Google search engine

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው ለሲዳማ ቡና ከቀኝ መስመር በመነሳት ክለቡን እያገለገለ የሚገኘው ሀብታሙ ገዛኸኝ በሊጉ የዘንድሮ ውድድር ክለባቸው ዋንጫውን ለማንሳት እንደሚጫወት አስተያቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፡፡
የሲዳማ ቡና ክለብ ውስጥ የአሁን ሰዓት ላይ 4 ግቦችን ከማስቆጠር ባሻገር ከ7 ያላነሱ የግብ ኳሶችን ለአጥቂዎች ያቀበለው ይኸው ተጨዋችን በተጨዋችነት ሕይወቱ ዙሪያና ስለ ክለባቸው የሊጉ ጉዞ አናግረነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- የትውልድ ስፍራ የት ነው? የእግር ኳስ ጨዋታ ጅማሬህስ ምን ይመስላል?
ሀብታሙ፡- የተወለድኩት እና ያደግኩት በሚዛን ቴፒ ነው፤ የእግር ኳስ ጨዋታንም የጀመርኩት ልጅ ሆኜ በሰፈር ደረጃ በመጫወት ነው፤ ከዛም ትንሽ ካደግኩ በኋላ የእግር ኳስን በዞን ደረጃ ተጫወትኩና ውድድሩን በኮከብ ግብ አግቢነት አጠናቀቅኩ፤ በዛም ተሳትፎዬ ጥሩ ሆኜ መመለሴን ስረዳ ወደ ክለብ ገብቶ ለመጫወት ጠንክሬ መስራት እንዳለብኝ ተረዳውና በዓመቱም ሆሳህና ላይ የተደረገውን ሌላ የክልል ውድድርን 6 ግብ አስቆጥሬበት በድጋሚ የኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ ስጨርስ ነው ከዚህ ውድድር ተሳትፎዬም በኋላ ወደ ክለብ ደረጃ የተሸጋገርኩት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትክበት ክለብ ማን ነው? በመቀጠልስ ወደየት ክለብ አመራክ?
ሀብታሙ፡- የእግር ኳስን በወረዳ ደረጃ ከተጫወትኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትኩበት ክለብ ስልጤ ወራቤ ውስጥ የሚገኝ ቡድን ነው፤ ይሄም ቡድን የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ይሳተፍ ነበርና በአንድ ጓደኛዬ አማካኝነት ተጠርቼ ወላይታ ላይ በተደረገው ጨዋታ ተጫወትኩላቸው፤ በውድድሩም 9 ግብ አስቆጥሬም በኮከብ ግብ አግቢነት ተሳትፎዬን አጠናቀቅኩ፤ በዚህ ውድድር ላይም የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽነር ውድድሩን እንዲመለከት ተጋብዞ ነበርና የእኔን እንቅስቃሴ አየና ድሬዳዋ ላይ የቶርናመንት ጨዋታ ስለነበራቸው ደውሎ አስጠራኝ፤ ቡድናችን የአጥቂ ችግር አለበት አንተ ብትመጣ ችግሩን ትቀርፍልናለክ አለኝ፤ ቡድኑም ይርጋለም ላይ ልምምዱን ይሰራ ስለነበር እኔም ወደ እነሱ ሄድኩና ቡድኑን ተቀላቀል ሲሉኝ ተቀላቀልኩና በቢጫ ትሴራ ቶርናመንቱን ለመጫወት ሄድኩኝ፤ በጊዜው ለሶስት ጨዋታ ያህልም የመጫወት እድልን አላገኘውም ነበር፤ በኋላ ላይ ቡድኑ ውጤት እምቢ ሲለው ቤንች ላይ ሆንኩኝ፤ ክፍሌ ቦልተናም በአንድ ጨዋታ ላይ 2-0 ስንመራ ቀይሮ አስገባኝ፤ ቀይሮ እንዳስገባኝም አንድ ኳስ አቀብዬ አንድ ግብ ባገባም ቡድናችን 3-2 ተሸነፈ፤ በሌላም የመጨረሻ ጨዋታ አሁንም ቤንች ነበርኩና ቀይሮ ሲስገባኝ ጥሩ ተጫወትኩ፤ በኋላም ቶርናመንቱ እንዳለቀ በቀጣዩ ለክለቡ ስልምትቀጥልበት ሁኔታ እናወራለን አሉኝና ተመለስኩ፤ ያኔ እነሱ ባናገሩኝ ሰዓት ወላይታ ድቻም ይፈልገኝ ነበር አሰልጣኙ መሳይም አንተ ገና ታዳጊ ነህ እኛ ጋር ለ5 ዓመት ፈርም ሲለኝ ወንድሜ ባዬ አይሆንም፤ ከታች ብትጀምር ይሻላል ሲለኝ ደቡብ ፖሊስን አናገርኩና እዛው ፈረምኩ፡፡
ሊግ፡- ለደቡብ ፖሊስ ለስንት ዓመት ነበር የፈርምከው? ቆይታክስ ምን ይመስል ነበር?
ሀብታሙ፡- የደቡብ ፖሊስን ስቀላቀል ለክለቡ የፈረምኩት ለሁለት ዓመት ነበር፤ ያኔም በክለቡ የነበረኝ ቆይታ ከመጀመሪያው ዓመት በተሻለ የሁለተኛ ዓመት ላይ ጥሩ ነበር፤ የመጀመሪያው ዓመት ላይ ለቡድኑ አዲስ ስለነበርኩም ያንን ያህል የጎላ ተሳትፎ አልነበረኝም፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ማንን ነበር የምታደንቀው?
ሀብታሙ፡- የልጅነቴ ዕድሜዬ ላይ ኳስ ስጫወት በጣም አደንቀው የነበረው ተጨዋች አዳነ ግርማን ነው፤ እሱንም ያኔ ተምሳሌቴ አድርጌዋለው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት በቤተሰብህ አካባቢ ተፅሆኖ ነበረብህ?
ሀብታሙ፡- በፍፁም፤ ቤተሰቦቼ በተለይ ደግሞ ወላጅ አባቴ ኳስ ተጨዋች ስለነበር እና ኳስንም በጣም ይወድ ስለነበር ያኔ በምጫወትበት ሰዓት ማንም የቤተሰቤ አካል ኳሱን እንዳልጫወት ተፅሆኖ አያደርጉብኝም ነበር፤ አባታችን እንደውም በየሜዳው ኳስን ይመለከትም ስለነበር እኛን ተሸክሞም ነበር ይሄድና ግጥሚያዎችንም ይከታተል የነበረው፤ ከዛ ውጪ ኳስ ተጨዋች እንድንሆንለትም ያበረታታን ነበር፡፡
ሊግ፡- ከእግር ኳስ ውጪ የእረፍት ጊዜህን በምን ታሳልፋለህ?
ሀብታሙ፡- በአብዛኛው እተኛለው፤ ተኝቼ ስነሳ ደግሞ መፅሐፍቶችን ነው የማነበው፡፡
ሊግ፡- ከደቡብ ፖሊስ በኋላ የሲዳማ ቡናን ነበር የተቀላቀልከው፤ ወደ ክለቡ እንዴት መጣክ? ቆይታህንስ እንዴት ነው የምትገልፀው?
ሀብታሙ፡- የሲዳማ ቡና ክለብን የተቀላቀልኩት አሰልጣኝ አለማየው አባይነህ አሌኮ አናግሮኝ ነው፤ ወደ ቡድኑ እንደመጣውም ለሊጉ አዲስ ስለሆንኩ የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ አልተሰለፍኩም፤ ከአምስት ጨዋታ በኋላ ግን የመሰለፍ እድሉን ተቀይሬ በመግባት ሳገኝ ጎል አካባቢ ድክመቶች ነበሩብኝና ይሄንን ችግሬን ተመልክቼያለውኝ፤ በኋላ ላይ ቡድኑ በአሰልጣኝ ዘርሀይ ሙሉ የሁለተኛው ዙር ላይ በሚመራ ሰዓት የመሰለፍ እድሉን ሳገኝ ሁሉንም ነገሮች በማስተካከል ጥሩ ልጫወት ችያለውና የሲዳማ ቡና የአሁን ላይ ቆይታዬ ጥሩ ነው፤
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ጉዞአችሁ ምን ይሆናል? ውድድሩንስ በምን ውጤት የምታጠናቅቁ ይመስልሃል?
ሀብታሙ፡- ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ዙር የሊጉን ውድድር በጥሩ ሁኔታ ከማጠናቀቁ አኳያ የሁለተኛው ዙር ላይም ከዚህ የተሻለ ነገር ይጠብቀዋል፤ የአንደኛው ዙር የቡድናችንን አቋም በሚገባ ተመልክተነዋል፤ በስኪመር ስፍራ ላይ ክፍተት ነበረብን፤ አሁን ግን በዛ ቦታ ላይ ስፍራውን የሚሸፍንልን ተጨዋች ስላገኘን ሲዳማ ጥሩ ውጤት ያመጣል የዘንድሮውን ውድድርም በሻምፒዮንነት ለማጠናቀቅም ነው የእኛ ዋንኛ እላማ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ታላቅ ወንድምህ ባዬ እየተጫወተ ይገኛል፤ እሱን እንዴት ነው የምትገልፀው?
ሀብታሙ፡- ባዬ በሊጉ ውድድር ላይ ለተለያዩ ክለቦች እና ለብሄራዊ ቡድን ሲጫወት አውቃለሁ፤ ጥሩም ችሎታ ያለው ተጨዋች ነው፤ እኔም የእሱን ፈለግ ተከትዬ በኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስንም እፈልጋለው፤ ባዬ እስከቅርብ ጊዜያት ድረስ የነበረበት ሁኔታ እንደ በፊቱ ስሙ ብዙ የሚጠራ እና ቀዝቀዝ ያለብኝ ቢሆንም አሁን ደግሞ ጎል ማስቆጠረ ስለጀመረ ደስ ብሎኛል፤ በብቃቱ ዙሪያ ከእኔ ጋርም እየተነጋገረ ይገኛል፤ ጠንክሮ ሰርቶም የበፊት ስሙን መመለስ እንዳለበትም ነው የእኔ ዋናው ምኞት፡፡
ሊግ፡- የሲዳማ ቡና ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድነው?
ሀብታሙ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ያለን ጠንካራ ጎን ቡድናችን በወጣት የተገነባ እና ለተቃራኒ ቡድን በጣም አስቸጋሪ የሆነ ቡድን ነው፤ በእንቅስቃሴ ደረጃ ስንጫወት ማንም አይቆምም፤ ከተከላካይ ክፍሉ አንስቶ እስከ አጥቂው ክፍል ድረስ ሁሉም ሯጭ ነው፤ ኳስንም ይዘን ነው የምንጫወተው እና ይሄ ነው ለውጤት እያበቃን የሚገኘው፤ ደካማ ጎናችንን በተመለከተ ለጨዋታ ወደ ክልል ሜዳዎች በምናመራበት ሰዓት እኛ አርቴፊሻል ሜዳ የለመድን ስለሆን ለጨዋታ ብዙ አመቺ ባልሆኑ ሜዳዎች ላይ መጨዋታችን ካልሆነ በስተቀር ያንን ያህል የጎላ ችግር የለብንም፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን በአንድ ወቅት ተመርጠህ ነበር፤ ያኔ ምን ተሰማህ? የወደፊት ምኞትህስ ምንድነው?
ሀብታሙ፡- የእግር ኳስን አሁን ላይ የምጫወተው በኳስ ችሎታው ራሴን አሳድጌ ለታላቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ነው፤ ለብሄራዊ ቡድንም መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያ ውጭም የፕሮፌሽናል ተጨዋች መሆንም የእኔ ዋናው ህልሜ ነው፡፡
ለብሔራዊ ወጣት ቡድን በአንድ ወቅት በአሰልጣኝ ግርማ አማካኝነት የተመረጥኩት ለደቡብ ፖሊስ ስጫወት ከአዲስ አበባ ከነማ ጋር ባደርግነው ጨዋታ ላይ ነበር፤ ያንን ጨዋታ እሳቸው ተመልክተው ነበርና ሶስት አና አራት ክሮስ ሳደርግ እና ሶስቱም ግብ ሲሆን አይተው ነው የጠሩኝ እንዲህ ክሮስ የሚያደርግ ተጨዋች ነው የምፈልገውም ብለው ሲጠሩኝ የተሰማኝ የደስታ ስሜት በጣም ከፍ ያለም ነበር፤ በጊዜው የመጫወት እድሉን ባላገኝም መመረጡ በራሱ ትልቅ ነገር እንደሆነ አስቤም ነው የተደሰትኩት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክስተቱ ቡድን ማን ነው?
ሀብታሙ፡- መቀሌ 70 አንደርታ በሊጉ የመሪነት ደረጃ ላይ ማንም አልጠበቃቸው ነበር እነሱ ግን ይሄን አስበውበታል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ?
ሀብታሙ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ክለባችን ዘንድሮ እየተጓዘበት ያለው መንገድ በጣም አስደሳች ነው፤ ይሄ ቡድን በዚህ ደረጃ ላይ እንዲገኝም የእግር ኳስን ተጫውቶ ያሳለፈው ወጣት የሆነው ከእኛ ጋርም እንደ ጓደኛ ነፃነት ሰጥቶንና ተግባብቶን የሚሰራው አሰልጣኛችን ዘርአይ ሙሉ ብዙ ነገርን እያደረገልን እና እየሰራም ይገኛልና በቅድሚያ እሱን ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ከእሱ ውጪ ደግሞ በእግር ኳሱ ህይወቴ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ወንድሜ ባዬ ገዘኸኝ ሁሌም ጠንክረህ ስራ የተሻለ ደረጃ ላይ ትደርሳለህም ስለሚለኝ ከጎኔም ሆኖ ስለሚመክረኝ እሱንም አመሰግነዋለው፤ ከእኔ ጎን ሆነው ብዙ የረዱኝ አካላቶችም አሉና እነሱም ይመሰገኑልኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: