የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ቅ/ጊዮርጊስን ጨምሮ ለድሬዳዋ ከተማ እና ለአሁኑ ክለቡ ሀድያ ሆሳዕና እየተጫወተ የሚገኘው ፍሬዘር ካሳ በዘንድሮ የውድድር ተሳትፎአቸው ከአምናው ጥሩ የሚባል ውጤትን እንደሚያስመዘግቡ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል።
የሀድያ ሆሳዕና እግር ኳስ ቡድን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች የሆነው ፍሬዘር ካሳ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያም ቆይታን ያደረገ ሲሆን አጠቃላይ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል። ተከታተሉት።
ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግንሃለን?
ፍሬዘር፦ እኔንም የሊግ ስፖርት ጋዜጣ እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ በተራዬ ከልብ አድርጌ አመሰግናችኋለሁ።
ሊግ፦ የ2015ቱን የፕሪምየር ሊግ ውድድር ጅማሬን እንዴት ተመለከትከው? ስለ እናንተ ቡድን ተሳትፎስ ምን አልክ?
ፍሬዘር፦ በቅድሚያ የሊጉ ውድድር እንደ በፊቱ መቆራረጦች ሳይኖሩ በተባለበት ቀንና ሰዓት ላይ መጀመሩ በጣም ጥሩና አሪፍ ነው፤ ይህ አሰራር ለሌላ ጊዜም ሊቀጥል ይገባዋል። ወደ እኛ ቡድን ስመጣ ደግሞ የመጀመሪያውን ጨዋታ በመቻል በመሸነፍ ነበር ጅማሬን ያደረግነው። በእዛ ጨዋታ ላይ ድክመቶቾ ነበሩብንና ያን አሻሽለን በመምጣትና ጥሩም በመንቀሳቀስ ሲዳማ ቡናን በሰፊ ግብ ልናሸንፈው ችለናል። ከእዚህ በኋላም በሚኖሩን ጨዋታዎች የበለጠ ተጠናክረን በመምጣት በሊጉ ጥሩ የውድድር ጉዞን የምናደርግ ይሆናል።
ሊግ፦ ሀድያ ሆሳዕና ካለፈው ዓመት የሊጉ ተሳትፎ ምን ነገሮችን ተምሮ መጥቷል? የአምናው ውጤታችሁስ በጠበቃችሁት መልኩ የተገኘ ነው?
ፍሬዘር፦ አምና እንደ ተጨዋቾች ስብስባችን የተሻልን ነበርን፤ ያም ሆኖ ግን በአንዳንድ ምክንያቶች የምንፈልገውን ውጤት እንዳናሳካ አድርጎናል። በዘንድሮ የውድድር ተሳትፎአችን ደግሞ ምንም እንኳን አቋሙን ለመለካት የሲቲ ካፕ ተሳትፎን ባያደርግም ቡድናችን ከአምናው የሚማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ ጥሩና የተሻለም ነገርን የምንሰራም ይሆናል።
ሊግ፦ በፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ተሳትፎ ምን ውጤትን ማምጣት አልማችኋል? እንደ አንዳንድ ክለቦች በሊጉ መቆየት፣ የደረጃ ተፎካካሪ መሆን ወይንስ ለሻምፒዮናነት መጫወት….
ፍሬዘር፦ የእዚህ ዓመት የእኛ ዋንኛው እልማችንና እቅዳችን ካሉት የሊጉ ተፎካካሪዎች ጋር ጥሩ ጨዋታን አድርገንና በተሻለ መልኩም በልጠን ተጫውተን ለሻምፒዮናነት ሳይሆን የደረጃ ተፎካካሪ ሆነን ለመጨረስ ነው የተዘጋጀነው፤ ያንን የማድረግም አቅሙ አለን።
ሊግ፦ የእዚህ ዓመት የተጨዋቾች ስብስባችሁ በምን መልኩ የሚገለፅ ነው?
ፍሬዘር፦ የዘንድሮ የተጨዋቾች ስብስባችንን በተመለከተ አምና ብዙ ልጆች የለቀቁብን በመሆኑ በእነሱ ምትክ ስም ያላቸው ተጨዋቾችን ብዙ አላመጣንም፤ ያም ቢሆን ግን ልጆቹ ጥሩ አቅም ያላቸው እና አሪፍም ላይ የሆኑ ናቸው።
ሊግ፦ የእዚህ ዓመት የሊጉ ፉክክር ምን መልክ ይኖረዋል?
