ሽመክት ጉግሳ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታው ፋሲል ከነማን በጥሩ ብቃቱ ያገለገለ ተጨዋች ነው፤ በቡድኑ ውስጥ ባሳለፋቸው የጨዋታ ጊዜያቶቹም አንድ ጊዜ የጥሎ ማለፍን አንድ ጊዜ ደግሞ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለማንሳትም ችሏል፤ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ለተጫወተባቸው ቡድኖች አቅሙን ሳይሰስትም መልካም የሚባል እንቅስቃሴን ለማሳየት ችሏል፤ በክለብ ተጨዋችነት ቆይታውም በሜዳ ላይ ተሯሩጦ በመጫወት የሚታወቅና አይድከሜ ሲሆን በአንድ አንዶች ባለሙያዎች፣ የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና የእግር ኳሱ ተመልካቾች ዘንድም ሶስት ሳንባ ያለው ተጨዋች እስከማለት የደረሱለት እና በችሎታውም የሚያደንቁት ነው፤ እንደ ፋሲል ከነማ ተጨዋችነቱ ሁሉ ለደደቢትም በሚጫወትበት ወቅት የጥሎ ማለፍን ዋንጫ ከክለቡ ጋር ለማሳካት የቻለው ሽመክት በክረምቱ ወራት በፋሲል ከነማ የነበረው የውል ጊዜ ቢጠናቀቅም ለቀጣዩ ጊዜም በክለቡ ለመቀጠል ፊርማውን አኑሯል፤ ከእዚህ ተጨዋች ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በእዚህ ጉዳይና ሌሎችን ጥያቄዎችን በማንሳት ቆይታን ያደረገ ሲሆን ተጨዋቹም ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሊሰጥ ችሏል ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ ውልህን አራዝመህ የመጪው ዘመን የቡድኑ ተጨዋች ሆነሃል፤ ለቡድኑ ለመፈረም ዘገየህ ልበል?
ሽመክት፡- በፍፁም፤ ብዙም አልዘገየውም፤ ከእነሱ ጋር ለመቀጠል ስለፈልግኩ እና በአንድ ነገሮች ላይም በድርድር ላይ ስለነበርኩ ነው የዘገየው የመሰለው፡፡
ሊግ፡- ለፋሲል ከነማ ከአንተ ውጪ ብዙዎቹ ነባር ተጨዋቾችም ውላቸውን ያራዘሙ ሆነዋል፤ ይሄ ለክለቡ መልካም ነገር ነው ማለት ይቻላል?
ሽመክት፡- በጣም፤ ምክንያቱም ተጨዋቾቹ ለክለቡ ምርጥነት ትልቁን ስራ ሰርተዋልና፤ ከዛ ውጪም ሌሎች የለቀቁብን ተጨዋቾችም እስካሁን ስለሌሉ እና ሌሎች ሊጠቅሙን የሚችሉ ተጨዋቾችም ወደ ቡድናችን ስለመጡ እኛን ይሄ ብዙ የሚያጠናክረንም ይሆናል፡፡
ሊግ፡- የክለባችሁ አጥቂ ሙጂብ ቃሲም እስካሁን ውሉን አላራዘመም፤ የእሱ በክለቡ መቆየትና አለመቆየት መቻል በቡድናችሁ የመጪው ጊዜ የውድድር ተሳትፎ ላይ ምንን ይፈጥርባችኋል?
