በመሸሻ ወልዴ
የፋሲል ከነማው የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ሙጂብ ቃሲም ሲዳማ ቡናን በእሱ ሁለት ግቦች 2-0 ካሸነፉ በኋላ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናው አሁን ላይ ዋንጫ የሚያነሳውን ቡድን ከወዲሁ ለመለየት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነና ቡድናቸው ደግሞ በጣም መሻሻል እንዳለበት ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ባደረገው አጠር ያለ ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ ስለ ዕለቱ ድላቸው፣ ስለ ቡድናቸው እና ሌሎችም ጥያቄዎች ከጨዋታው በኋላ የቀረቡለት ሙጂብ ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
ሲዳማ ቡናን ስላሸነፉበት ጨዋታ
“በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው ቀዝቀዝ ያለ ነበር፤ መሪ ያደረገንን ግብም ወደ እረፍት ልናመራ በተዘጋጀንበት ሰዓት ላይ አስቆጥረናል፤ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሞቅ ባለውና ጥሩ ፉክክር በነበረው የሁለታችን ቡድኖች ጨዋታ አሁንም በእኔ አማካኝነት አጠቃላይ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ባስቆጠርኳት ተጨማሪ ግብ ግጥሚያውን አሸንፈናል፤ ያ ውጤትም ደስተኛ አድርጎኛል”፡፡
ስለ ተጋጣሚያችሁ
“ሲዳማ ቡናን ከምናውቀው አንፃር ቀዝቀዝ ብሎ ነበር የቀረበው፤ ቡድኑን እንደጠበቅነውም አላገኘነውም፤ እኛ የተሻልን ስለነበርን አሸንፈናቸዋል”፡፡
ፋሲል ከነማ እየተሻሻለ እና ለውጥን እያመጣ ነው?
“አሁን ላይ እንደዛ ማለት አልችልም፤ ፋሲል ከነማ ብዙ ነገር ይቀረዋል፤ በፊት በነበርንበት አቋም ላይ አይደለንም፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ነን፤ በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ውጤትን ከማምጣት አኳያ በመጨነቅ እና ከጀርባም በጫና ውስጥም ሆነን ስለምንጫወት በእንቅስቃሴ ደረጃ በመቀዛቀዝ ውስጥም ሆነን ነው የምንገኘው፤ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ግን ወደ ለውጡ መምጣታችን የማይቀር ነው፤ የተሻለ ነገርን ለማምጣትም እየጣርን ነው፤ ለእዛም እያንዳንዱ ጨዋታዎችን እያሸነፉ መጓዝም በቀጣይነት ለምናደርጋቸው ጨዋታዎች የሚረዳን ነገር አለ”፡፡
ፋሲል ከነማ ወደ አስፈሪ ቡድንነቱ ይመለሳል
“ኢንሽ ዓላ አሁን ላይ ጥሩ አይደለንም ማለቴ ሳይሆን ያንን በጣም አስፈሪ የነበረውን ቡድናችንን ግን ገና አላገኘነውም፤ ያን ለመመለስ እና ከእዛም በላይ የሆነን ቡድንም ለመፍጠር ነው እየጣርን የምንገኘው”፡፡
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ቡድኖች መሪዎቹን በነጥብ ተቃርበዋል፤ ሻምፒዮናው ማን ይሆናል?
“እውነት ነው፤ በሊጉ መሪዎቹም ሆኑ ከስር የሚከተሉት ብዙ ቡድኖች በነጥብ በጣም እየተቀራረቡ ነው፤ ከዛ በታች ያሉት ቡድኖችም ሊጉ ገና መጀመሩና የስድስተኛው ሳምንት ላይም ያለ ስለሆነ የመድረስ አቅም አላቸው፤ ዛሬ ላይ አይደለንም እኛ ማንም ቡድን ዋንጫን አነሳለው የሚልበት ጊዜ ላይ አይደለም የሚገኘው፤ ይሄን ዋንጫ በመጨረሻ የተሻለ የሆነው ቡድን ያነሳዋል”፡፡
ለፋሲል ከነማ ዘንድሮ በቁጥር ደረጃ ምን ያህል ግቦችን ያስቆጥር እንደሆነ
“በቁጥር ደረጃ ይሄን ያህል ግቦችን አስቆጥራለው ብዬ ቃል የገባሁትም ሆነ ያስቀመጥኩት ነገር የለም፤ ቡድናችን ብዙ የግብ እድሎችንም እንደበፊቱ የሚፈጥርም ቡድን አይደለም፤ እንደዛም ሆኖ ግን አላምዲሊላሂ ፈጣሪዬ እየረዳኝ ጎሎችን እያስቆጠርኩ ስለሆነ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከእዚህ በኋላም ቡድናችን ጥሩ ሲሆን ከእዚህ የበለጠ ግብ የማስቆጥር ነው የሚሆነው”፡፡
አንተ እና አቡበከር በ8 ግብ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራችሁ ነው፤ ምን ትላለህ?
“አቡኪን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እኔ አውቀዋለው፤ ጓደኛዬም ነው፤ በጣምም እወደዋለው፤ ጥሩ ታለንት ያለው ተጨዋች ነው፤ በጣምም የማደንቀው ጎበዝ ተጨዋች ነው፤ ሁለታችንም ለክለባችን ጎልን እያስቆጠርንም መሆኑ አስደስቶኛል”፡፡
በግልህ ያቀድከው
“እንደ አጥቂ ከእኔ የሚጠበቀውን ነገር አደርጋለው፤ ቡድኔ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣም እመኛለው”፡፡
የቀድሞ ቡድኑ ላይ ጎል ስለማስቆጠሩ
“ይሄ እግር ኳስ ነው፤ የቀድሞ ቡድኔ ነው ብዬ ጎልን አልምርም”፡፡
ስለ ወንድሙ አድናን
“አሁን ላይ በታችኛው ሊግ ይጫወታል፤ ጥሩ ችሎታ የነበረው እና ብዙ መጓዝ የሚችልም ነበር፤ አሁን ላይም መጫወት ይችላል፤ ትልቅ ደረጃ አለመድረሱ ይቆጨኛል”፡፡