ፍሬዘር፦ ከአሁኑ እየታየ እንዳለው ውድድሩ ከባድ ይመስላል፤ አስቀድመህ ውጤትን ገምተህ የምትገባበት አይነት ውድድርም አይደለም። ትንሹ ክለብ ትልቁን ቡድን ሲያሸንፈውና በጣምም ሲፈትነው እያየንም ነው።
ሊግ፦ ለሀድያ ሆሳዕና ምን አይነት ግልጋሎትን ዘንድሮ ልትሰጥ ተዘጋጅተሃል?
ፍሬዘር፦ ለቡድናችን የሚጠቅሙ ብዙ ነገሮችን ከቡድኔ ልምምድ ውጪ በግሌም በምችለው አቅም ለማድረግ በጥሩ መልኩ እየተዘጋጀው ነው።
ሊግ፦ ወደ ቡድናችሁ የሚመጡ አዳዲስ ተጨዋቾችን በማላመዱ በኩል የሰራችሁት ስራ አለ?
ፍሬዘር፦ በአዲስ መልክ ከመጡት ጋር ከእዚህ በፊት ሌላ ቡድን ሆነው ሁሉ እንተዋወቃለን፤ ከእዛ አንፃር እነሱን ለማላመድ ጊዜ አልፈጀብንም። ከወዲሁ ካልተላመድክም ውጤቱ ላይ የሚያመጣው ችግርም አለና ከእነሱ ጋር በቅርብም እየሰራን ነው።
ሊግ፦ ለቅ/ጊዮርጊስ ጨምሮ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ ባሳለፍከው የኳስ ህይወት ደስተኛ ነህ?
ፍሬዘር፦ በጣም፤ ብዙ የተከፋሁበትን ጊዜንም አላስታውስም። ጥሩና መጥፎ ጊዜም ሊያጋጥምህ ስለሚችልም እንዳልከፋ ራሴን በጥሩ ሁኔታም አዘጋጀዋለሁ። በቆይታዬም ብዙ የተማርኳቸው ነገሮችም አሉ።
ሊግ፦ ከእግር ኳስ ውጪ ያሉትን ጊዜያቶችህን በምን መልኩ ታሳልፋለህ?
ፍሬዘር፦ ብዙ ጊዜዬን ባለትዳር ስለሆንኩኝ ከባለቤቴ ጋር ነው የማሳልፈው። ከእዛ ውጪም ማሻሻል ያሉብኝ ነገሮች ስላሉና ራሴንም ለጥሩ ደረጃ ለማብቃትም ስለምፈልግ የጂምናዚየም ልምምዶችንም እሰራለሁ። ሲቀጥል ደግሞ ሁሉም ተጨዋች የራሱ የሆነ ግብ አለው። ሀገርህን ማገልገልም ቀዳሚው ግብ ነው። ለእዛም ራሴን በሚገባ አሳይቼ ለቀጣዩ የዋልያዎቹ ስብስብ የመጀመሪያው ተመራጭ መሆንና ወደ ውጪ ወጥቶም መጫወት ዋንኛው ግቤ ነው።
ሊግ፦ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ነህ፤ እስካሁን በስምህ የተመዘገቡ ግቦች ስንት ናቸው?
ፍሬዘር፦ በስሜ እንኳን ያን ያህል የተመዘገቡ ጎሎች የሉኝም። አራት እና አምስት ግቦች ናቸው ያሉኝ።
ሊግ፦ እነዚህ ግቦች በግንባር ተገጭተው የገቡ ናቸው?
ፍሬዘር፦ አብላጫዎቹ አዎን።
ሊግ፦ ከአንተ የእግር ኳስ ህይወት ጀርባ የመሰረትከው ቤተሰብ አለ፤ በተ
ለይም ባለቤትህ፤ እሷ እንዴት ትገለፃለች፤ እንዴት ተዋወቃችሁ? ስሟስ ማን ይባላል? ልጅስ አፈራችሁ?
ፍሬዘር፦ ከባለቤቴ ጋር የተዋወቅነው በአጋጣሚ ነው። ቃልኪዳን ተስፋዬ ትባላለች። ከተወለደች ሁለት ወራት ያለፋት አቲ የተባለች ልጅም ልናፈራ ችለናል። ስለ ትውውቃችን ሳነሳ በሶሻል ሚዲያ ላይ ነው በመፃፃፍ ነው የተዋወቅነው። ከዛም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀራረብንና ግንኙነታችን ለፍቅር እና ለትዳር ሊበቃም ችሏል። እሷን በተመለከተ የምገልፃት ለእኔ ምርጧ ባለቤቴ ናት የምፈልገውን ነገር ሳልነግራት ታደርግልኛለች። ለእዛም ላመሰግናት እፈልጋለሁ።
ሊግ፦ ከአንተ የእግር ኳስ ህይወት ጀርባ ጥሩ ነገሮችን አድርገውልህ ልትገልፃቸው የምትፈልጋቸው ሰዎች አሉ?
ፍሬዘር፦ አዎን፤ ከፕሮጀክት ተጨዋችነቴ ጀምሮ እስከ ክለብ ደረጃ ያሰለጠኑኝ አሉ። የጥቂቶቹን ስማቸውን ብጠቅስ እነ ዘሪሁን ሸንገታ፣ ፋሲል ተካልኝ፣ አሳምነው ገብረወልድ እንደዚሁም ደግሞ ማርቲን ኖይና ሌሎችም አሰልጥነውኝ አሻራቸው እኔ ላይ አርፏልና እነሱን ጨምሮ ብዙ ነገር ያደረገችልኝን እህቴን ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።
ሊግ፦ ከሀድያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ፍሬዘር፦ በቅድሚያ የእኛ ደጋፊዎች ስለ ኳስ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። እዛ ከተማ ላይ በነበርንበት ሰዓት ላይም ልምምዳችንን በሚገባ ይከታተሉ ስለነበሩ በጥሩ ሁኔታ እንገናኝ ነበር። ከሀገር ሀገርም ጨዋታ ሲኖረን ይደግፉንም ነበር። በእነሱ እኛ በጣም ደስተኛም ነን። በእዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸውም እፈልጋለሁ።
ሊግ፦ በጨዋታ ዘመንህ እንደ ተከላካይ ስፍራ ተጨዋችነትህ ፈታኝ የሆነብህ አጥቂ ማን ነው?
ፍሬዘር፦ በእግር ኳስ ውስጥ ስትኖር ራስህን ሁሌም ዝግጁ ማድረግ ከቻልክ ነገሮችን መቆጣጠር ትችላለህ። ይህን ካልኩ በጨዋታ ዘመኔ በአህምሮም ሆነ በሁሉም ነገር ለእኔም ሆነ ለሌሎች የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾች ፈታኙ አጥቂ አሁን ላይ ለደቡብ አፍሪካው ማማሎዲ ሰንዳውንስ የሚጫወተው አቡበከር ናስር ነው። እሱን የምታቆመው በጥንቃቄ ስትጫወት እና አህምሮህ ፈጣን ከሆነ ብቻ ነው። ያለበለዚያ በእሱ ልክ የማታስብ ከሆነ ይቀጣሃልና ፈታኙና ትልቁ ተጨዋች አቡበከር ናስር ነው።
ሊግ፦ ወደ ባህርማዶ እግር ኳስ እናምራ፤ የማን ደጋፊ ነህ?
ፍሬዘር፦ የሊቨርፑል ደጋፊ ነኝ።
ሊግ፦ ከተጨዋቾች የምታደንቀውስ?
ፍሬዘር፦ ስቴፋን ጄራሬድንና ሰርጂዬ ራሞስን።
ሊግ፦ ሊቨርፑል አሁን ላይ በመሪው አርሰናል በ14 ነጥብ ተበልጦ በደረጃው ሰንጠረዥ 10ኛ ስፍራ ላይ ተቀምጧል። የክለቡን አቋም በሚመለከት ምን አልክ?
ፍሬዘር፦ አሁን ላይ ቡድኑን ካየነው በስኳድ ደረጃ ከእነ ሲቲ ጋር የምታነፃፅረው አይደለም። የስኳድ ጥበትም ይታይበታል። ከእዛ ውጪ ተጨዋቾችም ተጎድተውበታልና የአምናውንና የካቻምናውን ውጤት ማምጣት ተስኖታል። በቀጣይ ጨዋታዎች እንግዲህ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የምንጠብቅ ይሆናል።
ሊግ፦ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማን ያነሳል ብለህ ትጠብቃለህ?
ፍሬዘር፦ አሁን ላይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም ማንቸስተር ሲቲ ግን ለሻምፒዮናነቱ ቅድሚያውን የሚወስድ ይመስለኛል።
ሊግ፦ ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉ ሬንጀርስን 7-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፤ ይህን ስትመለከት ስለ እዚህ ውድድር ተሳትፎ ምን አልክ?
ፍሬዘር፦ ሊቨርፑልን ብዙ ጊዜ ስናየው ሊጉ ላይ ጥሩ ባይሆን በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ታገኘዋለህ። ዋንጫዎችን ያነሳበት እና ለፍፃሜም የቀረበበት ጊዜ ይገኛልና ዘንድሮም ጥሩ ውጤትን የሚያስመዘግብ ይሆናል።
ሊግ፦ ሊቨርፑልን የሰይዶ ማኔን በሽያጭ ማጣት ጎድቶታል፤ ትስማማለህ ?
ፍሬዘር፦ በጣም፤ የእሱ ተፅህኖ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ስለ ቡድኑ ውጤት ማጣት የታወቀውም እሱ ከለቀቀም በኋላ ነው።
ሊግ፦ በአዲስ ዓመት ላይ አንድ ሰው የራሱ የሆነ እቅድ አለው፤ አንተስ ምን ነገርን ነው ያቀድከው?
ፍሬዘር፦ ግዴታ አዲስ ዓመት ስለገባ ሳይሆን በየጊዜው የራስህ የሆነ እቅድ ይኖርሃል። እኔም ሁሌ የማቅደው ነገር ካሉብኝ ድክመቶች በመነሳት ከልምምድም ሆነ ከጨዋታ በኋላ ምንድን ነው የጎደለኝ፤ ምን ነገርን ማስተካከል አለብኝ በሚል በኳሱ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መገኘት መቻል ነው።
ሊግ፦ በየዓመቱ የተለያዩ በዓላቶች ይከበራሉ፤ ለአንተ የተለየው የቱ በዓል ነው?
ፍሬዘር፦ የእንቁጣጣሽ እና የፋሲካ በዓላቶች ናቸው ለእኔ ለየት የሚሉት፤ እነሱ ጥሩ ስሜትንም ይሰጡኛል።
ሊግ፦ ለሙዚቃ እና ለመዝሙር ስላለ ፍቅር አንድ ነገርን ብትል?
ፍሬዘር፦ ሙዚቃንም መዝሙርንም በጣም ነው የምወደው፤ እነሱን የምታዳምጥባቸው ጊዜያቶችም አሉና እሰማቸዋለሁ። መዝሙር ብዙ ጊዜ ራስህን እንድታዳምጥ የሚረዳህ ስለሆነም መስማቱ በጣም ያስደስተኛል።
ሊግ፦ በሙዚቃው ዓለም በጣም የምታደንቀው ማንን ነው?
ፍሬዘር፦ ቴዎድሮስ ካሳሁንን /ቴዲ አፍሮ/ እና ጂጂን ነው የማደንቃቸው።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዛሬ የቀድሞ ክለብህን ድሬዳዋ ከተማን ትፋለማላችሁ፤ ከጨዋታው ምን ውጤትን ትጠብቃለህ?
ፍሬዘር፦ ለእዚህ ጨዋታ በሚገባ እየተዘጋጀን ነው ያለነው፤ ሁሌም የፊት የፊቱን ጨዋታዎች ስለምናስብም ከግጥሚያው ሶስት ነጥብን ይዘን ለመውጣትም የግጥሚያውን ሰዓት እየተጠባበቅን ነው።
ሊግ፦ ካለፉት ዓመታቶች ጀምሮ ሊጋችን በዲ ኤስ ቲቪ መተላለፍ ስለመቻሉ ምን አልክ ?
ፍሬዘር፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዲ ኤስ ቲቪ መተላለፍ መጀመሩ ለሊጉ ብቻ ሳይሆን ለእግር ኳስ ተጨዋቾች ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው። አቡበከር ናስርንም ገበያ ላይ እንዲወጣ አድርጎት ለማማሎዲ ሰንዳውንስ እንዲጫወትም አድርጎታል። ከእዚህ በኋላም የእግር ኳስ ተጨዋቹ የተሻለ ነገርን የሚሰራ ከሆነም ወደ ሌላ ሀገራት ወጥቶ መጫወትም ይችላልና በእዚህ አጋጣሚ ይህ ጨዋታው የቀጥታ ስርጭትን አግኝቶ እንዲተላለፍ እና ዲ ኤስ ቲቪም እንዲመጣ ያደረጉትን ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ።