ፋሲል ከነማን በእዚህ ዓመት እንደመቀላቀልህ ቡድኑን የቱን ያህል ልትጠቀመው ችለሃል?
ሽመክት፡- ወደ ፋሲል ከነማ ከገባሁበት ጊዜ አንስቶ አሁንም ድረስ ለቡድኔ እየሰጠሁት ያለው ጥቅምና ግልጋሎት ከፍ ያለ ነው፤ የእዚህ ቡድን ውስጥ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም የእኛን ቡድን የተቀላቀሉት እንደዚሁም ነባር ተጨዋቾችም ለቡድኑ ውጤት ማማር ጥሩ ነገርና ሲሰሩም ተመልክቻለሁና በእዚህ ዓመት ያሳለፍኩትን ጊዜ በጥሩ መልኩ ነው የምገልፀው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከማንሳቱ በፊት በቡድኑ ውስጥ የነበረው አጠቃላይ የድባብ ስሜት ምን ይመስል ነበር?
ሽመክት፡- ፋሲል ከነማ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንዳጣ ወዲያውኑ ትኩረትን አድርጎ ሲሰራ የነበረው ወደ ኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ የውድድር ተሳትፎው ላይ ነበርና ቶሎ ብሎ ነው ሀዘኑን ረስቶ የዋንጫውን ግጥሚያ ለማድረግ የቻለው፤ ከፍፃሜው ጨዋታ በፊትም በሁሉም የቡድናችን ተጨዋቾች ዘንድ የነበረው ስሜትም ይህንን ዋንጫ ማጣት እንደሌለብን እና ደጋፊዎቻችንንም በዚሁ መካስ፣ ማስጨፈርና ማስደስት እንዳለብንም በማሰብ ነው የተጫወትነውን በሜዳ ላይ ያንን እውን ለማድረግ ችለናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ በመሆናችሁ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ትሳተፋላችሁ፤ የታንዛኒያውን አዛም ክለብም ትገጥማላችሁ፤ ለውድድሩ በምን መልኩ እየተዘጋጃችሁ ነው…. ምንስ ውጤትን ትጠብቃለህ?.
ሽመክት፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ባነሳንበት እና ደስታችንንም ለማጣጣም ብዙ ጊዜን ባላገኘንበት የአሁን ሰዓት ላይ በፍጥነት የታንዛኒያውን አዛም ክለብ ለምንፋለምበት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታችን ልምምዳችንን መስራት የምንጀምረው ሰኞ ቢሆንም ለእዚሁ ተሳትፎአችን ጥሩ ዝግጅትን ለመስራት ቀናቱን እየተጠባበቅን ይገኛል፤ በእዚህ የውድድር ተሳትፎም ቡድናችን ስለሚያመጣው ውጤት መናገር የምፈልገው ፋሲል ከነማ በአሁን ሰዓት ከያዛቸው የተጨዋቾች ስብስቡ አንፃርና የኢንተርናሽናል ልምድ ያላቸውንም ልጆች ከመያዙ አኳያ ጥሩ ውጤት የሚያመጣ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ሽመክት፡- የፋሲል ከነማ አጠቃላይ የቡድን አባላቶች ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ጊዜን እንዳሳላፍን ሁላችንም ተስማምተንበታል፤ የጥሎ ማለፉን ዋንጫን በማግኘታችንም ሀገራችንን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ልንወክልበትም ተዘጋጅተንበታል፤ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ መቻላችንም ለእኛ ተጨዋቾች የፕሮፌሽናል ተጨዋችነትን እድል የሚያስገኝልን ከመሆኑ ባሻገር ለምርጦቹም የክለባችን ደጋፊዎች በጣም የሚያስደስታቸው ጊዜ ይሆናልና በመጪው የውድድር ዘመንም ከእዚህ በመነሳት በተለይ ደግሞ ከቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾቻችን መካከል ቡድኑ ብዙም ስለማይፈርስ የመጪው ዓመት ላይ ሌላ አስፈሪ ቡድን የሚኖረን ይመስለኛልና ፈጣሪ ለእዛ ጊዜ እንዲያበቃን ምኞቴን እገልፃለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P