Google search engine

“ውጤት ያጣነው በኳስ ሚያጋጥም ሽንፈት እንጂ በምንከተለው የጨዋታ ፍልስፍና አይደለም ” ሚኪያስ መኮንን /ኢትዮጵያ ቡና/

በመሸሻ ወልዴ


የኢትዮጵያ ቡናው ሚኪያስ መኮንን በአሁን ሰዓት ለክለቡ በሚጫወትባቸው ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል፤ በቡና ክለብ ውስጥ የአራት ዓመታት ቆይታ ያለውን ይኸውን ተጨዋች በክለቡ የዘንድሮ የሊጉ ተሳትፎአቸው ዙሪያ እና ስለራሱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳለት አናግሮታል፤ ተጨዋቹም ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዙር ተሳትፎአችሁን በ11ኛ ደረጃ አጠናቃችኋል፤ የእስካሁን ጉዞአችሁን እንዴት አገኘኸው?
ሚኪያስ፡- በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያው ዙር ተሳትፎአችን ከምንከተለው አዲስ የጨዋታ ፍልስፍና፣ ከያዝነው አዲስ አሰልጣኝና ብዙዎቹ የቡድናችን ተጨዋቾችም አዲስ ከመሆናቸው አንፃር አሁን የያዝነው ውጤትና የምንገኝበት ደረጃ መጥፎ የሚባል አይደደም፤ ምክንያቱም ከአንድ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በፊት ወራጅ ቀጠናው ላይ ነበርንና ከዛ መሻሻልን እያመጣን በመምጣት የአሁን ሰዓት ላይ ከዛ ደረጃ በመውጣት በጥሩ አቋማችን ላይ ነው የምንገኘው የሁለተኛው ዙር ላይም ከመጀመሪያው ዙር ክፍተቶቻችን ብዙ ነገሮችን እያስተካከልን ስለምንጓዝ በጨዋታም ሆነ በውጤት ደረጃ ከፍተኛ ለውጦችም ነው በሜዳ ላይ የሚኖረን፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና የወራጅ ቀጠናው ላይ በነበረበት የቅርብ ሰዓት የቡድኑን ደጋፊዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከትቶአቸው ነበር፤ ያኔና አሁንስ እናንተን ካላችሁበት ደረጃ አኳያ ያላችሁበት ደረጃ አያሰጋችሁም?
ሚኪያስ፡- በፍፁም፤ ምንም ስጋት ውስጥ የሚከተን ነገር ፈፅሞ የለም፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ክለብ እና ቀጣይ የሊጉን ጨዋታዎች ሲያደርግ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ተጋጣሚዎቹን በምን መልኩ በልጦ ማሸነፍ እንደሚችል የሚያውቅ ቡድንም ስለሆነ ነው፤ የሊጉ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ሲጀምር ቡድናችን በእዚህ ደረጃ ላይ መገኘት ፈፅሞ አልነበረበትም ነበር፤ ለዛም ነው መጀመሪያ ላይ ወራጅ ቀጠናው ላይ በነበርንበት ሰዓት ደጋፊዎቻችን ስጋት ውስጥ ገብተው የነበረው፤ እኛ ግን በጊዜውም ሆነ አሁን ውጤታችን እንደምንፈልገው ሊሳካልን ባልቻለ ሰዓት እንደእነሱ ብዙም የሚያሰጋን ነገር አልነበረም፤ ይህን ልል የቻልኩት ከፊታችን ገና 15 ጨዋታዎች ከፊታችን ያሉ በመሆኑና ብዙም የምናሻሽላቸው ነገሮች ስላሉም ነው፤ ስለዚህም በቀጣይ የሊጉ ጨዋታዎቻችን ዋንጫ እናገኛለን ብለን ባናስብ እንኳን ጥሩ ቡድንና ጥሩ አሰልጣኝም ስላለን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን የሊጉን ውድድር እንጨርሳለን፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ የጨዋታ ፍልስፍና ነው የዘንድሮው ውድድር ላይ የገባው፤ የቡድኑ ታክቲክ እንደግልም እንደቡድንም ለአንተ ተመችቶሃል?
