የፋሲል ከተማ ስኬታማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሀብታሙ ተከስተ ስለ ቡድናቸው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ስለ ራሱ እና ስለ ቀጣይ ጊዜ የቡድናቸው ጉዞ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽን ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጉዞ በአንተ አንደበት እንዴት ይገለፃል?
ሀብታሙ፡- በውድድሩ ተሳትፎአችን እስካሁን ጥሩም ሆነን ሳንሆን የተጓዝንባቸው ግጥሚያዎች ቢኖርም በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ወደ ጅማ ከተማ ከመጣን በኋላ ክለባችን እያደረጋቸው ያሉትን ጨዋታዎች አሳማኝ በሆነ መልኩ እያሸነፈ እና እንደ ቡድን በመጫወትም ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነ ክለባችን ወደ አስፈሪነቱና ወደ ጠንካራ ቡድንነቱም በመመለስ ላይ ይገኛል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ከእዚህ በፊት የነበረውን ጥንካሬውንና አስፈሪነቱን አጥቷል ተብሎ በአንድ አንድ ሰዎች እና የሶሻል ሚዲያዎች ላይ አስተያየቶች ይቀርቡ ነበር፤ እነዛን ነገሮች እንዴት ነው የምትቀበላቸው?
ሀብታሙ፡- እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማን እንዳለም ሆነ ያነበብኩት ነገር ስለሌለ በእዚህ ዙሪያ ብዙም የምለው ነገር የለም፤ ቢኖር እንኳን ኳስ ነውና የሰዎች አስተያየት ነው ከማለት ውጪ ሌላ የምለው ነገር አይኖረኝም፤ ብዙ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ያሉ አስተያየቶች የሚቀርቡብህ ቡድንህ ሽንፈት በሚያስተናግድበት ወይንም ደግሞ ነጥብ በሚጥልበት ወቅት ነው፤ ወደ እኛ ቡድን አቋም ስመጣልህ ደግሞ እኔም ሆንኩ የቡድናችን ተጨዋቾች ስለ ክለባችን የምናውቀው በቡና ስንሸነፍ እና ከባህር ዳር ጋር ተጫውተን አቻ ስንለያይ ራሳችንን ወቅሰናል፤ ከዛ በኋላ ግን ቡድናችን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች እያሸነፈ ስለመጣ አሁን ላይ በአስፈሪ አቋሙ ላይ ይገኛል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ያለው ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምን ይመስላል?
ሀብታሙ፡- እስካሁን ባደረግናቸው አብዛኛዎቹ ጨዋታዎች እኛ ያለን ጠንካራ ጎን ክለባችን በግለሰቦች ላይ አተኩሮ ከመጫወት ይልቅ በህብረት እና እንደ ቡድን ለመጫወት መቻላችን ነው፤ ከዛም በተጨማሪ እርስ በርስ በመነጋገርም በከፍተኛ ፍላጎትም እያንዳንዱን ግጥሚያዎች ለማሸነፍ መጫወታችንም ለየት እንድንል ያደርገናል፡፡ ደካማ ወይንም ደግሞ ክፍተት ጎናችን ብለን የምናስበው ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በነበሩን ሁለት ጨዋታዎች ላይ ይሄም ማለት ከኢትዮጵያ ቡና እና ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች የእነሱ ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ወጥተው እና እኛ ደግሞ በትርፍ ሰው ተጫውተን የምንፈልገውን የድል ውጤትን ልናስመዘግብ ያልቻልንበትን ጨዋታ መቼም የማንረሳው እና በጣም የተቆጨንበት ነው፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስትጫወቱ አንድ ሰው ከእነሱ በቀይ ካርድ ወጥቶ የተሸነፋችሁበት እና ከባህር ዳር ከተማ ስትጫወቱ ደግሞ ሁለት ተጨዋቾች ከእነሱ በቀይ ካርድ ወጥቶ አቻ የተለያያችሁበት ጨዋታ አሁን ላይ አስተምሮአቸዋል ማለት ይቻላል?
ሀብታሙ፡- በጣም ነዋ! ግጥሚያዎቹ ስላስተማሩንም እኮ ነው ከዛ በኋላ ያደረግናቸውን ጨዋታዎች እያሸነፍን በመምጣት አሁን ላይ በመሪነቱ ስፍራ ላይ ልንቀመጥ የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው የት ድረስ የሚጓዝ ይመስልሃል?
ሀብታሙ፡- እስከ ዋንጫው ባለቤትነት ድረስ ነዋ! ይሄንን ክለብ ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ ቡድናችን ለዋንጫ ነው ሲጫወት የነበረው፤ ስለዚህም ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ይሄንን እልማችንን ዘንድሮ እናሳካለን፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ለዋንጫው ባለቤትነት የሚያሰጋችሁ ወይንም ደግሞ የሚያስፈራችሁ ቡድን ማን ነው?
ሀብታሙ፡- ይሄ እግር ኳስ ነው፤ ሊጉ ደግሞ በርካታ ጨዋታዎች ከፊቱ አሉት፤ ያ ስለሆነም አሁን ላይ እኛን ስለሚያሰጋንም ሆነ ስለሚያስፈራን ቡድን ለማወቅ ጊዜው ገና ነው፤ አሁን ምንም የሚታወቅ ነገርም የለም፤ ከዛ ይልቅ በጣም ጠንካራ ተፎካካሪዎቻችን ስለሚሆኑት ቡድኖች አንድ አንድ ነገርን ብል እመርጣለውኝ፡፡
ሊግ፡- እሺ ቀጥል….የትኞቹ ቡድኖች ናቸው የእናንተ ጠንካራ ተፎካካሪዎች የሚሆኑት?
ሀብታሙ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ምልከታዬ እኛን ይፎካከሩናል ብዬ የምጠቅሳቸው ቡድኖች ቅ/ጊዮርጊስን፣ ኢትዮጵያ ቡናን እና ባህር ዳር ከተማ ክለቦችን ነው፤ እኛም ያን ስለምናውቅ እና ዘንድሮ ደግሞ ይሄን የሊግ ዋንጫ የግድ ማግኘት እንዳለብንም ስለምናምን በቀጣይነት ለምናደርጋቸው ለእያንዳንዳቸው ቡድኖች ጨዋታም ሆነ ከሌሎች ቡድኖችም ጋር ለምናደርጋቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገን ወደ ሜዳ በመግባት የድል ውጤትን ይዘን ለመውጣት ተዘጋጅተናል፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ፋሲል ከነማ ውጤትን ባጣባቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ አሰልጣኝ ስዩም የተወቀሰበት ሁኔታ አለ፤ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ስትሰሙ ምንድን ነው የምትሉት? ስለ አሰልጣኛችሁ ብቃትስ አንድ ነገር ብትል?
ሀብታሙ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ውጤት ሲጠፋ ማንም ይደግፍሃል፤ ውጤት ስታጣ ደግሞ ይወቅሱሃል፤ ይሄ የእግር ኳሱ ባህሪይው ነው፤ ወደ እኛ ቡድን ስመጣ ፋሲል ከነማ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ካደረጋቸው የጨዋታ ተሳትፎው አኳያ ያንን ያህል ውጤት አጥቷል ብዬ አላስብም፤ 9 ጨዋታዎችን አድርገን 7ቱን አሸንፈናል፤ በአንዱ ተሸንፈናል፤ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተናል፤ ቡድኑ ውጤት ቢያጣ እንኳን ሊወቀስ የሚገባው አሰልጣኙ ብቻ ሳይሆን እኛም ተጨዋቾች ጭምር ነውና ሁላችንም ቡድናችንን እያሰብን የምንገኘው በእዚሁ መልኩ ነው፡፡ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ስላለው ብቃት በእኔ የተጨዋችነት አቅም ብቻ የሚገለፅ አይደለም፤ ስለ እሱ ጥሩ አሰልጣኝነት ብዙ ተብሏል፤ ወደ እኛ ቡድን ከመጣ በኋላም ጥሩ ጥሩ ልምምዶችን እያሰራንም ይገኛል፤ ከዛ ውጪም ያለን ግንኙነት እንደ አባት እና ልጅ ያህልም ነው፤ ሁሉን ነገር በመነጋገርም ነው ስራችንን የምንሰራው በአጠቃላይ መልካም እና ጥሩ የሆነ አሰልጣኝ ነው ያለን፡፡
ሊግ፡- ብዙዎቹ የቡድኑ ተጨዋቾች ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር ጥሩ ግንኙነት የላችሁም ነበር ስለሚባለውስ ነገር….?
ሀብታሙ፡- ይሄን ማን ነው ያለው? ከተባለም ወሬው መሰረተ-ቢስ እና ቡድናችንን ወደአልሆነ አቅጣጫ ለመውሰድ የሚፈልግ ነው፤ በእኛ ተጨዋቾች እና በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ መካከል ምንም ልዩነት የለም፤ ቢኖር ኖሮ ይሄን ውጤት አናመጣም ነበር፤ ከዛ ውጪም በደረጃው ሰንጠረዥም በመሪነቱ ስፍራ ላይ አንቀመጥም ነበር፤ ያለን ግንኙነት ከላይም እንደገለፅኩት የአባትና የልጅም ነው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ እያስመዘገበ ላለው ስኬታማ ውጤት የመሀል ሜዳው ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረግክለት ነው፤ ከወቅታዊ አቋምህ በመነሳት ምን ትላለህ?
