Google search engine

“ከብሄራዊ ቡድን ልምምድ ስመለስ በቆመጥ ቀጠቀጡኝ” አፈወርቅ ጠናጋሻው

ከበጋሻው አየለ

የዛሬው እንግዳዬን ከማናገሬ በፊት በኳስ ተጨዋችነት አብረውት ከተጫወቱት አንድ ሁለቱን አናግሬ ነበር አፈወርቅ ከነበረው አቅም አንፃር የትም ሀገር ሄዶ መጫወት ይችል ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ኢትዮጵያ ከሀገር ወቶ መጫወት ስለማትፈቅድ እንጂ በጣም ብዙ ጀግኖች ነበረን፡፡ እኔን ጨምሮ በማለት ስለ አፈወርቅ ግብ ጠባቂነት ምንም እንከን የማይወጣለት አጠገቡ በነበሩ ተከላካዮች ደግሞ በጣም የሚተማመን በነገሮች አለመመቻቸት እንጂ ኢትዮጵያ በእሱ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ማግኘት ነበረባት፡፡ ሁሉም ተጨዋች ከሀገር ሲወጣ ኳሱን ከተጫወተ በኋላ በእዛው ሰለመጥፋት ነበር የሚያስበው፡፡ ካልተሳሳትኩ በተለያ ጊዜ ሶስት ብሄራዊ ቡድን የሚወጣው የኢትዮጵያ ቡድን ከሀገር በወጡበት ቀርተዋል፡፡ ወዲያው እነዚህን ተጨዋቾች መተካት ከባድ ስለሆነ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ብርቅ ይሆንብናል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ የሚያነሳ ቡድን ነበረን፡፡ እንኳን የሚሳተፍ ግን ምን ያረጋል ብቻ ተወው በማለት በመተባበር ስለወቅቱ ብሄራዊ ቡድን አፈወርቅ ጠናጋሻው አጫውቶኛል፡፡

ጥያቄ፡– ስምህ ማን ይባላል?

መልስ፡- አፈወርቅ ጠናጋሻው እባላለው

ጥያቄ፡– የት አካባቢ ነው የተወለድከው?

መልስ፡- ተወልጄ ያደኩት ፈረንሳይ ለጋሲዮን በቀበሌ 06 ነው ጨፌ ሜዳ በሚባል ሰፈር ነው፡፡

ጥያቄ፡– በልጅነትህ ከኳስ ጋር በተያያዘ ምን ትዝ የሚል ነገር አለ?

መልስ፡- ልጅ ሆነን ኮታችንን በፊት ለፊት በማድረግ ግብ የምንጠብቀው የኮቱን ፊት አዙረን የምንጓዝበትን ጊዜ አረሳውም፡፡ ቁጥርም ካስፈለገ ጀርባችን ላይ በመፃፍ በስፒል እያስያዝን የምንጫወተው በጣም ትዝ ይለኛል፡፡ እንዲሁም ግጥሚያ ስናደርግ ላለመሸፍ የምናደርገው ትግል በጣም ልዩ ነበር፡፡ አይ ጊዜ ተመስገን ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡– የክለብ አገባብህ ምን ይመስላል?

መልስ፡- የ8 ዓመት እና የ9 ዓመት ልጅ እያለሁ ሰፈር ውስጥ በጣም እጫወት ነበር፡፡ የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ለት/ቤት ስጫወት ጥሩ ስለነበርኩኝ ለት/ቤቱ ምርጥ የሚደረጉትን ውድድሮች የሚከታተሉ ሰዎች ወይም መልማዮች ስለ ነበሩ እኔም በወቅቱ ጥሩ ለነበረው ለአንበሳ ሲ ቡድን ልመረጥ ችያለሁ፡፡

ጥያቄ፡– ለስንት ክለቦች ተጫውተካል?

መልስ፡- ለአንድ ክለብ ብቻ ለአንበሳ ነበር የተጫወትኩት፡፡ በኋላም ክለቦች ሲፈርሱ ለስድስት ዓመት ያህል በቋሚነት ለወደፊት ቡድን ተጫውቻለሁ፡፡

ጥያቄ፡– ወደ በረኝነት እንዴት ልታዘነብል ቻልክ?

መልስ፡- ወደ በረኝነት ያዘነበልኩበት ዋናው ምክንያት ወንድሜ ያሬድ ይባላል በጣም ጎበዝ አጥቂ ስለነበር እኔም እሱ የሚመታቸውን ኳሶች ለመዳን እና በሬዲያ እና በቴሌቪዥን ስለበረኞች ሲወራ እኔም ሙሉ ለሙሉ ወደ በረኝነቱ ልሳብ በዚህ አጋጣሚ ወንድሜ ያሬድን መፎካከሬ ግን ሳይረሳ የእሱን ኳሶች ለማዳን ስጥር እኔም ጎበዝ ግብ ጠባቂ ልሆን እችላለሁ፡፡

ጥያቄ፡- በጨዋታ ዘመን ጎል አግብተህ ታውቃለህ?

መልስ፡- በጨዋታ ዘመኔ ያስቆጠርኳቸው ብዙ ጎሎች አሉኝ፡፡ ፍፁም ቅጣት ምት ጥሩ አስቆጣሪ ነኝ፡፡ ከሀገር ከወጣው በኋላም በአሜሪካ ሀገርም በትምህርት ላይ እያለሁም ጥሩ ፔናሊቲ መቺ ስለሆንኩ ብዙ አግብቻለሁ፡፡ ጋገባከው ምርጥ ካልከኝ ለእኔ ሁሉም ቆንጆ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡– ከገቡብክ ጎል የማትረሳው አለ?

መልስ፡- ከገቡብኝ ጎል የማልረሳው ናዝሬት የክረምት ጨዋታ አየር መንገድ እና አንበሳ ስንጫወት ኳሱ ፊት ለፊት መጥቶ ልይዛት ስል ሜዳው አባጣ ጎባጣ ስለነበረ ልይዛት ስል በአናቴ ላይ ዘላ የገባችብኝ ኳስ መቼም ቢሆን አልረሳውም ተመልካቹም ብዙ ጮሁብኝ፡፡ አስወጣው ቀይረው አሉ በኋላ የእኔ ጥሩ መሆን ሲመለከቱ በማቀፍ እና በማበረታታት አቅፈውኝ ይቅርታ በማለት እንደገና አበረቱኝ እልካለው፡፡

ጥያቄ፡– ካንተ ፊት ሲቆሙ የምትደሰትባቸው ተከላካዮች እነማን ነበሩ?

መልስ፡- ንጉሴ ገብሬ፣ አስፋው ባጆ፣ ሸዋንግዛው ታረፈ፣ ክብሮም ተ/መድህን፣ ተስፍሽ ወሎ በጣም አደንቃቸዋለሁ፡፡ ከእነሱ አልፋ ከመጣችም በእኔ ቁጥጥር ስር እንደምትሆን ጥርጥር የላቸውም፡፡

ጥያቄ፡– የአንተ ልዩ ኳስ ተጨዋች ማን ነበረ?

መልስ፡- የእኔ ልዩ ተጨዋች በጣም የምኮራበት እና የማደንቀው የቀድሞ ምርጥ ተጨዋች እና ምርጥ አጥቂ ሰለሞን ሽፈራው የዘመኔ ምርጥ አጥቂና ተጨዋች ነው፡፡ በእዛ ላይ እኮ ሲዘል በጣም ልዩ ነው፡፡

ጥያቄ፡– ከሀገር አወጣጥህ ምን ይመስላል?

መልስ፡- ሀገር ቤት እያለው ፕላን የተደረገ ስለነበር ከብሄራዊ ቡድን ጋር ስጫወት ስንወጣ ከጊኒ ጋር በነበረን ጨዋታ ነው በእዛው ልቀር የቻልኩት፡፡

ጥያቄ፡– ነገሮች እስኪመቻቹ የደረሰብህ ነገር ነበረ እንዴ?

መልስ፡- ሁሌም በስደት አለም ውስጥ ስታልፍ አልጋ በአልጋ አይሆንልክም፡፡ የሚሆንልህ ነገር እና የሚገጥሙ ገሮች ስለሌሉ በተለይ በባህል እና በቋንቋ በደንብ ስለማትግባባ ትንሽ ግርታ ይኖራል፡፡ ለሀገሩ ባዶ ለሰው እንግዳ ስለሆንክ ማንን እርዳታ እንደምትጠይቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ደግሞ በተለይ ከሀገር በመለየቴ እና ከዘመዶቼ መራቄ አንዱ ትልቅ የአእምሮ ማሰላሰል እና ሁሌም ሀገር ቤትን ማሰብ ለአዲስ ገቢ ስደተኛ የማይቀር ነው፡፡

ጥያቄ፡– በስደት ላይ እያለ የማትረሳው ነገር አለ?

መልስ፡- በስደት ላይ እየለሁ የማረሳው ነገር ምግብ እንዴት ለራሳችን እንደምናበስል እንዲሁም ገበያ ሄደን እንዴት እንደምንገበያይ የቋንቋ እንዲሁም የገንዘብ አለዋወጥ መቼም የማይረሱኝ ገጠመኞቼ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡– ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጨረሻ ጨዋታ ያደረከው ከማን ጋር ነበር?

መልስ፡- ለመጨረሻ ጊዜ የሀገሬን ባንዲራ ወክዬ የተጫወትኩት ጊኒ ከናክሪ ላይ ለ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ለሀገሬ ያለኝን ነገር ሁሉ የሰጠሁበት ሀገሬ ብለው ሀገር ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እኔም እንኳን በወቅቱ የነበሩ ተጨዋቾች ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለን ውጤቱን 2ለ2 በማለቁ በመልሱ ጨዋታ በሀገራችን እና በሕዝባችን ፊት ስለሆነ ጊኒን በመጣል ለ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ጨዋታዬን አድርጌ በእዛው ቀረው፡፡ የእኔ የመጨረሻ ጨዋታ ጊኒ ኮናክሪ ላይ ነው፡፡

ጥያቄ፡– ካዳንከው የፍፁም ቅጣት ምት ማትረሳው አለ?

መልስ፡- ካዳንኩት የፍፁም ቅጣት ምት የማይረሳኝ ለ12ኛው አፍሪካ ዋንጫ ከሩዋንዳ ጋር ስንጫወት በጥሎ ማለፍ የመጨረሻውን ጎል በማዳኔ እና ወደ ቀጣዩ ግጥሚያ ለማለፍ አስችሎኛል፡፡ ስለዚህ ይህንን ፍፁም ጣት ምት መቼም አረሳውም፡፡

ጥያቄ፡– የሚቆጭህ ነገር አለ?

መልስ፡- የሚቆጨኝ ነገር ከሁሉ ጊዜ በላይ ከጊኒ ጋር የነበረውን የመልስ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ አለመጫወቴ ሲሆን የእኛ አቋም በእዛው ቢቀጥል ኖሮ በእውነት በእውነት ነው የምልህ ከፍተኛ ውጤት እናመጣ ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው ቡድን በጣም እተማመናለሁ፡፡

ጥያቄ፡– ከዳኛ የማን አድናቂ ነበርክ?

መልስ፡- ከአጫወቱኝ የመሀል ዳኞች በጣም የማደንቀው እና የማከብረው አቶ አየለ ጅቦ ሁሌ አንተን ሲያጫውት በማስፈራራት እና አንተን ዝቅ በማድረግ ከእኔ ጋ አተካሮ እንዳትገጥም ችሎታ ሲያንስክ እና ስትደክም እየመጣቹ እኔ መጥፎ ነገር እንድናገር አታድርጉኝ ብሎ ተጨዋቾቹን ሲናገራቸው ሁሌም ዝቅ ብሎ አጫውቷል፡፡ እሱም ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ይወጣል ተጨዋቹም ደጋፊም አያነሳሳብክም፡፡ እሱም ቆራጥ ዳኛ ስለሆነ ማንንም ተጨዋች ወደ እሱ ዝር አይልም፡፡

ጥያቄ፡– በአንተ ጊዜ ከነበሩት የአንተን ምርጥ አስራ አንድ ንገረን ከነ አሰልጣኙ?

መልስ፡- በእኔ ጊዜ ከነበሩት የእኔ ምርጥ አስራ አንድ አፈወርቀ ጠና ጋሻው፣ አያሌው ሙላለም፣ እጅጉ ሸዋንግዛው፣ ተረፈ፣ ንጉሴ ገብሬ፣ ክብሮም ተ/መድህን፣ አቦነህ ማሞ፣ ዳዊት ኃይሉ፣ ጎሹ ተስፋሚካኤል፣ ዳኛው ሰለሞን፣ መኮንን (ጎሹ) እንዲሁም ሌሎችም ምርጥ ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ ለጊዜው ስማቸውን ዘነጋሁት እንጂ ይሄንን ቡድን እንዲያሰለጥነው የምፈልገው ምንጊዜም ቢሆን ወደር እና ተተኪ ለሌለው ለመንግስቱ ወርቁ ነው እንዲያሰለጥን የምሰጠው፡፡ ሁሉም አክብሮት እና ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡

ጥያቄ፡– በወቅቱ በነበረው ፖለቲካ የደረሰብህ ነገር አለ?

መልስ፡- በጊዜ እኔ የደረሰብኝ ለኢትዮጵያ ተስፋ ቡድን ተመርጬ አዲስ አበባ ስታዲየም ማታ እስከ ሁለት ሰዓት ድረስ ልምምድ ሰርተን እራት ከበላን በኋላ ወደየቤታቹ ሂዱ በማለት የትራንስፖርት ከሰጡን በኋላ ወደ ሰፈር በአውቶቢስ ሄጄ ቤቴ ፈረንሳይ ለጋሲዮ ስለነበር ሻንጣዬን ይዤ በእግሬ ወደ ቤት ልገባ ስል ሮድ የሚዞሩ ወታደሮች አስቁመውኝ ከፈተሹኝ በኋላ ለካ ወረቀት የምትበትነው አንተነህ በማለት ያለምንም ምክንያት በቆመት ዱላ ደበደቡኝ፡፡ እግሬንም ወገቤንም ጎድተውኝ መንገድ ላይ የጣሉኝን አረሳም፡፡ ለሁለት ለሶስት ሳምንትም ከጨዋታ እርቄ ነበር፡፡

ጥያቄ፡– አሁን የት ትገኛለህ?

መልስ፡- አሁን የምገኘው በአሜሪካን ሀገር በሎስአንጀለስ ከተማ ከቤተሰቦቼ ጋር እገኛለሁ፡፡

ጥያቄ፡– አግብተሀል? ስንት ልጆች አሉ? የባለቤትህ ስም እና የልጆችህን ስም ብትነግረኝ?

መልስ፡- አዎ አግብቻለሁ፡፡ በጣም ከምወዳት ባለቤቴ ገነት መነገሻ ጋር ሃያ አምስት ዓመታችንን ይዘናል፡፡ የመጀመሪያ ልጄ ክርስቲያን አፈወረቅ ትባላለች፡፡ ሃያ ሁለት ዓመቷ ነው፡፡ የሳይኮሎጂ ምሩቅ ነች፡፡ ወንዱ ልጄ ዳግማዊ አፈወርቅ ይባላል ሃያ ዓመቱ ነው፡፡ የኮምፒዮተር ሳይንስ ፐሮግራሚንግ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ይጨርሳል፡፡

ጥያቄ፡– ማመስገን የምትፈልገው ካለ?

መልስ፡- ለመጀመሪያ ፈጣሪዬን ከፊት ሆኖ መንገዴን ስለሚመራኝ በመቀጠል ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ ባለቤቴን ገኒ ልጆቼን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እኔ ያለ እነሱ ድጋፍ ምንም ስለሆንኩ ቤተሰቦቼ ኑሩልኝ፣ ክበሩልኝ፡፡ ፈጣሪ ከፊት ሆኖ ስራችሁን ይከውንላችሁ፡፡ በተረፈ በጋሻው ያለሁበትን በማፈላለግ ባለመሰልቸት ለትዕግስትህ ክብር ይስጥልኝ፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: