ከቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ጋር በእግር ኳስ ህይወቱ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ጨምሮ የተለያዩ ጣፋጭ ድሎችን በወጣትነት ዕድሜው ሊጎናፀፍ ችሏል፤ በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ በሚጫወትበትና ተስፋ ሰጪም እንቅስቃሴ በሚያሳይበት የቀኝ መስመር የተከላካይ ስፍራው ላይ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ካመራ በኋላ ቡድኑ ባስመዘገበው አጠቃላይ ውጤት በጣም እንደሚቆጭና ያ ውጤትም የዘንድሮን የድሬዳዋ ከተማን ቡድን የማይመጥን እንደሆነም ፍሬዘር ካሳ ይናገራል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ቡድንን ካለፈው ዓመት አንስቶ በማገልገል ላይ የሚገኘውን ይኸውን ተጨዋች ስለ ዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአቸውና ስላሳለፈው የኳስ ህይወት እንደዚሁም ከራሱ ህይወት ጋር በተያያዘ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርቦለት ምላሽ ሰጥቶታል፤ ተከታተሉት፡፡
ስለ ትውልድ ሰፈሩና ስለ እድገቱ
“የተወለድኩት በአዲስ አበባ ከተማ ገዳም ሰፈር ነው፤ በልዩ ስሙም ከገዳም ሰፈር ውጪ ኦሲስ በሚል መጠሪያም ይታወቃል፤ የእኔን አስተዳደግ በተመለከተ ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ የእግር ኳስን እየተጫወትኩ ነው ወደዚህ ሙያ የመጣሁት፤ ያኔ ፉትሳልና በሙሉ ሜዳ ላይም በመጫወት ችሎታዬን አሻሽዬ ለዛሬ ደረጃ ላይ ልደርስም ቻልኩ”፡፡
የእግር ኳስን ልጅ ሆኖ ሲጫወት የዛሬ ደረጃ ላይ እደርሳለው ብሎ አስቦ እንደሆነ
“በፍፁም! ያኔ በሰፈር ደረጃና ለትምህርት ቤት ለቤተልሄም ነበር ኳስን ስጫወት የነበርኩት፤ በወቅቱ ኳሱን ስጫወትም ለስሜትና ለመዝናናት ከመጫወት በስተቀር ለእዚህ ደረጃ እበቃለው ብዬ አስቤ አላውቅም”፡፡
የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ቤተሰብ ጋር ስለነበረው አመለካከት
“ቤተሰቦቼ በእዛን ወቅት ስለ ኳስ ምንም የሚያውቁት ነገር ስላልነበር ፈፅሞ እንድጫወት አይፈልጉም ነበር፤ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ መግባቴን ሲያውቁና ስለ ኳስም በመጠኑ እያወቁ ሲመጡ ግን ከእኔ ጎን መሆን ጀመሩና ያበረታቱኝ ነበር”፡፡
በቤተሰቡ ውስጥ የእግር ኳስ ተጨዋቹ እሱ ብቻ እንደሆነ
“አዎን፤ ለእናቴም ለአባቴም ብቸኛው ልጃቸው እኔ ብቻ ነኝ፤ የእነሱ ልጅ በመሆኔና በኳስ ተጨዋችነቴም በጣሙን ደስተኛ ነኝ”፡፡
በልጅነት ዕድሜው ተምሳሌት እና ሞዴሉ ስላደረጋቸው ተጨዋቾች እንደዚሁም ከባህርማዶ ስለሚደግፈው ቡድን
“የእግር ኳስን መጫወት ስጀምር መጀመሪያ ላይ ብዙ ባላየውም ሞዴል አድርጌ የተነሳሁት ተጨዋች ደጉ ደበበን ነው፤ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከገባው በኋላ ደግሞ እሱን ጨምሮ ሳላህዲን ባርጌቾም ሌላው ተምሳሌቴ ተጨዋች ሲሆን ከእነሱ ውጪም አዳነ ግርማና አስቻለው ታመነም ከጥሩ ተጨዋችነታቸው ባሻገር ልክ እንደ ደጉና ሳላህዲን ሁሉ ለእኔም እዚህ ደረጃ ላይ መገኘትም አስተዋፅኦ ያደረጉ ስለሆኑም እነሱንም ጭምር ነው አርአያዬ የማደርገውና የማመሰግነው፤ ከባህርማዶ ክለቦች እኔ የምደግፈው ሊቨርፑልንና ሪያል ማድሪድን ነው”፡፡
በክለብ ደረጃ ገብቶ እግር ኳስን ለመጫወት ስላመራበት መንገድ
“የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ካጠናቀቅኩኝ በኋላ ነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ ለወጣት ቡድኑ የተጨዋቾች ምርጫን ያደርግ ስለነበር ለሙከራ ወደ እነሱ ጋር የሄድኩት፤ ጊዜውም 2005 ላይ ነበርና ለወጣት ቡድኑ ተመረጥኩ፤ ከዛም በዓመቱ ውድድር ለክለቡ ጥሩ የተጫወትን ተጨዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ታድጋላችሁ ተብለን ስንጠበቅ በጊዜው የነበረው አሰልጣኝ ዓለምሰገድ አንቼ ወደ አሜሪካ ሊያመራ በመቻሉ እኛ ሳናድግ ቀረን፤ እኔም ያኔ ቅ/ጊዮርጊስ የወጣት ቡድን ምርጫን ያደርግ ስለነበር ያን አልፌ 2006 ላይ ቡድኑን ተቀላቀልኩ”፡፡
ስለ ቅ/ጊዮርጊስ ቆይታውና ለክለቡ ስላደረገው የመጀመሪያ ጨዋታው
“ቅ/ጊዮርጊስን የተቀላቀልኩት ከወጣት ቡድኑ ጀምሮ ነው፤ ከቡድኑ ጋር እስከተለያየሁበት ሰዓት ድረስም በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ ያም ሆኖ ግን ከዚህ ከምወደው ቡድኔ ጋር የተለያየሁበትን ሁኔታ እስካሁን ድረስ ለማወቅ አለመቻሌ በጣም ነው የሚቆጨኝ፤ የእዚህ ቡድን ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት ቡድኑ ካለው ታላቅ ክለብነት አንፃር ብዙ ውጣ ውረድ ነገሮችን አሳልፌያለው፤ የሊጉን ዋንጫዎችንም አንስቻለው፤ የእዚህ ቡድን ተጨዋች ሆነህ መሸነፍ የማይታሰብና የማይጠበቅ ነገር መሆኑን ልረዳም ችያለው፤ ሁሌም ለእያንዳንዱ ጨዋታዎችም ራስህን በጣምም ታዘጋጃለህና በዚህ መልኩ ነው በ2008 በቢጫ ትሴራ ከተጫወትኩበት ጊዜ አንስቶ ቡድኑን እስከለቀቅኩበት 2011 መጨረሻ ድረስ ስጫወትም የነበርኩትና በዚህ ቡድንና እስካሁን ድረስ ባሳለፍኩት የኳስ ህይወቴም ብዙ ነገሮችን ለመማር እንደቻልኩ መናገርም እፈልጋለውኝ፤ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረግኩት የመጀመሪያዬ ጨዋታ ደግሞ በ2008 ላይ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በነበረን ነው፤ ቋሚ ተሰላፊ ሆኜም ነው ይህን ጨዋታ ያደርግኩት”፡፡
ለቅ/ጊዮርጊስ መጫወት መቻል
“ስሜቱ ከባድ ነው፤ ይህ ቡድን የሀገሪቱ ትልቅና በብዙ ደጋፊዎቹም ፊት ታጅበህ ኳስን ስለምትጫወት የተለየ አይነት የደስታ ስሜትም ይሰማካል፤ እኔም ያኔ በቡድኑ ሲኒየር ተጨዋቾች ብርታትና በኮቺንግ ስታፉ ድጋፍም እጫወት ስለነበርም በተለይ 2009 ላይ ብዙ ነገሮች እየቀለሉልኝ ሊመጡ ችለውም ነበርና ይህ ቡድን ለእኔ ራሴን እንድጠይቅም ያደረገኝ ቡድንም ነው”፡፡
ስለ ኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎው
“በእግር ኳስ ህይወቴ እንዲህ ያሉ የመጫወት እድሎችን ያገኘሁት ለቀድሞ ክለቤ ቅ/ጊዮርጊስ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ያደረግኩት ጨዋታና በአንድ ወቅትም የእዚሁ ቡድን ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት ለኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ የተጫወትኩበትን ነው፤ በተለይ ለቅ/ጊዮርጊስ በምጫወትበት ሰዓት ታላላቅ የአፍሪካ ክለቦች ከነበሩት የቱኒዚያው ኤክስፕሪያንስ፣ ከደቡብ አፍሪካው ማማሎዲ ሰንዳውንስ እና ከሌሎችም ቡድኖች ጋር በእዚሁ የወጣትነት ዕድሜዬ በአጠቃላይ ከ9 በላይ የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ያደረግኩባቸውም አጋጣሚዎች ስለነበሩ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ለእዚህ ታላቅ ቡድንም በእንደዚህ አይነት የውድድር መድረክ ላይ በመጫወቴም ራሴን እንደ እድለኛም አድርጌ እቆጥረዋለው”፡፡
በእግር ኳስ ህይወትህ በጣም የሚቆጭህ ግጥሚያ
“ያ ጨዋታ መቼም ቢሆን ከአህምሮዬ ፈፅሞ አይወጣም፤ ቅ/ጊዮርጊስ ከደቡብ አፍሪካው ሰንዳውንስ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ወደ ሩብ ፍፃሜው ስምንት ውስጥ የምንገባበት ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በጥቃቅን ስህተቶች በሜዳችን 1-0 ተሸነፍንና እልማችን ሳይሳካ ቀርቷል፤ በዛም እኔን ጨምሮ የቡድኑ ተጨዋቾች በጣም ልንቆጭም ችለናል”፡፡
ከቅ/ጊዮርጊስ በመለያየት ወደ ድሬዳዋ ከተማ ስላደረገው ጉዞ
“ከቅ/ጊዮርጊስ የተለያየሁበትን ምክንያት ከላይም ገልጬዋለው አሁንም ድረስ አላወቅኩትም፤ ባውቀው በጣም ደስ ይለኝ ነበር፤ ስላላወቅኩት ግን አሁንም ድረስ ይቆጨኛል፤ ያም ሆኖ ግን ከቡድኑ እንደተለያየው በቀጥታ ያመራሁት ወደ ድሬዳዋ ከተማ ክለብ ነበር፤ በዚህ ቡድን ቆይታዬም ዓምና በተወሰነ ደረጃ ጥሩ ልንቀሳቀስ ብችልም ኮቪድ መጣና ሊጉን አቋረጠው፤ ዘንድሮ ግን ጥሩ በመጫወት ራሴን በሚገባ ተመልክቼበታለው፤ በአቋሜም ላይ መሻሻሎችን አሳይቻለው፤ በመጪው ዘመን በሚኖረው የቤትኪንግ ውድድር ላይ ደግሞ ከአሁን በበለጠ ምርጥ ብቃት ላይ ለመገኘት ራሴን በደንብ አድርጌ አዘጋጀዋለው”፡፡
እንደ ድሬዳዋ ከተማ ተጨዋችነትህ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለእናንተ ቡድን እንዴት እንዳለፈ
“የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ለእኛ ሁለት አይነት መልክ ያለው ነው፤ የመጀመሪያውና ቅድሚያው አጀማመራችን ከመቀናጀት ችግር ጋር በተያያዘ ጥሩ አልነበረምና በጣም የተቆጨንበት ነው፤ በዚህም ውጤቶችን ልናጣ ችለናል፤ በኋላ ላይ ደግሞ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስ ወደ ቡድናችን ከመጣ በኋላ ባለን ስብስብ ላይ አንድአንድ ተጨዋቾችን ጨምሮ ጥሩ ነገርን በሜዳ ላይ እንድንሰራና በውጤት ደረጃም ቢሆን የስጋት ክልል ከሆነው የወራጅ ቀጠና ላይ እንድንወጣ አድርጎናልና ይሄ ሊፈጠር በመቻሉ በመጠኑም ቢሆን እንድንደሰት አድርጎናል”፡፡
የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ያስመዘገቡት ውጤት ለእነሱ በቂያቸው እንደሆነ
“በፍፁም፤ ለእኔ በቤትኪንጉ ተሳትፎአችን ድሬዳዋ ከተማን በሚገልፅ መንገድ ጥሩ ውጤት አስመዝገበናል አልልም፤ እንደ ድሬዳዋ ከተማ ተጨዋችነቴ ዘንድሮ ምንም እንኳን አጀማመራችን ላይ የልምድ ችግር ይሁን ሌላ አላውቅም በውጤት ማጣት መቀመጥ በማይገባን ደረጃ ላይ አስቀምጦን አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ቢያስቀምጠንም የሁለተኛው ዙር ላይ ግን በአዲሱ አሰልጣኝ አማካኝነት ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ መልኩ ውጤት አምጥተን በ10ኛ ደረጃ ላይ ሊጉን ለማጠናቀቅ በመቻላችንና ወደ ታችኛው ሊግ ባለመውረዳችን ብቻም ልንደሰት የቻልነው”፡፡
ከድሬዳዋ ከተማ ጋር መጪውን ዘመን ይቀጥል እንደሆነ
“እንደ ቡድኑ ተጨዋችነቴ የእኔ የውል ዘመን የሚጠናቀቀው ሰኔ 30 ቀን ነው፤ ከዛ በኋላ በሚኖረው የራሴ ውሳኔዬም ነው መቀጠሌ አልያም ደግሞ አለመቀጠሌ የሚታወቀው”፡፡
ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ እልሙ
