ፋሲል ከነማ ወደ ሱዳን ኢትዮጵያ ቡና ባህርዳር ላይ ወሳኙን የመልስ ጨዋታ ያደርጋሉ
ኢትዮጵያ ቡና VS ዩ አር ኤን
ፋሲል ከነማ VS አል ሂላል
እሁድ መስከረም 9/2014
የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና የኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናቶች በአፍሪካ የተለያዩ ከተማዎች ላይ ተካሂደዋል፤ በዚህም ውድድር አገራችንን በመወከል የተሳተፉት ሁለቱ ክለቦቻችን ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ ቡና ግጥሚያቸውን ከሜዳቸው ውጪና በሜዳቸው አድርገው ፋሲል ከነማ በሜዳው ባህርዳር ስታድየም ላይ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያው ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር ጨዋታውን አድርጎ 2-0 ከተመራ በኋላ በረከት ደስታና ኦኪኪ አፉላቢ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች አቻ ሲለያይ ለአል ሂላል መሐመድ አብዱልራህማንና ያስር መሐመድ አስቆጥረዋል፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከስምንት ዓመታት በኋላ በተመለሰበት የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎው የኡጋንዳውን ክለብ ዩ አር ኤንን ከሜዳው ውጪ በኮንፌዴሬሽን ካፑ ገጥሞ 2-0 ከተመራ በኋላ ዊሊያም ሰለሞን ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ 2-1 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፏል፤ ለድሉ ባለቤት ደግሞ ስቴቨን ሙኩዋላ ሁለቱንም ግቦች አስቆጥሯል፡፡
ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የአሁኑ ተሳትፎው የመጀመሪያው ሲሆን ከዚህ ቀደም ተሳትፎ አድርጎ የነበረው በኮንፌዴሬሽን ካፑ ላይ ነው፤ ይህ ቡድን በመጀመሪያው ጨዋታ ከ2-0 መመራት በማንሰራራት አቻ የተለያየ ሲሆን በአብዱራህማኑ የመልስ ጨዋታ ደግሞ ብርቱ ፍልሚያ ስለሚጠበቀው ለእዛ ውድድር በሚገባ መዘጋጀቱም ታውቋል፤ ቡድኑ ለእዚህ ወሳኝ ጨዋታም በትናንትናው ዕለት ወደ ስፍራው ማምራቱና አጠቃላይ ተጨዋቾቹም በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና ውጤቱን ቀልብሰው ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው እንደሚጫወቱም ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ ይህ ቡድን በሚሳተፍበት የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎው የአሁኑ የመጀመሪያው ሲሆን ከዚህ ቀደም ግን ከስምንት ዓመት በፊት በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ የኮሞሮሱን ኬይኖርድ ቡድን በማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር ካለፈ በኋላ ጉዞው በግብፁ አልአህሊ ተገቶ የነበረ ሲሆን በ1990 ዓ/ም ላይም ትልቁን ተሳትፎ ባደረገበት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሲሸልሱን ቅ/ሚካሄል እንደዚሁም ደግሞ የግብፁን አል አህሊን ከውድድሩ ካስወጣ በኋላ በታንዛኒያው ያንግ አፍሪካ በመሸነፍ ስምንት ቡድኖች ወደሚካፈሉበት የዙር ውድድር ሳያልፍ ቀርቷል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው የኡጋንዳ ጨዋታ ተሳትፎው ቆይታ በኳስ ቁጥጥር ከተጋጣሚው በተሻለ መልኩ መጫወቱ የታወቀ ሲሆን ይህ ቡድን ከሜዳው ውጪ ከተሸነፈበት ጠባብ ውጤትና ከሜዳው ውጪም ጎል ከማስቆጠሩ አኳያ የመልሱ ጨዋታ ላይ ወደተከታዩ ዙር የሚያልፍበት ዕድሉ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች እየተናገሩለት ይገኛል፤ ኢትዮጵያ ቡና ለእዚህ ባህርዳር ላይ ለሚያደርገው ጨዋታ በመጀመሪያ ጨዋታው ጉዳትን ካስተናገደው ሚኪያስ መኮንን ውጪ ብዙዎቹን ተጨዋቾች እንደሚጠቀምባቸውም ታውቋል፡፡
የፋሲል ከነማንና የኢትዮጵያ ቡናን የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ተሳትፎን በተመለከተ ከሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች መካከል ከፋሲል ከነማው ተከላካይ አብዱልከሪም መሐመድና ከኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ወንድሜነህ ደረጀ ጋር ቆይታ አድርገን የሰጡንን ምላሽ አቅርበንላችኋል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችንን በእነዚህ ሁለት የኢንተርናሽናል ውድድሮች በመወከል የሚጫወቱት ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ ቡና መልካም ውጤት እንዲገጥማቸው ዝግጅት ክፍላችን ይመኛል፡፡