ሀብታሙ፡- ፋሲል ከነማ በሚያደርጋቸው እያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ በሜዳ ላይ የማሳያቸው እንቅስቃሴዎች ለእኔ ትልቅ የሞራል ስንቅ እየሆኑኝ ነው፤ ለእዚህ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍ እድልን ያገኘሁት በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዘመን ላይ ነበር፤ ጥሩም መንቀሳቀሴን ተከትሎ ችሎታዬን አሳደግኩበት፤ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ደግሞ ብዙ ነገሮችን አሻሽዬ በመምጣቴ በአሁን ሰዓት ለክለቤ ስኬታማ ግልጋሎትን እየሰጠሁት ነው የምገኘው፤ ወደፊትም ምርጥ ችሎታዬን በተደጋጋሚ ጊዜ አሳያለው፡፡
ሊግ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለአንተ የትኞቹ ተጨዋቾች ምርጥና የተዋጣለት ብቃታቸውን እያሳዩ ነው?
ሀብታሙ፡- እንደ እኔ ምልከታ ከእኛ ቡድን ሙጂብ ቃሲም፣ ያሬድ ባየህ እና እንየው ካሳሁንን ከቅ/ጊዮርጊስ ጌታነህ ከበደ፣ አቤል ያለው እና ሄኖክ አዱኛን ከኢትዮጵያ ቡና አቡበከር ናስር እና ታፈሰ ሰለሞንን ከወልቂጤ ከተማ አብዱልከሪም ወርቁን፣ ከባህር ዳር ከተማ ደግሞ ባዬ ገዛኸኝን ነው በተዋጣለት ብቃት ላይ ያየዋቸው፡፡
ሊግ፡- የእናንተው ሙጂብ ቃሲም በርካታ ጎሎችን እያስቆጠረላችሁ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል፤ በተለየ ሁኔታ ስለ እሱስ የምትለው ነገር ይኖርሃል?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ ሙጂብ ቃሲም በአሁን ሰዓት ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ምርጥ አጥቂዎች መካከል በቀዳሚነት ስፍራ ላይ የማስቀምጠው አጥቂ ነው፤ የቦታ አጠባበቁ /ፖዚሽኑ/ ኳስን ደጋግመህ እንድትሰጠው ያስገድድሃል፤ ኳሷን ሲያገኛትም ከመረብ ላይ ያዋሃዳታልና የማደንቀው አጥቂ ነው፡፡
ሊግ፡- ከባህር ማዶ የምታደንቀው ተጨዋች እና የምትደግፈው ቡድን ማንን ነው?
ሀብታሙ፡- ከአውሮፓ ቡድኖች በክለብ ደረጃ የምደግፈው አርሰናልን ነበር፤ አሁን ግን እንደ በፊቱ አይደለሁም፤ ከተጨዋቾች ደግሞ በጣም የማደንቀው እና የምወደው ተጨዋች የባርሴሎናውን አማካይ ሰርጂዬ ቡስኬትን ነው፤ ለእሱ ልዩ ፍቅርም ነው ያለኝ፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ አጋጣሚውን ለማግኘት ብትችልም ተሰልፎ የመጫወት እድሉን ግን ብዙም ማግኘት አልቻልክም፤ ለምን?
ሀብታሙ፡- ይሄን እድል ያጣሁት በአሰልጣኝ ችግር ሳይሆን በራሴ ድክመት ነው ብዬ ነው የማስበው፤ ምክንያቱም የመመረጥ እድሉን ካገኘው በኋላ አሰልጣኙ ያላጫወተኝ ከእኔ ብቃት ያጣቸው አንድ ወይንም ደግሞ ሁለት ነገሮች ስላሉና እነዚህን ደግሞ በእኔ ስፍራ ላይ ከሚጫወቱት ተጨዋቾች ላይ ያገኘ በመሆኑ ነው፤ አሰልጣኝ ሁልጊዜም ሜዳ ላይ የሚያጫውተውም ሆነ የሚመርጠው ተጨዋች ለሚፈልገው ታክቲክ የሚሆንለትን ነው፤ ይህን አውቃለው፤ አሰልጣኙ ከመረጠኝ በኋላ ከእኔ የሚፈልገውን ሁሉን ነገር ቢያገኝና በጣም ደግሞ ጥሩ ብሆንለት እኮ እሱ ያጫውተኝ ነበር፤ ለቀጣዩ ጊዜ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ግን ከእኔ የሚጎለውን ነገር በማሟላት እና ራሴንም በጥሩ ሁኔታ በማቅረብ የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን በተሳካ መልኩ ማገልገልን ነው በጣም የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ስለ ክለብህ ፋሲል ከነማ በአጭሩ አንድ ነገር በል ብትባል ምላሽህ ምንድን ነው የሚሆነው?
ሀብታሙ፡- ፋሲል ከነማ ማለት ለእኔ ብዙ ነገር ነው፤ ስለ ቡድኑም ለማውራት ብዙ ቃላቶችም ናቸው የሚያንሱኝ፤ ከዛ ውጪም ቡድኑ የሚገኝበት ክልልም እኔ የተወለድኩባት የጎንደር ከተማም ናትና ለዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሴ ያላት አስተዋፅኦና ቡድኑ ደግሞ በጣም ለእውቅና እንድበቃም እያደረገኝ ያለና እየተጫወትኩበትም ስለሆነ ደጋፊዎቻችን ደግሞ ለቡድኑ የሚከፍሉት መስዋዕትነትም ከእዚህ በፊትም ታይቷል ህይወታቸውን እስከማጣት ደረስ ስለሚዘልቅም ለእዚህ ቡድን ያለኝ ፍቅር ልዩ ነው፡፡
ሊግ፡- ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዲ.ኤስ.ቲቪ በመተላለፉ ዙሪያ ምን አልክ?
ሀብታሙ፡- ጨዋታዎቹ በእዚሁ መልክ መተላለፋቸው ብዙ ጥቅሞች ነው ያሉት፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እኛም ላይ የደረሰ በደልና ብዙም ነገር አለና፤ ለምሳሌ ጨዋታዎች ከእዚህ በፊት እንዲህ ያለ የቀጥታ ስርጭት በማያገኙበት ጊዜ ክልል ላይ ሄደህ ስትጫወት የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች በሜዳቸው እንደመጫወታቸው በዳኞች ላይ እና በእኛም ተጨዋቾች ላይ ተፅህኖ የሚፈጥሩበት ሁኔታ ስለነበር ነጥቦችን የምንጥልበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን ግን በዲ.ኤስ.ቲቪ ስለሚተላለፍ እና እንደ ሰውም ጥሩ ያልሆነ ነገርን ላለመስራት የምንጠነቀቅበት ሁኔታዎች ስላሉ አሁን እየተሰራ ያለው ነገር ጥሩ ነው፤ የጨዋታዎቹ መተላለፍ ሌላው ያለው ጥቅም ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት እና ተጨዋቾቻችንም በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወደ ውጪ ሀገር ወጥተው የሚጫወቱበት እድሉ ስለሚኖራቸው ነውና ይሄ መሆኑ ለሁላችንም አስደሳች ነው፤ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ና
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
ሀብታሙ፡- የእግር ኳስን ስጫወት ብዙ ሰዎች የሰውነቴን ደቃቃ መሆን ቢያዩም ኳስን በአህምሮ /በጭንቅላትህ/ ነው የምትጫወተው በሚል ጥሩ አድናቆትን ሲሰጡኝ እሰማለው፤ ይህን ስሰማም ለእኔ ትልቅ ግብ ስለሚሆነኝ ከዚህ የበለጠ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሁሌም በርትቼ ልምምዴን እሰራለውና አድናቂዎቼ ለምትሰጡኝ አድናቆት ከፍተኛ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፤ ከእናንተ በፊት ግን እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሴ በቅድሚያ ማመስገን የምፈልገው ድንግል ማሪያምን ነው፤ እሷ ለእኔ ብዙ ነገሮችን አድርጋልኛለች ክብርና ምስጋና ይገባታል፤ ሌሎች የማመሰግናቸው ደግሞ እኔን አሰልጥነው ያለፉትን አሰልጣኞች፤ የአሁኑን አሰልጣኜን የክለባችንን ደጋፊዎች እና ጓደኞቼን ነው፡፡
“ፋሲል ከነማ ውጤት ሲያጣ መወቀስ ያለበት አሰልጣኙ ብቻ ሳይሆን እኛም ጭምር ነን” ሀብታሙ ተከስተ (ጎላ)
ተመሳሳይ ጽሁፎች