“የእግር ኳስን ከአሁን ቡድኔ በፊት ለታላቁ ቅ/ጊዮርጊስና ጥሩ ስብስብም ለነበረው የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በወጣትነት እድሜዬ ላይ ተጫውቻለው፤ ይሄ የመጀመሪያው እልሜ ነበር፤ ቀጥሎ ደግሞ የማልመው ሀገሬን ወክዬ ለመጫወት በምፈልግበት ደረጃ ለብሔራዊ ቡድናችን ተመርጦ መጫወት መቻል ነውና ለዛ ባሉብኝ ክፍተቶች ላይ ራሴን በአካልም ሆነ በአህምሮ እያዘጋጀሁት እገኛለው”፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እንደተጠናቀቀ ስለሚገኝበት ሁኔታ
“መጀመሪያ አካባቢ እረፍት ላይ ነበርኩ፤ ከዛ በመቀጠል ደግሞ ላለፉት አንድ ወራቶች ያህል የዘንድሮ የሊግ ውድድር በዲ.ኤስ.ቲቪ የተላለፈበት አጋጣሚዎች ስላሉ የራሴን አቋም በቪዲዮ ደረጃ የተመለከትኩባቸው ሁኔታዎች ስላሉ ከዛ በመነሳት ራሴን ለመጪው የውድድር ዘመን በጥሩ ብቃት ላይ ይዤ ለመቅረብ እየተዘጋጀው ያለሁበት ሁኔታ ነው የሚገኘው”፡፡
ፕሪምየር ሊጋችን በዲ.ኤስ ቲቪ ስለመተላለፉ
“ይህ ሊሆን መቻሉ ለሁላችንም ጥሩ ነው፤ የሀገራችንን እግር ኳስም አንድ ደረጃ ወደላይ ከፍ ያደርገዋል፤ ሌላው የራስህን አቋም የት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም የምትረዳበት ሁኔታም ይኖራልና ጨዋታዎቹ መተላለፋቸው ይበል የሚያሰኝም ነው”፡፡
ስለ ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናነት
“እነሱ ዓመቱን ሙሉ የተሻሉ እና ምርጥ ነበሩ፤ ሌሎቹ ቡድኖች ደግሞ በእነሱ ደረጃ ጥሩ አለመሆናቸው ውጤትን አሳጥቷቸዋልና ለፋሲል ከነማ የዘንድሮ የሊግ ዋንጫ የሚገባው ነው፤ አራት ጨዋታ እየቀረውም ይህን ድልም ተቀዳጅቷልና አንድ ተመዝግቦ የማያውቅን ታሪክም ሰርቷል”፡፡
ስለ ውድድር ዘመኑ ኮከብ ተጨዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ ስለሆነው አቡበከር ናስር
“የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ዘንድሮ ያገኛቸው ሽልማቶች ከዕድሜው በላይ የበሰለ ብቃቱን ያሳየበት የውድድር ሲዝን ስለሆነ የሚገባው ነው፤ እኔ እንደውም ክብሮቹንና ሽልማቶቹን በተመለከተ ያንሰዋልም ነው የምለው፤ ከዛ በላይም አቡኪ ከሀገር ወጥቶ መጫወት ይገባዋል ብዬም ነው የማስበው”፡፡
የኡቡበከር ናስርን በኮከብነት መመረጥ ሰምተህ ለነገ እኔስ የሚል ነገርን በአህምሮህ አልጫረብህም…?
“ይሄማ መቼ ይቀራል ብለህ ነው፤ በዚህ በኩል ራስህንም ትጠይቀዋለህ፤ ከዛም ይህን የመመረጥ እድል ለማግኘት ጠንክረህ፣ ትሰራለህ”፡፡
ወደ ትዳር ዓለሙ አምርቶ እንደሆነ
“አሁን ላይ ወደዛ እየተቃረብኩኝ ነኝ፤ ወ/ሪት ቃልኪዳን ተስፋዬ የምትባል ፍቅረኛም አለችኝ፤ ከእሷ ጋር እንጣመራለን”፡፡
እናጠቃል
“በእግር ኳስ ተጨዋችነት እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ እኔን በተለያዩ ነገሮች ያገዙኝን አካላቶች ለማመስገን እፈልጋለው፤ ኪዳነምህረት ለእኔ ብዙ ነገርን አድርጋልኛለችና እሷ ቅድሚያን ትወስዳለች፤ ከዛ ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ እናቴን፤ ከእነሱ ውጪም በችሎታዬ ጥሩ እንድሆን ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞችም አሉ እነሱንና በአካባቢም ደረጃ የፉትሳል ጨዋታን ፒያሳ ሜዳ አካባቢ ስጫወት በችሎታዬ ላይ እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮችን አድርግ በሚል ይነግረኝ የነበረው አሰልጣኝ ታምሩ ከበደም ነበርና ለእነሱ ምስጋና ይደረስልኝ”፡፡