ሚኪያስ፡- በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው እንደ ቡድንም እንደግልም ለእኔ አዎን! በጣም ተመችቶኛል ነው የምለው፤ ሊጉ ሲጀመር ታክቲኩ አዲስ ከመሆኑ አኳያ ላይገቡን የቻሉ ነገሮች ነበሩ፤ አሁን ግን እየገባንና በእንቅስቃሴያችንም እየተሻሻልን መሄዳችንን ስናየው ቡና የያዘው የጨዋታ ፍልስፍና ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚጠቀም ብዙ ነገሮችንም አይተንበታልና ያ በጣሙን ነው እያስደሰተኝ የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ቆይታህ ላይ ብዙ አሰልጣኞችን አይተኸል፤ አሁን ደግሞ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በመመራት እየሰለጠንክ ይገኛል… በእነዚህ አሰልጣኞች ከመመራትህ አኳያ እንዴት አገኘኸቸው?
ሚኪያስ፡- በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ቆይታዬ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ጨምሮ ብዙ አሰልጣኞችን አይቻለሁ፤ ለእኔ ሁሉም ጥሩዎችም ናቸው፤ መጥፎ አሰልጣኝም አጋጥሞኝ አያውቅም፤ ካሳዬ ደግሞ ከሁሉም በላይ ጥሩ አሰልጣኝ ነው፤ በጣም የሚገርምና ጥሩ ስብዕናም ያለው ሰው ነው፤ እንደ አሰልጣኝ ሳይሆን እንደ ተጨዋችም ነው ሰዎችን የሚረዳው፤ ተጫውቶ ያሳለፈ ስለሆነ እኛን የሚረዳበት መንገድ የሚገርም ነው፤ ከዛ ውጪም የራሱን የአጨዋወት ፍልስፍና ይዞ መጥቷል፤ ላመነበትም ፍልስፍና መቶ ፐርሰንት እየታገለ ያለ አሰልጣኝ በመሆኑም ለእሱ ልዩ ቦታ ነው የምሰጠው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አማካኝነት የሚከተለው የጨዋታ ፍልስፍና በአንተ አንደበት እና አመለካከት እንዴት ይገለፃል?
ሚኪያስ፡- የአሁን ሰዓት ላይ እየተከተልን ያለነው የጨዋታ ፍልፍስና ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን በእንቅስቃሴ ደረጃ የበላይነቱን ይወስዳል የሚለውን ነው፤ ይሄም ማለት አሁን አለም ላይ የሚታየው እነ ማንቸስተር ሲቲና ባርሴሎና የመሳሰሉት ክለቦች እንደሚከተሉት አይነት እንደማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እንደውም ሁሉም ቡድኖች ይሄንን የጨዋታ ፍልፍስናን ከተወሰኑ አሰልጣኞች በስተቀር እየተከተሉት ይገኛል፤ ይሄ ፍልስፍና እኛ ሀገር ላይም አሁን ላይ በእኛ እየተሞከረና እየተጀመረም ስለሆነ ወደፊት በሂደት መሻሽሎች ሲኖሩና የተጨዋቾች ጥራት ሲመጣ እንደዚሁም ደግሞ አንድ አንድ ነገሮችም እየተስተካከሉ ሲመጡ እንቅስቃሴው ይበልጥ ይሻሻላል ሌሎች አሰልጣኞችም የእዚያ ተከታይም ይሆናሉ ብዬም አስባለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና እንደትልቅ ቡድንነቱ ስኬታማ ውጤትን እያስመዘገበ አይደለም፤ ዋናው የቸገራችሁ ነገር ምንድነው?
ሚኪያስ፡- የአሁን ሰዓት ላይ ቡድናችን በሚፈለገው እና በሚጠበቀው መልኩ ውጤት እያጣ ያለው ኳስ ስለሆነ ብቻ እንጂ በጨዋታ ፍልፍስናችን ወይንም ደግም ሌላ ነገር ተፈጥሮ አይደለም፤ በኳስ ጨዋታ ውስጥ ውጤት ማግኘትና ውጤት ማጣት ያጋጥማል፡፡ ውጤት ያጣነውም ሽንፈት በሚያጋጥመን ሰዓት ጫናዎች ስለሚፈጠሩብንም ነው፤ የወላይታ ድቻን ቡድን ባለፈው ጨዋታ ስናሸንፍ ይሄን ግጥሚያ ያሸነፍነው ከወልቂጤ ከተማ እና ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየንበት ጨዋታ በፊት አድርገነው የነበረ ቢሆን ሁሉንም ጨዋታ ነበር እናሸንፍ የነበርነው እና እኛን እየጎዳን የነበረው ውጤት ሲጠፋ ጫና ውስጥ የምንገባበት ሁኔታ ስለሚኖር እና በስነ-ልቦናው ስለምንወርድ ብቻ ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና የሚከተለውን አጨዋወት የሚደግፉም የማይደግፉም ደጋፊዎች አሏችሁ..እነሱን እንዴት ነው የምትመለከቷቸው?
ሚኪያስ፡- የአሁን ሰዓት ላይ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ተጨዋችነቴም ሆነ የሌላ ቡድን ተጨዋች ብሆን እንኳን ክለባችን ውስጥ ከተመለከትኩት ነገር በመነሳት የምንከተለው የጨዋታ ፍልስፍና በጣም አዋጪ ስለሆነ የዛ እንቅስቃሴ ደጋፊ ነኝ፤ ይህ እንቅስቃሴም አለም ላይም እየታየ ከመሆኑ አንፃር ለደጋፊዎቹ ከፍተኛ ክብር አለኝ፤ እንቅስቃሴውን የማይደግፉም ካሉ የራሳቸው አስተሳሰብ እና መብታቸው ነው፡፡ ግን ጥሩ ፍልስፍና ስለሆነ መቀራረብ ይቻላል ብዬ አስባለው፡፡
ሊግ፡- በያዛችሁት እንቅስቃሴ ተቃውሞ ሲቀርብባችሁ ምን አይነት ነገር ውስጥ ነው የምትገቡት? አሰልጣኛችሁስ ያኔ ምንድን ነው የሚላችሁ?
ሚኪያስ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ተቃውሞ ውስጥ መግባት ያለ ነገር ነው ምክንያቱም ሁሉም ሰው ሊወድህና ሊደግፍህ እንደዚሁም ደግሞ ስትሸነፍ አይዞህ ሊልህ አይችልምና የቡና ደጋፊ ደግሞ ሁሌም ማሸነፍን ይፈልጋል ደግሞም ማሸነፍም የሚገባው ደጋፊ ነው፤ ደጋፊው ማሸነፍን ስለሚፈልግ ተቃውሞ ያመጣብሃል፤ ተቃውሞውም ጫና ውስጥ ይከትሃል፤ በእዚህ ሰዓት ብዙ ሰው አብሮህ ላይሆን ይችላል፤ በእዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ግን እኛ እንደውም በጣም እድለኞች ነን አሰልጣኛችን ከጎናችን አለና አይዟችሁ ብሎን ነው ብዙ ነገሮችን የሚከላከልልንና ስለዚህም ይህን ከተረዳን ጫናዎችን ተቃቁሞ ማለፉ የእኛው ኃላፊነት ነው፡፡
ሊግ፡- የአንደኛው ዙር ተጠናቋል፤ በሁለተኛው ዙር በምን መልኩ ነው የምትመጡት?
ሚኪያስ፡- የአንደኛው ዙር የውድድር ጉዞአችንን ከውጤት አንፃር በምንፈልገው ደረጃ ላይ ራሳችንን አላስቀመጥነውም፤ ስለዚህም የሁለተኛው ዙር ላይ በራሳችን ጥቃቅን ስህተቶች ያጣናቸው ግጥሚያዎች ላይ ጠንክረን በመስራት ክፍተቶቻችንን በመድፈን የአጨራረስ ችግሮቻችንን በማስተካከል የሊጉ ጠንካራና ጥሩ ተፎካካሪ ቡድን እንሆናለን ብዬ አስባለው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈትን ባስተናገደበት ጨዋታ ጎል ያስቆጥራል፤ በአዳማ ከተማ ሲሸነፍ ደግሞ ጎል አላስቆጠረም… ጨዋታው ከብዶት ነበር ማለት ይቻላል?
ሚኪያስ፡- አዎን፤ የአዳማው ጨዋታ ለእኔ በሊጉ ከገጠምናቸው ቡድኖች እንደ ቡድን አቀራረባቸው በጣም የከበደንና ጠንከር ያለብንም ግጥሚያ ነበር፤ ሁሉም ቡድን ከእኛ ጋር ለመጫወት ሲመጣ እንደ ቡድን ከሌላ ቡድን ጋር እንደሚጫወተው ሳይሆን እኛን ለመቆጣጠር እና ጨዋታችንን ለማበላሸት ነው የሚመጡት፤ አዳማዎች ግን በኳስ ቁጥጥር ባይበልጡንም በ90 ደቂቃው እንቅስቃሴ እኛን ለመቆጣጠርና ከራሳችን ሜዳም እንዳንወጣ ያደረጉበት ሁኔታ ስላለ ለዛም ነው አሸንፈውን ሊወጡ የቻሉት፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና መጀመሪያ ላይ አትሰለፍም ነበር፤ አሁን ደግሞ ተሰልፈህ እየተጫወትክ ነው፤ ምንድን ነው ምክንያቱ?
ሚኪያስ፡- እሱ የአሰልጣኝ ስራ ነው፤ መጀመሪያ ላይ ሳልሰለፍ የቀረሁት ከጉዳት ከመምጣቴ አኳያ የሰውነት ክብደቴ ጨምሮ ስለነበር እና ወደ ማች ፊትነሴም ስላልመጣው ነው፤ አሁን ግን አሰልጣኙን በችሎታዬ አሳምኜ እየተጫወትኩ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- ተጠባባቂ ተጨዋች በምትሆንበት ጊዜ ታኮርፋለህ?
ሚኪያስ፡- በፍፁም፤ ምክንያቱም ይሄ ኳስ ነው፤ ለጓደኞቼም እንደዛ አይነት ፊትን ማሳየት አልፈልግም፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ ቆይታ ከአንድአንድ ተመልካቾች አንድአንዴ መሳሳትን ስትፈጥር ተቃውሞ የሚቀርብብህ ወቅት ይታያል…ያኔ ምንድን ነው የሚሰማህ?
ሚኪያስ፡- እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲቀርቡብኝ እኔ ሁሌም ኳስ ነው ብዬ ነው ነገሮቹን የማልፋቸው፤ አይደለውም እኔ በዓለም ላይም ምርጥ የሚባሉ ተጨዋቾች ይሳሳታሉና ሜሲን ብትውስድ እንደሚወደደው ሁሉ የማይወደውም አለና እኔን እንዲህ ያሉ ነገሮች አይረብሹኝም፤ ጫናዎች ውስጥም አይከቱኝም፡፡
ሊግ፡- ብዙዎች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ጥሩ የኳስ ችሎታ እና ብቃቱ እንዳለህ ቢያምኑም ኳሱን አይለቅም፤ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችና ህዝቡን ጭምር ካላለፈም ኳስን አይሰጥም በሚልም ይተቹሃል?
ሚኪያስ፡- ኸረ! ኳስ አልለቅም እንዴ? ከቦታዬ አንፃር ሲጀመር እኔ በዛ ደረጃ ላይ የምገለፅ ተጨዋች አይደለውም፤ ምክንያቱም እኔ እንደ ተከላካዮችና አማካዮች ኳስን በአንዴ መስጠት የለብኝምና የእኔ የጨዋታ ቦታ ከመስመር ላይ ነው የምነሳው በዛም ስፍራ ላይ ስጫወት ድሪብል ማድረግ ይጠበቅብኛል፤ ከዛ በኋላም ሰብሬ ወደውስጥ መግባትም ጎል ለማግባትም መጣር ይኖርብኛልና በዛ ደረጃ ነው የምጫወተው መስጠት ካለብኝም ወዲያው ነው ለጓደኞቼ ኳስን የማቀብለው፡፡ አትለቅም ከተባልኩ እንኳን አንድአንዴ እኮ አለመልቀቅም ጥሩ ነው ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ተጨዋች እኛ ሀገር የለምና፡፡
ሊግ፡- ጎል ማስቆጠር አልናፈቀቅም?
ሚኪያስ፡- በጣም ነው እንጂ የናፈቀኝ፤ ምክንያቱም በቡና ቆይታዬ እስካሁን ጎል አላስቆጠርኩምና፡፡ ያም ሆኖ ግን ዋናው ነገር ጎል ጋር መድረስም ነውና አንድ ቀን ለቡና ጎሎችን ማግባቴ አይቀሬ ነው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት የተለየ ስሜት አለው?
ሚኪያስ፡- አዎን፤ ኢትዮጵያ ቡና ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ቡድኖች ትልቁ ነውና ለክለቡ ሁሌም ቢሆን በጣም ደስ ይለኛል፤ ጓደኞቼም በእኔ መጫወት ይደሰታሉ፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት እልምህ ነበረ?
ሚኪያስ፡- እኔንጃ፤ እኔ ትልቅ ቦታ ደርሼ እጫወታለው ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፤ ለቡናም እጫወታለው የሚል እልም አልነበረኝም፤ ሁሉም የሆነው በአጋጣሚዎች ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ በምን ሙያ ላይ እንገናኝ ነበር?
ሚኪያስ፡- ዝም ብዬ ሠፈር ውስጥ የምውል ይመስለኝ ነበር፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ጥሩ ችሎታ የነበረህ ተጨዋች ነበርክ… ወይንስ ኳስን ብዙ የማትችል?
ሚኪያስ፡- ኸረ ድሮ በጣም ሃይለኛ ተጨዋች ነበርኩ፤ እያደግኩ ስመጣ ግን ያለህን ችሎታ የሚነጥቁ አሰልጣኞች ስለሚኖሩ ያ ድንቅ ችሎታ አሁን ላይ ጠፍቶኛል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ልጅ ሆነህ ስትጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመልክቶህ ለወደፊቱ ትልቅ ደረጃ ላይ ትደርሳለህ ያለህ ሰው ማን ነው?
ሚኪያስ፡- እስማኤል አቡበከር ይመስለኛል፤ ለሐረር ሲቲ ታዳጊ ቡድን እሱ መልምሎን ስንገባ አንተ ራስህን ጠብቅ ጂምም ስራ ትልቅ ደረጃም ላይ ትደርሳለህ ብሎ በመምከር ነው ለወደፊቱ የሆነ ነገር እንዳስብ ያደረገኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት የማን ችሎታ ነው ቀልብህን የሳበው?
ሚኪያስ፡- የምንያህል ተሾመ /ቤቢ/ ነዋ! ያኔ አባቴ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ እንድንመለከት ስታድየም ይዞኝ ገብቶ ነበር፤ ገና እንዳየሁት ሕፃን ብሆንም በእውቀት ኳስን ባላይም አጨዋወቱን ወደድኩትና የእሱ አድናቂው ሆንኩኝ፡፡
ሊግ፡- አንተ ተወልደህ ባደግክበት አካባቢ ምን ይበዛል…? ስፖርተኛ፣ ነጋዴ፣ ምዑር፣ ወይንስ አርቲስት? አካባቢህን እንዴት ትገልፀዋለህ?
ሚኪያስ፡- የትውልድ አካባቢያችን ጉቶ ሜዳ ነውና ስፖርተኛ ይበዛል፤ ያም ሆኖ ግን በእዛ አካባቢ እንዳለው የተጨዋቾች ችሎታና አቅም ብዙ ልጆች ለትልቅ ደረጃ አልበቁም ይሄ ያናድደኛል፤ ሰፈራችንን በተመለከተ በጣም ጥሩ ሰፈር ነው፤ ሰፈሩ ጥሩ ተጨዋቾችንም ማፍራት ይችላል፤ አሁን ግን ሜዳውን አጥረውት ወጣትና ተጨዋች ከዛ አካባቢ እንዳይወጣ እያደረጉት ይገኛልና በዚ ላይ የሚመለከተው አካል ሊያስብበት ይገባል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትክበት ጨዋታ የትኛው ነው.. ያኔ ደጋፊዎቹን እንዴት አገኘሃቸው?
ሚኪያስ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትኩት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በተደረገው የአባይ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ነው፤ ጥሩም ነበርኩ፤ ደጋፊዎቹንም እኔ እየተጫወትኩ ሳያቸው የሚገርሙ ሆኖም ነው ያገኘዋቸው፤ ከዛ በኋላም ጀምሮ እነሱ የሀገር ኩራት እና የተለዩም ናቸው የሚለውን ነገር እኔም ለማረጋገጥ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- ለቡና ከመጫወትህ አኳያ ትልቅ ተጨዋች ነህ?
ሚኪያስ፡- አይደለውም፤ ግን ትልቅ ቡድን ውስጥ እየተጫወትኩ ነው፤ ስለዚህም ትልቅ ተጨዋች ለመሆን ጥረትን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- በጣም የምትደሰትበት ነገር በምንድን ነው?
ሚኪያስ፡- የተቃራኒ ቡድን ተጨዋች ላይ ሎጬ በማግባት፡፡
ሊግ፡- የሚከፋህስ?
ሚኪያስ፡- ቡድናችን በሚሸነፍበት ጊዜና አንድ ነገርን ማድረግ ሳልችል ስቀር፡፡
ሊግ፡- ሙዚቃ ትወዳለህ? ማንን ታደንቃለህ?
ሚኪያስ፡- ሙዚቃ በጣም ነው የምወደው፤ ቴዲ አፍሮንም ነው የማደንቀው፡፡
ሊግ፡- ከባህር ማዶ ክለቦች የማን ደጋፊ ነህ? የማንስ ተጨዋች አድናቂ ነህ…በዓለም ላይ ብታገኘው በጣም ደስ የሚልህስ ሰው… ብታገኘውስ ምን ትለዋለህ?
ሚኪያስ፡- የአርሰናል ደጋፊ ነኝ፤ የማደንቀው ተጨዋች ደግሞ ሊዮኔል ሜሲንና ጃክ ዊልሸርን ነው፤ ሜሲን ባገኘው ደግሞ በጣም ደስ ይለኛል፤ ባገኘውም እንደምወደውም እነግረዋለሁ፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ተመርጠህ ነበር.. ያኔ መመረጥህን ጠብቀህ ነበር?
ሚኪያስ፡- በፍፁም፡፡ እኔ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ብዙ አላስብም ነበር፡፡ ኳስ መጫወትን ብቻም ነበር እፈልግ የነበረው፡፡ ያም ሆኖ ግን በተመረጥኩበት ጨዋታ ላይ ግብፅን ስናሸንፍ ጎል ከማስቆጠሬ ባሻገር ምርጥ የሚባል ብቃትንም ለማሳየት ችያለው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ስትጫወት የሚቆጭህ ነገር?
ሚኪያስ፡- እስካሁን ለክለቤ ጎል አለማስቆጠሬ ነው የሚቆጨኝ፡፡
ሊግ፡- ከአጠገብህ አብሮ ተጣምሮ ሲጫወት ደስ የሚልህ?
ሚኪያስ፡- በተደጋጋሚ ጊዜ ስለተጫወትንና በጣምም ስለምንግባባ ከጓደኛዬ አቡበከር ናስር ጋር ስንጫወት ነው በጣም የሚስማማኝ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ውስጥ አዝናኙ እና ቀልደኛው ተጨዋች?
ሚኪያስ፡- ታፈሠ ሠለሞን፡፡
ሊግ፡- ዝምተኛውስ?
ሚኪያስ፡- አስራት ቶንጆ፡፡
ሊግ፡- አኩራፊውስ?
ሚኪያስ፡- እኛ ጋር ማንም የለም፡፡
ሊግ፡- የአንተ የቅርብ ጓደኛ?
ሚኪያስ፡- አቡበከር ናስር፤ እሱ ከጓደኛም በላይ ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በአጭር ቃላት?
ሚኪያስ፡- ከፍቅርም በላይ ነው፡፡
ሊግ፡- ቡናን ከሌሎች ቡድኖች ምን ይለየዋል?
ሚኪያስ፡- በብዙዎች የሚወደድ፣ ጥሩ ኳስ የሚጫወት እና ያማረ ደጋፊዎች ያሉት ነውና ይሄ ይለየዋል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
ሚኪያስ፡- የኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬ ላይ ለክለቤ የሚጠበቅብኝን ነገር አድርጌ ውጤታማ ተጨዋች ለመሆን ጥረትን አድርጋለው፤ የሀገሬን ብሔራዊ ቡድንም የምጠቅምበት ጊዜ አንድ ቀን ስለሚኖር ከተሳካ ያንን ወቅት ብዙም ሳልጓጓ እጠብቃለው፤ ከዛ ውጪ ማለት የምፈልገው ደግሞ በኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሴ ምርጥ የሆኑትን ቤተሰቦቼን እና በተለይም ደግሞ አባቴን በጣሙን እንደምወደውና እንደማመሰግነው ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P