ሽመክት፡- ሙጂብ ቃሲም ለእኛ የቡድናችን ተጨዋቾች በጣም ጓደኛችንና ጥሩም የውድድር ጊዜን በክለቡ ውስጥ ያሳለፈ ተጨዋቻችን ነው፤ ከክለቡ ጋር ስለመቀጠሉና አለመቀጠሉን በተመለከተ እስካሁን ያለውን ነገር ባላውቅም እኔ ግን ከክለቡ ጋር ይቀጥላል ብዬ ነው የማስበው፤ የሙጂብ መቀጠል ለእኛ ለክለቡ ካበረከተው ጥሩ አስተዋፅኦ አኳያ በጣም ነው የሚጠቅመን፤ ካልቀጠለ ደግሞ የሚጎዳን ነገር ይኖራል፤ ምክንያቱም ለአንድ ቡድን አይደለም እንደ እሱ ያለ ቋሚ የቡድኑ ተሰላፊ ተጨዋች እና ጎል የሚያስቆጥርልህ በተጠባባቂ ስፍራ ላይ የተቀመጠ ተጨዋች እንኳን በሀሳብ ዙሪያ ለክለብህ የሚጠቅምህ ብዙ ነገር አለና ይሄን ነው ለማለት የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ለፋሲል ከነማ ለመጫወት መቻልህ ተመችቶሃል?
ሽመክት፡- አዎን፤ ክለቡ በጣም ምርጥ ነው፤ ጥሩ እግር ኳስንም የሚጫወት ነው፡፡ ከዛ ውጪ ደግሞ ከተጨዋቾቹ ጋር ያለኝ ግንኙነት ጥሩ መሆኑና ደጋፊውም አስገራሚ ስለሆነ ይሄን ስለተመለከትኩም ነው በብዙ ነገሮች ክለቡ ሊመቸኝ የቻለው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ እስካሁን ከተጫወትክባቸው ክለቦችስ በጣም ምርጡ ነበር ማለት ይቻላል?
ሽመክት፡- በሚገባ! ግን ፋሲል ከነማ ብቻ አልነበረም ለእኔ ምርጡ ደደቢትም እንደ ፋሲል ከነማ ሁሉ ጥሩ ጊዜን ያሳለፍኩበት ሌላው የምወደው ክለቤ ነው፤ ፋሲል ከነማን ግን ከሌላው የሚለየው ሌላ ነገር አለ፤ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት ታጅበን የምንጫወት መሆናችንና ምርጥ ስብስብም ስላለን ለእዚህ ቡድን መጫወት የተለየ ደስታንም ጭምር ይሰጥሃል፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ እና በደደቢት ቆይታህ ጥሩ የጨዋታ ጊዜያቶችን ለማሳለፍ ብትችልም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ግን አልቻልክም?
ሽመክት፡- ልክ ነህ፤ በዛ ዙሪያ ብዙም እድለኛ ነኝ ማለት አልችልም፤ በተለይ ደግሞ ለፋሲል ከነማ ስጫወት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት በጣም ተቃርቤ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን መጨረሻ ላይ ውጤታችን ተበላሸብን፡፡ ዘንድሮም ቢሆን ይሄን የሊግ ዋንጫ ለማንሳት የሚያስችል ምርጥ ቡድን ቢኖረንም፤ የሊጉን ውድድር ለመምራት ብንችልም በኮቪድ 19 ምክንያት ግን የእግር ኳስ ውድድራችን ሙሉ ለሙሉ ስለተሰረዘ ይሄ ዋንጫ የማንሳት እልሜ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 የእግር ኳሱ ባይሰረዝ ኖሮ ፋሲል ከነማ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ይችል ነበር?
ሽመክት፡- አዎን፤ በዛ ዙሪያ ምንም አልጠራጠርም፤ ቅድም እንደገለፅኩልህ ዋንጫ ለማንሳት የሚያስችል ምርጥ ቡድን ነበረን ፤ ዋንጫው የእኛ ይሆን ነበር፡፡
ሊግ፡- የአምናው የክለባችሁ ስብስብ አሁንም አብሯችሁ እንዳለ ነው፤ በመጪው ዘመን ውድድርስ ይሄን ዋንጫ የምታሳኩ ይመስልሃል?
ሽመክት፡- በእዛ እርግጠኛ ነኝ፤ ፋሲል ከነማ የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ የግድ ያስፈልገዋል፤ ይሄን ዋንጫም ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለተደጋጋሚ ጊዜም ማግኘት የሚገባው ክለብም ነው፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ቆይታህ ላይ ዋንጫ ለማግኘት ተቃርባችሁ ስኬቱን ያጣችሁበት ዋንኛ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?
ሽመክት፡- በቅድሚያ እንደ ዋንኛ ችግሮች የምጠቅሳቸው የመጀመሪያው ዙር ላይ በሜዳችን ላይ የጣልናቸውን ነጥቦች ነው፤ እነዛ ውጤቶች ሊጠፉ የቻሉበት ምክንያትም ክለባችን በአዲስ መልክ የተገነባም ስለነበር ነው፤ በተደጋጋሚ ጨዋታ ላይ አቻ እንወጣ ነበር፤ እነዛን ውጤት ባናጣ ኖሮ የሁለተኛው ዙር ላይ ቡድናችን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ሲያመራ ምርጥ አቋሙን ከማሳየት ባሻገር ጥሩ ውጤትም እያመጣን ስለነበር ለዛ ደረጃ ሁሉ አንደርስም ነበር፤ ሌላው ለቡድናችን ውጤት ማጣት ሊጠቀስ የሚችለው የመጨረሻው ቀን የሊጉ ጨዋታ ላይ የእኛ ቡድን ዋንጫ እንዲያነሳ ስላልተፈለገ ከስዑል ሽረ ጋር ያደረግነው እና ነጥብ የጣልንበት ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠው ጨዋታ ነው፡፡
ሊግ፡- ለአንተ እንደ አንድ የእግር ሊግ ኳስ ተጨዋችነትህ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ለማንሳት መቻል አልናፈቀህም?
ሽመክት፡- የእውነት ነው፤ እስካሁን በነበረኝ የኳስ ተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ የጥሎ ማለፉንና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫዎችን ለማግኘት ችያለው፤ ስለዚህ አሁን ላይ ደግሞ ወደፊት ኳስ ሳቆም ሁሌ ላወራው ስለምችለው ታሪክ ይኸውም የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫን ማግኘት ከፍተኛ ፍላጎቴ ስለሆነ ያን ድል ማግኘት በጣም እየናፈቀኝ ነው፤ ይሄን ዋንጫ የማንሳት ጥማቴንም በፋሲል ከነማ ቆይታዬ የምወጣውም ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- የቀጣዩ ዓመት የፕሪምየር ሊጉ ውድድር በኮቪድ 19 ምክንያት ያለ ደጋፊ እንዲካሄድ ተወስኗል፤ ያን ስትሰማ ምን አልክ?
ሽመክት፡- በመጀመሪያ ብዙ ደጋፊ ላለው ክለብ በእዛ መልኩ መጫወት መቻል በጣም እንደሚከብድ እና ብዙ ስሜትንም እንደማይሰጥ ነው የተረዳሁት፤ በዚህ ዙሪያም የሊቨርፑልን ነገርም ማንሳት ይቻላል፤ ይሄ ክለብ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ ሲያነሳ ያለ ደጋፊው ፊት በመጫወት ነው፤ ደስ አይልምም ነበር፤ እነሱ ቢኖሩ ድባቡ ምን ሊሆን እንደሚችለው አስበው፤ ግን ፈጣሪ ባለው ነገር ዋንጫውን አንስቷል፤ ሲቀጥል ደግሞ የአንተ ክለብ በጥሩ መልኩ ከተሰራ በደጋፊውም ሆነ ያለ ደጋፊው ፊት ሲጫወት ግጥሚያዎችን በምን መልኩ ለማሸነፍ እንደሚችልም የአሰልጣኞቹ ስራና የተጨዋቾችም ብቃትን የምንመለከትበት ሁኔታም አለና ይሄም ነው ትልቁ ነገር፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ ቆይታህ ቡድናችሁን የሚለየው የተለየ ነገር ምንድን ነው?
ሽመክት፡- ሁሌም እንደ ቡድኑ ተጨዋችነት ብቻ አይደለም የምንተያየው፤ እርስበርሳችን ቤተሰባዊ የሆነ ግንኙነትም ነው ያለን በተለይ ደግሞ አንድ ተጨዋች ካጠፋ ያ ጉዳይ ከክለቡ አይወጣም፤ ችግሩን እዛው ፈተነው ወደ ቤታችን ነው የምንሄደው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ለጨዋታ ሜዳ ስንገባም ሁሉ ግጥሚያዎችን ስለ ማሸነፍ እንጂ አቻ ስለመውጣትም ባለመሆኑ ይሄ ቡድኑ ውስጥ እንደ ባህል እየሄደ ያለው ነገርም ነው እኛን የሚለየን፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ለወራቶች እድሜ ከእግር ኳሱ ለመራቅ ችለሃል፤ ይሄ ሁኔታ በአንተ እና በቤተሰብህ ዘንድ የፈጠረባችሁ ነገር አለ?
ሽመክት፡- ኮቪድ ወደ አገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከኳሱ ለበርካታ ወቅቶች ስርቅ የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፤ ከዚህ በፊት ለእዚህን ያህል ጊዜ ከኳሱ የራቅኩበት ወቅትም ፈፅሞ አጋጥሞኝ አያውቅም፤ ስለዚህም ከኳሱ መራቄ እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች የሚሰማኝ ጥሩ ያልሆነ ነገር ቢኖርም በሌላ በኩል ደግሞ ቤተሰቦቼን ለብዙ ጊዜያት እንዳገኛቸው መቻሌና አንድ አንድ ስራዎችንም ከእነሱ ጋር ለመስራት ጊዜያቶችን ያገኘሁበት አጋጣሚዎችም ስላሉ ይሄ ጥሩ አጋጣሚም ሊሆንልኝ ችሏል፡፡
ሊግ፡- ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባ አሁን ላይ አምስተኛ ወሩን አስቆጥሯል፤ ጊዜያቶቹን በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው?
ሽመክት፡- ብዙዎቹን ቀናቶች የማሳልፈው በክለብ ደረጃ እንደምንሰራው ልምምድ በመስራት ሳይሆን ለእኛ በቂ ነው በሚባል ደረጃ በግሌ እና የወላይታ ድቻ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ከሆኑት ወንድሞቼ ጋር ነው ማለትም ከቸርነት ጉግሳ እና አንተነህ ጉግሳ ጋር በመሆን የአካል ብቃት ልምምድን እየሰራው የምገኘው፤ ከዛ ውጪም ኮቪድ በእኛ ክልል ወላይታም እንደ አዲስ አበባም እየተስፋፋ የመጣበት ሁኔታም ስላለ አስፈላጊውን ጥንቃቄም በማድረግ ነው በቤት ውስጥ እያሳለፍኩም የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ባሳለፍካቸው ጊዜያቶች ደስተኛ ነህ?
ሽመክት፡- በአብዛኛው አዎን፤ በተለይ ደግሞ በኳሱ ደስተኛ እንድሆን የተጫወትኩባቸው ክለቦች ትልቁን አስተዋፅኦም አበርከተውልኛልና ስለ እነሱም ማለት የምፈልገው ነገር አለ፤ በኳስ ጨዋታ ዘመኔ ደደቢትን በጣም የምወደው ክለቤ ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ ሌላ በጣም የወደድኩት ክለብ ፋሲል ከነማ ነውና ለእነዚህ ክለቦች ትልቅ አክብሮትም ነው ያለኝ፤ ምክንያቱም ኳስን ስጫወት ሁሌም ኳሱ ስራዬና እንጀራዬ ሆኖም የምጫወተው ስለሆነና በምሰራው ስራ ልክም የአቅሜን አውጥቼም በመጫወት እየተጠቀምኩበት ያለም በመሆኑ ይሄ ያስደስተኛል፤ በኳሱ የተከፋሁበት ወቅት ቢኖር ደግሞ ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ተቃርቦ ሲያጣና ጥቂት ደጋፊዎቻችን ደግሞ ባህርዳር ላይ የነበረንን ጨዋታ አይተውና ደግፈውን በሚመለሱ ሰዓት በሞት የተለዩን ጊዜ እነዚያን የማልረሳቸው ናቸው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከተመለከትካቸው ነገሮች የሚያበሳጭህ ነገር ምንድን ነው? ጉዞአችንና አካሄዳችን ትክክል ነው ብለህ ታስባለህ?
ሽመክት፡- በፍፁም፤ እንደ እኔ አመለካከት ሁሉ ቦታ ላይ ስትሄድ ብዙ ጊዜ ሰዎች የራሳቸውን ሀሳብ ብቻ ነው የሚያንፀባርኩት፤ እኔም ብቻ ነኝ ትክክልም የሚሉ ይበዛሉ፤ ሌላው ደግሞ በፌዴሬሽን አካባቢ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ክለቦችን በመለያየት እና አንዱን ክለብ የእገሌ ነው አንዱን ክለባ የዛኛው ነው በሚል በመከፋፈል እኩል ፍርዶች የማይሰጡበት ሁኔታም አለና ይሄ ድርጊት ደግሞ የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎችንም እርስበርስ እንዲጣሉም መንገድን የሚከፍትበት ሁኔታም ስላለ በእዚህ ኳሱ ሁሌም ከሚጎዳ ከዚህ ደርጊት ልንቆጠብ ይገባል፤ ስለዚህም ለሁሉም ክለብ እኩልና ትክክለኛ የሆኑ ውሳኔዎችን በመወሰን የእግር ኳሳችን ላይ ለውጥን ልንፈጥር የምንችልበት ስራ ላይ ብናተኩር ጥሩ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ከባህር ማዶ የማን ደጋፊ ነህ?
ሽመክት፡- የማንቸስተር ዩናይትድ፡፡
ሊግ፡- በሊቨርፑል የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማንሳት ደስተኛ ነህ?
ሽመክት፡- አንድ አንድ ሰዎች በማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊነታቸው የሊቨርፑልን ዋንጫ ማንሳት ባይፈልጉም እኔ ግን እንደዛ አይደለውም፤ ከማንቸስተር ደጋፊነቴ ውጪ ሊቨርፑልን ዋንጫ ከማንሳቱ በፊት እንደዚሁም ደግሞ ቶተንሃምንም በጣም የማደንቃቸው ቡድኖች ናቸውና የሊቨርፑል ድል የሚገባው ነው፡፡
ሊግ፡- ሽመክት ወደ ትዳሩ ዓለሙ መች ዘልቆ ይገባል?
ሽመክት፡- አሁን ላይ የራሴ የሆነ አንድ ፕሮጀክት አለኝ እሱን ሳጠናቅቅም በአዲሱ ዓመት ላይ ያን እቅዴን ተግባራዊ በማድረግ የትዳር ዓለሙን የምቀላቀለው ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- በክልላችሁ ወላይታ በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ተጎድተዋል፤ በአንድ ታዳጊ ኳስ ተጨዋች ላይ ጨምሮም በሌሎች ላይ እስከ ሞት ደረጃም ላይ ሊደረስ ችሏል፤ ይሄን ስትሰማ ምን አልክ?
ሽመክት፡- በረብሻው በደረሰው አደጋ በጣም ነው ያዘንኩት፤ ምንም የማያውቁ ሰዎች ጭምርም ነው ሊጎዱና ሊሞቱ የቻሉት እና ፈጣሪ ሌላ ችግር ከመፈጠሩ በፊት በዚሁ ይብቃችሁ ይበለን፤ መንግስትም ለጉዳዩ ፍትህን በፍጥነት ይስጥም ነው የምለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ሽመክት፡- ፈጣሪ አገራችንን ይጠብቅልን፤ ኮሮናንም ያጥፋልን፡፡