Google search engine

በሻምፒዮኖቹ በር ላይ ያንፀባረቀው ፀሐይ ባንክ አቶ አበባው ዘውዴ የፀሐይ ባንክ የማርኬንግና ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር

በአለም ሰገድ ሰይፉ

በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ አቻ የማይገኝለት አንጋፋና ታላቅ ክለብ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ከሀገር አልፎ በኢንተርናሽናል ውድድር ተሳትፎውም ኢትዮጵያን በማስጠራት ረገድ ግንባር ቀደም ነው፡፡ በአንፃሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምስረታውን አድርጎ ፈጣን እመርታን ያስመዘገበና ሌሎች ባንኮች ተግባራዊ ያላደረጉትን ክሬዲት ካርድን ጨምሮ የአሸናፊዎች ቁጠባን፤ የቴሌግራም ቡት ባንኪንግ፤ ይቆጥቡ ይበደሩ እና ሌሎች አዳዲስና ፈጠራ የታከለባቸው የባንክ አገልግሎቶችን  ለሕብረተሰቡ በማቅረብ ዘመናዊ የባንክ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የባንክ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው ባለደማቅ ብራንዱ ፀሐይ ባንክ፤ በጋራ ሊሰሩ ተጣምረዋል፡፡

በተለይ ይህ ታሪካዊ ክለብ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ የፋይናንስ ቀውስ በተመታበት በዛ ፈታኝ ጊዜ “እኔ ከጎናችሁ ነኝ” በማለት አጋርነቱን ላሳየው ፀሐይ ባንክ የክለቡ ማህበረሰብ መቼም የማይዘነጋ ውለታ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡የሁለቱ ወገኖችን ጥምረት በተመለከተ የሊግ ስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አለም ሰገድ ሰይፉ ከፀሐይ ባንክ የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ አበባው ዘውዴ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡መልካም ዕለተ ሰንበት፡፡

ሊግ፡– እንደመነሻነት ስለ ፀሐይ ባንክ በአጭሩ ቢያብራሩልን?

አቶ አበባው፡– ፀሐይ ባንክ በቁጥር አነስተኛ በሆኑ በ373 ባለሃብቶች፤ በኢትዮጵያ የባንክ ምስረታ ታሪክ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በትንሽ ቁጥር ባላቸው ባለአክሲዮኖች፤ በከፍተኛ ካፒታል የተቋቋመ ዘመናዊና ግዙፍ ባንክ ነው፡፡

ሊግ፡– የባለአክሲዮን ቁጥሩንና የመነሻ ካፒታሉን ማወቅ ይቻለናል?

አቶ አበባው፡– በሚገባ እንጂ! በ373 ባለሃብቶች የተቋቋመና 2.8 ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል የተመሠረተ ባንክ ነው፡፡በወቅቱ ባንክ ለማቋቋም ዝቅተኛ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር ሲሆን፤ ፀሐይ ባንክ ግን በከፍተኛ ገንዘብ በ2.8 ቢሊዮን የተፈረመ ካፒታል የተመሰረተ ነው፡፡ የአክሲዮን ሽያጩም በወቅቱ ከሌሎች ባንኮች በተለየ መልኩ ዝቅተኛ የአክሲዮን ሽያጩ አንድ መቶ ሺ ብር በላይ ሲሆን፤ ከፍተኛው ደግሞ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር በመሆኑ፤ በትንሽ ቁጥር ባላቸው ባለሃብቶች አክሲዮኑን በአጭር ወራት ውስጥ በመሸጡ ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል መጠሪያውን “ፀሐይ ለሁሉ” በሚል መሪ ቃል ሁሉንም ማህበረሰብ ለማገልገል በራሱ ደማቅ ቀለምና ብራንድ ኢትዮጵያዊ አሻራውን አጉልቶ ወደ ስራ የገባ ባንክ ነው፡፡

ፀሐይ ባንክ የራሱን ደማቅ ብራንድ ይዞ በመምጣቱ፤ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለማገልገል ለሁሉ ብሎ ወደ ስራ በመግባቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘት በመላ ሀገሪቱ በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈት የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ባንኩ ወደ ስራ ከገባም አንድ ዓመት ከአራት ወራት ያስቆጠረ ሲሆን፤በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም ከ83 በላይ ቅርንጫፎችንና ከ350 ሺህ በላይ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡

ሊግ፡– የአገልግሎት አይነቶቹስ እንዴት ይገለፃሉ?

አቶአበባው፡– የባንክ አገልግሎቱን በተመለከተ መደበኛ የባንክ አገልግሎትና “ፈጅር” የተሰኘ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እኩል የጀመረ ባንክ ሲሆን፤ በተለይም በአሁኑ ጊዜ የዘመኑን የባንክ ቴክኖሎጂን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀም ከመሆኑ አንፃር የሞባይል፣ የኢንተርኔት፣ የካርድ ባንኪንግ ወዲያውኑ በመጀመር ወደ ስራ የገባ ዘመናዊ ባንክ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡

ሊግ፡– እንደሚታወቀው ባንካችሁ ከሻምፒዮኖቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ማድረጋችሁ ይታወቃል፡፡ ፀሐይ ባንክ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የመጀመሪያ ምርጫው ያደረገበት ምክንያት ምንድነው?

አቶአበባው፡– ፀሐይ ባንክ ወደ ስራ ሲገባ ከሌሎች ባንኮች ምን የተለየ አዲስ አገልግሎቶችን ይዞ ይገባል? የሚል ጥያቄ ከተለያየ አቅጣጫ ይነሳ ነበር፡፡ በእኛ በኩልም በደንበኛው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻልበትና ጥራት ላይ ትኩረት ያደረጉ አዳዲስና የፈጠራ ውጤት ያላቸውን በባንክ ቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን ይዘን ነው የገባው፡፡

ሊግ፡– ምሳሌ ማንሳት ይቻላል?

አቶአበባው፡– አዎ፤ ለምሳሌ “ይቆጥቡ ይበደሩ” የሚል የትኛውም ባንክ የማይሰጠውን አገልግሎት ጀምረናል፡፡ይቆጥቡ ይበደሩ ማለት ሰው በቆጠበው ልክ ብድር እንዲመቻችለትና ከዛም ከፍ ያለ ነገር ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ስፖርቱን ለመደገፍና በስፖርቱ ዙሪያ ያለውን የደጋፊዎች ሃብት ፕሮዳክቲቭ በማድረግ መልሶ ለስፖርቱ ለማበርከት በማቀድ “የአሸናፊዎቹ የቁጠባ ሂሳብ” የሚል አካውንት አስተዋውቋል፡፡ እናም ስፖርቱን በስሜት ሳይሆን በስሌት የሚደግፍ ሁሉ አሸናፊ ነኝ የሚል አካውንት እንዲከፍትና ራሱንም እንዲሁም እወደዋለሁ የሚለውን ክለብ እንዲደግፍ ለማስቻል የተዘጋጀ አገልግሎት ነው፡፡

ይሄንን ፕሮዳክት ወደ ገበያው ይዘነው ስንመጣ እዚህ ሀገር ውስጥ ሕዝባዊ ክለቦችን አፈላልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖብን ነበር፡፡ ምክንያቱም ክለቦቻችንን በተጨባጭ ካየናቸው አብዛኛዎቹ የማዘጋጃ ቤት ክለቦች እንጂ፤ሕዝባዊ ክለብ ተብለው የሚጠሩ አይደሉም፡፡ በደጋፊዎች የአባላት መዋጮና በስፖንሰር እንዲሁም በሌሎች ገቢዎች ብቻ የሚተዳደሩ ህዝባዊ ክለቦችን ለማለት ነው፡፡ ባስቀመጥነው መስፈርት መሰረት ሰፊ ቁጥር ያላቸው፤ ከፋይ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች አንድ ሁለት ብለን በጣት የምንቆጥራቸው ክለቦች ብቻ ናቸው፡፡ እንዲያውም እነዚህ ክለቦች ከመዲናችን የሚያልፉ አይደሉም፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ክለቦችንና ስፖርቱን ስንደግፍ ከክለቡ ጀርባ ያሉ ደጋፊዎችን ማግኘት እንፈልጋለን፡፡ደጋፊዎቹን ክለባቸውን በትክክል እንዲደግፉ ፕላትፎርሙን ነው ያመቻቸነው፡፡ ይህ ማለት ደጋፊው በቀጥታ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን፤ የባንክ ተጠቃሚነታቸውን በባንካችን ሲያደርጉ፤ ባንካችን የበለጠ የሚወዱትን ክለባቸውን በመደገፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ይህ ተደጋጋፊ ስራ ነው፡፡የክለቡ ደጋፊዎች የእኛ ደንበኛ ሲሆኑና እኛም ክለቡን ስፖንሰር ስናደርግ ተደጋግፈን እናድጋለን እንደማለት ነው፡፡

ከዚህ መነሻነትም በዕድሜ አንጋፋ፣በታሪክም ስመ ጥር የሆነውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ለማነጋገር ነው እቅድ ይዘን የተንቀሳቀስ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ምርጫችንም ትክክል ነበር፡፡ ከዚያም የክለቡን የቦርድ አመራር አባላት ማነጋገር ጀመርን፡፡ በተለይ የክለቡ የቦርድ አመራርና የማርኬቲንግ ዘርፉን የሚመሩት አቶ ዳዊት ውብሸት በጣም ቀናና ተባባሪ እንዲሁም በክለቡና በባንኩ መካከል የነበረውን የአብሮ መስራት ዘርፈ ብዙ የአጋርነት ጥቅም በማስጠበቅና በማመቻቸት በኩል የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ለነበራቸውን እስከአሁንም ለሚያደርጉት ያልተቋረጠ ድጋፍ ልባዊ ምስጋናዬን ላቀርብላቸው እወዳለሁ፡፡

ሊግ፡– ዘርፈ ብዙ የአጋርነት ስምምነት ነው ያደረግነው ያልከኝ መሰለኝ? ምን አይነት ስምምነት ነው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጋር ያደረጋችሁት?

ባለፈው በመስከረም ወር ላይ ያበሰርነው የመግባቢያ ሰነድ በስካይ ላይት ሆቴል ስናካሂድ ለመገናኛ ብዙሃን በይፋ ለማሳወቅ ሞክረናል፡፡ይሁንና መረጃውን በትክክል ባለማግኘትም ይሁን ባለመረዳት ዘርፈ ብዙ የአጋርነት ስምምነቱን በግልጽ ለደጋፊዎችም ሆነ ለስፖርት ወዳዱ የተገለጸ አይመስለኝም፡፡ ወደ ስምምነቱ ስንመጣ የስፖንሰር ሺፕ፤የቁጠባና ተያያዥ እንዲሁም የብድር አገልግሎቶችን በቅንጅት የያዘ ስምምነት ነው፡፡ አንድ በአንድ ስንመለከተው የስፖንሰር ሺፕ ስምምነቱ ለአምስት አመት የሚታሰር ሆኖ በየአመቱ አስር በመቶ ጭማሬ እያሳዬ የሚሄድ የአምስት ሚሊዮን ብር የመጀመሪያ አመት ስምምነት አንዱ ነው፡፡በስፖንሰር ስምምነቱ መሰረት ክለቡ በሜዳም ይሁን በስፖርት ትጥቁ፤በተለያዩ ዝግጅቶቹ፤በሶሻል ሚዲያው፤በጋዜጣው ፤በሬዲዮና በመሳሰሉት ለደጋፊውና ለስፖርት አፍቃሪው ባንኩን ያስተዋውቃል ማለት ነው፡፡ ሌላኛው ከቁጠባ ጋር ተያይዞ አካውንት የማስከፈቱ ጉዳይ ደጋፊዎች በባንካችን አካውንት በከፈቱ ቁጥር ከሌላው አካውንት በተለዬ መልኩ አንድ በመቶ ጭማሬ ያለው ሂሳብ በማመቻቸት፤ አንድ በመቶውን ለክለቡ ገቢ እንዲደረግለት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም አካውንት ሲከፈት ወዲያውኑ አስር ብር ተቆርጦ ወደ ክለቡ አካውንት ገቢ ይደረግለታል፡፡ እዚህ ላይ ደጋፊው በደንብ አካውንት ቢከፍትና የንግድም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴውን በባንኩ ቢያደርግ ባንኩ ተጨማሪ ክፍያ ለክለቡ የሚከፍል በመሆኑ ክለቡን ተጠቃሚ ያደርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው የቁጠባ ሂሳብ ወለድ 7 ፐርሰንት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ በአዲስ መልክ ለከፈትነው የሻምፒዮኖቹ አካውንት 8 በማድረግ አንዷን ፐርሰንት ለክለቡ ገቢ ለማድረግ የሚቻልበትን መንገድ አመቻቸን፡፡ ይህ አካሄድ እስከሁን የትኛውም ስፖንሰር አድራጊ ፈፅሞት የማያውቅና ክለቡን በሁለንተናዊ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርገው አሰራር ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ደጋፊው የእውነት ክለቡን ከልቡ የሚወደው ከሆነ የትኛውም ባንክ የሚጠቀመውን አገልግሎት እዚህ መጠቀም የሚችል በመሆኑ ከእርሱ ምንም ገንዘብ ሳይነካ ባንኩ ለክለቡ ድጋፍ የሚያደርግበትን አሰራር ይዘን ነው የመጣነው፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው የሚያስችለው ደረጃውን የጠበቀ የመለማመጃ ሜዳ ግንባታን በዙሪያው ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች በረጅም ጊዜ ብድር እና በነአስተኛ ወለድ ተመን ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ በሚያስገባና ገቢ እንዲያመነጭ የሚረዳ ስምምነት ፈጽመናል፡፡ ይሄ ስምምነት ስፖርቱን ለማሳደግና በተለይም የመለማመጃ ሜዳቸውን ወደ ውጤት ለመቀየር ከማሰብም ባሻገር በሜዳው ዙሪያ የተለያየ ገቢ ማመንጨት የሚችሉ የንግድ ማዕከላት መገንባት የሚያስችለውን ብድር ለክለቡ ያመቻቸ ነው፡፡ይህ ሁሉ አራትና አምስት አይነት ዘረፈ ብዙ አመራጮች ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስናቀርብ የክለቡ እውነተኛና ቅ/ጊዮርጊስን ከልቡ የሚወድ ደጋፊ ሂደቱን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን፤ ይሄን ሁሉ ጠቀሜታ የሰጠውን የፀሐይ ባንክ ደንበኛ በመሆን ክለቡንም ይደግፋል፣ ባንኩንም ይጠቅማል የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡ እናም በዚህ መልኩ ተደጋግፈን ስፖርቱን ማሳደግ እንችላለን፡፡ አንተም እንደምታውቀው እዚህ ሀገር ስፖንሰር በማድረግህ የምታገኘው የተለየ ጥቅም እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ብዙዎችም ለምን ወደ ስፖርቱ ተስበው አይመጡም? ለምን አይደግፉትም ብለን ለመውቀስ የማንችለው በትክክል የክለብ ደጋፊው ሚናውን ያለ መለየት ችግር እናስተውላለን፡፡ ስፖንሰር ሆኖ የሚመጣውን ድርጅት አሊያም ተቋም በምን መልኩ ባግዘው የበለጠ ክለቤን ይደግፍልኛል? ብሎ የራሱን ሚና የመጫወት ጉድለቶችን እንመለከታለን፡፡

ሊግ፡– ከወዲሁ ተስፋ እየቆረጣችሁ ነው ማለት ነው?

አቶአበባው፡– በፍፁም! ቀደም ብዬ ነግሬሀለሁ እኮ እኛ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስንመጣ በቀጥታ ወዲያው ትርፋማ ለመሆን በማሰብ ሳይሆን፤ ሰፊ ቁጥር ያለውን ደጋፊ የባንካችን ደንበኛ የማድረግና ከማህበራዊ ኃላፊነት አንፃር ክለቡን የማገዘና የመደገፍ ሃሳብም ጭምር ይዘን ነው፡፡ ከዚያ በሂደት ሁሉ ነገር ይስተካከላል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የአውሮፓና የሌሎች ሀገሮችን የስፖንሰር አድራጊዎችን ጥቅምና ድጋፍ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየተረዳና እየገባው ስለመጣ፤ተመክሮና ልምድ እየቀሰመ ስለመጣ ንግዱንም፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውንም አመቺ በሆነ መልኩ በባንካችን ቢጠቀም፤ የተሻለ ራሱንም የሚወደውንም ክለብ መጥቀም ይችላል በሚል የተመቻቸ ነገር አዘጋጅተናል፡፡

በነገራችን ላይ እነዚህን ነገሮች ብቻ በይፋ ገለፅናቸው እንጂ፤ ከዚህ በተጨማሪ ለክለቡ አመራሮችና ለተጨዋቾቹ እንዲሁም ለደጋፊዎች እንደ እንቅስቃሴያችን መጠን የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችና የብድር ፋሲሊቲዎችን ለማቅረብ ፀሐይ ባንክ ይሄን ያክል ርቀት ሄዷል፡፡

ሊግ፡– ባንኩ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ይሄን ታላቅ ስምምነት ለማድረግ ስታስቡ ስጋት አልፈጠረባችሁም?

አቶአበባው፡– እውነት ነው አንተም እንደምትለው ብዙዎቹ ተገርመውብናል፡፡ እንዴት ብትደፍሩ ነው፤እንደሚታወቀው ከስፖርት የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡በሁለተኛ ደረጃ ስፖርቱ ስሜታዊነት የሚበዛበት እግር ኳስ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ብለውናል፡፡ አንዱን ክለብ ስፖንሰርስ ታደርግ ሌሎች የማኩረፍ ሁኔታ የሚፈጠርበትም አጋጣሚ አለ፡፡እንደ ፀሐይ ባንክ እምነት አቅም ኖሮን ሁሉንም ክለቦች ስፖንሰር ብናደረግ ደስታችን ወደር የለውም፡፡መሆን ግን አንችልም፡፡ የአቅም ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ስፖንሰር ማድረግ የምትችለው አንዱን ክለብ ብቻ ነው፡፡እናም የብዙሃኖቹ ጥያቄና ስጋት ይህ ነበር፡፡ ይሄን ሁሉ አድርጋችሁስ እናንተ በአንፃሩ ምን ልታገኙነው? እያሉ የሚጠይቁን አሉ፡፡እኛ ግን በዚህ ብራንዱ ከፍ ባለና ገናና ክለብ ጋር በመስራታችን ክብር እየተሰማን፤ ጠንካራ የቦርድ አመራር፤ ባለ ሰፊ ልምድ እና በሳል ማኔጅመንት እየታገዝንና ክለቡን ከልብ የሚወድ ጨዋ ደጋፊ ባለቤት በሆነው በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሙሉ እምነት ስላለን ከክለቡ ጋር ስኬታማ ስራዎችን እንደምንሰራ ፍጹም እምነት አለኝ፡፡ ከህጻናት እስከ አዛውንት እድሜ ያለውና በመላ አገሪቱና በውጭ አገር ሳይቀር የደጋፊ ሃብታም የሆነውን ክለብ ጋር በመስራታችን ቀስ በቀስ እቅዳችንን እንደምናሳካ ምንም ስጋት የለኝም፡፡

ከዚያ ውጪ በአግባቡ አልተጠቀምንበትም እንጂ ቅ/ጊዮርጊስ ትልቅ ብራንድ ያለውና በአፍሪካ ደረጃ የሚታወቅ ታላቅ ክለብ ነው፡፡ ይህን ክለብ እየመሩ ያሉ ግለሰቦችም በክለቡ ተጫውተው ያሳለፉና ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ስፖርት ስታነሳ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ አብሮ ይነሳል፡፡ከዚህ ክለብ ጋር አብረን መስራታችን ለእኛም በረከት ነው፡፡እናም እንደ ጀማሪ ሌሎች ትልልቅ ባንኮች መድፈር ያልቻሉትን እኛ ሰብረን የገባነው አንድም ክለቡን ስለምንወደው በሌላ በኩል ደግሞ ደጋፊው ዝም ብሎ ከመደገፍ ባለፈ ፕሮዳክቲቭ መሆን እንዲችል በማሰብ ነው፡፡ ውጤት ሲመጣ ዝም ብሎ መጮህ ብቻ ሳይሆን፤ እኔ ለክለቤ ምን አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ? የሚለውን መንገድ እንዲያውቅ የማበረታታት ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ በነገራችን ላይ የንቅናቄ ስራዎችንም አብረናቸው እየሰራን እንገኛለን፡፡ ስታዲየም እየተገኘን ሂሳብ የማስከፈት፣በሶሻል ሚዲያዎችም የሚወዷቸውን ተጨዋቾች በማቅረብ የማነቃቃትና አብረውን በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል በትጋት እየሰራን ነው፡፡ይህንን ስናደርግ ግን የሌላ ክለብ ደጋፊዎች ቅር ሊሰኙ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ይህ ስፖርት ነው፡፡በሌላም ሀገር ይሁን ወደ አውሮፓ ብትሄድ ስፖንሰሮች አንድ ክለብ ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ይሄን ክለብ ደገፍክ ተብሎ የሚቃወም የለም፡፡ለምሳሌ በባንክ ደረጃ ብንወስድ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በቡና ባንክ ስፖንሰር ይደረጋሉ፡፡ስለዚህ አንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ ቡና ባንክን አይጠቀምም ማለት አይደለም፡፡ነገር ግን ማግኘት የሚገባውን ያክል ማግኘት ስለሚገባው ቡና ባንክም ሆነ ፀሐይ ባንክ ስፖንሰር ላደረጓቸው ክለቦች ደጋፊዎቻቸው ለባንኩ አጋርነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡

ሊግ፡– የቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የስፖንሰር ሺፕ ስምምነቱ ምን ያክል ዘላቂ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል?

አቶአበባው፡– እኔ ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ደጋፊው ለክለቡ ቅ/ጊዮርጊስ ትልቅ ፍቅር እንዳለው ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ በርካታ ደጋፊዎች አካውንት ከፍተዋል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን በባንካችን በኩል እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ አባላትን በመቀስቀስና ወደ ባንኩ እንዲመጡ ጥረት ሲያደርጉ ታያለህ፡፡ የተለያዩ ሃሳቦችን ያማክሩናል፡፡የባንኩን ሎጎና መለዮ በክብር ይወዱታል፡፡ የራሳቸውን ዜማም እያዜሙለት ይገኛሉ፡፡ ይሄ ለእኔ ትልቅ ትስስርና አብሮ የሚዘልቅ የወዳጅነት ማሳያ ነው፡፡ ዘላቂነቱን አመልካችና የአብሮነት ጉዟን ካስማ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አብሮ ለመዝለቅ የክለቡ ደጋፊ የሆነ ሁሉ በባንኩ ደንበኛ ከሆነ፤ ገንዘባቸውን በሙሉ በባንኩ የሚያንቀሳቀሱ ከሆነ ስፖንሰር አድራጊው ጥያቄው ተመልሶለታል ማለት ነው፡፡

ከዚህ ላይ ደጋፊዎች ሊረዱት የሚገባ ክለቡን ለመደገፍ የመጡትን ፀሐይ ባንክ፣ ዊነር፣ሃይላንድና ቢጂአይ ወደፊትም ሌሎችም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ የእነዚህን አጋሮች ፕሮዳክት በመጠቀም አጋርነታቸውን ማስመስከር መቻል አለባቸው፡፡ለምሳሌ ፀሐይ ባንክ ስፖንሰር ሲያደርግ ይነስም ይብዛ ባንኩ ያደረገለትን ድጋፍ አውቆ የባንኩ ደንበኛ ቢሆን፤ባንኩም የዚህ አይነት ታማኝ ደንበኞች እንዳሉት ሲያውቅ ግንኙነታችን የበለጠ ዘላቂ ይሆናል፡፡ዞሮ ዞሮ ባንኩ ለትርፍ የተቋቋመ ከመሆኑ አንፃር ቢያንስ ለሚያደርገው ድጋፍ ኪሳራ ውስጥ እስካልገባ ድረስ በተለያየ መንገድ ባንኩን ማስተዋወቅ እስከቻሉ ድረስ ስታዲየም ሊሆን ይችላል፤ አሊያም የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ባንኩን በሚገባ ፕሮሞት እስካደረጉ ድረስ አምስት ዓመት አይደለም ከዛም ለበለጠ ዓመታት አብረን የምንጓዝነው የሚሆነው፡፡

አንተም እንደታዘብከው በሀገራችን የተለመደው አካሄድ ስፖንሰሮች ይጀምሩና ትንሽ እንደተጓዙ የሚቋረጥ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄን ችግር ማስወገድ የምንችለው ጥቅሙን ማስጠበቅ ስንችል ብቻ ነው፡፡ደጋፊውም ሆነ የክለቡ አመራሮች ጠንክሮ ደጋፊው ወደባንኩ እንዲመጣ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡በአንፃሩ ባንኩም አቅሙ በፈቀደው ሁኔታ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ እየተገኘ ከእነዚህ ከገለፅናቸው ውጪም የራሱን ድጋፍ እያደረገ ቤተሰባዊ ግንኙነቱን ማጠናከር ከቻልን አምስት ዓመታት አይደለም ከዛ ለበለጠ ጊዜ ሊሄድ ይችላል፡፡ዋናው ነጥብ ሁሉም ጥቅሙን አስጠብቆ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡

ሊግ፡– ቅዱስ ጊዮርጊስን ምርጫችሁ ስታደርጉ የአሸናፊነት ባህሉን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ላለፉት ሁለት ዓመታትም ዋንጫ ማንሳት የቻለ ክለብ ነው፡፡በቀጣይነት ይሄን ድል ማሳካት ባይችል ይህ ባንክ ወደ ኋላ ያፈገፍጋል?

አቶአበባው፡– ቅዱስ ጊዮርጊስ በተቻለ አቅም አሸናፊነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ደግሞ የሚቻለንን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በተረፈ ግን ለምን ውጤት አልመጣም ብለን ወደ ኋላ አናፈገፍግም፡፡እንደሚታወቀው ቅ/ጊዮርጊስ ሰፊ የሆነ የደጋፊ ቁጥር እንዳለው ይታወቃል፡፡እናም ይህን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ደጋፊ ፕሮዳክቲቭ /ምርታማ/ ማድረግ አለብን፡፡ ክለቡም ተጠናክሮ ዘመናዊ አካሄዶችን መከተል አለበት፡፡እውነተኛ ደጋፊዎቼ እነማን ናቸው? የተመዘገቡትስ ከፋይ ደጋፊዎቼስ እንማን ናቸው? የሚለውን ሂደት ለማጥናት ክለቡ ራሱን ማዘመን አለበት፡፡ ያሲሆን አቅሙን ከማወቅም ባሻገር ከደጋፊው፣ ከስፖንሰር ድርጅቶች፣ ከሜዳገቢ፣ማግኘት የሚችለውን የገበያ ጥናቶች መስራት መቻል አለበት፡፡

ከዛ ውጪ የማርኬቲንግ ስራውን ማጠናከር አለበት፡፡ አንዳንዴ አንተም እንደምታውቀው የተወሰኑ ቅሬታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ቅሬታዎች የምትፈታበት የሰለጠነ አካሄድ ሊኖር ይገባል፡፡ትልቁ ነገር ክለብህን የምትወድ ከሆነ እስከመጨረሻው ለክለብህ መስጠት ያለብህን አሟጠህ መስጠት አለብህ፡፡ “እወደዋለሁ” ስትል የእውነት ከመናገር በዘለለ መልኩ መውደድህን ማሳየት አለብህ፡፡ በውሃ ቀጠነ ምክንያት እየፈለጉ ክለብን አለመደገፍ አስተዋይነት አይደለም፡፡ የምር ለምትወደው ክለብ ከአንተ የሚጠበቀውን ብቻ ማድረግ ክለቡንም ስፖርቱንም ያሳድጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን እኛ የጠየቅነው ቀላል ጥያቄ ነው፡፡ አካውንት ክፈት ማለት በጣም ቀላልና ተራ ጥያቄ ነው፡፡በየትኛውም ቦታ ላይ እንቅስቃሴ ለማድረግ ካለገንዘብ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡እሱ ደግሞ እዚህ ፀሐይ ባንክ ላይ አክሰስ ተደርጎልሃል ከተባለ ይህን ለማድረግ ከባድ ያልሆነና ያን ያክል ቅስቀሳ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡

እኔ አንድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር አንዳንዶች በየአካባቢያቸው መጠነኛ ማህበራት ለመመስረት ጥረት ያደርጋሉ፡፡እናም ደጋፊዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ይሄን ያክል ርቀት ከሄዱ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው አካላት ሊያግዙዋቸውና ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ደጋፊዎችን የሚያበዛልህ የዚህ አይነቱ ነገሮች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ አሸናፊነት የሚገኘው በውጤት ብቻ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚ ውል ታሸንፍ ትችላለህ፤ በተወዳጅነት ልታሸንፍ ትችላለህ፣ በአጠቃላይ በብዙ መልኩ ሊገለፅ ይችላል፡፡ እናም ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ዓመታት አሸንፏል፡፡ በቀጣይ ማሸነፍ ካልቻለ ፀሐይ ባንክ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነቱን የሚያቆምበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡እኛ ይህ ስምምነት እስካለ ጊዜ ድረስ ሁሌም ከቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ጎን እንደምንቆም ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፡፡

ሊግ፡– ከስፖንሰርሺፕ ስምምነቱ በተጨማሪ ክለቡ ለማስገንባት ላቀደው የተጨዋቾች መለማመጃ ሜዳ ግንባታ የሚውል 40 ሚሊዮን ብር ለማበደር ቃል ገብታችሁ ነበር፡፡ አሁን ባለኝ መረጃ ደግሞ ፀሐይ ባንክ ለክለቡ ቃል ከገባው ገንዘብ መጠን በላይ ለማበደር እንደተዘጋጀ ሰምቻለሁ መረጃው ልክ ነው?

አቶአበባው፡– ትክክለኛ መረጃ ነው ያገኘኸው፡፡ በነገራችን ላይ ፀሐይ ባንክ ይህን ብድር ሌላ ንግድ ላይ ለተሰማራ አካል ቢያበድረው በከፍተኛ ኢንተርስት መስራት ይችላል፡፡ ስፖርቱን ማገዝ እንፈልጋለን ስንል ከልባችን ነው፡፡ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የትኛውም ስፖንሰር አድራጊ እኛ ባደረግነው ልክ የሰጠ የለም፡፡ ለእኔ እስከሚገባኝ ጊዜ ድረስ ደጋፊው በትክክል የገባውና ያወቀው አይመስለኝም፡፡ አሁን እኛ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያደረግነውን ስምምነትበፍፁምአልገባቸውም፡፡ብዙዎች የሚያውቁት 5 ሚሊዮን ብር የምትለዋን ብቻ ነው፡፡ ይህ የገንዘቡ መጠን በየዓመቱ 10 በመቶ እያደገ የሚሄድ መሆኑን ራሱ በሚገባ የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡

ሌላው ኢንተርስቱም ከሌላው በተለየ መልኩ መሆኑን ደጋፊው አያውቀውም፡፡ይሄ ከእነርሱ የማይነካና ባንኩ የሚከፍለው ነው፡፡ ሌላው ክለቡ ከከተማ አስተዳደሩ የተረከበው 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ አለ፡፡ይሄን ቦታ መገንባት ለክለቡ ሁለንተናዊ ጥቅም እንዳለው እንረዳለን፡፡ የክለቡ ማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ዳዊት ውብሸት እንደነገሩን በዚህ ቦታ ላይ ወደ 46 የሚጠጉ የንግድ ማዕከላት እንደሚገነባ ነው፡፡ በመሆኑም ለታቀደው ፕሮጀክት አስፈላጊ ዶክመንቶች ተሟልተው ከመጡ ለዚህ ግንባታ የሚውለውን ወጪ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ እኛ ከጎናቸው ነን፡፡ምክንያቱም 40 ሚሊዮን ብር እንደመነሻ የተያዘነው እንጂ ከዚያ በላይ ሊሄድ ይችላል፡፡ እናም ይሄን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክትን መደገፋችን ተገቢነው ብለን እናስባለን፡፡ እንደማንኛውም ተበዳሪ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ክፍያና በአነስተኛ ወለድ ይሄን አድርገናል፡፡ ከዚህ በኋላ ፕሮፖዛሉ ተሰርቶ እስኪመጣ እየጠበቅን ነው፡፡ እንደመጣልንና ሕጋዊ ሰነዶች ተሟልተው ሲመጡ ብድሩን እናመቻቻለን፡፡ ያው አንተም እንደምታውቀው አሁን ላይ ትንሽ የብሄራዊ ባንክ አንድ መመሪያ አውጥቷል፡፡ ይህ መመሪያም በአጭር ወራት ውስጥ ይነሳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እናም ይህ ብድር የመስጠት ፈቃድ እውን ሲሆን፤ ክለቡ የሚያቀርበው ፕሮዛል ተጠንቶ እኛም ብድሩን እንፈቅደለን፡፡ እነርሱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቀው ወደኪራይ ከሄዱ ክለቡ ዘርፈ ብዙ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆን እናደርጋለን፡፡እናም ይሄን ሁሉ የምናደርው ክለቡ ወደፊት በሁለት እግሩ እንዲቆም ለማስቻል በመሆኑ ደጋፊው ይሄን እውነታ ማወቅ አለበት፡፡ ለዚህም ነው ፀሐይ ባንክ ለቅ/ጊዮርጊስ በተለየ ሁኔታ ነው የመጣው የምንለው፡፡

ከዚህ አኳያ እውነቱን ለመናገር ደጋፊው በስፋት ወደ ባንኩ ሊመጣ ይገባል፡፡ የእስካሁኑ በፈለግነውና ባቀድነው ልክ አይደለም፡፡ሆኖም ጊዜው ገና በመሆኑ ወደፊት ደጋፊው ሁሉ ነገር በሚገባ እየተገነዘበ ሲመጣና ግጥሚያዎቹ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የተሻለ ነገር ሊፈጠር ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ሆኖም ክለቡን የሚወድ የልብ ደጋፊ ይህ መረጃ እንደደረሰው በሚቀርበው ቅርንጫፍ በመሄድ አካውንት ቢከፍቱና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ደግሞ ግብይታቸውን በፀሐይ ባንክ በኩል ቢያደርጉ የበለጠ ክለባቸውን መጥቀም ይችላሉ፡፡በነገራችን ላይ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ ስለክለቡ ተናግሮና አውርቶ የማይጠግብ ጨዋ ደጋፊ ነው፡፡ እናም ይህ ደጋፊ ጥያቄያችንን ተግባራዊ እንደሚያደርገው ታላቅ ተስፋ አለኝ፡፡

ፀሐይ ባንክ በአዲስ አበባ ብቻ ከ40 በላይ ቅርንጫፎች አሉን፡፡ እኔ ባለፈው ሳምንት ለስራ ጉዳይ ወደ ሃዋሳ ተጉዤ ነበር፡፡ በዛ ቆይታዬ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎችን አግኝቼ አካውንት ሲከፍቱ አይቼ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡በሁሉም ክልል ብትጓዝ በሺዎች የሚቆጠሩ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ የልብ ደጋፊዎች አሉ፡፡እናም እነዚህ የልብ ደጋፊዎች አካውንት በከፈቱ ቁጥር ተጠቃሚው የሚወዱት ክለባቸው በመሆኑ ፈጥነው የክለባቸውን ጠንካራ አጋር የፀሐይ ባንክ ደንበኛ ይሁኑ እላለሁ፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ ሲባል እንደምንሰማው ክለቦች ለተጨዋቾች ደሞዝ መክፈል አቃታቸው ይባላል፡፡ የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ቋሚ የገቢ ምንጭ ያለ መፍጠር ችግር ነው፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ 88 ዓመታት ያስቆጠረ ታሪካዊ ክለብ ነው፡፡እናም ይሄን ታላቅና አንጋፋ ክለብ ማስቀጠልና ቅ/ጊዮርጊስን መደገፍ ካለብን ሰዎቹን አይተን ሳይሆን፤ክለቡን ብለን ነው መደገፍ ያለብን፡፡እናም የታላቁ ክለብ ደጋፊዎች በርቱ አካውንት ያልከፈቱ ጓደኞቻችሁን በመንገር ሁለንተናዊ ድጋፍ እጅግ ለምትወዱት ክለብ እገዛ በመሆኑ በነቂስ በመውጣት ዛሬውኑ የፀሐይ ባንክ ደንበኛ ሁኑ ለማለት እወዳለሁ፡፡ሌላው በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ የምፈልገው ነገር ቢኖር ሌላው ባንክ ያልጀመረውና በእኛ ባንክ ብቻ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የክሬዲት ካርድ ግብይት ፈቃድን ብሄራዊ ባንክ ፈቃድ ሰጥቶናል፡፡ ክሬዲት ካርድ ማለት ብድር ይሞላልሀል ለ6 ወርና ለአንድ ዓመት የሚቆይ፤ እንደደሞዝህ መጠንና እንደገቢ ምንጭህ የሚሰጥህ ይኖራል፡፡እናም ይህን ዘመናዊና ብቸኛ የሆነ አገልግሎት እየሰጠን በመሆኑ በዘመናዊ አሰራራችን በመደሰት የታላቁን ክለብ የፋይናንስ አቅም አሳድጉ እላለሁ፡፡ ዛሬም ወደፊትም ፀሐይ ባንክ ከታላቁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጎን ይሆናል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P